Saturday, 18 August 2012 12:44

የ”ዛፍ” እና “ባህር ዛፍ” ነገር

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(4 votes)

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሳተመው መዝገበ ቃላት ውስጥ “ባህር ዛፍ” ለሚለው ቃል “በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ፍሬው ከአውስትራሊያ እንዲመጣ ተደርጐ ኢትዮጵያ ውስጥ የለማ፣ የተለያዩ ዝርያዎች ያሉትና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለአገልግሎት የሚደርስ የትላልቅ ዛፎች አይነት” የሚል ትርጉም ሲሰጥ “ዛፍ” ለሚለው ቃል ደግሞ “ግንድና ቅርንጫፍ ያሉት፣ መጠኑ ትልቅና ትንሽ የሆነ፣ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚችል የእፅዋት አይነት” በሚል ይገልፀዋል፡፡ከውጭ መምጣቱን ለማመልከት “ባህር” የሚል ቅፅል ጨምሮ “ባህር ዛፍ” የራሱን መጠሪያ ከማግኘቱ በፊት በጥቅል “ዛፍ” በሚል ስያሜ የሚታወቁ አገር-በቀል እፅዋት ነበሩ፡፡ እነዚህ እፅዋት በጥቅል ዛፍ ተብለው ለምን ሊጠሩ ቻሉ? ስያሜውን መች አገኙ? እንዴት፣ በምንና በማን አማካኝነት? መልሱ እንደ ጥያቄው ቀላል አይደለም፡፡

የስያሜ መነሻ፣ ምክንያትና ትርጉማቸው ምን እንደሆነ ሳናውቅ በንግግራችን ውስጥ ከምንጠቀምባቸው ቃላት አንዱ “ዛፍ” መሆኑን “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች” በሚል ርእስ በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ተዘጋጅቶ በ1997 ዓ.ም በታተመው መፅሐፍ ውስጥ ተመልክቷል፡፡

“ቀደም ብለው የወጡ የሕዝብና የቦታ ስሞች ትርጉማቸው በጊዜው ሳይመዘገብ ከቀረ ወይም በቋንቋችን ውስጥ ሕያው ካልሆነ የተፀውኦ ስም ቢሆኑም እንደ “ዛፍ”፣ “ጠላ”፣ “ፈረስ” የዘመን ርቀት ትርጉማቸውን ደብቋቸዋል፡

…”ዛፍ” ለምን “ዛፍ” እንደተባለ ምክንያት ቢኖረውም፣ ያንን ምክንያት” ማወቅ እንዳልተቻለ ይገልፃሉ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የብዙ ቃላት ስያሜ መነሻ እና ትክክለኛ ትርጉማቸው አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ ትርጉም ለመስጠት ድፍረት አብዝተናል ብለው በምሳሌነት ያቀረቡት “ጠመንጃ” የሚለውን ቃል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በመፅሐፉ የግርጌ ማስታወሻ (ማብራሪያ) ባቀረቡት ፅሁፍ፡-

“ጠመንጃ” ማለት “ጠብ መንጃ” ከሚለው የመጣው ነው የሚለውን ማስጣል አልቻልንም፡፡ ዘመኑ የመምህር ቃል የማይከበርበት ዘመን በመሆኑ፣ “ጠመንጃ” ወይም “ጠብ መንጃ” የቱርክ ቃል ሆኖ ከእኛ የደረሰው በአረቢኛ በኩል ነው፤ የዚህን የቱርክ ቃል ትርጉም “ጠብ መንጃ” ለማድረግ መጀመሪያ ቱርኮችን አማርኛ ተናጋሪ ማድረግ ያስፈልጋል ቢባልም ብዙ ሰሚ አልተገኘም” ይላሉ፡፡

ዛፍ ለምን ዛፍ እንደተባለ መልስ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ “ባህር ዛፍ”ን አጥፍቶ በአገር በቀል እፅዋት ለመተካት እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ ሥራው ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ባህር ዛፍ ብዙ ውሃ በመፈለጉ ምክንያት፣ ለመሬት ድርቀትና ለሌሎች እፅዋት እድገትም እንቅፋት ሆኗል በሚል ነው በአገር በቀል እፅዋት እንዲተካ እየተደረገ ያለው፡፡

