Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 12:58

የማዬት ፍሬ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ነይ ነይ በዳመና

ነይ ነይ በዳመና

ዱሩን ጥሶ፣ ሣሩን አጭዶ ፣ ባወጣው ጎዳና

ነይ ነይ በዳመና

(ዮፍታሔ ንጉሤ)

የተሣፈርንበት አውሮፕላን ምድሪቱን ሲለቅ ዐይኔን ጨፈንሁ፡፡ የከፍታ ፍርሃት አለብኝ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዕርገት መኪና (ሊፍት) ለመሣፈር አልደፍርም ነበር፡፡ የሦስተኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ተማሪ እያለሁ The future of an illusion የሚል የሲግመንድ ፍሮይድን መፅሐፍ አነበብኩና ከሃይማኖት ጋር ፍቺ ፈፀምኩ፡፡ ይሁን እንጂ አውሮፕላን ላይ በወጣሁ ቁጥር ለአጭር ጊዜ ሃይማኖተኛ እሆናለሁ፡፡ አውሮፕላኑ ሰማይ ላይ ሲደላደል የበረራ አስተናጋጇ ብቅ አለችና አደጋ ቢፈጠር ልናደርገው የሚገባንን ጥንቃቄ ታብራራልን ጀመር፡፡ ይህንን የጉዞ እድል ያገኘሁበትን ቀን በልቤ ረገምሁ፡፡

እንግዲህ ምን ይደረግ? ይቺን ዳመና አሳልፋችሁ አውርዱኝ አይባል ነገር!! “አውሮፕላኑ በባህር ላይ እንዲያርፍ ከተገደደ ከወንበርዎ ሥር ያለውን መንሣፈፊያ ትጥቅ እንዲህ አድርገው ይልበሱት፡፡ ከለበሱትም በኋላ እዚህ ጋ የሚታየውን ክር በተደጋጋሚ ይሳቡት፡፡ ያኔ ከረጢቱ በአየር ይሞላል” አለች አስተናጋጇ፡፡ ወይ አበሳ! ወይ ቀን አያውቁ! ወይ መንሣፈፊያ ከረጢት!

 

ለመሆኑ በአደጋ ሠዓት ከወንበሬ ሥር መንሣፈፊያ ከረጢት መኖር አለመኖሩን ይቅርና፣ ወንበር ላይ ልቀመጥ ጉቶ ላይ እንዴት ትዝ ሊለኝ ይችላል? ሰው አለቅጥ ሲደነግጥ እንዲህ ያለውን የጥንቃቄ ዝርዝር ይቅርና በሽንት ቤት እና በሱሪው መካከል ያለውን ልዩነት እንኳ ይረሣዋል፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ድንጉጦች በአደጋ ሠዓት ሽንታቸውን ለሱሪያቸው የሚያስረክቡት፡፡ አሁን አስተናጋጇ የምታቀርበውን የአደጋ ጥንቃቄ ተግባራዊ አድርጎ የዳነ ሰው ካለ ጀምስ ቦንድ መሆን አለበት፡፡ እኔ የበረራ አስተናጋጅዋን ብሆን ኖሮ የሚከተለውን ማለቴ አይቀርም ነበር፡፡ “ክቡራን መንገደኞቻችን አውሮፕላኑ ድንገተኛ አደጋ ከገጠመው በወንበርዎ ሥር የፀሎት መፅሐፍ ስላለ ያንን አውጥተው አጠር ያለ ፀሎት መርጠው ይድገሙ፡፡”

ትዝ ይለኛል፣ በመጋቢት ማጠናቀቂያ ላይ እንደ ገጠር ሎንቺና የሚንገጫገጭ አውሮፕላን ተሣፍሬ ወደ ባህር ዳር ስበር እንቅልፍ ሸለብ ያደርገኛል፡፡

