Print this page
Saturday, 18 August 2012 12:38

የ‹‹የሺሕ ጋብቻ›› ፕሮጀክት ተራዘመ አንድ ሺሕ ተጋቢዎችን በሕዳር እሞሽራለሁ ብሏል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ኤሚነንስ መቼ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድነው?

ኤሚነስን ሶሻል ኢንተርፕረነርስ ኃ.የተ.ማ የተመሰረተው በ2002 ዓ.ም ነው፡፡የድርጅቱ ስያሜ እንደሚገልጸው፣በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶች ምንድናቸው? ደንበኞቻችን ምን ይፈልጋሉ?፣እነዚህ ክፍተቶች እንዴት ነው መጥበብ የሚችሉት? የትኞቹ ችግሮች ናቸው ተሟልተው በቅርቡ በገበያ ውስጥ ተቀባይነት የሚኖራቸው?ብሎ በማጥናት አዳዲስ የአሠራር ስልቶች በመንደፍ የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ በተለያዩ ዘርፎች እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም ነው፡፡

በምን በምን ዘርፎች ነው የምትንቀሳቀሱት?

ኤሚነንስ በዋነኛነት የሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ነው፡፡በዚህ ዘርፍ ሰፋፊ ዘጋቢ ሥራዎች፣ዌብሳይት ዴቬሎፕመንት፣ ማስታወቂያዎች፣ ዓመታዊ ሪፖርቶች፣ ዝግጅቶች ላይ ተገኝቶ በቪዲዮና ካሜራ መቅረፅ፣ ግራፊክ ዲዛይን … ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ሌላው ከደንበኞቻችን በሚቀርብልን ጥያቄና ፍላጎት መሠረት ሥልጠናዎችን አዘጋጅተን እንሰጣለን፣ የተለያየ መጠን ያላቸው አዳራሾች ስላሉን ስብሰባዎችን እናዘጋጃለን፡፡

ዋነኛውና ሁለተኛው ዘርፍ ክዋኔ ማዘጋጀት ነው፡፡በዚህ ዘርፍ ሁለት ሥራዎች አሉ፡፡ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ዝግጅት ኖሯቸው ሲጠይቁን ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ባለሞያዎች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ በሚፈልጉት መንገድና የጥራት ደረጃ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡

ትልቁና ዋነኛው የኤሜነስ ክዋኔ ዘንድሮ ልናካሂድ አቅደን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ 2005 የተሸጋገረው ‹‹የሺህ ጋብቻ 2004›› ፕሮጀክት ነው፡፡ይህ ፕሮጀክት ‹‹ቤተሰብ መመሥረት፤ ኅብረተሰብን መመሥረት›› በሚል መርህ ላይ ተመሥርቶ የተንዛዛውን የሠርግ ድግስ፣ የጊዜና የገንዘብ ብክነት ከማዳኑም በላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋብቻ ባህልና ወግ ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ነው፡፡

ከማኀበራዊ ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው ቤተሰብ ነው፡፡ቤተሰብን ስናስብ የሚጀመረው ከጋብቻ ነው፡፡ በአገራችን ጋብቻ ምን ይመስላል? ምን ይዘትስ አለው? የቤተሰብስ ሁኔታ ወይም አቅም ምን ይመስላል? የሚሉትን በመፈተሽ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ተቀባይነት ባለው ደረጃ አገራዊ ይዘት ጠብቆ ሕዝብንና አገርን በሚጠቅም መልኩ ቤተሰብ መመሥረት አለበት ብለን ስለምናምን ከመላ አገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ አንድ ሺህ ጥንዶች፣ ባህልና ወጋቸውን እንደጠበቁ ለመዳር ሰፊ ዝግጅት አድርገናል፡፡

የሺህ ጋብቻ ዋነኛ ዓላማ ቤተሰብ ለመመሥረት ፈቃደኛ የሆኑ ጥንዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ካለው አላስፈላጊና ኋላ ቀር የሠርግ ድግስ ወጪን በማስቀረት ቤተሰብን በቀጣይነት መምራት እንዲችሉ ተጋቢዎችን ያለ ምንም ክፍያ (ወጪ) በነፃ በመዳር ለድግስ ያሰቡት ወጪ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን ለመለወጥ ሀብት እንዲሆናቸው ለመርዳትና ለማስተማር ነው፡፡