ባህር ዛፍ ፋይዳው በጐጅነት ከመፈረጁ በፊት ለአገር፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ያበረከተው ብዙ ውለታ ነበረው፡፡

አፄ ምኒልክ አዲስ አበባ የመንግሥታቸው መቀመጫ እንድትሆን መወሰን የቻሉት ከአውስትራሊያ የመጣው ባህር ዛፍ ለማገዶ ችግር አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ በመገኘቱ ነበር፡፡

ባህር ዛፍን ጨምሮ የደን ልማት ለአገርና ለሕዝብ ያለውን ጠቀሜታ የተረዳው የአፄ ኃይለሥላሴም መንግሥት ከሐምሌ 9 ቀን 1948 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የደን በዓል ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኖ እንደነበር “ፍሬ ከናፍር 3ኛ መፅሐፍ” በሚል ርእስ በ1957 ዓ.ም የታተመው ጥራዝ ውስጥ ታሪኩ ተዘግቧል፡፡

በዘመኑ በሆለታ ከተማ በተከበረው የደን በዓል ቀን ላይ ንግግር ያደረጉት የእርሻ ሚኒስትሩ ባላምባራስ ማህተመሥላሴ ወልደመስቀል ለበዓሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ችግኝ መዘጋጀቱን፣ ችግኞቹን መትከያ 120,000 ሜትር ካሬ መሬት መሰናዳቱን፣ ከሚተከሉትም ችግኞች የሚበዙት ከውጭ አገር የመጡ መሆናቸውን፣ ለፕሮጀክቱ መሳካት የተባበሩት መንግሥታት የእርሻና የምግብ ድርጅት እገዛ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የደን በዓል ቀን ተቆርጦለት መከበር ከመጀመሩ በፊት በተሰራው ሥራም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ እፅዋት መተከላቸውን ያመለከቱት አፄ ኃይለሥላሴ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር “አስፈላጊውን ችግኝ ምንም እንኳን የእርሻ ሚኒስቴር እንዲሰጥ ቢታዘዝ ከእርሻ ሚኒስቴር እየተወሰዱ የሚተከሉት ዛፎች ሁሉ የባለርስቱ ንብረት ናቸውና ይህን ሥራ ያለማቋረጥ በትጋት መፈፀም ግዴታ ነው፡፡”

የእርሻ ሚኒስትሩና ንጉሠ ነገሥቱ “በሆለታ ዛፍ ተክል መፈተኛ ጣቢያ” ተገኝተው ካደረጉት ንግግር መረዳት እንደሚቻለው ካለፈው ብቻ ሳይሆን ዛሬ ከሚታየውም እውነታ ጋር እያያዝን ብዙ ጥያቄ እንድናነሳ ግድ የሚሉ መረጃዎች ሰፍረዋል፡፡

ለሐምሌ 9 ቀን 1948 ዓ.ም የደን በዓል ቀን እንዲተከሉ የቀረቡት እፅዋት የሚበዙት ከውጭ የመጡ ከሆነ አሁን ባህር ዛፍን በአገር በቀል እፅዋት የመተካቱ ተግባር በዚያ ዘመን በብዛት ወደ አገር ውስጥ የገቡትንም ያካትት ይሆን? “የሆለታ ዛፍ ተክል መፈተኛ ጣቢያ” ጥናትና ምርምር ዛሬ ተግባራዊ እየሆነ ላለው ተግባር ምን አስተዋፅኦ አድርጓል? ለ1948 ዓ.ም የደን በዓል ቀን የተባበሩት መንግሥታት የእርሻና የምግብ ድርጅት እገዛ ዛሬም ለተመሳሳይ ዓላማ እያገኘናቸው ካሉ እርዳታዎች ጋር ስናነፃፅረው ስለነገ መድረሻችን ምን ያሳየናል? በዘመኑ አፄ ኃይለሥላሴና የእለቱ የክብር እንግዶች የተከሏቸው ችግኞች አሁን ይኖሩ ይሆን?

