Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 02 June 2012 08:54

ጊዜ የጣላቸው ጋስፖሪ እስትራዮቶ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በልጅነታቸው በጣሊያናዊ አባታቸው ጋራዥ ውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡በኋላ የራሳቸውን ትልቅ ጋራዥ ከፉቱ- እነታታቸው በገዙላቸው ቦታና ከባንክ ባገኙት ብድር ፡፡ የድሮዎቹ ውይይት ታክሲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀጥቅጠው የተሰሩት በእሳቸው ጋራዥ ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ - ጋስፖሪ እስትራዮቶ፡፡ በደርግ ዘመን ጋራዣቸውና ሌሎች ድርጅቶች ተወርሶባቸው ጐጃም ሄደው  ተቀጥረው ለመስራት ተገደዋል፡፡  ኢህአዴግ ሲገባ ንብረታቸው ተመልሶ እንደድሮው ቢዝነሳቸውን እንደሚሰሩ ተማምነው ነበር፡፡ ግን እንዳለሙት አልሆነም፡፡ አገር ውስጥ ገቢ ድርጀቱ በደርግ በተወረሰበት ጊዜ የተወዘፈውን ግብር 406ሺ ብር እንዲከፍሉ ጠየቃቸው፡፡ መክፈል ስላልቻሉ በሃራጅ ተሸጠ፡፡ አሁን ድርጅቱን አሁን ኤልፎራ ገዝቶ እየተጠቀመበት ነው የሚሉት ጋስፖሪ እስትራዮቶ፤ ሼክ አላሙዲ በገንዘብ እንዲረዷቸው ጠይቀዋቸው ወደ ዶ/ር አረጋ እንደመሯቸው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም ብለዋል፡፡ ዓይናቸው ስለደከመ ተቀጥረው ለመስራት እንደማይችሉና የሚጦራቸው እንደሌለ የተናገሩት ጋስፖሪ  በችግር እየማቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ፤ከጋስፖሪ ጋር ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ እነሆ፡-

ስለትውልድዎና አስተዳደግዎ  ይንገሩኝ ?

ጋስፓሪኖ እስትራዮቶ እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ ነው - በ1938 ዓ.ም፡፡ አባቴ ጣሊያናዊ፤እናቴ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ሰንጋ ተራ አካባቢ የመጀመሪያውን የጣሊያን ሬስቶራንት የከፈተችው እናቴ ናት፡፡ አባቴም እዛው ሰንጋ ተራ ጋራዥ ነበረው፡ ጣሊያኖችና ሾፌሮች ምግብ የሚመገቡት በዚሁ በእናቴ ሬስቶራንት ውስጥ ነበር፡፡ እናቴ በጣም ጎበዝ ሰራተኛ  ነበረች፡፡ እሁድ ቀን ብቻ ነበር እረፍቷ፡፡ ሲኒማ ትወድ ስለነበር፤ ፒያሳ ኪንግ ጆርጅ ባር አይስክሬም ትጋብዘኝና፤ሲኒማ ኢትዮጵያ ይዛኝ ትገባ ነበር፡፡

ትምህርትስ የት ተማሩ?

መጀመርያ እዛው ሰንጋ ተራ አካባቢ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቼ የግብረገብ ትምህርት ተማርኩ፡፡ ከዚያ በየነ መርድ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ከተማርኩ በሁዋላ ጣሊያን ት/ቤት ገብቼ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፡፡ ከትምህርት ቤት 10 ሰዓት ላይ ስወጣ አባቴን ጋራዥ እየሄድኩ እረዳው ነበር፡፡ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ነበር የምሰራው፡፡ ያኔ የትራንስፖርት ችግር ስለነበር ትሬንታ ካድሮ ዜታዋ የሚባሉ መኪኖችን ግራና ቀኙን ለሰዎች ትራንስፖርት አመቺ አድርገን እንሰራ ነበር፡፡ የጋራዡ ደንበኞች ጣሊያኖች ስለነበሩም በጋራዡ ውስጥ በስራ አስኪያጅነት የምሰራው እኔ ነበርኩ፡፡

አባትዎት ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጡ?