የሺህ ጋብቻ ዓላማ ቤተሰብ መመሥረት ብቻ ሳይሆን፣ ቤተሰብ፣ ሀገርና ኅብረተሰብ የተመሠረተበት ተቋም በመሆኑ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት ቅድመና ድህረ ጋብቻ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው፡፡ ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊት ሥልጠናና የምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተሰብ ከመሠረቱም በኋላ ከእርግዝና፣ ከወሊድና ልጅ ከማሳደግ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን በየአካባቢያቸው ባሉ ተቋማት የሚጠቀሙበት ሁኔታ ያመቻቻል፡፡

ይህ ጋብቻ ሌላም ይዘትና መልክ አለው፡፡ ይህም የአገራችንን ባህል በጠበቀ መልኩ መፈፀሙ ነው፡፡ አገራችን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የያዘች ናት፡፡ የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ባህል የጋብቸ አፈጻጸም አለው፡፡

ይህ ጋብቻም በጥንዶቹ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ አሸብርቆ በሰርግ ዘፈንና ጭፈራ ደምቆ፣ ባህላችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ አገራችን ለዘመናት የምትታወቅበትን መጥፎ ገጽታ በመለወጥ ኢትዮጵያ የአብሮትና የአንድነት፣ ልዩነት ውበት የሆነባት አገር መሆኗን ለዓለም አቀፉ ኀብረተሰብ የምናሳውቅበት ትልቅ ፕሮጀክትና አጋጣሚ ነው፡፡

የሺህ ጋብቻ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም አለው፡፡ 75 የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋብቻ በዓል ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሲተላለፍ (በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ታቅዷል) በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ ገበያን የመሳብ አቅም ያለው ዝግጅት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአገር ውስጥ የቱሪስት እንቅስቃሴንም ያጐለብታል የሚል እምነት አለን፡፡ በአካባቢው አነስተኛና ጥቃቅን አምራቾች የተወሰነው የባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች ምርት እሴት፣ ጥራትና ደረጃ ጨምረው በኢንዱስትሪ ደረጃ በፋብሪካ ተመርተው፣ የአገር ውስጥ ገቢና የውጭ ምንዛሪ ሊገኝበት የሚችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ፣ አንዱ የሌላውን ባህል፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጥ፣ አዘፋፈን፣ አጨፋፈር፣ … የወግ ዕቃ፣ … እንዲያውቅ፣ እንዲያከብር፣ እንዲጠቀምበት፣ … ሊያደርግ ይችላል፡፡

አንድ ሺህ ጥንዶችን እንዴት ነው የምትመርጡት?

ይህን ፕሮጀክት ከቀረፅን በኋላ የተለያዩ መንግሥታዊ አካላትን ማናገር ነበረብን፡፡ ከእነዚህ አካላት ደግሞ ዋነኛው በሚወክለው ም/ቤት በጥልቀት ከተመረመረና ከተጠና በኋላ አፈ-ጉበኤው ለዘጠኙ ክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በክልላቸው ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተጋቢ ጥንዶችን መልምለውና መርጠው ለፕሮጀክቱ እንዲያዘጋጁ የተለያየ ኃላፊነቶችን የሰጠ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከም/ቤቱ፣ ከፕሮጀክቱና ከተለያየ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ወደየክልሎቹ ተጉዞ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በመሆንም የተለያዩ ሥራዎችን ስለሠራን ቢሮዎቹ ጥንዶቹን እየመረጡ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ 125 የምሥረታ በዓሏን እያከበረች ስለሆነ 125 ጥንዶችን እንድትመርጥ ኮታ ስለተሰጣት መስተዳድሩ በየክፍለ ከተሞች መረጣ እያካሄደ ነው፡፡

ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሰጠው ኮታ 10 ነው፡፡

በእነዚህ መዋቅሮችና በመገናኛ ብዙኃን በሚካሄድ እንቅስቃሴ ነው ምልመላው እየተካሄደ ያለው፡፡

በምን መስፈርት ነው ጥንዶቹ የሚመረጡት?

በእኛ ድርጅት የተረቀቀ እና በተለያዩ አካላት ተተችቾ ሥራ ላይ የዋለ የመመልመያ መስፈርት አለ፡፡

እነዚያን ሕጋዊ መስፈርቶች ያሟሉ ጥንዶችን ነው የምናጋባው፡ ከመስፈርቶቹም ጥቂቱ ዕድሜዋ/ው ለጋብቻ የደረሰ፣ ለመጋባት ፈቃደኛ የሆኑ፣ ራሳቸውን መደገፍ የሚችሉበት ገቢ ያላቸው፣ ከአሁን በፊት ያላገቡ፣ … የሚሉ ናቸው፡ የክልል መንግሥታት ባላቸው መዋቅር መሠረት መስፈርቶቹን የሚያሟሉ ጥንዶችን መልምለውና መርጠው ይልኩልናል፡፡

ጋብቻው የሚደረገው መቼና የት ነው?

