Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 10:56

‘አንቺ ሆዬ ለእኔ’… ገና ከማህፀን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!

እኔ የምለው… ይሄ የክረምት ነገር ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው ነገርዬው እንዴት ነው! ያዝ ለቀቅ የእኛ ነገር ብቻ መስሎኝ! የምር ግን… አለ አይደል… “ኸረ እኛ አካባቢ ገና ጠብም አላለም!” ሲባል ስንሰማ አሪፍ ነገር አይደለም! እኔ የምለው… እዚህ አገር ምን የበዛ ነገር አለ መሰላችሁ… ቃለ መጠይቅ፡፡ የምር እኮ የቃለ መጠይቅ ራሽን ምናምን ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እናማ… “የፀሀይን በምድር ዙሪያ መዞር እንዴት ትመለከተዋለህ?” የሚል ጠያቂ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው፡፡

የምር ግን… ዘንድሮ የምንሰማቸው ብዙ ጥያቄዎች “የፀሀይን በምድር ዙሪያ መዞር እንዴት ትመለከተዋለህ?” አይነት ናቸው፡ ወይ ደግሞ ኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ምናምን ከተጨመረበት ጠያቂው “በልጅነትህ በጨርቅ ኳስ ስትጫወት አሪፍ ነበርክ አሉ” ሲል ተጠያቂው ደግሞ “እናንተ ጋዜጠኞች መቼም ምንም ነገር አያመልጣችሁም… ደግሞ ይህን ምስጢር ማን ነገረህ?” ይለዋል፡፡ እናላችሁ… ‘ድሮ በጨርቅ ኳስ’ መጫወቱን ማወቅ እንደ ‘ምርመራ ጋዜጠኝነት’ አይነት ሆኗል፡፡

ታዲያላችሁ… ዘንድሮ ለሆነ ሰው ሲሳካለት ወይም ‘ተሳካለት’ ሲባል “ለቃለ መጠይቅ ፈልገንህ ነበር” የሚል መአት ነው፡፡

የሆነ ኮሚክ ነገር እኮ ነው… ሰፈር ውስጥ ገና እኮ እዳ ባለመክፈል ገሚሱ የእድር አባሎች ይፈልጉታል፡፡

ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል ዘንድሮ ከፍተኛ የልብ ወለድ የፈጠራ ችሎታ ያለው የት መሰላችሁ… ቃለ መጠይቆች ላይ፡፡

ቀላል ‘ኤዲቲንግ’ አለ መሰላችሁ! በሰፈር ውስጥ፤ አይደለም ሀይቅ ምናምን ነፍስ ያለው ኩሬ በሌለበት “ሰፈር ውስጥ ውሃ ዋና እየዋኘሁ ነው ያደግሁት…” እኛ ጠያቂዎች ደግሞ “በእውነቱ በጣም ደስ የሚል ፓሺን ነው…” ምናምን የምንልበት ዘመን ነው፡፡

እናላችሁ… ዘንድሮ ቃለ መጠይቅ ላይ ‘ባዮግራፊን’ እንደ አየሩ ሁኔታ ማስተካከል ይቻላል፡፡

እንበል ሰውየው ‘ቦተሊከኛ’ ነው፡፡ (ጥያቄ አለን በፖለቲከኝነት የሆነ አይ.ኤስ.ኦ ምናምን ማረጋገጫ ይሰጥልንማ! አሀ… መደበሪያ መሆን ሰለቸና! ደግሞ… “እንትን የሚባል ፓርቲ ተቂቋመ…” ብቻ ሳይሆን “እንትን የሚባለው ፓርቲ ፈረሰ…” የሚል ዜና ያለመኖሩ እንዳሳሰበን ይመዝገብልንማ! አክስዮን ማህበር ብቻ ሲፈርስ ደስ አይልም፡፡)

እናላችሁ… ‘የእለቱ እንግዳችን’ እንትን የሚባል የፖለቲካ ቡድን ውስጥ ያለ ነው፡፡

“ለመሆኑ እንዴት ወደ ፖለቲካ ሊገቡ ቻሉ?”

“ብዙ የማይሆኑ ነገሮች ሳይ ዝም ብዬ ከመበሳጨት ለምን አልታገልም ብዬ ነው፡፡”

(ሀሳብ አለን… ምን አይነት መልስ ቢሰጡ አሪፍ ነበር መሰላችሁ… “ከሆነልህ ስልጣን፤ አሪፍ መኪና፣ የእንትናዬን ዋይፍ ምናምን ታገኛለህ ካልሆነ ደግሞ በቃ… መደበሪያ ታደርገዋለህ ቪዛ ማግኘትስ ቀላል አደረግኸው እንዴ!” ቢባልልን እንመርጣለን፡፡)

“ይሄ ስሜትዎ መቼ ጀምሮ የመጣ ነው?”