በሕልሜ ከፓይለቱ ክፍል በማጉያ የሚመጣ ድምፅ “ክቡራንና ክቡራት ደንበኞቻችን በአሁኑ ጊዜ ከባህር ጠለል በላይ በሁለት ሺህ ሜትር ላይ እየበረርን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በድንገት የአውሮፕላኑ ሞተር ስለጠፋብን በከባድ ጭንቀት ላይ እንገኛለን፡፡

ስለዚህ ካሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ሞባይላችሁን ከፍታችሁ ለቤተሰቦቻችሁ የስንብት ቃል ወይም ኑዛዜ ማስተላለፍ እንደምትችሉ ስገልፅ ሐዘን ይሰማኛል” ይላል፡፡ ወዲያው የአውሮፕላን ሆድ በሽብር ይታመሣል፡፡ ሽንትና እንባ ተቀላቅሎ ይፈሣል፡፡ ከጥቂት ትርምስ በኋላ ፓይለቱ “ክቡራንና ክቡራት ደንበኞቻችን የጠፋውን ሞተር ካፖርት ኪሴ ውስጥ ስላገኘሁት ተረጋጉ፡፡ በነገራችን ላይ አፕሪል ዘ ፉልን ምክንያት በማድረግ ያዝናናኋችሁ ካፒቴን ገብረመስቀል ነኝ፡፡ መልካም በረራ” ይልና ይስቃል፡፡

ከዚህ ህልም በኋላ አውሮፕላን ላይ ላለመተኛት ወሰንኩ፡፡

የበረራ አስተናጋጇ በአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ አስቦክታኝ ወደ ኩሽና ስትገባ ወደ ግራዬ ዞር አልሁ፡፡ በጢም ቁጥቋጦ የተሸሸገ ተሣፋሪ አጠገቤ ተቀምጧል፡፡

እድሜ ለቢንላደን ጢማም! ሰው ባየሁ ቁጥር የሚቃጠል ሕንፃ አብሬ አያለሁ፡፡ ጢምና ነውጥ ተቆራኝተው ታዩኝ፡፡ በዓላማችን ላይ የተፈራረቁ ነውጠኞች ወይም የነውጥ ሰበቦች ጢማም ወይም ሙስታሻም ሲሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ልጩዎች ናቸው፡፡ የማሕታማ ጋንዲን፣ የማርቲን ሉተር ኪንግን እና የማንዴላን ጢም አልባ አገጭ ይመለከቷል፡፡ ስልጣኔ ማለት ተፈጥሮን መከርከም ነው፡፡ ጢሙን መግታት የማይቻል ሰው ምናልባት ደም ፍላቱንም መግታት አይችል ይሆናል፡፡ ጢማሙን ነውጠኛ ጢመ-በራውን ሰላማዊ የሚያደርገው ምደባዬ፣ ከአጉል እምነት የሚጠጋ ሀሳብ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ቢሆንም አእምሮዬ እንዳይቦዝን አገልግሎኛል፡፡ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ሀሳቤ ሲያልቅ ሰውዬውን ደግሜ ተመለከትሁት፡፡ እጅግ ጠብደል ከመሆኑ የተነሣ ያለ ምንም የጦር መሣሪያ በጥፊና በእርግጫ ብቻ አውሮፕላኑን መጥለፍ የሚችል ነው፡፡ በአይነ ቁራኛ እሾፈው ጀመር፡፡ ትንሽ ቆይቶ ብድግ አለና ከፓይለቶቹ ክፍል አጠገብ በሚገኘው ሽንት ቤት ውስጥ ገብቶ ሰነበተ፡፡ ኧረ ይሄ ነገር አላማረኝም፡፡ ሰውዬው ኑሮውን ነው የሚፀዳዳው? ሽንት ቤቱን ለብቻው ነጥሎ ሳይጠልፈው አልቀረም፡፡ Ladies and gentlemen  the toilet has been hijacked! so please remain seated የሚል ማሳሰቢያ መጠበቅ ጀመርሁ፡፡ አውሮፕላኑ የኔን ሥጋት እያስተባበለ ካርቱምን አልፎ ካይሮን ቁልቁል ገላምጦ ሜዲትራኒያንን ማቋረጥ ጀመረ፡፡