የጋብቻው ሥነ-ሥርዓት የሚፈመው በአዲስ አበባ ስታዲየም ነው፡፡ ቀደም ሲል የዚህን ዓመት የሺህ ጋብቻን ለማድረግ የታቀደው ሰኔ 17 ቀን 2004 ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኅዳር 8 ቀን 2005 ተላልፏል፡፡

በምን ምክንያት ተላለፈ? በእናንተ ችግር ወይስ በሌላ?

በእኛ ችግር አይደለም፤ ክልሎች ባቀረቡት ጥያቄ ነው፡ ያቀረቡት ምክንያትም አሳማኝ በመሆኑ ሊተላለፍ ችሏል፡ የተጋቢ ጥንዶች ምልመላ ከፆም ወቅት ጋር በመያያዙ ተፅዕኖ መፍጠሩን፣ በመስፈርቱ መሠረት ተጋቢዎቹን መርጦ ለማቅረብ የጊዜ እጥረት ስላጋጠማቸውና የመኸር እርሻ ወቅት በመሆኑ ቀኑ እንዲተላለፍ በጠየቁት መሠረት ነው ከፌዴሬሽን ም/ቤት ጋር ተመካክረን ቀኑ የተለወጠው፡

እያንዳንዱ ተጋቢ በባህሉ አልባሳትና ጌጣጌጥ የሚሞሸረው ብላችኋል፡፡ ለአንድ ሺህ ጥንዶች እነዚህን ቁሳቁስ መሰብሰብ አይከብድም?

በዚህ ሠርግ እንዲታይ የምንፈልገው ባህላዊ አልባሳትና አለባበሳቸው፣ባህላዊ ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ የፀጉር አሠራር፣… ሌሎች የመዋቢያ ሁኔታዎች፣ ዘፈንና ጭፈራ ነው፡፡

የእያንዳንዱ ክልል መንግሥት የጥንደቹን አልባሳትና ጌጣ-ጌጥ፣ ደርሶ መልስ የትራንስፖርት ወጪ ይችላል፡፡ የጋብቻ ሥነ-ሥርዓቱ ግን ለሁሉም አንድ ዓይነትና ወጥ ይሆናል፡፡

በማዘጋጃ ቤት ሥነ-ሥርዓት ይሆንና ከጋብቸው ቀን በፊት የጋብቻ ፊርማ የሚፈፀምበት ሥነ ሥርዓት ይኖራል፡፡ እዚህ እንዲታይ የሚፈለገው ኀብረ-ቀለማዊ የሆነ የአልባሳት፣ የጌጣ-ጌጥ የተለያዩ መዋቢያ፣ … ትርዒት ነው፡፡ የምግብ፣ የአልባሳትና የጌጣ-ጌጥ ኤግዚቢሽንም ይኖራል፡፡

ጥንዶች ጋብቻ የሚፈጽሙት ብቻቸውን አይደለም፡፡ ወላጆች፣ ዘመድና ጐረቤት፣ ሚዜና አጃቢ፣ እድምተኞች፣ ሠርጉን የሚያደምቁ ሙዚቀኞች .. ይኖራሉ፡፡ እንዴት ነው እነዚህ ክፍሎች የሚሳተፉት?

ባህላዊ የሆነው ጭፈራና ጨዋታ በባህል ቡድኖች የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በየክልሉ ያሉ የባህል ቡድኖች ለየክልላቸው ተጋቢዎች ባህላዊ ጨዋታዎችን የማቅረብ ዕድሉ አላቸው፤ የጠየቁም ክልሎች አሉ፡፡ ወላጆች፣ ሚዜዎችና አጃቢዎች ወጪያቸውን ራሳቸው ችለው በዚህ ፕሮግራም ላይ መገኘት ይችላሉ፡፡

አንድ ሺህ ጥንዶች ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሲጋቡ ማረፊያ፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት፣ … ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ምን ታስቧል?

