Saturday, 21 July 2012 10:11

“ሁለቱም ተለዩ ከእናት ከአባታቸው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

ስሙኝማ… ስለ ወፍራምነት ካወራን አይቀር… ከዚህ በፊት አንስተናት ሊሆን የሚችለውን አንዲት ‘ስቶሪ’ ስሙኝማ… ሴትየዋ በጣም ወፍራም ነች፡፡ አንድ ጊዜ ለአንዱ ወዳጇ “የገዛ ጥላዬ ከኋላዬ ሲሆን ያስፈራኛል…” ትለዋለች፡፡ እሱ ምን ቢላት ጥሩ ነው… “መፍራት ይገባሻል፡፡ የአንድ ቀበሌ ህዝብ የሚከተልሽ ነው እኮ የሚመስለው!”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ይቺን ስሙኝማ… አንድ ወዳጄ ለልጆቹ ባቅላባ ሊገዛላቸው አንዱ ፒያሳ ኬክ ቤት ይገባል፡፡

እንዳጋጣሚ ባቅላባ የለም ነበርና ከአንዱ ገበያተኛ ጋር ወግ ቢጤ ይይዛል፡፡ ታዲያ ወዳጄ የባቅላባን መወደድ አንስቶ ትንሽ የንጭንጭ ዲስኩር ቢጤ ሲያሰማ ሰውዬው “አንተ ባቅላባ የምታውቀው በስንት በሚሸጥበት ጊዜ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ወዳጄም “እኔ ብር ተስሙኒ በነበረ ጊዜ ነበር ስበላ የነበረው” ይላል፡፡ ይሄኔ ሰውዬው ምን አለው መሰላችሁ… “በዛ ዋጋ ባቅላባ የበሉት ሁሉ እኮ አልቀዋል!”

እናላችሁ… ምን ነገር አለ መሰላችሁ… ብዙ ጊዜ ከድሮ ነገር መላቀቅ ያቅተናል፡፡ የምር እኮ… የሚገርም ልማድ ነው፡፡ ለጡረታ አምስት ወር ከአስራ ሰባት ቀን የቀረው ሰውዬ መጀመሪያ ሥራ በተቀጠረ በአራተኛው ወር የገዛት ካፖርት አብራው ልትኖር ትችላለች፡፡

ወይም ደግሞ… ሰውየው አንድ ለክረምት የምትሆን ጃኬት አድርጐ ታዩትና “ይቺን የምትሞቅ ጃኬት የት አገኘሃት?” ምናምን ስትሉት ምን ይላል… “ይገርምሃል፣ ያኔ የኮሪያ ዘመቻ ጊዜ የማረኩት አንድ የሰሜን ኮሪያ ወታደር በመልካም ሁኔታ ስለያዝኩት ስጦታ የሰጠኝ ነው…” ቢባል አንዳንዴ ላይገርም ይችላል፡፡ (ማጋነን ለሁሉም የተፈቀደና ብቃት ማረጋገጫ፣ ቲኦቲ… ቅብጥርስዮ የሚባል ነገር ስለሌለው ለእሱም ‘የአፈፃፀም መመሪያ’ እስኪወጣለት እንክት አድርገን እናጋንናለን!”)

እናማ… ልማድ ሆኖብን ሁሉን ነገር ሙጭጭ እንልና አንድ ቀን ጐተት አድርገን… “ይገርምሻል፣ ይቺ ጫማ አንቺን ከማግባቴ በፊት ውድ ተብሎ በስድሳ ብር የገዛኋት ነች፡፡” የባልና ሚስቱ የመጀመሪያ ሴት ልጅ ሦስተኛ ልጇን ከተገላገለች ይኸው ነሐሴ ሲመጣ ድፍን ሁለት ዓመቷ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… ጥያቄ አለን… ዩኔስኮ አሮጌ ልብስና ጫማ በዓለም ቅርስነት የሚመዘግብበትን ህግ ያውጣልንማ!

እናላችሁ… ችግሩ ምን መሰላችሁ… የልብስና የጫማ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ብዙዎቻችን የድሮው ነገር ላይ ሙጭጭ ብለን “እስቲ የሚነቀንቀኝን ወንድ አያለሁ!” አይነት ነገር የምንል ነወ የሚመስለው፡፡ “የነበራችሁን ሁሉ ጣሉ” እንደሚባለው እንደ አንዳንድ ቀሺም ሰበካ ሳይሆን ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ጋር የማይመቹ አስተሳሰቦችን መተካቱ አሪፍ ነው፡፡