አባቴ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በግዳጅ ለመንገድ ስራ ነበር፡፡ አባቴ እንዴት ያለ ባለሞያ መሰለሽ፡፡ አናፂ ነው፤ ምን የመሰለ ዳቦ ቤት ነበረን፡፡ ቪኖም  ይጠምቃል፡፡ ቤታችን የወይን ተክል ነበረን፡፡ በየዓመቱ 2 ኩንታል ያፈራል፡፡ ከዱከም  ደግሞ ሌላ 2 ኩንታል ያመጣና ይጠምቅ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ደረጃ  ለቤ/ክ እና ትላልቅ ሰዎች ሲመጡ ይጋብዛል፡፡ ለራሱም ለጤንነቱ ሲል ይጠጣል፡፡ ጓደኞቹ ሲመጡ ሁለተኛውን ደረጃ ይጋብዛል፡፡ ሶስተኛውን ለሠራተኞች ነበር የሚጋብዘው፡፡

የአሁኑ የአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ ባለቤት ጣሊያናዊ ነበር፡፡ ያኔ ያልቻቪላ ነበር የሚባለው፡፡ ጣልያኑ የአባቴ ጉዋደኛ ስለነበረ እያማከረው  ጉደር፣ ሳሪስ፣ አክሱማይትና የመሳሰሉትን ስድስት አይነት ቪኖዎች ይጠምቅ ነበር፡፡ በሁዋላ ወደ አስር መኪኖች አስመጣና ወደ 200 ሰራተኞችን ቀጥሮ የወይን ጠጅ በሰፊው ማምረት ጀመረ፡፡ ጓደኞቹ የንስር ባለቤት የነበሩት   በወቅቱ እያንዳንዳቸው እስከ 20 አውቶብስ የነበራቸው እነ መኮነን ነጋሽ፣ ማሞ ካቻ፣ ማሞ ይበርበሩ የሚባሉት ነበሩ፡፡

ስለ ንጉሱ ምን ያውቃሉ?

ትምህርት ቤት ሳለን በገና በዓል  እርሳቸው ፊት ቀርቤ  ስጦታ እቀበል ነበር፡፡ ንጉሱ የጣሊያን ክልስ ይወዱ ነበር፡፡ ሲያዩኝ “አደግክ አደግክ” ይሉኝ ነበር፡፡ እሳቸው ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንድንቆይ ያደረጉን፡፡ አባቴን ቢያባርሩት ኖሮ እኛም አንኖርም ነበር፡፡ ያኔ የፈረንሳይ ክልሶችም ነበሩ፡፡ እሳቸው ፈረንሳይኛ በደንብ ስለሚችሉ ያነጋግሯቸው ነበር፡፡

አባትዎ አገር አልሄዱም ?

ጣሊያን አገር ሄጄአለሁ፡፡ ፊያት የመኪና ኩባንያን ጎበኘሁ፡፡ ከዛ ተመልሼ ለአባቴ “ዘመናዊ መኪናዎች መጥተዋል ፤ 45 ተሳፋሪ የሚያዙ፤ ደብረዘይት ናዝሬት የሚሠሩ፤ ሳሺዎችን እዚሁ ሞደፊክ እያደረግን እንስራ” አልኩት፡፡ ጣሊያን አገር በተነጋገርኩት መሠረት 20 ሳሺዎች አስመጣን፡፡ እኛ ነበርን የመጀመሪያዎችን 40 ሰዎች የሚጭኑ አውቶብሶች የሰራነው፡፡ ከዚያ በሁዋላ አምቼ ከጣሊያን አገር አመጣ፡፡ ያኔ አንበሳ አውቶብሶች የደከሙ ነበሩ፡፡ ክ/ሃገር በቂ ትራንስፖርት አልነበረም፡፡ አምቼ የእኛን ድርጅት አይቶና ከእኛ ጋር ተመካክሮ ቦሌ መንገድ ቢሮውን በመክፈት እዚሁ አውቶብስ መስራት ጀመረ፡፡ ከዛ ለምን ኦሪጅናል አውቶብስ አታስመጡም ብሎ ራሱ ሶስት አውቶብሶችን አመጣ፡፡ የመንግስት ድርጅቶች ኦሪጅናሎቹን መግዛት ጀመሩ፤ ያኔ ቅጥቀጣው ቀዘቀዘ፤ እኛም ጋ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ የጋራዥ ሰራተኞች ተበታትነው የየራሳቸውን ጋራዥ ከፍተው መስራት ጀመሩ፡፡ገነት ሆቴል አካባቢ ያለው ጠማማ ፎቅ ባለቤት የነበረው ሪሶ የተባለ ጣሊያናዊ  ለእናቴ “ኢትዮጵያ ውስጥ አፈር አለ፤ አፈሩን አቅልጬ ብረት እሰራለሁ ፤ ብረት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም”  መንግስትም ፈቀደለት፡፡ የድሮ ታንክ፤ በየመንገዱ የተጣለ ብረታ ብረት ነበር፡፡ አፈሩን ከመጀመሩ በፊት ብረቱን እያቀለጠ ቱቦላሬ፤ ላሜራ በኪሎ መሸጥ ጀመረ፡፡ እኛም ከጋራዥ የሚተራርፉ ብረታ ብረቶችን በኪሎ እንሸጥለት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አባቴን ምን ይለዋል ---- “ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ማግኘት ከፈለክ በሰፊው መስራት አለብህ፡፡ አሁን ያለህበት አካባቢ የኢንዱስትሪ ዞን አይደለም፤ ወደፊት ፍራሽ ነው ጥቅም አታገኝበትም” ያኔ ሰንጋ ተራ ቆንጆ መኖሪያ ቤት፤ ሬስቶራንት፤ ጋራዥና ዳቦ ቤት ነበረን፡፡

