Saturday, 01 September 2012 10:48

ሀበሻ…ደስታውም፣ ሀዘኑም ቅጥ ያጣ…!

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(0 votes)

አቶ መለስን ዓለም የሚያከብራቸው፣ በእውቀታቸው!

እኛ ስለ ርዕያቸው ደርሰን ከመዘባረቅ፣ ርዕያቸውን እንወቅ!

ፈር መያዣ:-  የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈተ ህይወት ዓለምን ሁሉ አነጋግሯል፤ ለአብዛኞች መሪ ሀዘን ሲፈጥር፣ ለጥቂቶች መተከዣ ሆኗል፡፡ የአብዛኞቹ ፊቶች በእምባ ሲንገረገቡ፣ የጥቂቶቹ አኩርፈዋል፡፡ የብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሀዘን ከአንጀት፣ የጥቂቶቹ ደግሞ ከአንገት ይመስላል፡፡ የእኚህ ታላቅ መሪ ህልፈት፣ የፈጠረው ከባድ “ሃገራዊ” ሀዘን በራሱ ቅኔ ነው ማለት ይቻላል፤ ከሀበሻ የሠምና ወርቅ ፍልስፍና የተቀዳ፣ “ርዕዮተ ዓለማዊ” ሀዘን አይነት እያስመሰልነው ነውና፡፡

የሀገራዊ ሀዘናችንን ወርቅ ለፖለቲካ ባለቅኔዎቻችን ትቼ፣ በሠም ሀዘናችን ላይ እንኳ የምር ብንወያይ መልካም ነው፡፡ በርግጥ፣ ወርቁ ሀዘናችን፣ ከሀበሻዊው የቅኔ ፍልስፍናችን የተቆነጠረ የመጠራጠር ህመማችን (Skepticism) ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሣሌ የጋናው መሪና አቶ መለስ በተከታታይ በማረፋቸው፣ ምዕራባዊያኑ በአንዳች ነገር መርዘው ገድለዋቸው ይሆናል ብለን መጠራጠራችንን ልብ ይሏል፡፡ በሌላ በኩል የክፉ ቀን ደራሻችን የሆኑት ሼህ ሙሃመድ አሊ አሙዲን በዚህ መሪር ሀዘናችን ጊዜ ለአንድ አፍታ ብቅ ብለው “ፈጣሪ ያጽናችሁ” አለማለታቸው ሌላው የሀዘናችን ቅኔ ሆኗል፡፡ የቅኔውን ወርቅ የሚቀጥሉት ቀናት ይፈቱት ይሆናል፡፡ እኛ ግን ሀዘናችን ቅጥ እንዳያጣ፣ የባለ “ራዕዩን” መሪ ርዕይ እንዳናጨናግፍ የምር ብንመካከር ይበጃል…

መለስን እንደ እውቀት ተምሣሌት…

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብልህ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆኑ አዋቂም ናቸው፡፡ መሣጭና ሞጋች ንግግራቸው፣ ገና ከወጣትነት የጫካ ትግል ጀምሮ እየተገራ ከመጣ የሕይወት ልምዳቸውና የጠለቀ የንባብ እውቀታቸው የተቀዳ እንደሆነ በብዙዎች የሚታመን ይመስለኛል፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመዲናችን እንዲሆን፣ በፉኦ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ምዕራባዊያን ከሚሰጡን ስንዴ የበለጠ የማንነታችን መገለጫ የሆነው አክሱም ሀውልታችን እንደሚርበንና እንዲመለስ፣ ያደረጓቸው ሞጋችና መሣጭ ንግግሮችን ካዳመጥኩ በኋላ፣ በአዋቂነታቸውና በበሣል ተናጋሪነታቸው ዙሪያ አልደራደርም፡፡ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ሳያስፈልገኝ ሁሉንም ንግግራቸው አዳምጥ ዘንድ የመንፈስ ባሪያቸው እንዳደረጉኝ መደበቅም አልፈልግም፡፡ ሁሉንም ንግግራቸውን ለማዳመጥ እተጋለሁ ማለት ግን፣ በሁሉም ንግግሮቻቸው የቀረቡ ሀሳቦችንና ርዕዮተ ዓለሞችን እቀበላለሁ ማለት አይደለም፡፡ ከአንዳንዶቹ ሀሳቦች ጋር እንደውም መሠረታዊ ልዩነት ያጋጥመኛል፡፡

በፓርላማም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጓቸውን ንግግሮች ለማዳመጥ በመትጋት ብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚጋሩኝ ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቃታቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በብዙ መልኩ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አርአያ የሚያደርጓቸው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ለሆዱ አደር ካድሬዎች፣ አንዳንድ ጥጋበኛ ጐጠኞች፣ አንዳንድ ሙሰኛ “የመንግስት ሌቦች” ባሥመረሯቸው ጊዜ፣ ጣቱን ወደ አቶ መለስ የሚቀስረው ሁሉ፣ በህልፈታቸው ተደናግጧል፤ እምባውን ተራጭቷል፡፡

የተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ ዘረኞች፣ አክራሪዎች…በሚሠሩት ግፍ አቶ መለስን ማማረራቸው የፀፀታቸው ብዙ ናቸው፤ ሀገራቸውን ለመለወጥ ያስችለኛል ባሉት ተግባር ላይ ተወጥረው ሲባክኑ አንድም ቀን ሳያርፉ መሞታቸው ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ፀፀት ሆኗል፡፡ ወደፊት ሀዘናቸው የእግር እሳት እንደሚሆንባቸው የሚሠጉም ብዙዎች ይመስሉኛል፡፡ መለስ በርግጥም ተጽእኖ ፈጣ፣ ታላቅ መሪ መሆናቸው ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ወደ አንድ መሥመር የሚያቀራረብ ቁልፍ ጉዳይ አድርጐ መጠቀም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ በተለይ ሀገር ተረካቢው ወጣት፣ “አዋቂን ሰው” ሁሉም እንደሚያደንቀው፣ ሁሉ ባይወደው እንኳን ሁሉም ሊያከብረው እንደሚችል መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡

አቶ መለስን ዓለም የሚያከብራቸው በእውቀታቸው ነው፤ አፍሪካዊ በመሆናቸው ወይም፤ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ በህልፈተ ህይወታቸው የተደናገጠው፣ ከልቡ ያዘነውና ስላጣቸው የተቆጨው ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ወይም በኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው አሊያም የአድዋ ተወላጅ በመሆናቸው ሳይሆን በብልህነታቸው፣ በአዋቂነታቸውና በተለያዩ መድረኮች የማያሳፍሩ አንደበተ ርቱዕ በመሆናቸው ነው፡፡

መለስን ለሀገር አንድነት ተምሣሌት…

ጀግናና አዋቂን ሁሉም ይፈልገዋል፤ የልብ ወዳጅ ባያደርገው እንኳን የልብ አማካሪ ያደርገዋል፡፡ በጠንካራ ሰብዕና የተገነባን አዋቂ፣ ጀግና፣ ባለርዕይ ሌሎች አዋቂዎችም ሆኑ ጥራዝ ነጣቂ ይፈልጓቸዋል፡፡ ይወዷቸዋል፤ ይመኩባቸዋል፡፡ እንኳን በቅርብ የተዛመዱ፣ ሀገር የተጋሩ ዜጐች ቀርቶ የሩቆችም ያደንቋቸዋል፡፡ በላይ ዘለቀን፣ የጐጃም ሰዎችና የወሎ ሰዎች የራሣቸው ወገን እንዲሆን ለማስረገጥ በጥናትና ምርምር አስደግፈው ሁሉ የተሟገቱለት፣ ጀግና ስለሆነ ነው…አፄ ቴዎድሮስን ቅማንት ነው፣ አማራ ነው እየተባባሉ የሚራኮቱበት ለሌላ እንዳይመስልህ፣ ጀግናን፣ ብልህን፣ አዋቂን ሰው ሁሉም ስለሚፈልገው ነው፤ በተለይ የሀገር መሪ ከሆነ፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጐጠኞች፣ ቀሽም የፖለቲካ ካድሬዎች በየዋህነትም ሆነ በጽንፈኝነት አቶ መለስን ወደ አንድ ወገን ለማምጣት የሚጥሩበት ሁኔታ በየቀበሌውና በየመሥሪያ ቤቱ በተዘረጉ የሀዘን መግለጫ ጣቢያዎች ላይ ሣይቀር ቢታዩም፣ አቶ መለስን ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚፈልጋቸውና እንደተቆጨባቸው ማወቅ ብልህነት ነው፤ ምክንያቱም አዋቂ፣ ብልህ፣ ጀግና ናቸውና፡፡

በመገናኛ ብዙሃንም የሚቀርቡ የሀዘን መግለጫዎች በብልህነትና በሃላፊነት የተመረጡ ቢሆኑ መልካም ነው፤ አንዳንዱ “ሀዘንተኛ” አያሳዝንም ወይም አያስተዛዝንም፤ እንደውም ያናድዳል፡፡ የሚናገሩት ነገር ጨለምተኛና ፍሬከርስኪ ሆኖ ይታያል፡፡

አንዳንዱ የሀዘን መግለጫ ደግሞ ከምንም በላይ አበሳጭነቱ ያመዝናል…በተለይ ኢቴቪ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች በጥንቃቄ፣ በእውቀትና በብልሃት ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ በባለርዕዩ መሪ ሞት ቆሽቱ ያረረ ህዝብን፣ በአልኩ ባይ አስተዛዟኞች ቅጥ ያጣ የሀዘን መግለጫ የበለጠ እንዳያዝንና ተስፋ እንዲቆርጥ መደረግ የለበትም፡፡

ባልበሰሉ የፖለቲካ ካድሬዎች እየተወናበደ፣ በምክንያታዊነት (Rationality) የባልተገራ  መናኛ አስተሳሰቡ እየባከነ፤ በጠባብ ብሔርተኝነት፣ ጐሠኝነትና የሃይማኖት ጽንፈኝነት እየተናጠ ሀገራዊ መብሰክሰክ የሚታይበት ዜጋ ሁሉ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈተ ህይወት ላይ ተመሳሳይ የሀዘን ስሜትና ፀፀት የተሠማው ይመስላል፡፡ እናም፣ ይህን ቢያንስ በመሪው ሀዘን ላይ የመጣ የሚመስለውን ብሔራዊ መግባባት በብልሃትና በእውቀት እየገፋ የሀገራዊ አንድነት ተምሣሌት ለማድረግ መንግስትና ኢህአዴህ የተለመደው አይነት የታይታና የፕሮፖጋንዳ ዲስኩር ከማቅረብ በዘለለ፣ የምር ሥራ ሊሠሩበት ይገባል፡፡ አሊያ፣ ሀበሻ ሀዘኑም፣ ደስታውም ቅጥ ያጣ ነው ከመባል አንድንም፡፡

 

 

 

 

Read 1715 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:52