Saturday, 16 June 2012 12:02

ትዳር ሲፈርስ የልጆች ህይወት ይፈርሳል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ጂል ክርስቲና እና ቨርጂኒያ አሊስ በተባሉ እንግሊዛውያን የተዘጋጀው መፅሃፍ “Where is Dady?” የተሰኘ ሲሆን በቅርቡ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለአንባቢያን ቀርቧል - ንጋቱ ኃይሉ በተባሉ ተርጓሚ፡፡ መፅሃፉ በእንግሊዛውያን የፈረሱ የትዳር ታሪኮች ላይ ተመስርቶ የተሰናዳ ሲሆን በመረጃና በጥናት የዳበረ ነው፡፡ “አባባ የት ሄደ?” በሚል ከተተረጐመው መፅሃፍ ላይ ያገኘኋቸውን ጥቂት ታሪኮች እንደማሳያ ላቅርብና ቅኝታችንን እንቀጥላለን፡፡ልጅቷ አባቷን በልጅነቷ በሞት ስለተነጠቀች ስለ አባቷ ማንነትና ታሪክ የሰማችው ከእናቷ ነበር፡፡ በኋላ ለአቅመ ሄዋን ደርሳ ትዳር መስርታ ስትኖር ጥሩ ሚስት ለመሆን ብዙ ጥራለች፡፡ ሆኖም ግን ትዳሯን በፍች እያጣች ስትቸገር የምክር አገልግሎት ለማግኘት ወደ ባለሙያ ጋ ትሄዳለች፡፡ ከባለሙያ ጋር ከተወያየችና ምክር ከተሰጣት በኋላ የደረሰችበት ድምዳሜ እንዲህ የሚል ነበር - “በሁለቱም ጋብቻዎቼ እፈልግ የነበረው ባል ሳይሆን አባት ነበር ማለት ነው፡፡”

ሌላዋ ወጣት ደግሞ ወላጆቿ በፍቺ ሲለያዩ የ18 ወር ህፃን ነበረች፡፡ የ18 ዓመት ጉብል ሆና ስለራሷ ስታጠና የተገነዘበችው እውነታ ግርምት የሚፈጥር ነው፡፡ ለጓደኝነት የመረጠቻቸው ልጆች ሁሉም አባት የሌላቸው ነበሩ፡፡ “የወላጆቼ መፋታት በእኔ ላይ ጉዳት ያመጣል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ እያደግሁ ስሄድ ግን የጐዳኝ መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብኩ መጣሁ” ብላለች - ወጣቷ፡፡

አባት ሚስቱንና ልጁን ጥሎ ሲኮበልል ልጅ የ8 ዓመት ህፃን ነበር፡፡ በአባት ፍቅር እጦት በመረበሽ የሚሰራው ያጣው ህፃን በተስፋ መቁረጥ ራሱን ጠላ፡፡ ከዛፍ ላይ ወደ መሬት በመፈጥፈጥ እግሩን ለመስበር ሞከረ፡፡ ቢስኪሌቱን ሰባብሮ ጣለ፡፡ ጭንቅላቱን ካገኘው ነገር ጋር ማጋጨት ፊቱን መቦጫጨር ሆነ ስራው፡፡ አንድ ምሽት እናቱ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን ለምን እንደሚፈፅም በእርጋታ ጠየቀችው፡፡ እሱም “አስቀያሚ ልጅ ከሆንኩ አባቴ እኔን ለመጠየቅ አይመጣም፤ ስለዚህ እረሳዋለሁ” የሚል አስደንጋጭ መልስ ሰጣት፡፡

ሕፃናት የቱንም ያህል በእድሜ ትንሽ ቢሆኑም የወላጆቻቸውን ፍቅርም ሆነ ጥላቻ መረዳት የሚችሉበት ተፈጥሮ እንዳላቸው ማሳያ ሆና የቀረበችው ባለ ታሪክ፤ አባቷ እሷንና እናቷን ጥሏቸው ሲሄድ የሁለት አመት ሕፃን ነበረች፡፡ የ18 ዓመት ጉብል ሆና ግን አባቷ በሕፃንነቷ አዝሏት የተነሳውን ፎቶግራፍ እያየች ታለቅስ እንደነበር መፅሃፉ ላይ የሰፈረው ታሪክ ይገልፃል፡፡

አንድ ታሪክ ላክል፡፡ አባትና እናት በመሃላቸው ችግር እንዳለ ቢያቁም ልጆቻቸው ተረድተውታል ብለው አልገመቱም ነበር፡፡ አንድ ቀን አባት ቤተሰቡን ይዞ ለጉብኝት ራቅ ወዳለ ቦታ ይሄዳል፡፡ እናትና ልጆቿ በጉብኝቷ ደስተኛ ነበሩ፡፡ አባቱ ደስተኛ እንዳልነበር ያስተዋለው ልጅ “አባባ በእነዚህ ደረጃዎች ሲያማርር እማማ ግን ደረጃዎቹን በወጣን ቁጥር በጣሪያው ላይ ያሉትን ድንቅ ጌጣጌጦችን ስታደንቅ ተመለከትኳት” በማለት በአባትና በእናቱ መሃል የነበረውን የስሜት ልዩነት ገልጿል፡፡

