Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 12:49

የአሞሌ ነገር…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…ሀሳብ አለን፡፡ መገበያያ እንደ ድሮ በአሞሌ ጨው ይሁንልን! አሀ…እነኚህ ‘ብር’፣ ‘ዶላር’፣ ‘ፓውንድ’ ምናምን የሚባሉ ነገሮች አባልተው ሊጨርሱን ነዋ፡፡ “እንትናን ደረቅ ቼክ ሰጥተው ጉድ አደረጉት እኮ!” “ፎርጅድ ዶላር ሰጥተው ገዝቶ የወሰደውን የዕቁብ ገንዘብ ውሀ በላው”፣ “ስንት እንደነጩት ታውቃለህ! አንድ ሚሊዮን ብር!” የሚባሉ ነገሮች ከመብዛታቸው የተነሳ እንዴት እስከ ዛሬ ዜማ ተሠርቶላቸው ኮንሰርት እንዳልተዘጋጀላቸው ሊገርመን ምንም አልቀረን፡፡ እናማ…አሞሌ ጨው ድሮ የነበረንን መተሳሰብ ይመልስልን ይሆናል፡፡ (ይሄ የአፈ ታሪኩንና አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በ‘አስተያየታቸው’ የሚሉት አይነት ሳይሆን እውነተኛውን መተሳሰብ ለማለት እንደሆነ ይሰመርበትማ!) እናላችሁ… ወደ አሞሌ ጨው ብንመለስ ደረቅ ቼክ፣ ‘እርጥብ ቼክ’ የለ፣ ፔይመንት ኦርደር፣ ‘ፔይመንት ዲዝኦርደር‘ የለ፣. …ጥሬ ገንዘብ፣ ‘ብስል ገንዘብ’ ብሎ ጣጣ የለ…አሞሌያችንን እየተለዋወጥን ወደየጉዳያችን፡፡

እናላችሁ…ዘንድሮ ከብዙ ነገሮቻችን ጀርባ (“ከሁሉም ነገሮቻችን…” እንዳልል የ‘ሀበሻ ጨዋነት’ ተጭኖኝ ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ያለው ብቸኛ ጉዳይ ገንዘብ ነው፡፡ አንዳንዴ ሰው ስንጨብጥ እኮ እጆቻችን ራሳቸው “ባለሚሊዮን ብር…” “ባለ ሺህ ብር…”፣ “ባዶ ኪስ…” ምናምን የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…እስቲ ገንዘብ አላችሁ ሲባልና “ክሪዝ ወግሮታል” ሲባል የሰዉን አጨባበጥ ጥብቀትና መላላት ነገሬ በሉ! እናማ፣ ለምን ይዋሻል (እኔም ሳልላት አይቅርብኝ ብዬ ነው፡፡)…መጨባበጥ እንኳን በገንዘብ እየተሰላ ነው… ደግሞ ከእጅ አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ምን ችግር አለ…ከእነማርክስ ማስታወሻ ጢማችን…አለ አይደል… ጉንጫችንን መከስክስ ነዋ! (“ኪሲንግ ተከሳከሱ…” የሚለው አባባል ዜማ እንዳለው ቆይቶ ነው የገባኝ መሰለኝ!) ጥምጥም ማለት ነዋ! ጀርበ ያለው ለአርቱ ብዬ ነው እንጂ…

ሰብሰብ ብሎ ተዝናንቶ ሸሽገው ቢል መክፈል እንኳን ‘ታሪከና ምሳሌ’ ነገር ሆኖ ቀረ አይደል! ለምሳሌ ሦስትም አራትም ሆናችሁ የሆነ ቢራ ምናምን ስትሉ ተቆያላችሁ፡፡ ከዛ አንዱ “እዚህ ጋ ቢል ታመጪልን…” ምናምን ነገር ይላል፡፡ ህዝቤ ሁሉ በሌላ ወሬ ተጠምደን ያልሰማን ይመስል እናደፍጣለን፡፡ አሳላፊዋ መጥታ…እሱ ከኪሱ ቦርሳውን አውጥቶ… ብሪቱን አንድ አንድ እያለ መዞ…  ለልጅቷ ሰጥቶ…እሷ ይዛ ሄዳ ገንዘብ ተቀባዩዋ ጋር ስትደርስ በምክር ይመስል ሁሉም ያዙኝ ልቀቁኝ የሌለበት “ይሄንንማ እኔ ነኝ የምከፈለው!” ቲራቲር ይጀመራል፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ልጅቱ መልሱን ይዛ እስክትመለስ ከኪስ የሚወጣ እጅ የለም፡፡

ሰዎቹ ስለ አንድ ጓደኛቸው ሲያወሩ አንዱ “እሱ እኮ እጁን ኪሱ ለመክተት የመጀመሪያ ነው…” ይላል፡፡

ሌላኛው ምን አለ መሰላችሁ…“እጁን ከኪሱ ለማውጣት ደግሞ መጨረሻ ነው፡፡” ይሄ ነገር ስንታችንን እንደሚገልጽ ‘ኦፒኒየን ፖል’ ምናምን ነገር ይካሄድልንማ! እኔ የምፈራው ምን መሰላችሁ… አንዳንዴ ዘው ብሎ የገባ እጅ ምች ይመታውና…ተዉት ብቻ፡

