Saturday, 16 June 2012 12:01

ኪሎ ምስርና ኩንታል‘ አራድነት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

በዛ ሰሞን መሃል ፒያሳ ሁለቱ ሰዎች በሆነ ነገር አልተግባቡም መሰለኝ፡፡ እናላችሁ… አንደኛው ራቅ ካለ በኋላ ምን ይላል መሰላችሁ… “ስማ እኔ እኮ የጨስኩ አራዳ ነኝ!” ቅሽምና! እውነተኛው ‘ጄኒዩን’ አራዳ “እኔ አራዳ ነኝ…” አይልም፡፡ችግሩ ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ማዕረግ የሚሰጠው በራስ ተነሳሽነት ነው፡፡ የክብር ዶክትሬት ያገኙ ሰዎች እኮ ከስማቸው ፊት ‘ዶክተር’ የሚለው ማዕረግ እየተቀጠለ ያለበት ዘመን ነው!ጥያቄ አለን… ‘የዘመናዊ አራዳነት መገለጫዎች’ ምናምን የሚል ኤግዚቢሽን ይዘጋጅልንማ! ብቻ… የሆነ ድብልቅልቁ የወጣ ነገር አለ፡፡ ‘አራድነት’ ትርጉሙ ተገልብጦ ውበቱ እየጠፋ ነዋ! ሞባይል መያዝና መነቀስ የ’አራድነት ታፔላ’ የሆነበት ዘመን አይገርማችሁም! ቅልጥ ያለ ማጭበርበር ‘አራድነት’ የሆነበት ዘመን አይገርማችሁም!

አራድነት… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ.. ‘ፈረንጆች’ (የፈረደባቸው ፈረንጆች!) ‘ስቴት ኦፍ ማይንድ’ ምናምን የሚሉት ነገር ይመስለኛል፡፡ ገጣሚዎች ‘ነፍስያ’ እንደሚሉት አይነት ነገር፡፡

ልጄ… የዘንድሮ አራድነት የሶፍትዌር ‘ሲሪያል ነምበር’ና ‘ፓስወርድ’ ሰበራ ሆኖላችኋል፡፡ ሶፍትዌሮች ላይ እኮ ‘ክራክድ ባይ’ እየተባለ የሚፃፍበት ጊዜ ነው፡፡ ምን ያሳፍራል! ፓስወርድ ‘ክራክ’ ማድረግ አራድነት ሆኗላ! ኮሚክ ጊዜ ነው፡፡

የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እኛ የምናውቀው አራድነት ‘ኤቲክስም’ ነበረው፡፡ ለሰው ይታሰባላ!

አሁን እንትናዬዎቹ ሲጋበዙ መቶ ብር አጠገብ የደረሰውን ክትፎ ምናምን ሆኗል የሚያዙት፡፡ አራድነት ነዋ! እሷ የቀለጠች አራዳ ሆና በምንቸት አብሽ ያንን የመሰለ ‘መስዋዕትነት’ ልትከፍል! ቂ…ቂ…ቂ… በፊት እኮ “ግዛልኝ…” የሚባል በጣም ከተወደደ ባቅላባ ነው፡፡ ከዛ ነገርዬው ከተገባደደ በኋላ ለአንበሳ አውቶብስ አሥራ አምስት ሳንቲም ትኬት መቁረጥ ነው፡፡

ስሙኝማ… የዘንድሮ አራድነት ዲጂታል ሆነና… አለ አይደል… የሆነ ሰብአዊነት የሌለው ደረቅ ‘ማፍጠጥ’ ነገር ሆኖላችሁ አረፈው! (ሳልረሳው… ኤፍ.ኤም ጣቢያው ላይ የ’አራድነት ቃና’ ከምታሰሙት… አንዳንዶቻችሁ… አለ አይደል… ስለ አራድነት የአቅም ግንባታ ምናምን ያስፈልጋችኋል፡፡ አሀ… እኛ ተሳቀን አለቅና! እንደገና ሳልረሳው… የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞች አቅራቢዎች እርስ በእርስ የሚያወሩት ነገር… በውጩው እኮ ልምምድ ተደርጐበት አየር ላይ የሚውል ነው እንጂ… እንደ እኛ አሰቃቂና “ኸረ ምን የጉድ ዘመን መጣ!” የሚያሰኙ ነገሮች እንደተፈለገው የሚለቀቁበት አይደለም፡፡ ስሙኝማ… ሃሳብ አለን… የእነኚህ የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞች ነገር ግን ባለሙያዎቹና አድማጩ የምር ቢያወሩበት አሪፍ ይመስለኛል፡፡ (ብስሉም፤ ጥሬውም ተደበላልቀው የኤፍ.ኤም ሰፈር ለይቶለት ሙሉ ለሙሉ ‘ሳይቀወጥ’ እናውራበትማ!) ግን “እኔ እኮ አራዳ ነኝ…” የሚል የተፈጠረው አሁን ነው፡፡