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በብሔራዊ ደረጃ ተይዞ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ኮሚቴው ከባህልና ቱሪዝም፣ ከአ.አ ከተማ አስተዳደር፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ማኅበር፤ ከአስጐብኚ ድርጅቶች ማኅበር፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ፣ ከፌዴሬሽን ም/ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር፤ ከየሺህ ጋብቻ ፕሮጀክት የተውጣጡ አባላትን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

እርግጥ ነው፤ ጥንዶቹ ሲመጡ፣ ምግብ፣ ማረፊያ፣ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት፣ … ያስፈልጋቸዋል፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው የድርጊት መርሐ ግብር ነድፎ፣ የእያንዳንዱ አካል ኃላፊነት ተለይቶ ለእያንዳንዱ አስፈላጊ ነገር ወጪ ተመድቦ በመንቀሳቀስ ላይ ነን፡፡

ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድ እንደ አዘጋጅነቱ ከክልል ለሚመጡት 875 ጥንዶች የመኝታ አገልግሎት አዘጋጅተናል፡፡125ቱ የከተማዋ ነዋሪ ስለሆኑ የራሳቸው ማረፊያ ስላላቸው አገልግሎቱ አይመለከታቸውም፡፡ ምግብና ድንገተኛ አደጋን በተመለከተ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እየተዘጋጁበት ነው፡፡

የየሺህ ጋብቻ ፕሮጀክት በዓለማችን የመጀመሪያው ነው ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የሚሳተፉት 75 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የራሳቸው ቋንቋ፣ የራሳቸው ባህል፣ የራሳቸው አለባበስ የራሳቸው አፈጣጠር፣ ያላቸው ናቸው፡፡

በቻይና፣ ኮሪያ፣ …በመሳሰሉ አገሮች ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ጥንዶች በአንድ ጊዜ ይጋባሉ፡፡ የእኛን ልዩ የሚያደርገው በጋብቻ ወቅት የሚለበሱ ልብሶቻችን፣ አጋጌጣችን፣ አዋዋባችን፣ ምግባችን፣ ሙዚቃችን፣ አጨፋፈራችን ነው፡፡

የሺህ ጋብቻ ሥነ ሥርዓት በቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፍ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ባህላችን ሊከበር፣ ዋጋ ሊኖረው፣ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ፣ ጥቅም ሊያስገኝ፣…ይገባል፡፡ ይኼ ነው ትልቁ ጉዳይ፡፡ ለዚህ ነጥብ ስኬት ኤሚነንስ ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣…በአጠቃላይ መላው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

የሺህ ጋብቻ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን በጐ ገጽታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

ከአካል ጉዳተኞችና ኤችአይቪ በደማቸው ከሚገኝባቸው ሰዎች ማኅበራት ከእያንዳንዱ 50 በአጠቃላይ 100 ጥንዶች፣ ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 375 ከአ.አ 125 ከድሬዳዋ 10፣ ከትግራይ 32፣ ከአፋር 10፣ ከአማራ 140፣ ከኦሮማያ 180፣ ከሶማሌ 25፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ 5፣ ከሐረሪ 5፣ ከጋምቤላ 5፣ ከደቡብ 20 ጥንዶች በየሺህ ጋብቻ -2004 ፕሮጀክት ጐጆ ይመሠርታሉ፡፡

በመጨረሻ

ከእነዚህ ጥንዶች መካከል ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተመረጡት 375 ሙሽሮች በባህላዊ አለባበስ፣ አጋጌጥ፣ ዘፈን፣ ጭፈራና ዳንስ ደመቀው ይሞሸራሉ፡፡ለክልሎችና ለሁለቱ ከተሞች ከተሰጠው ኮታ ውጭ ያሉ ለጋብቻ የተዘጋጁ ጥንዶች “እኛም’ኮ ዕድሉን ብናገኝ ሙሉ ወጪያችንን ችለን አዲስ አበባ ሄደን በባህላዊ አልባሳችን፣ ጌጣችን፣ መዋቢያችን፣ … አምረን፣ ተውበንና ደምቀን እንጋባ ነበር” የሚሉ ሰዎች ካሉ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መጋባት እንደሚችሉ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች፣ የወጣውን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጋዊ ማስረጃ ያላቸው ሰዎች እስከ መስከረም 10 ቀን 2005 ድረስ በየክልሉ ባሉ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮዎች ተመዝግበው ማረጋገጫ መያዝ አለባቸው፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻ እንዳይፈሙ፣ ሁለቱም ፆታዎች ከአሁን ቀደም ያላገቡ መሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ አቅርበው ሳያፀድቁና ማረጋገጫ ሳይዙ ወደ አዲስ አበባ መንቀሳቀስ የለባቸውም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

 

 

Read 1602 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 12:43