እናላችሁ…ለመክፈል መግደርደር የበዛው ሁልጊዜ የችግር ብቻ ሳይሆን…እያለንም ራሳችን ለተጠቀምንበት እንኳን ሌላው ትከሻ ላይ መጣል ስለለመደብን ነው፡፡  ኮሚኩ ነገር እኮ ሂሳቡ ተከፍሎ አሳላፊዋ ወደ ሌላ ጠረጴዛ እየሄደች “አንቺ፣ እንኪ ይሄን፣ እሱን ብር መልሺ…” የምንል የስታዲየም በር ከተዘጋ በኋላ የምንደርስ ‘ሶምሶማ ሯጮች’ መብዛታችን ነው፡፡

እናላችሁ…እደግመዋለሁ፣ መገበያያችን ወደ አሞሌ ጨው ይለወጥልን! አሁን፣ አሁን ደግሞ “ሲስተሙ ስታክ አድርጎ…” ምናምን የሚሉት ነገር አንዳንድ ባንኮችን ጎጃም በረንዳ በበዓል ዋዜማ አይነት ነገር እያደረጋቸው ነው፡፡ አሞሌ ጨው በስንት ጣዕሙ… ሲስተም የለ፣ ኮር ባንኪንግ የለ…በቃ “እንካ፣ እንኪ” መባባል ነው፡፡ ምን እናድርግ…ገንዘብ ‘ሂዩማኒቲያችንን’ እየቀማን ነዋ! የምር…ገንዘብ የሁሉ ነገሮች አልፋና ኦሜጋ እየሆነ ነው፡፡

አሁን ለምሳሌ የሰማይ ቤት መንገዳችንን እንዲያመቻችሉን ነገራችንን ሁሉ በእነሱ ላይ የጣልንባቸው የሃይማኖት ሰዎች አንዳንዴ በአደባባይ ከእንትን ሰፈር ስድብ በመለስ ሲወዛገቡ “በቃ… የዚህ የትልቁ መጽሐፍ ትርጉም በዚህ ዘመን እያወዛገበ ነው!” ትላላችሁ፡፡ ትንሽ ይሰነብትና…ነገርዬው ምን ሆኖ ይገኛል አትሉኝም…‘ፈረንካ’! በሽምብራ ቆሎና በአሹቅ ወስፋታቸውን እየዘጉ ይጸልዩልናል፣ ኬዛችንን ያቀርቡልናል ያልናቸው… ከጂ ፕላስ ምናምን ቤት፣ ከእንትን አይነት መኪና፣ እንትናና እንትና ከሚባሉ የከተማ ቆንጆዎች ጋር ምናምን አብረው ሲነሱ…ገንዘብ ምን እያደረገን እንደሆነ ታያላችሁ፡፡

ሌላ ለምሳሌ…ቅልጥ ያለ፣ በአንደበቱ ርቱዕነት “ወንድምና እህትን ማጋባት ይችላል…” የሚባልለት ‘ቦተሊከኛ’ ይኖራል፡ እናላችሁ…“እሰይ፣ ለተበደሉት ከልቡ የሚያስብ የቼ ጉቬራ አርማ የሚያነሳ ተገኘ…” ምናምን ይባላል፡፡  ትንሽ ቆይቶ “የዓለም ወዛደሮች ከሰንሰለታችሁ ሌላ የምታጡት የለም…” ምናምን እያለ ዲስኩር የሚያደርገው በሺህ ምናምን ካሬ ሜትር ላይ ባለው መኖሪያ ቤቱ እንደ ሆሊዉድ ተዋንያን እየተዝናና…አለ አይደል… ሠራተኞቹን የባሪያ ፈንጋይ አይነት እያሰቃያቸው መሆኑን ስትሰሙ…ገንዘብ ምን እያደረገን እንደሆነ ይታያችኋል፡፡ የሰንሰለቱ ዋናውን ቁልፍ ከያዙት አንዱ እኮ እሱው ነው! ቂ…ቂ…ቂ…

እነኚህ እንደማያልቁት የአገራችን ‘መመሪያዎች’ በወር ሀያ አምስት ጊዜ አቋማቸውን የሚበውዙት ‘ቦተሊከኞች’ እንዲህ ከአጥር አጥር የሚዘሉት አብረው የሚበውዙት ‘ፈራንካ’ ቢጤ ሲኖር ነው የሚል ጥርጣሬ አለን፡፡ እኛ ሞኞች…አለ አይደል… “የቦስተን ቲ ፓርቲ ምናምን የሚሉት አይነት ታሪክ እዚሀ ሊመጣ ነው እንዴ!” ምናምን እንላለን፡፡ (‘አማሪካን’ ያነሳሁት ለክፉም፣ ለደጉም ብዬ ነው፡፡ አሀ…እንደ መሰንበቻችን የ‘ኒውስ ሱናሚ’ ከሆነ…ይቅር ብቻ… )