እናላችሁ… የበፊቱ አራድነት ማኑዋል ስለነበር ሁሉም ነገር ፊት ለፊት ነው፡፡ ልክ ነዋ… “ቴክስት ላክልኝ…” የለ “ፔጅ አድርገኝ” የለ… በቃ “ልክ የዛሬ ወር ቅዳሜ ስምንት ሰዓት ተኩል ላይ አሥራ ዘጠኝ ቁጥር ማቆሚያ ጋር እንገናኝ…” ምናምን መባባል ነው፡፡ በዘንድሮ “ኋ’ሳፕ” ዘመን… ስንት ቁጥር አውቶብስ የትኛው ፌርማታ ላይ እንደሚቆም የማያውቁ ‘ዲጂታል አራዶች’ በዙና… ‘አድቬንቸር’ ነገሩ ጠፍቶላችኋል፡፡

ስሙኝ… አራድነት እኮ የ’ፕራይድ’ ነገር አለበት! “እናትህ እንዲህ ትሁን…” ማለት ከአራድነት የሚቆጠርበት ዘመን… በቃ ብዙ የላሉ ቡሎኖች አሉ ማለት ነው፡፡

በፊት “በእናትህ አንዷን የቅምብቢት ልጅ ሲኒማ ኢትዮጵያ ላምነሸንሻት ነው፡፡ ድቡልቡል ማስቲካ ይኖርሃል…” ምናምን የሚባልበት ጄኒዩን አራዳነት ነበር፡፡ አውራ ጣቱ የተዘቀዘቀበት ትልቅ የእጅ ስዕል የሚለበስበት ዘመን አይደለማ፡፡ (ስማ ጐረምሳው… ሁላችንንም ‘ዘቀዘቅከንሳ!’) እናላችሁ… “እነሱን አትንካ እንጂ እዚህ አገር እንደፈለግኸው መሆን ትችላለህ…” የሚሉት ነገር ካልቀረ ነገ ምን አይነት ህብረተሰብ እንደሚመጣ አያሳስባችሁም! “የእኔን አጥር አትነቅንቅ እንጂ የህብረተሰቡን አጥሮች ለምን ከስራቸው መንግለህ አትጥላቸውም!” አይነት ‘ኬሬዳሽነት’ ብዙም ‘ሲቪላይዜሽን’ ነገር አይታይበትም፡፡

ስሙኝማ… አንዱ የሆነ ሰውዬ የለየለት መላጫ ነገር መሆኑን ሲገልፅ ምን አለ መሰላችሁ… “የለየለት ሞጭላፋ በመሆኑ ከጨበጥኩት በኋላ ጣቶቼ በቦታቸው ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እቆጥራቸዋለሁ፡፡” እናማ… ዘንድሮ ከጭበጣ በኋላ ‘ጣት የሚያስቆጥር’ መላጭነት እንደ አራድነት ተቆጥሮ አረፈላችሁ! “እንዴት ያለ አራዳ መሰለህ… ሙልጭ አድርጐ ነው እኮ የበላቸው!” መባል የአራድነት ጫፍ ሆኗል፡፡

እናላችሁ… ዘንድሮ “ብራዘር አሥር ብር አለህ?” የሚለውም ‘አራድነት’ ሆኗል፡፡ (እኔ የምለው… ጥያቄ አለን፣ የአራድነት ‘የብቃት ማረጋገጫ’ ምናምን የማይሰጠው ማረጋገጫውን ለመስጠት በቂ አራዶች ስለሌሉ ሊሆን ይችላል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን በፊት የሆነ መሥሪያ ቤት ስትገቡ አንድ በቃ ፈገግ የሚል፣ ተግባቢ አራዳ ነገር እንደምንም ይገኝ ነበር፡፡ ዘንድሮ… በተለይ አሁን፣ አሁን… አለ አይደል… ጠቅላላ ባለጉዳይ ሳይገባ ቢሮው የወፍጮ ቤት አገልግሎት የሚሰጥ ነው የሚመስለው፡፡ አሀ… ‘የቦነበበት’ ሰው በዛብና!)

እኔ እኮ… አንዳንዴ መንገድ ላይ “ብራዘር ሃያ ብር ይኖርሃል!” ምናምን የሚሉት ተንቀሳቃሽ ‘ኢንካም ታክስ’ ነገር ሰብሳቢ ይመስሉኛል፡፡ አሀ… የምንሰጠው ‘ተወስኖ’ ነዋ የሚነገረን! ዜሮ፣ ዜሮ የሚበዛበት ቁጥር ደግሞ ወይ ‘ቲ.ኦ.ቲ.’ ወይ ‘ቫት’ ሲገባት ሲመስለንስ! ሀሳብ አለን… “ብራዘር ሃያ ብር ይኖርሃል!” ለሚሉት ደረታቸው ላይ “ደረሰኝ ካልተሰጠዎት አይክፈሉ” የሚል ነገር ይለጠፍልና! የሚያሳዝነው ባለ ሉካንዳው ሰውየውን አያምነውም ነበር፡፡ ምን አለፋችሁ… እንደ እንስሳ ነው የሚያየው፡፡ እናላችሁ… ይኸው ሰውዬ ሉካንዳ ይመጣና “እስቲ ለውሻ የሚሆን ሥጋ ሰጠኝ…” ይላል፡፡ ባለ ሉካንዳው ምን አለው መሰላችሁ… “ይዘኸው የምትሄደው ነው እዚሁ የምትበላው!” እናላችሁ በደጐቹ አገር ባለ ሉካንዳ እንኳን ‘ቅኔ ይቀኛል፡፡’

እናማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ለፍላፊነት እንደ አራድነት የሚቆጠርበት ዘመን ነው፡፡ በቃ ምንም እርባና የሌለው ነገር መለፍለፍና “ይሄ ሰውዬ ማውራት አይደክመውም እንዴ?” ለመባል መብቃት አራድነት ሆኗል፡፡ ስሙኝማ… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ ሴትየዋ ለባሏ “ሳይንቲስቶች አንድ ሰው በቀን በአማካይ አሥር ሺህ ቃላት ይናገራል አሉ” ትለዋለች፡፡ ባል ሆዬ ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው… “በዚህ አይነት አንቺ ጊነስ ቡክ ላይ መግባት ትችያለሻ!” እኛ ዘንድ ብትመጣ እንዲህ አይሾፍባትም ነበር… “እንዴት አይነት የጨሰች አራዳ መሰለቻችሁ!” ይባልላት ነበራ!

አንዳንዶቻችን የአራድነትን ፅንሰ ሃሳብ ሌኒን ካስቀመጠው ውጪ እያሰብን ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ… ሌኒን የመሰለ ‘ሶሺሌ አራዳ አልነበረማ!’

“አንተ ሱፍህን ግጥም አድርገህ ነው ለላብ አደሩ እታገላለሁ ምናምን የምትለው…” ነገር ሲሉት አይደል እንዴ… “የእኔ ትግል እናንተን ወደ እኔ ለማምጣት ነው እንጂ እኔን ወደ እናንተ ለማውረድ አይደለም…” ያለው! ዘንድሮ… አለ አይደል… አንድም የቸገረን ነገር “የእኛ ትግል እናንተን ወደ እኛ ለማምጣት ነው እንጂ እንደ እናንተ ለመቸሰት አይደለም…” የሚለን ቢኖር ኖሮ “ይሄ ህንፃ እኮ የእንትና ነው…” “እንትና እኮ ዘጠኝ ሎቤድ አለው…” ምናምን ከሚሉት አይነት ‘ጐሲፕ!’ እንድን ነበር፡፡

ማጭበርበር ላይ አጨበርባሪ እንዳለ ሁሉ ተጭበርባሪም አለላችሁ፡፡ እና ድርጅቱን ‘ጆሮውን ብሎ’ ሲወጣ “እንዴት አይነት የገባው አራዳ መሰለህ!” ይባላል፡፡

እናማ… በቦተሊካውም ይሄ ‘ምናምን ሊበራል’፣ ‘ሊበራል ምናምን’ እያሉ ኤስፔራንቶ ነገር ከሚወራብን የቡድኖች አመዳደብ… ‘ዲሞክራቲክ አራዳ’፣ ‘ሪቨሉሺነሪ አራዳ’፣ ‘ምናምን ፍሮንት አራዳ’ ይባልልን፡፡ “የእንትን ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ…” ነገር ሲሰለቸንስ! ማንቼ ከተመሰረተ ጀምሮ ያልለውጠውን ያህል የማልያ አይነት በሁለትና በሦስት ዓመት እየለዋወጡ ተቸገርና! ነፋስ ሲመጣ ጐንበስ ብሎ እንደማሳለፍ ‘የነፋሱ አካል’ መሆን አይነት አራድነት በዛብና! ቢያንስ ስማቸውን ይለውጡልንና ‘አዲስ ነገር’ ይምሰለን!

ይቺን ስሙኝማ… እንግዲህ የስኮትላንድ ሰዎች የሆኑ ‘የማይደማቸው’ ናቸው ይባላል፡፡ (እኔ የምለው… እዚህ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁላችንም ስካቲሾች ሆንን እንዴ!”) እናላችሁ… ሁለት የስኮትላንድ ሌቦች በሌሊት ወደ አንድ ወርቅ ቤት ይሄዳሉ፡፡ የሱቁን መስታወት በጡብ ሰብረው ገብተው ጐልድየውን ሙልጭ አድርገው ይወስዱና እግሬ አውጪኝ ይላሉ፡፡ ታዲያ ያንኑ ዕለት ሌሊት እዛው ወርቅ ቤት እንዴት ተያዙ መሰላችሁ… መስኮቱን የሰበሩበትን ጡብ ለመውሰድ ሲመለሱ! የእኛ መለኪያዎች አራዶች ያደርጓቸዋል፡፡

እናላችሁ… ኪሎ ምስር ከመግዛት ኩንታል አራድነት በነፃ ማግኘት የቀለለበት ዘመን ሆኖላችኋል፡፡ እስቲ በቅዳሜ ጉልበቴን እያፍታታሁ ‘የጉልቤ አራድነት’ እያየሁ ልዝናናማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

 

Read 2176 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:09