አባትዎት የጣሊያኑን ሃሳቡን ተቀበሉት ?

እናቴ ጥሩ ገንዘብ አስቀምጣ ነበር፡፡ የመንግስት ለውጥ ከመምጣቱ ስድስት ወር በፊት 8ሺ ካሬ ቦታ በእኔ ስም ገዛች፡፡ ጎተራ አሁን ሊቢያ ኦይል ከሆነው ነዳጅ ማደያ ፊት ለፊት ማለት ነው - ቦታው፡፡ ከዚያ ዙሪያውን አጠርንና ከባንኮ ዲ ሮማ  (ቴዎድሮስ ቅርንጫፍ ማለት ነው 30ሺ የኢትዮጵያ ብር ተበደርን (በዛሬ ስሌት 3 መቶ ሺ ብር ማለት ነው) በገንዘቡ ጥራቱን የጠበቀ ጋራዥ ተሰራ - ሶትሮያዋቶ ጋራዥ የሚባል፡፡ በወቅቱ እንደዚያ ዓይነት ጋራዥ አልነበረም፡፡ የፊያት መኪና ባለቤቶች አዲስ አበባ ሲመጡ እየጎበኙን  ማሽኖችና ቀለም መቀቢያዎችን ይሰጡን ነበር- እኛን ለመርዳት፡፡ እኛ ፋብሪካ የተቀባ መኪና አዲስ መኪና ነው የሚመስለው፡፡ አምቼዎች በራሳቸው አንድ ጋሻ መሬት ወሰዱ፡፡ ከዛም ትራክ ማስመጣት ጀመሩ፡፡ ታዲያ እኛ ነን መጀመሪያ ያስተዋወቅናቸው፡፡ በቼንቶ ዲ ኤች ኤ፣ በፊያት ኤንትሪ ገልባጭ መኪኖች፣ በቦቴዎች እኛ ነን ማንነታቸውን ያሳወቅናቸው፡፡ በጣም ሃብታሞች ነበርን፤ ወደ ሁለት መቶ ገደማ ሠራተኞች ነበሩን፡፡ ደርግ ከመጣ በሁዋላ አባቴ ያመው ጀመር፡፡ ከሁለተኛ ሚስቱ የወለዳቸውን ልጆች ሰብስቦ ጠራኝና “እነዚህን ወንድሞችህን አሳድጋቸው፡፡ ጣሊያን አገር ሄደው ይማሩ፣ ይረዱሃል፣ ይጦሩሃል” አለኝ፡፡ ከዚያ አባቴ ጣሊያን አገር ሄደ፤ ህመሙ ጠንቶበት እንደሞተ ሰማሁ፡፡ አንድ ወንድሜ ጣሊያን አገር ልኬው ተምሮ ኢንጂነር ከሆነ በኋላ ከንቲባ ለመሆን እየተንቀሳቀሰ እያለ ታመመና ሞተ፡፡ በኋላም ከእኔ እናት የተወለዱት ሁለቱ ወንድሞቼም እዚሁ ታመው ሞቱ፡፡ አሁን አንድ ወንድሜ ጣሊያን አገር ይኖራል፤ እሱም ታማሚ ነው፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከቡናና ሻይ ፊት ለፊት የነበረ አንድ ጋራዥ በጨረታ ገዛሁት፡፡ ጋራዡን አስተካክዬ ሠራሁት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የትራንስፖርት ችግር ነበረ፡፡ በከተማ ውስጥ ያሉትን ውይይት የተባሉ አሮጌ ታክሲዎች የቀጠቀጥኩት እኔ ነበርኩ፡፡ በእኔ ጋራዥ አንድ ታክሲ በ24 ሰዓት ውስጥ ተሰርቶ ያልቅ ነበር፡፡ ከዛ መንገድ ትራንስፖርት ጠራኝና በአስቸኳይ 500 ውይይቶችን እንድትሠራ ብሎ አዘዘኝ፡፡ የተለያዩ ባለሃብቶችም እንደዚሁ ትዕዛዝ ይሰጡ ነበር፡፡