በትዳርና በልጆች ዙሪያ እነዚህን የመሳሰሉ አያሌ ምሳሌዎችና አስተማሪ የሆኑ ታሪኮችን የሚያስቃኘን መፅሐፉ፤ የወላጆችን መለያየትና በልጆችን ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅእኖ ያሳያል፡፡

“Where is Daddy” የተሰኘው መፅሐፍ ደራሲዎች እናትና ልጅ ናቸው፡፡ እናትየው ጂል ከርቲስ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ፤ ለ39 አመታት በትዳር ውስጥ ቆይተው በርካታ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሁለተኛዋ የመፅሐፉ አዘጋጅ (ልጅየው) ትዳራቸው በፍቺ ቢፈርስም ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ደራሲያኑ ስለመፅሐፉ በመግቢያው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤

“የማስተማሪያ መፅሐፍ አይደለም፡፡ የቤተሰብ መፍረስን በተመለከተ ደረጃ በደረጃ ልንከተለው የሚገባ መመሪያም አይደለም፡፡ የዚህ መፅሐፍ ተልዕኮ ከወላጆች መለያየትና ከፍቺ ጋር በተያያዙ በልጆች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችን ለወላጆች ማሳየትና የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ መጠነኛ የሆነ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ነው” ይላሉ፡፡

ተርጓሚው በበኩላቸው፤ በመፅሐፉ የቀረቡት ተመክሮዎች በእንግሊዝ ሕብረተሰብ ላይ የተካሄደን ጥናት መሰረት ያደረጉ ቢሆኑም በአገራችን በፍቺ የተነሳ ለሚያጋጥሙ ከቤተሰብ መፍረስ ጋር የተያያዙ ችግሮች መፍትሄዎችን ያመላክታሉ ይላሉ - ስለመፅሃፉ ሲገልፁ፡፡ ከመፍትሄዎቹ መካከልም:-

በተለያዩ እድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለሚያነሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት፤

ትዳር ፈርሶ አዲስ ህይወት ሲጀመር ምን ማድረግ እንደሚገባ፤

በትዳር ውስጥ ከሀብትና ከገንዘብ ጋር ለሚነሳ ግጭት መፍትሄውን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል፤

በትዳር ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ፤

የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮችን መቅረፊያ ዘዴውን ማመላከት ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ - ተርጓሚው፡፡

በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት የትዳር ህይወት ተመክሮዎች ውስጥ የሚበዙት በአገራችን ከምናውቀው ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆኑም አንዳንድ ከባህላችን ወጣ ያሉና ግር የሚያሰኙም አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ ከባሏ ጋር ከተፋታች በኋላ ስለተዋወቀቻቸው የወንድ ጓደኞቿ (ፍቅረኞች) ለልጆቿ በግልፅ የምትናገር እናት ተጠቃሽ ነው፡፡ “የፍቅረኞችሽን ቁጥር ቀንሺ” ብላ ለልጇ ምክር የምትለግስ እናትም ለባህላችን እንግዳ ይመስላል፡፡

አንዲት ሴት ባሏ ጥሏት ከሄደ በኋላ ልጆቹ ለአባታቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው የምታደርገው ጥረት ሲታይም ሊያስገርም ይችላል፡፡ በእኛ ዘንድ እምብዛም የሚታይ ባለመሆኑ፡፡

እንግሊዛዊቷ እናት ይህንን የምታደርገው ለራሷ፣ ለልጆቿ፣ ለሕብረተሰብና ለአገር አርቆ ከማሰብ መሆኑን ስንገነዘብ ደግሞ የሥልጣኔን አዎንታዊ ገፅታ የበለጠ እናደንቃለን፡፡ በእርግጥ ከእንግሊዛውያኑ እናቶችም ለምሳሌነት የማይበቁ አይጠፉም፡፡ ጥሏት የሄደው ባል በልጆቿ እንዲጠላ ለአመታት የተጋች ሴት በመጀመሪያ እራሷን በመቀጠል ሌሎችን ለጉዳት እንደምትዳርግ በቀረበው ተመክሮ “እናታቸውን ትቻት በመሄዴ ሴቶች ልጆቼ ይቅርታ ሳያደርጉልኝ ይኸውና ሰላሳ አመታት አለፉ” ሲል አባት በቁጭት ይናገራል፡፡