“እንዴት መሰለህ… ከልጅነቴ ጀምሮ ጥቃት አልወድም፡፡ አይደለም እኔ ተጠቅቼ፣ ሌላ ሰው ላይ በደል ሲፈፀም ማየት አልፈልግም፡፡

ከቤተሰቦቼ ጀምሮ ማንም ሰው እንዲች አድርጐ እንዲነካኝ አልፈቅድም ነበር፡፡”

(ከአልጋ እግር ጋር መታሰሩስ! መቀመጫን በሳማ መለብለቡስ! በርበሬ መታጠኑስ!... የእድር አባላት ቤት ተሰብስበው “ኸረ እባካችሁ ይሄ ልጅ በእጃችሁ ላይ አንድ ነገር ይሆንና ፀፀቱ ለሁሉም ይተርፋል!” ብለው የተማፀኑትስ!)

“ምን ላይ ለማተኮር ነው የወሰኑት?”

“እ… ምን መሰለህ በአሁኑ ጊዜ ሙስናው ገደብ አጥቷል፡፡ በስልጣን አላግባብ መጠቀሙ ተባብሷል፡፡

እነኚህን ሁሉ አቅሜ በፈቀደው መጠን ለመታገል ወስኛለሁ፡፡ እውነቴን ነው የምልህ… ከልጅነቴ ጀምሮ እንደ ሙስና የምፀየፈው ነገር አልነበረም፡፡”

(የእቁብ ፀሀፊ እያሉ የገባበት ጠፋ የተባለው ሃያ ምናምን ሺህ ብርስ! ከልብ ደገኛ በብድር ተወስዶ ‘ውሀ የበላው’ አሥራ ምናምን ሺህ ብርስ! “ስምንት ሺህ ብር ከሰጠኸኝ በኮሚቴው አስወስንልሃለሁ…” ተብሎ ስምንት ብር ሳይገኝ የከሸፈውስ!)

እናላችሁ… ቦተሊከኞች አብዛኞቹ ሁለት ሁለት ታሪክ አላቸው፡፡ አንደኛው እውነተኛውና ዘመድ አዝማድ፣ አብሮ አደግና ጐረቤት የሚያውቀው… ሁለተኛው፣ ሰማንያ በመቶ ማሻሻያ ተደርጐበት በቃለ መጠይቅ የቀረበው፡፡

እናላችሁ… እዚች እኛው አገር አጠቃላይ የአገሪቷን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የግለ ታሪክም እንደልብ መለዋወጥ አስተዛዛቢ ሳይሆን ‘የጨዋታው ህግ የገባው’ ሰው ሥራ ሆኗል፡፡

ደግሞ የሆነች ‘የማን በመፅሐፍ ስሙ ወጥቶ ማን ይቀራል!’ በሚል ከፍተኛ ወኔ የግጥም መፅሐፍ ያሳተመች ልጅ ትኖራለች፡፡ (ድሮ እኮ “የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ…” ነበር… እናላችሁ ዘመን እዚህ ድረስ ነው የተለወጠው፡፡)

እናማ መፅሐፍ በድፎ ዳቦም፤ በፈንዲሻም በምናምን ደምቆ ይመረቃል፡፡ (አንዳንድ የመፅሐፍ ምርቃቶች… የጠበል ጠዲቅ ጥሪ አይነት የመምሰላቸውን ምስጢር የምታውቁ ንገሩንማ!)

ታዲያላችሁ ገጣሚዋ ለአቅመ ቃለ መጠይቅ ትደርሳለች፡፡

“ግጥሞችሽን ስታነቢ አዳራሹ በጭብጨባ ሲናጋ ነበር፡፡ ምን ተሰማሽ?”

“በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኔ እንዲህ አይነት ስሜት ይፈጠራል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር፡፡”

(ጥያቄዎች አሉን… ከ’ማዘር’ የሴቶች እድር ስንት ሰው ነው ያልመጣው፣ ተራርቀው የነበሩ አብሮ አደጐች ከስንት ጊዜ በኋላ መገናኘታቸው ነው! ያለመምጣታቸው የታወቀባቸው ክላስሜቶች ቁጥራቸው ከሞባይል ላይ የሚሰረዘው መቼ ነው?)

“ለመሆኑ ግጥም መፃፍ መቼ ነው የጀመርሽው?”

“ልጅ ሳለሁ እቤት ውስጥ የምናገረው ነገር ሁሉ እንደ ግጥም ይጥማል ይሉኝ ነበር…”

(አበባየሆሽ ላይ “እንጨት ሰብሬ…” የሚለውን “አንጀት ሰብሬ…” ተብሎ ከጓደኞች ጋር የተጣላችውስ! “እንደው አንድ ቀን እንኳን ሙሉ አረፍተ ነገር በትክክል ላትናገሪ ነው!” የሚሉት የሰባተኛ ክፍለ አማርኛ አስተማሪ አባትስ!)

