Print this page
Saturday, 02 June 2012 09:03

“ዳር ዳሩ አበባ፣ መሀሉ…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…ክረምትም መጣ፣ የደህና ጋቢም ዋጋ ጣራ ነክቷል…ብቻ በቆሎን በደህና ያምጣልንማ!

ስሙኝማ…ይቺን ነገር ስሙኝማ… ልጁ በቅርብ ጊዜ ከገጠር የመጣ ነው፡፡ እናላችሁ…የከተማ ጮሌዎች ያገኙትና “ሎተሪ ደርሶን እንዳናወጣ መታወቂያ የለንም፡፡ አውጣልንና የድካምህን እንከፍልሀለን …” ይሉታል፡፡ (ይቺ ማታለያ እኮ መአት ሰው ጉድ አድርጋለች!) እሱም “እሺ…” ይላል! አምስት መቶ ብር ገደማ ነው ከተባለው የእጣ ክፍያው ሰባ አምስት ብር ገደማ ያገኝበታላ! እናላችሁ… ሄዶ ለመቀበል ሲጠይቅ መታለሉን አወቀ፡፡ ይሄኔ ምን አለ መሰላችሁ… “ይሄ ምን አዲስ አበባ ነው! ዳሩ አበባ መሀሉ ሌባ ነው እንጂ!” አሪፍ አባባል ነች፡፡ እናላችሁ… ዘንድሮ የ‘ዳር ዳሩ አበባ’ ብቻ እየታየ ህዝቤ በብዙ ነገር ጉድ ነው፡፡ ገንዘቡንና ሀብቱን የሚጭበርበር፣ እንትናዬውን በሌሎች ሦስት ሰዎች የሚነጠቅ (ቂ…ቂ…ቂ…ከሦስት ‘ነጣቂ’ ጋር ምን ማድረግ ይቻላል!)

እናላችሁ… ብዙ ነገር ውጪው እያማረ ‘ውስጡ ለቄስ’ እየሆነ ነው፡፡ “የጨስኩ አራዳ ነኝ…” የሚለው ሁሉ በቀላሉ ሲታለል ታያላችሁ፡፡ (ጥያቄ አለን… እንዴት ነው ነገሩ…የአራድነት ቦታ ልውውጥ ተደረገ እንዴ! አሀ…የዘንድሮ ‘አራዶች’ የሚሠሩትን ስታዩ… አለ አይደል… “እነዚህ አራዶች ከተባሉ አገርዬው ውስጥ ወተቴዎች ጠፋን ማለት ነው!” ትላላችሁ፡፡ ‘አራዶች’ የሚኖሩት ‘ወተቴዎች’ ስንኖር ነዋ! አራድነትን በጉልቤ ይሏችኋል ዘንድሮ ነው፡፡)

ሰሞኑን ሠርግ በሽ፣ በሽ አይደል…ለሁሉም የአብረሀም የሣራ ትዳር ይሁንላቸውማ!

ታዲያላችሁ…እንደ ሠርጉ ሁሉ ፍቺውም በዝቷል ይባላል፡፡ ደግሞላችሁ እኮ የሚያሳስበው መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ፍጥነቱ! “የዛሬ ዓመት የማሚቱ እናት…” ተብሎ የተዘፈነው ጊዜ ላይ ሳይደርሱ የሚለያዩ እየበዙ መሆናችሁ ነው፡፡ (ብዙ ጊዜ እንደሚባለው እዚህ አገር ከሚያሳዝኑት ነገሮች አንዱ እንዲህ አይነት ማህበራዊ ክስተቶችን በጥልቅ ለማጥናት የሚሞከሩ ባለሙያዎች ብዙም አለመኖራቸው ነው፡፡ የድንገት ፈቺ መብዛት እኮ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የትውልድም ጉዳይ ነው!)

ስሙኝማ…ብዙ ባለትዳሮች ነገራቸው ዳር ዳሩ አበባ የሆነ ነው፡፡ ጧት ማታ ቤታቸውን በጠብ የሶርያዋን ሆምስ ከተማ እያስመሰሉ… አለ አይደል… አደባባይ ሲወጡ ግን አርቲፊሻል ፈገግታቸውን ‘ከት ኤንድ ፔስት’ አድርገው የደላቸው ይመስላሉ፡፡

እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ቀልድ ስሙኝማ…የመኖሪያ ቤት ነው አሉ፡፡ እንግዳው ምድር ቤት ሆኖ ባለቤቶቹን እየጠበቀ እያለ ፎቅ ከነበረው የመኝታ ክፍል ድምጽ ይሰማል፡ ይሄኔ አጠገቡ የነበረውን የሰዎቹን ትንሽ ልጅ “የምን ድምጽ ነው የምሰማው?” ይለዋል፡፡  ልጅም… “እማዬ የአባዬን ሱሪ መሬት ለመሬት እየጎተተች ነው፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ሰውየውም በሰማው ድምጽ ጮክ ማለት ተገርሞ “ታዲያ ሱሪ መሬት ላይ ሲጎተት ይህን ያህል ይጮሀል እንዴ!” ብሎ ሲጠይቅ ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ሱሪው ውስጥ አባዬ አለ’ኮ!”