ዛፍ እንደ ቅርስ፣ እንደ ሐውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ሆኖም አገልግሏል፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ፊት ለፊት በ”አፍሪካ ፓርክ” ውስጥ ያሉት እፅዋት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአህጉሪቱ መሪዎች የተከሏቸው ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም በታዋቂ ሰዎች የተተከሉ እፅዋት እንዳሉ መረጃ ከሚሰጡን መፃሕፍት አንዱ የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው “ዐፈር ያነሳ ሥጋ” የግጥም ስብስብ መድብል ነው፡፡

በ1964 ዓ.ም የታተመው ይህ መፅሐፍ ጥር 24 ቀን 1961 ዓ.ም የተፃፈና “አንድ ያልታደለ ዛፍ” የሚል ርእስ ያለው ግጥምን ይዟል፡፡ በዘመኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ኡ፡ታንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በደብረዘይት ከተማ የዛፍ ተከላ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡ ያንን ታሪክ ያዩት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በፃፉት ግጥም ውስጥ ቀዳሚው ስንኞች እንዲህ ቀርበዋል፡-

በቃ እንግዲህ ማጣቱ ነው

ነፃነት

ያ ዛፍ ኡ ታንት ተክሎት፡፡

ጠዋት ማታ፣ ያትክልቱ ጠባቂ

ያ አዋቂ

ሲደባብስ፣ ሲያካክክ፣ ሲኮተኩት

ዐይኑን ዐይኑን ሲያየው

ዛፍም ዐይን እንዳለው

ምናልባት

እና እያደነቀ ሲልለት

የኡ ታንት ዛፍ፣ እዩ አቆጠቆጠ

አበበ ፍሬ ሰጠ፡፡

ግጥሙ በአንድና ቀጥተኛ አቀራረቡ ታሪክን ሲያመለክት በምሳሌያዊ ትርጉሙ ደግሞ ተፈጥሮአዊ የሆነ በረከት፣ ፀጋና ስጦታ እንዴት እንደሚጠፋ፣ እንዴት እንደምንቀማ ያሳያል፡፡ የግጥሙ ማብቂያ ስንኞችም ለዚህ መልእክት አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ደኅና ሁኝ ነፃነት፣ ደኅና ሁኚ

የዚያ ዛፍ ነፃነት ደኅና ሁኚ

ሁለት ነገር አትመኚ፡፡

ሥልጣን! ሥልጣን! ሥልጣን ሥልጣኔ

ጽድቅና ኩነኔ

ሥልጣን፣ አትተፋ አትዋጥ

ነፃነት ቀማኛ፣ ሌሎች ነገሮችን ስትሰጥ፡፡

የዛፍና ባሕር ዛፍ ነገር ከአፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ የመንግሥት አንዱ ሥራ ወይም የፖሊሲ አካል ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡ በደርግ ዘመን ሰፊ የደን ልማት ፕሮጀክት ተነድፎ ተግባራዊ ሥራዎችም ተጀምሮ ነበር፡፡ የሚሊኒየም በዓልን ምክንያት በማድረግም ከግንቦት ወር 1999 ዓም ጀምሮ በየዓመቱ እፅዋትን በመትከል የሚታሰብ በዓል ተጀምሯል፡፡

እፅዋትን መትከል የአካባቢ ጥበቃ አካል መሆኑ የዓለም አገራት አጀንዳ ሆኖ ስለቀረበም ችግኝ ተከላ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ … ተበራክተዋል፡፡

ነሐሴ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ሻርፕ ኮምዩኒኬሽን ከወሊማ ሪዞርት ጋር በመተባበር በዱከም ከተማ ባከናወኑት የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኘው አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) አገር በቀል እፅዋት ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጿል፡

ከባህር ማዶ የመጡ ተክሎችን በአገር በቀል እፅዋት በመተካቱ ሥራም ቆም ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ብዙ ነገር ያለ ይመስላል፡፡

በ1948 ዓ.ም ከውጭ አገር በብዛት የመጡት የትኞቹ እፅዋት ናቸው? ባህር ዛፍ ከ120 ዓመት በኋላ የአገር በቀል እፅዋት አካል መሆን ሳይቻለው ለምን ቀረ? ለእፅዋት መተካካቱ የተመደበው በጀት ቢቋረጥ የአሳቡን ጠቃሚነት አምኖበት ገበሬው እንዲተጋበት ተደርጓል ወይ? የዛፍና የባህር ዛፍ ነገር ብዙ ሳያነጋግር አይቀርም፡፡

 

 

 

Read 5910 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:49