“ከገጣሚዎች ማንን ነው የምታደንቂው?”

“እንዴት መሰለህ… እ… ምን መሰለህ… እኔ ብቻ ሁሉንም አደንቃቸዋለሁ፡፡”

(ጥያቄ አለን… “ደጋግመው ደበበ ሰይፉ፣ ደበበ ሰይፉ የሚሉት የትኛው ባንድ ነው የሚጫወተው?” ተብሎ የተጠየቀውስ ጥያቄ! ፀጋዬ ገብረ መድህን የተባለው አክተር ከሙሉአለም ጋር ይተውን ነበር እንዴ ተብሎ የተጠየቀውስ ጥያቄ!)

‘እውነት እውነት እላችኋለሁ’… አንዲት የግጥም መፅሐፍ ሳናነብ ጥይት ገጣሚዎች የሆንን፣ አንድ ስክሪፕት ሳናነብ ጉድ የምናሰኝ የፊልም ስክሪፕት ፀሀፊዎች፣ አንድ አጭር ልብ ወለድ ሳናነብ “ድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተካከለኝ ሾርት ስቶሪ ፀሀፊ የለም…” የምንል በዝተናል፡፡ ስሙኝማ… የሆነ መፅሐፍ ላይ “በሁሉም ነገር ‘ከእኔ በላይ ላሳር’ የሚሉ በበዙ ጊዜ የምፅአት ቀን መቃረብ ምልክት ይሁናችሁ!” ተብሎ የተፃፈ ነገር መኖር አለበት፡፡

እናማ… ነገራችን ሁሉ ሁለት ቢላ፣ ሁለት ምላስ፣ ሁለት እንትናዬ፣ ሁለት ባዮግራፊ… ሆኖላችኋል፡፡

እንትና… በዘመኑ ‘ፋሽን’ የሆነ ሲንግል የሚባል ነገር ይለቃል፡፡ ፖስተሩ ‘በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው አዲስ ድምፃዊ’… አለ አይደል… ሲንግል መልቀቁን ይነግረናል፡፡ (እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አይደለም ሰፊው ህዝብ፣ ዘመድ አዝማድ እንኳን ለይቶ የማያስታውሰው ዘፋኝ፣ ተዋናይ፣ ገጣሚ… ምናምን “በናፍቆት” ሊጠበቅባት የሚችለው ብቸኛዋ አገር የእኛዋ መሆን አለባት!)

እናላችሁ… ከሲንግል በኋላ አቅመ ቃለ መጠይቅ ይደረሳል፡፡

“ለመሆኑ የሙዚቃ ስሜት መጀመሪያ ያደረብህ መቼ ነው?”

“እ… ምን መሰለህ… አትሳቅብኝና ስወለድ እንደ ሌላው ልጅ እያለቀስኩ አልተወለድኩም፡፡ ሲነግሩኝ… የምዘፍን እመስል ነበር አሉ፡፡”

(ማዋለጃ ሆስፒታሉ እኮ አሁንም አለ… አይደለም የልብ ምታቸው ቀዩን መስመር ያለፈ በሽተኞች… ዘበኞች ሁሉ “ምን ጉድ ነው የተወለደው!” ብለው የጥበቃ ቤታቸውን ጥለው የተሯሯጡትስ! አባት “ከአሁኑ እንዲህ መጮህ የለመደ ትንሽ ከፍ ሲል በአገርም አያኖረን…” ብለው ስጋታቸውን የገለፁትስ!)

ብቻ ምን አለፋችሁ… ዘንድሮ የማይፈቀድ ቢኖር የማይገፋ ነገር ለመግፋት መሞከር ነው፣ ቂ…ቂ…ቂ… አይደለም ሁለት አይነት ሃያ ሁለት አይነት ባዮግራፊ መፃፍ ይቻላል፡፡

እኛ ‘ጋዜጠኞች’ እንደሁ ብልጥ ሆነናል፡፡ ማን በጥያቆ አፋጦ የስፖንሰር ገመዱን ይበጥሳል!

እናላችሁ… የዘንድሮ ቃለ መጠይቆችን እንደ መረጃ ማግኛ ሳይሆን ከፈለጋችሁ እንደ ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’፣ ከፈለጋችሁ እንደ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’… ከፈለጋችሁ ደግሞ እንደ ዋልያና ጭላዳ ዝንጀሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ ሎካል ከለር ያለው ኮመዲ ውሰዱት፡፡ ያኔ ዘና ትላላችሁ፡፡ ለምን ብትሉኝ… ‘አንቺ ሆዬ ለእኔን’ እያፏጩ ሊወለዱባት የሚችሏት ብቸኛዋ አገር የእኛው ብቻ ነችና!

ደህና ሰንብትሉኝማ!

 

 

Read 1633 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 11:05