አልፎ አልፎ እንዲህ አይነት የጥላቻና የቂም ታሪኮችን የሚተርከው መፅሃፉ፤ ትዳራቸውን በፍች ያጡ አብዛኞቹ እንግሊዛዊያን ግን ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለመተሳሰብ… ዋጋና ክብር እንደሚሰጡ ያመለክታል፡፡ በጣም ከባዱና አስቸጋሪው ከፈረሰው ትዳር ውስጥ የተወለዱት ልጆች የሚያነሱት ጥያቄ የሚፈጥረው ጭንቀት ነው፡፡ የልጆቹን ችግርና ህመም ለማስታመም እናቶቻቸው ከሚወስዱት የመፍትሄ እርምጃዎች አንዱ እውነቱን ይፋ ማድረግ ነው፡፡ አባት ቤቱን ጥሎ ስለመሄዱ፣ ስለመታሰሩ፣ ዘመቻ ላይ ስለመሆኑ፣ ስለመሞቱ… ወዘተ.

ልጆቹ ቆይተው ማወቃቸው የማይቀረውን እውነት በጊዜና በወቅቱ ማሳወቅ ይጠቅማል የሚል አመለካከትና እምነት በእንግሊዝ ማሕበረሰቡ ውስጥ እንዳለ መፅሐፉ ያመለክታል፡፡ ይሄን የሚያጠናክር አንድ ታሪክ ለአብነት ቀርቧል:-

የልጁ እናትና አባት በፍቺ ተለያይተዋል፡፡ ልጁ የልደት በዓሉን ሲያከብር አባቱ እንዲገኝለት ፈለገ፡፡ አባትየው ቢጠራም እንደማይመጣ የምታውቀው ወላጅ እናቱ፤ ልጇ አባቱን ለልደቱ እንዲጠራው ፈቀደችለት፡፡ አባት እንደማይመጣ እያወቀች ልጇ ለምን አባቱን እንዲጋብዝ እንደፈቀደችለት የተጠየቀችው እናት፤ ልጇ እውነታውን በተግባር እንዲያረጋግጥ በመፈለጓ እንደሆነ ተናግራለች፡፡

እንዲህ አይነቱን ግልፅነት የምናገኘው ሕብረተሰቡ ጋ ብቻ ሳይሆን የትዳር የምክር አገልግሎት የሚሰጡት ባለሙያዎችም ጋር እንደሆነ መፅሃፉ ይጠቁማል፡፡ በፍቺ በሚፈርሰው ቤት ውስጥ ላሉ ልጆች እየሆነ ስላለው ነገር ማሳወቅ ተገቢ ቢሆንም ስለሚነገራቸው ነገር ጊዜ ወስዶ ማሰብና በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በቂ ዝግጅት እስኪደረግ ግን ለጊዜው መሸፋፈን ይደገፋል፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ አንዷ እናት ተመክሮዋን ስታጋራ እንዲህ ብላለች:- “አባባ ለጥቂት ወራት ወደ ውጭ አገር ሄዷል በማለት ነገርኳቸው፡፡ ይህንን በማድረጌ ራሴን ለማረጋጋትና አቅሌን ለማወቅ እችል ዘንድ ጊዜ ሰጥቶኛል፡፡ ከዚያም ባለሙያ አማከርኩ፡፡ አንድ ጊዜ ጠንከር ስል አባታቸው ትቶን የሄደበትን ምክንያት እንዲረዱ ለማድረግ ልጆቹን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ላዘጋጃቸው እችላለሁ፡፡ ሁኔታውን ማድበስበስና እንዳያውቁት ማድረግ ጨካኝነት ይመስለኛል፡፡”

መፅሃፉ ከትዳር ህይወትና ከፍቺ ጋር የተያያዙ በርካታ ተመክሮዎችንና መረጃዎችን ይዟል፡፡

መውለድ ትዳሬን ያፀናልኛል ብለው ያመኑ ሴቶች ግምታቸው ትዳራቸውን ከመፍረስ እንዳላዳናቸው የሚጠቁም ተመክሮ፤ በተደጋጋሚ እየተዋሹ በተደጋጋሚ ለማመን ጥረት እያደረጉም ትዳራቸውን ማዳን ስላልቻሉ ሰዎች… እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በስፋት የሚተርከው መፅሐፍ፤ በውስጡ የያዛቸው ታሪኮች ከእንግሊዝ ማህበረሰብ የተወሰዱ ቢሆንም የሚያነቡት ሰዎች ሁሉ የሚማሩበት ነገር አያጡበትም፡፡ እንዲህ አይነት ጥናታዊ ሥራዎች በአገራችንም እየተሰሩ ቢቀርቡ የሚል ሃሳብ በመጠቆም ዳሰሳዬን እቋጫለሁ፡፡

 

 

Read 2257 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 13:21