ዞር ዞር ስል ጥቂት ተሣፋሪዎች በንባብ ተጠምደዋል፡፡ እኔም የገዛ ሐሳቤን ማንበብ ጀመርሁ፡፡

አውሮፕላን የሰው ልጅ የመብረር ምኞት ያስገኘው የቴክኖሎጂ ፍሬ ነው፡፡ የጥንት ኢትዮጵያውያን የመብረር አምሮታቸውን በስዕልና በተረት ተወጥተውታል፡፡ ባህላዊ ስዕላችንን ብታዩ በክንፍ የተሞላ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ዝነኛው የስክንድስ ተረትም እዚህ ላይ ሊነሣ ይችላል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እስክንድስ የተባለ ጀግና፣ ፈረስና ንሥር አዳቅሎ (ለተረት ምን ይሣነዋል!) የሚበር ሥጋ በል ፍጡር አስገኘ፡፡

እስክንድስ በራሪው ፈረስ ላይ ይወጣና የሥጋ ብልት በሜንጦ ይዞ በፈረሱ አፍ ግድም ያንጠለጥለዋል፡፡ በራሪው ፈረስ ሥጋውን አገኛለሁ እያለ እመር ሲል ምድሪቱን ለቅቆ ወደ ሰማይ ይወጣል፡፡ ተረቱ ወደ ገሀድ ሲተረጐም የእስክንድስ ፈረስ አውሮፕላን፣ የሜንጦው ስጋ ያውሮፕላኑ ትኬት ይሆናል፡፡

አባቶቻችን (እናቶቻችንም) አስደናቂ ምናብ እንደነበራቸው አያጠራጥርም፡፡ የምናባቸውን ስዕል ወደ እውን ለመቀየር ግን ድፍረት የነበራቸው አይመስልም፡፡ ምናልባትም ትሕትና ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ አድርጓቸው ይሆናል፡፡ በዳመና ላይ የመጋለብ መብት ያላቸው መላእክት እና እንደ ኤልያስ ያሉ መላእክት አከል ቅዱሳን ብቻ ናቸው ብለው የታቀቡ መሰለኝ፡፡ “አልበር እንዳሞራ ሰው አርጐ ፈጥሮኛል” የሚለው ዘፈን ሁኔታውን በደንብ ይገልጠዋል፡፡

ሰው ራሱን በአሞራ አምሳል እንደገና መፍጠር እንደሚችል የተገለጠለት ዳቪንቺ ግን የበረራ መኪናዎችን ነደፈ፡፡ እነሆ እኔም አባቶቻችን ባልለሙት የራይት ወንድማማቾች በተረጐሙት የእስክድስ ፈረስ ላይ ተፈናጥጬ ወደ ሀገረ እንግሊዝ ለመጋለብ በቃሁ፡፡

አውሮፕላን ወደ አገራችን በገባ ሰሞን ህዝቡ እንዲሳፈር ማሳመን ቀላል አልነበረም፡፡ የዛሬ ዘጠና ዓመት አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ለቅስቀሳ የፃፈውን ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ማንበቤ ትዝ አለኝ፡፡

“በድፍን አውሮፓ” ይላል አፈወርቅ “በድፍን አውሮፓ እንኳን ወንዶች ሴቶች ሳይቀሩ  ራሳቸው እየነዱ በዚህ በአይሮፕላን አገር በአገር ሲሮጡ ሲራወጡ ይኖራሉ፡፡ ምንም አያገኛቸውም፡፡

አሁን በቅርቡ ያገራችን ወይዘሮ የነጋድራስ መኮንን ባለቤት ወይዘሮ ዘውዲቱ በዚሁ በአይሮፕላን መሄዳቸውን ብርሃንና ሰላም አስታውቆናል፡፡