ውይይቶች የእርስዎ የፈጠራ ስራ ስለመሆናቸው በምን ይታወቃል ?

ከውስጣቸው እኮ ጽሑፍ አላቸው፤ “ካርስፒየ ጋስፓሪኖ” ይላል፡፡ በተጠቃሚዎች አስተያየትም እያሻሻልነው መጣን፤ “ፐርፌክት” የሚባል ታክሲ መጣ፤ መንገድ ትራንስፖርት የ“ጐልድ ሜሪኩሪ” ተሸላሚ አደረገኝ፡፡ ጥሩ እየሠራን እያለ መኢሠማ በወቅቱ ከእኔ ጋራዥ ፊት ለፊት ነበር ቢሮው፤ በወቅቱ ሃላፊ የነበሩ ግለሰብ አላሰራ አሉን፤ ቁጥጥራቸው በዛብን፡፡ በጣም ፈራን፡፡  ጐተራ አካባቢ የነበረውን ትልቁን ፋብሪካ እንደሚወስዱት እጠረጥር ነበር፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላም እንደፈራሁት አሸጉብኝ፡፡ የወሎ ድርቅ ሲመጣ ለእናት አገር ጥሪ 150ሺ ብር ክፈል አሉኝ፡፡ ከድርጅቱ ውጪ ሆኖ ይከፈል ስል፤ ገንዘብ ቤቴ “ያለ መኢሠማ ትዛዝ አምስት  ሳንቲም አልከፍልም” አለች፡፡ በጣም ፈተና በዛብኝ፤ አሠሩኝ ደበደቡኝ፡፡ በቃ አዲስ አበባን ጥዬ ወጣሁ፡፡

ወዴት ሄዱ?