እናላችሁ…ምናልባት እየረዘሙ፣ እየሰፉ እየሄዱ ያሉትን ስንጥቆቻችንን ትንሽ ገታ ያደርግልን ከሆነ…መገበያያችን በአሞሌ ጨው ይሁንልንማ! ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…አባትዬው ቀብቃባ ቢጤ ነገር ናቸው አሉ፡፡ እናላችሁ… የሆነ ሰው ትንሹን ልጅ ምን ብሎ ይጠይቀዋል መሰላችሁ… “አባትህ አሥር ሺህ ብር ቢያገኝና ስምንት ሺውን ለእናትህ ቢሰጣት እናትህ ምን ትሆናለች?”

ልጁ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“በልብ ድካም ጸጥ ትላለች፡፡” ልክ ነዋ…ልጄ፣ እንኳን ቀብቃባነት ተጨምሮበት! (ስኮቲሹ ሰውዬ ቀብቃባ ከመሆኑ የተነሳ ምን አደረገ አሉ መሰላችሁ…የጫጉላ ሽርሽሩን ብቻውን ሄደ! ቂ…ቂ…ቂ…)

እናላችሁ…ለምሳሌ ብዙም የማይቀርባችሁ ሰው በድንገት የእቅፍ ሰላምታ ሲጀምርና… በተገናኛችሁ በማግስቱ “አንተ ይህን ያህል የሚያጠፋህ ምንድነው?” ሲላችሁ ነገርዬው የ‘ፈራንካ’ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ሳምንት ሳይሞላ ምን ሊል ይችላል መሰላችሁ… “እባክህ ሚስቴ ሀኪም የማህጸንሽ አቀማመጥ አቅጣጫ ስቷል ብሏት…” ምናምን ይልና “ለኦፕራሲዮን ማሟያ አንድ መቶ ብር ያህል ይኖርሀል?” ሊላችሁ ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…ሰላምታ ሁሉ ከጀርባው ተመጣጣኝ የብር መጠን ይቀመጥለታላ!

እግረ መንገዴን…እንግዲህ ጨዋታምን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ “አሥር ብር ይኖርሀል?”  “መቶ ብር ይኖርሀል?” ምናምን የሚሏቸው አባባሎች…አለ አይደል… “ኪስህን ብፈትሸውና ያገኘሁትን ብወስድ ቅር ይልሀል?” አይነት ትርጉሞች አይሰጧችሁም! ሌላ ‘ጥቆማ’ ደግሞ…የሆነ ሰው ከመሬት ተነስቶ ካኮረፋችሁ መለስ ብላችሁ ለማስታወስ ሞክሩ፤ የሆነ ብር አበድራችሁት ረስታችኋል ማለት ነው፡ ልክ ነዋ…ለማኩረፍም፣ ለመታረቅም ወሳኙ ‘ፈራንካ’ እየሆነ መጥቷላ! ከዛሬ ነገ “አንተ ያበደርኩህን ‘ናይን ብር ናይንቲ ናይን’ አትከፍልም?” የምትሉት ይመስል አጠገባችሁ ሲደርስ እንትኑን መጣል ይጀምራል፡፡ በዛ ሰሞን አንድ ወዳጃችን ባላወቀው ምክንያት ያኮረፈውን የመሥሪያ ቤት ባልደረባውን ሲገልጸው “ገና ያልተጠረበ ኮብልስቶን መሰለ”፣ ብሎታል፡፡ ነፍስ የሆነች፣ ‘ከረንት አፌርስ ታሳቢ ያደረገች’ አገላለጽ ይሏችኋል ይቺ ነች፡፡

ስሙኝማ…ካነሳነው አይቀር ይሄ የኮብልስቶን ነገር…በየቦታው መሠራቱ አሪፍ ነው፡፡ በተለይ…በምሽት መንደር ለመንደር ‘ገርል’ ምናምናቸውን ለሚሸኙ እንዴት ሸጋ ነገር መሰላችሁ! ልክ ነዋ…እቤቱ ሲገባ በማዘር “አንተ! ጉልበትህ ድረስ እንዲሀ የተጨማለቅኸው ጭቃ ስታቦካ ነው እንዴ የዋልከው!” ከመባል ያድናል፡፡  እኔ የምለው…እግረ መንገዴን፣ ጨለም ሲል ‘የሚሸኙ ገርሎች’ ያሉባቸው ሰፈሮች ሁሉ ለምንድነው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጭቃ የሚሆኑት? ቂ…ቂ…ቂ…

እናላችሁ…ዘንደሮ ሁላችንንም ቀንድና ጭራ ያበቀለልን የ‘ፈራንካ’ ፍቅር ትንሽ ቀዝቀዝ ቢል አሞሌን የማንሞክረውሳ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3625 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:58