ቦተሊካችን እንዲህ አይንና ናጫ ያደረገን እኮ… አለ አይደል… ብዙዎቻችን አሁንም አስተሳሰባችን ብዙ ክፍለ ዘመን ወደኋላ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴማ… ክርክሮችን ስትሰሙ ኢዲ አሚን ኔሬሬን “ህዝባችን ከሚጣላ እኔና አንተ ይዋጣልን” አሏቸው የተባለውን አይነት ነገር ይመስላል፡፡

እናማ አስተሳሰብ እየተሻሻለና ከጊዜው ጋር አብሮ እየተለወጠ ካልሄደ “መማር ምን ዋጋ አለው!” ያሰኛል፡፡ ከቦተሊካው ገመድ በሁለቱም ተቃራኒ ጫፍ ያሉት ትምህርቷን የበጠሷት ናቸው ይባል የለ፡፡

እናላችሁ… ከድሮ ነገር መላቀቅ አለመቻል አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የሆነች… አገሩን ሁሉ ‘ቴስቲንግ ላቦራቶሪ’ አድርጋው የኖረች እንትናዬ ሁሉን ነገር ትታ፣ ‘ጨምታ’… አለ አይደል… “እንትና እኮ ልታገባ ነው…” ሲባል ብዙዎቻችን ምን እንል መሰላችሁ… “የፈረደበት ማን ይሆን! ጠብሳ ትገድለዋለች” እንጂ… “ጐሽ ከዛ ህይወት ወጥታ እንዲህ ቁም ነገር ላይ ስትደርስ ደስ ይላል…” አይነት ነገር አንልም፡፡ (በቦተሊካውም ቢሆን… አለ አይደል… ስለአሁኑ አጠገባችን ስላለው ነገር ከመከራከር ይልቅ “እንትና ያኔ ከእነእንትና ጋር አልነበር እንዴ!” ምናምን ሲባባሉ ስትሰሙ ያሳዝናል፡፡ ያኛውን ሰው “ከእነ እንትና ጋር ነበር ብሎ የሚከሰው ራሱ እኮ አልበስል እንዳለ እርጥበት የበዛበት በቆሎ ከቡድን ቡድን ሲገላበጥ አሁንም እንኳን ‘ቃ’ ሊል ሞቅም አላለ፡፡)

እናላችሁ… ይሄ ከድሮ ነገር ላይ አልላቀቅ ማለት አንዳንዴ ኮሚክ ነው፡፡ ለምሳሌ የሆነ ቤት ምሳ ነገር ትጋበዙና ግጥም አድርጋችሁ እየበላችሁ ሳለ የጭልፋዋ ቀለም ይገርማችኋል፡፡ አለ አይደል… በምን አይነት ቀለም ውስጥ ልትመደብ እንደምትችል ስትመራመሩ… ባለቤቱ ምን ይላሉ… “ይቺ ጭልፋ መቼ እንደገዛች ታውቂያለሽ… ጭልፋዋን ከመርካቶ ገዝቼ ቤት ስገባ ራዲዮኑ የከተማ ቤት ተወረሰ እያለ አዋጅ ይናገር ነበር፡፡” ይሄኔ የማይክል ጃክሰን ጭልፋ ብትሆን ኖሮ ሲ.ኤም.ሲ. ጂ ፕላስ ፎር የሚያሰራ ገንዘብ ታስገኝ ነበር፡፡

የምር ግን የድሮ ነገር በሙዚቃ… ኦልዲስ ምናምን አለ አይደል… ሲሆን አሪፍ ነው፡፡ አንዳንዱ እኮ በፎቶ እንኳን ያላየውን የጥንት ዘመዱን ሊያስታውስ ይችላል፡፡

ለምሳሌ ከእንትናዬ ጋር ኩሼ ነገር ብላችሁ ድንገት ስትንሰቀሰቅ ትሰሟታላችሁ፡፡ ምን አጠፋሁ ብላችሁ ትደነግጣላችሁ፡፡ (አሀ… ‘ሰከንድ ራውንድ’ ልትከለከሉ ትችላላችኋ!) እናላችሁ ምን እንደሆነች ስትጠይቋት “ማይጨው ዘመቻ ጊዜ የሞተው አያቴ ትዝ ብሎኝ ነው” ብትል የምር አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

ስሙኝማ… “እንትና እኮ የእንትና ሚስት ውሽማ ነው፣” “የእንትና ሚስት እኮ በተደራቢ የእንትናም ሜክአፕ ሚስት ነች” “የእንትናን እጮኛ እኮ እንትና አወጣት አሉ…” ምናምን እየተባለ በሚፎከርበት ዘመን ያ የድሮ ‘የነጠላ ክንብንብ ጊዜ ይናፈቃል፡፡’ ምን መሰላችሁ… ስልጣኔና የሞራል ውድቀት ተቀላቀሉና ነገረ ሥራችን ሁሉ ለልብወለድ ፀሐፊ ሀሳብ ማፍለቂያ እንኳን አልመች እያለ ነው፡፡

ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ወዳጄ የተገኘበት ሠርግ ነው፡፡ እናላችሁ ሁለቱም ወልደው ከብደው ከቀድሞ ሰዎቻቸው ተፋተው ነው እንደገና በሠርግ የሚጋቡት፡፡ መቼም የዚህ አገር የሠርግ ዘፈን እንደመጣ አይደል… ምን ተብሎ ቢዘፈን ጥሩ ነው… “ሁለቱም ተለዩ ከእናት ከአባታቸው…” ኮሚክ አይደል!... የእናት አባታቸው ሰባተኛ ሙት ዓመት ከወጣ እንኳ አራት ዓመት ሆኖታል እኮ!

ለምሳሌ ድሮ ውፍረት አሪፍ ነገር ነበር፡፡

ወፈር ያላለች እንትናዬማ በቃ… ዘወር ብሎ የሚያያት የለም፡፡ እንደውም ምን ይባላል መሰላችሁ… “ምግብ አያበሏትም እንዴ! ተመልከቷት፤ አፄ ልብነ ድንግል ቤተ መንግሥት ውስጥ ከአሞሌ ጨው ጋር የተገኘች ቋንጣ መስላ!”

ዘንድሮ ግን… ስሊምነት (“ቀጫጫነት” የሚለውን ‘አዛማጅ ትርጉም’ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ፋሽን ሆኗል፡፡ ወፍራምነት… ማስፎከሩ እየቀረ ነው፡፡ ከድሮ ነገር የቀረ አንድ ቢገኝ ይኸው ነው፡፡

ስሙኝማ… ስለ ወፍራምነት ካወራን አይቀር… ከዚህ በፊት አንስተናት ሊሆን የሚችለውን አንዲት ‘ስቶሪ’ ስሙኝማ… ሴትየዋ በጣም ወፍራም ነች፡፡ አንድ ጊዜ ለአንዱ ወዳጇ “የገዛ ጥላዬ ከኋላዬ ሲሆን ያስፈራኛል…” ትለዋለች፡፡ እሱ ምን ቢላት ጥሩ ነው… “መፍራት ይገባሻል፡፡ የአንድ ቀበሌ ህዝብ የሚከተልሽ ነው እኮ የሚመስለው!”

የምር ግን… ጨዋታም አይደል… ስሊምነት ፋሽን የመሰለውን አይነት እኮ ነገሬ በላችሁ ካያችሁ በጣም ወፍራም የሆኑ ሰዎችም እየበዙ ነው.. በተለይ ሴቶች፡፡ አለ አይደል ‘ኦል ኢንክሉሲቭ’ (ቫትን ያካተተ) የሚሉት አይነት ውፍረት፡፡ እንዲህ ሲበዛም ጥሩ አይደለም፡፡ ራስን መጥላት ሊያስከትልም ይችላል፡፡እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው መልኩ የእኔ ቢጤ እዚህ ግባ የማይሉት አሸር በአሸር ነበር… አለ አይደል… መሶቡ ባዶ ከሆነ ‘አፕታይት መቆለፊያ’ ሊሆን የሚችል መልክ፡፡ እናላችሁ… ይኸው ሰውዬ አንድ ጓደኛው ላይ ሽጉጥ ይደግንና… “ለመሞት ተዘጋጅ፣ ግንባርህን ልልህ ነው” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም ግራ ገብቶት “ለምንድነወ የምትገድለኝ” ሲለው፤ ያኛው የእኔ ቢጤው ሰውዬ ምን ይላል መሰላችሁ… “መልኩ ቁርጥ እኔን የሚመስል ሰው ካየሁ እገድለዋለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ” ጓደኝየውም “እኔ አንተን እመስላለሁ እንዴ?” ብሎ ሲጠይቀው ሰውየው “ቁርጥ እንጂ” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “እንግዲያውስ ግደለኝ” (እኔ የምለው ቢጤውን ለማያጣ ምን ያበሳጨዋል!) እናላችሁ… አልላቀቅ ያሉንን የድሮ ነገሮቻችንን ሁሉ (በተለይ አስተሳሰቦችን)… አለ አይደል… እንደገና ብንመረምራቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ “ሁለቱም ተለዩ ከእናት ከአባታቸው…” አይነት ጊዜን ድብልቅልቁን ማውጣት አሪፍ አይደለማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 1780 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:30