በአማሪካ አገር ገረዶች ሳይቀሩ ማለዳ ማለዳ ለጌቶቻቸው የሚገዙትን የለት ምግብ ባገለልግላቸው ቆልፈው ይዘው ታንዱ ገቢአ ወደ አንዱ እየሳቁ እየተሳለቁ በዚህ በሰማይ መርከብ ሲሄዱ እንሞታለን ብለው ምንም አይፈሩ፡፡ በአውሮፓ አገር በየከተማውና በየተራራው ሺህ የሺህ ኤሮፕላን እንዳንበጣ አየሩን እያላበሰ ነፋስና ዳመናውን እየቀደደ ሲራወጥ ይውላል፡፡ እንደ ብዛቱ መጠን ግን ሞት የለበትም፡፡ አያስፈራም፡፡ ከሺህ አንድ ቀን አንዱ ቢወድቅና ሰው ቢሞት አያስደንቅም፡፡ ስለምን ሞት ጉግሥ ሲጫወቱ ፈረስ እየተንደላቀፈ፣ ፈረሰኛ እየወደቀ ይሞታል ይሄም ይሄን አከል ነው”

በአፈወርቅ ጽሑፍ ውስጥ ያውሮፕላን ኢትዮጵያዊ ስሙ “የሰማይ መርከብ” እንደነበር እንረዳለን፡፡

ስያሜው በዘፈቀደ የወጣ አይመስልም፡፡ አባቶቻችን በአየር ላይ ባህር አለ ብለው ያምኑ ነበር፡፡ “አንዱ እጅ ውኃ ከጠፈር በላይ ተሰቀለ፤ ስሙንም ሀኖስ አለው” እንዲል መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት፡፡ በአየር ላይ ባህር ካለ አውሮፕላን የሰማይ መርከብ መሆን አለበት፡፡

በጊዜው ወይዘሮ ዘውዲቱ በአውሮፕላን ላይ ለመሳፈር መድፈራቸው ለጋዜጣ የሚበቃ ክስተት ኖሯል፡፡ ይህም በወቅቱ በአውሮፓ ስልጣኔ እና በኢትዮጵያ ውጥን ስልጣኔ መካከል የነበረውን መራራቅ ያሳየናል፡፡ በአውሮፓ አውሮፕላን የእለት ተእለት ልምድ በሆነበት በዚያን ዘመን፣ በእኛ አገር በመንኮራኩር የመምጠቅን ያክል ትንግርት ነበር፡፡  የአፈወርቅ አላማ ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ አውሮፕላን ላይ እንዲወጣ ማደፋፈር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከጠላት ጋር የመተናነቅ ድፍረት እና ከአዲስ መሺን ጋር የመግባባት ድፍረት ለየቅል መሆናቸው የተገለጠለት አይመስልም፡፡

አፈወርቅ በቅስቀሳ ጽሑፉ ውስጥ “ከሺህ አንድ ቢወድቅ እንኳ” ብሎ እንደገና አስቦካኝ፡፡

ይሄ አውሮፕላን ከሺህ አንዱ አለመሆኑን በምን ላውቅ እችላለሁ? አፈወርቅ ሞትን ቢያናንቅ አይገርመኝም፡፡ ይሄንን በሚጽፍበት ጊዜ ሸምግሏል፡፡ ኑሮን ካጤ ምኒልክ ቤተመንግስት እስከ አውሮፓ ድረስ አጣጥሞታል፡፡

እኔ ግን…

ከወንበሬ ጋር የተቆራኘሁበትን ቀበቶ ፈታሁና እየተንገዳገድሁ የበረራ አስተናጋጆች ምግብ ወደሚያበስሉበት ያውሮፕላኑ ኩሽና ሄጄ መጋረጃ ገልጬ ገባሁ፡፡ ሁለት ቆነጃጅት የበረራ አስተናጋጆች ከምድጃቸው ላይ ቀና ብለው በግርምት ተመለከቱኝ፡፡