እናማ…እነኚህ ሰዎች ወደ እንገዳው ሲወረዱ…ምን አለፋችሁ…በዳር ዳር አበባ ፈክተው የሆነል፡፡ የምር ግን…ዘንድሮ የብዙዎቻችን ፈገግታና ጨዋታ ዋናው ጉዳይ ሳይሆን… አለ አይደል…  የውስጡን መሸፈኛ ይመስላል፡፡ አጠገባችሁ…ሆዱን ይዞ በሳቅ ሲንፈራፈር የነበረው ሰው ዘወር ስትሉ በአንድ ሴከንድ ተኩል ፊቱን ሀሳብ የገባው የሦስተኛው ዓለም ፖለቲከኛ ፊት የሚያስመስለው መጀመሪያም ቢሆን ሳቁ ‘የዳር ዳር አበባ’ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡

እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ… ሚስት ሆዬ በሆነ ባልሆነው ባሏ እያበሳጨ ቢያስቸገራት ምን ትለዋለች… “እኔን የመሰለች ሚስት ደግመህ አታገኝም!”  ባል ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ… “አንቺን የመሰለች ሚስት ማን እፈልጋለሁ አለሽ!”

እናላችሁ…ብዙዎቻችን የ‘ዳር ዳር አበባችንን’ ለማሳመር የምናደረገው ጥረት…ራሱን የቻለ ማለቂያ የሌለው ተከታታይ ድራማ ሆኖላችኋል፡፡ በተለይ “እከሌ ከተባለ ሀብታም ጋር እኮ ቤተኛ ነን…” “እከሌ የተባለውን ባለስልጣን በደንብ ነው የማውቀው…” ምናምን መባባል የተለመደ ‘የዳር ዳር አበባ’ ሆኖላችኋል፡፡

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ዘንድሮ ስለሆነ ሥራ ስታወሩ ጥያቄው “ሥራውን በደንብ መሥራት ትችላለህ?” ሳይሆን “ሰው አታውቅም እንዴ!” ነው፡፡ (በነገራችን ላይ… ዘንድሮ ‘ሰው’ የሚለው ቃል የ‘ስፒሺየስ’ ጉዳይ ሳይሆን የ‘ክላስ’ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እናላችሁ… ‘ሰው’ ለመባል ክራይቴሪያው ለወጥ ያለ ይመስላል፡፡) አዎ…የችሎታ፣ የእርፍና ምናምን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዋናው ነገር ሰው የማወቅ ሆኗል፡፡

ታዲያላችሁ…‘ሰው ማወቅ’ አሪፍ የአገናኝነት ሙያ እየሆነ ስለመጣ… ወደፊት “እከሌ ምንድነው የሚሠራው…” ሲባል መልሱ ምን ሊሆን ይችላል መሰላችሁ… “ሰዎች ያውቃል…” ሰው ማወቅ ‘ብሬድ’ ማግኛ ሆኗላ! “የሆነ ጉዳይ አለኝ፡፡ ሰው ታወቃለህ?” ሲባል “አውቃለሁ፣ ስንት ትበጥሳለህ?”

ስሙኝማ… እዚህ አገር በአፍ የሚነገረው ግለ ታሪክና በጽሁፍ የምናነበው ልብ ወለድ ታሪክ በጣም እየተመሳሰለብን…አለ አይደለ… “ሉድለም መጽሀፍ ላይ ያለው ገጸ በህርይ አንተ ነሀ እንዴ!” ለማለት ምንም አይቀረን! ኮሚክ እኮ ነው… ከእናንተ ጋር እየተጋፋ ጮርናቄ እንዳልተናጠቀ… “ቤታችን ከድሮ ጀምሮ ያለብላክ ፎረስት ኬክና ያለባቅላባ በልተን አናውቅም…” እያለ ‘የዳር ዳር አበባ’ የሚተክል ሞልቶላችኋል፡፡ በአደባባይ የመብት ተሟጋች በቤቱ ሚስቱና ልጆቹ ጀርባ ላይ መጥረጊያ ሲሰብር የሚያድር በዳር ዳር አበባ የሚኖር ሞልቶላችኋል፡፡ ቀን ቀን ስለ ቅጠል ተሸካሚዋ ምስኪን ተሳታፊዎችን ያስጨበጨበ የጥናት ወረቀት አቅርባ ቤቷ ስትገባ ሠራተኞቿ ላይ “ካዛንቺስ ለጣልያኖች፣ መርካቶ ለአበሾች…” አይነት ‘አገዛዝ’ የምታካሂድ በ‘ዳር ዳር አበባ’ የምትኖር ሞልታላችኋለች፡፡

እናማ “ዳር ዳሩ አበባ፣ መሀሉ ሌባ” ያለው ምስኪን እንዴት አሪፍ ነገር እንደተናገረ መላእክት ሹክ ይበሉትማ!