የወሎ ድርቅ ነበር ወቅቱ የተማሩ ሰዎች ይፈለጉ ነበር፡፡ የጋራዥ ሞያ አለኝ ፤መካኒክ ነኝ ስለ መኪና ሙያ አውቃለሁ ብዬ ሄድኩና ስራ አገኘሁ፡፡ “ጣና በለስ” የሳሊኒ ፕሮጀክት ነበር፤ ተነስቼ ጐጃም ገባሁ፡፡ አስር ዓመት ሙሉ የተለያዩ ስራዎች ስሰራ ቆየሁ፡፡ በዛ መሃል ኢህአዴግ መጣ፡፡ ከመምጣቱ በፊት ግን “ወያኔ አርነት” በሬዲዮ ተናገረ፡፡ እኔን ስሜን ጠቅሶ “አንድ የደርግ ከፍተኛ ባለስሥልጣን ባለ ፋብሪካውን ደብድቦ አባረረው ስንመጣ ይሄን ሁሉ እናስተካክላለን” ሲል ሰማነው፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ ገቡ፡፡  ከገቡ በኋላ ሰው ሁሉ አመልክት ታገኛለህ ብለው መከሩኝ፡፡ የሚመለከተው ቦታ ሄጄ አመለከትኩ፡፡ አልሆነም፡፡ በቃ ለፋሁና ተውኩት፡፡ በኋላ ዘዴ ዘየድኩ፤ በወቅቱ ለድርጅት ቦታ ሲጠየቅ ኢንዱስትሪ ዞን ተብሎ 1ሺ ካሬ ቦታ ይሰጥ ነበር፡፡ እንደምንም ብዬ ጐተራ ከሲሚንቶ ፋብሪካ ጀርባ ቦታ ወሰድኩ፡፡ ሳሊኒም 200 መኪና ጋረጋንቲና አሸዋ ረዳኝ፤ዙሪያውን አጠርኩት፡፡ ከባንክ 200 ሺ ብር ወሰድኩና 14 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ አስገባሁና ኢትዮጵያ ውስጥ የማይታወቅ ሜታል ወርክሾፕ ከፈትኩ፡፡ በርካታ ስራዎችንም መስራት ጀመርኩ፡፡ እፎይታ ተሰምቶኝ ኑሮዬን ቀጠልኩ፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ችግር ተፈጠረ፡፡ አገር ውስጥ ገቢ 406ሺ ብር ክፈል አሉኝ፡፡ “ለምን? ስል ጠየቅሁ”ከ15 ዓመት በኋላ በደርግ ጊዜ የተወረሰብኝና ለስደት የዳረገኝን፤ ስራ አቁሞ የነበረውን ድርጅት ሂሳብ አስልተው እዳ ይዘውብኝ መጡ፡፡ ከቡናና ሻይ ፊት ለፊት የነበረውን ማለት ነው፡፡ አሁን ሼክ መሐመድ አሊ አሙዲ ገዝተውት እየሠሩበት ይገኛል፡፡ አገር ውስጥ ገቢ አፈፃፀም ይዞ መጣ፤ንግድ ባንክ ደግሞ በእኔ ገንዘብ ነው የተሠራው ብለው መፋተግ ጀመሩ፡፡ በጨረታ ይሸጥ ተባለ፡፡ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሄድኩና ለመንኳቸው፡፡ አልሆነም፡፡ አገር ውስጥ ገቢ “ፓክትራ ለተባለ ሺፒንግ ላይንስ ድርጅት በ751 ሺ ብር ሸጠና ሁለቱ ተካፈሉ፡፡ እኔ ያለ አምስት ሳንቲም ሙልጬን ወጣሁ፡፡

አሁን በምን ይተዳደራሉ?

አሁን ይሄው የሰው እጅ እያየሁ ነው፡፡ ተቀጥሬ እንዳልሠራ አይኔ ደክሟል፡፡ በደህናው ጊዜ እኔ በገንዘብም በጉልበትም የረዳኋቸው ዛሬ ትልልቅ ቦታና ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ሸሽተውኛል (ለቅሶ) ያለጧሪ ቀባሪ አገር ውስጥ ገቢ ከቡናና ሻይ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውንና በደርግ ጊዜ በግፍ ለተወሰደብኝ በወቅቱ ከ2ሺ በላይ ውይይት ታክሲ በመስራት ከትራንስፖርት ችግር ህዝቡን ላወጣ፤ ከፍርድ አፈፃፀም የገዛሁት ጋራዥ በገፍ ከተወሰደብኝ በኋላ ኢህአዴግ ገባ ብዬ አገር አማን ብዬ ስራ ከመጀመሬ 406 ሺ ብር ክፈል ተብዬ፤ንብረቴን ልፋቴን አጥቼ እየተንከራተትኩ ነው፡፡ የቀረችኝን እድሜ በመንከራተት እያሳለፍኩ ነው፡፡

ይህ 406ሺ ብር የተጠየቀበት ከቡናና ሻይ ፊት ለፊት ያለው ዛሬ ሼክ ሙሐመድ አሊ አሙዲ ገዝተውት ሰፊ ስራ እየሰሩበት ይገኛል፡፡

በአካል ቀርቤ ችግሬን አወራኋቸው አዝነውልኝ “እኔ አሊ አሙዲ ቃሌ አንድ ናት፤ ሂድና እገሌ ከተባለ ግለሰብ መልስ ታገኛለህ” ብለው ካናገሩኝ በኋላ የላኩኝ ቦታ ሄጄ በተደጋጋሚ ብጠይቅ አልተሳካም፡፡

እርሳቸውንም ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ዛሬ የቤት ኪራዬንና ወጪዬን የምችልበት እንኳን አቅም የለኝም፡፡ ገንዘብ ባገኝ እንኳን በአባቴ ጣሊያናዊ ስለሆንኩ አገሬ ሄጄ እንደማንኛውም ጣሊያናዊ ጡረታ ይከፈለኝ ነበር፡፡

 

 

Read 2303 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:02

Latest from