“ትርፍ ፓራሹት ይኖራችኋል?” አልኳቸው፡፡

ሲስቁልኝ ጊዜ ፍርሃቴ ጥሎኝ ጠፋ፡፡

ከዚያ እንድቀመጥ ጋብዘውኝ፣ የክት ምግብና መጠጥ አቅርበውልኝ እንደ ጋዳፊ በቆነጃጅት ታጅቤ የሮማን ሰማይ አለፍሁ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ያውሮፕላኑ ምክትል ነጂ ያለሁበት ድረስ መጥቶ የምፈልገው ነገር እንዲዘጋጅልን አሳሰበ፡፡ በርግጥ የምፈልገው ካውሮፕላኑ መውረድ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር ያውሮፕላኑ ቤተሰቦች ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢሚግሬሽን ዘበኛ ያደረሰብኝን በደል ካሱኝ፡፡ ትዝ ይለኛል፡፡

የይለፍ ጦማሬን (ፓስፖርቴን) ለማሳደስ ኢሚግሬሽን ገስግሼ ብሄድ፣ የደጅ ጠኚው ሰልፍ አሥር ቦታ ተጠማዞ የኮንሶን እርሻ መስሎ ጠበቀኝ፡፡ እውን ይሄ ሁሉ ሠልፍ የፓስፖርት ነው ወይስ ኢሚግሬሽን ስኳርና ዘይት ማደል ጀምሯል? በማለት እያጉተመተምሁ አጠር ያለውን ሠልፍ መርጬ ቆምሁ፡፡

ወድያው ግን ከየት መጣ ያላልኩት፣ በአንገቱ ላይ የታይሰን ፊት፣ በትከሻው ላይ የተርምኔተር ክንድ የተገጠመለት ዘበኛ እንደ በቆሎ በገዛ ኮቴ አንጠልጥሎ ቢወረውረኝ በአካባቢው በሚገኝ የጉልት አምባሻ ላይ ባፍጢሜ ወደቅሁ፡፡ የአረብ መንደገኛ ሁላ ለጊዜው ትካዜውን ረስቶ ባወዳደቄ ሳቀ፡፡

ለንደን ገባሁ፡፡

ለንደን እንደገባሁ በመጀመሪያ ያደረግሁት የፊደል ገበታ የሠፈረበት ካናቴራ ለብሼ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ በመንሸራሸር አገሬን ማስተዋወቅ ነበር፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ ግን ባለፊደል ካናቴራ ቀርቶ የቄስ ትምህርት ቤት ተሸክሜ ብሔድ እንኳ ትኩረት እንደማላገኝ ገባኝ፡፡ በርግጥ አንድ ሁለት ፈረንጆች ዞር ዞር እያሉ ባድናቆት ተመልክተውኛል፡፡ ያድናቆታቸው ምንጭ ግን እንዴት በዚህ አጥንትን በሚቆረጥም ብርድ ካናቴራ ለብሶ ይወጣል የሚል እንደሆነ ጠርጥሬያለሁ፡፡ ለንደን ውስጥ አይን ማግኘት በጣም ብርቅ ነው፡፡ በዚያው መጠን ዞር ብሎ ከማያያቸው ሕዝብ ጋር እልህ የተጋቡ የሚመስሉ፣ ለመታየት ተግተው የሚሠሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከላይ እስከ ታች በንቅሳት ተዥጐርጉሮ የጥምቀት ሽመል የሚመስል ወደላ ፈረንጅ ተመልክቻለሁ፡፡ ፊቷ ላይ አራት ትልልቅ ቀለበት ደርድራ ጽናጽል የመሰለች ሴትዮ ተመልክቻለሁ፡፡ በዚህ መሀል የኔ ካናቴራ ብርድ እንጂ ትኩረት እንደማትስብ ስገነዘብ ሆቴሌ ገብቼ ካፖርት ደረብሁ፡፡

 

 

Read 7906 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 13:02

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.