ስሙኝማ…እውነት ማውራት ያለመሰልጠን ምልክት እየሆነ የመጣ አይመስላችሁም! እንዴ.. ኮሚክ ነገር እኮ ነው፡፡ ‘ከሜዳ እስከ ሚዲያ’…አገር ሁሉ ቀላል ይረግጣል እንዴ! እናላችሁ…ትንሽ ያዝ ማድረግ የለ፣ ግንባርን ዳር ዳር አያልብ፣ ዓይን አይቁለጨለጭ…ብቻ “ሠፈራችን ከማርስ የመጣ ፍጡር ተያዘ…” አይነት ነገር ሊል ይችላል፡፡ (አንቺ እንትናዬ… የበቀደሙ ሰውዬ ከፕሉቶ ምናምን ነው እንዴ የመጣው፡፡ ኽረ… በዛች ‘እግር ተብዬ’ ቁምጣ መልበስ… የሆነ ባቡር ያመለጠው ቻርሊ ቻፕሊን ነገር ያስመስልሀል በዪልን! ዘንድሮ ‘ቬቴራኑ’ ሁሉ “እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ…” ምናምን ማድረግ የጀመረ መሰለሳ!)

ወንዝ በሌለበት ድልድይ እሠራለሁ የሚል ፖለቲከኛን… አለ አይደለ… “ወንዙ የታለ!” የሚባልበት ዘመን እየጠፋ ይመስላል፡፡ ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ… “ድልድይ እሠራለሁ…” ብሎ የዳር ዳሩን አበባ ማሳየት እንጂ ሰፈሩ ዶፍ ሲወርድ እንኳን ውሀ ሰብሰብ የሚያደርግ ጎድጎድ ያለ ቦታ የሌለው ሊሆን ይችላል…

ስሙኝማ…በየመሥሪያ ቤቱ ‘ራዕያችን፣’ ‘ተልኳችን’ ምናምን የሚሉ በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ አሥርቱ ትዕዛዛት የሚመሳስሉ ነገሮች በየመግቢያው ላይ አለላችሁ፡፡ ውስጥ ደግሞ “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል የ‘ዳር ዳር አበባ’ አለላችሁ፡፡ በቀደም አንድ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘ መሥሪያ ቤት ባለጉዳዩ አገልገሎት ለማግኘት ሲራኮት ግድግዳው ላይ በትልቁ ተጽፎ ሰዉ ላይ ‘የሚያሾፍ’ የሚመስል “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሁፍ ነበር፡፡ ‘ዳር ዳሩ አበባ’ ይላችኋል እንዲህ ነው፡፡ (ድጋሚ ጥያቄ አለን…ቢ.ፒ.አር. ቀረ ወይስ ወደ ታሳቢነት ወርዷል፡፡ ልክ ነዋ…በአንድ ጊዜ አገሩ ሁሉ እንዲህ መላው እየጠፋ እንጉላላለን እንዴ!)

እኔ የምለው…የዘንድሮ ሲኒማዎች ማስታወቂያዎች አንዳንዴ ከፊልሞቹ ይልቅ በድርጊት የተሞሉ ልብ አንጠልጣይ አይሆኑባችሁም! መቼም ከንግግር ክፍሎች ቅጽል ያለአግባብ እየባከነ ያለው…..እዚሁ እኛ ዘንድ ነው፡፡ ነገርዬው ያው ‘ዳር ዳሩ’ አበባ ነው፡፡

እግረ መንገዴን… የዘንድሮ ማስታወቂያዎቻችንን ነገሬ ብላችሁ ከሆነ አሁን፣ አሁን ሁሉም  ከእንትናዬዎች ጋር የተያያዙ አይመስሏችሁም! አለ አይደል… ያንን ምርት ከተጠቀሙ “እንትናዬዎች ሁሉ…በሰልፍ ይመጣሉ…” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ እኔ የምለው…ዘንድሮ ለማግኘት ቀላል፣ እንዲሁም ለማግኘት ከባድ የሆኑ ነገሮች ይለዩ እንጂ! አሀ… ድሮ ያጓጓ የነበረው ሁሉ አሁንም ያጓጓል ያለው ማነው! አሥራ ዘጠኝ ቁጥር ማቆሚያ ላይ በጸሀይ መንቃቃት በቀረበት ዘመን! ቂ…ቂ…ቂ…

የማስታወቂያ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው ለጓደኛው … “ማስታወቂያ ማስነገር አስቸኳይ ውጤት እንደሚያመጣ አረጋገጥን…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም “እንዴት?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“ለድርጅታችን ዘበኛ እንደምንፈልግ ያስተዋወቅን ዕለት ማታውኑ ሞጭላፎች መጥተው ዕቃችንን ጥርግ አድርገው ወሰዱታ!”

እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገር ከገጠር የመጣው እንግዳ እንዳለው “ዳር ዳሩ አበባ፣ መሀሉ ሌባ…” እየሆነ ስለሆነ የምንረግጠውን ድንጋይ ልብ እንበልማ፡፡ የሚረገጠው ድንጋይ ዳር ዳሩ አበባ ነገር ሆኖ ይዞን ጭልጥ እንዳይልማ!

ደሀና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 3169 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:30