Saturday, 26 May 2012 11:22

ጋብቻ የከለከለ የውሃ ችግር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ጀማል መሐመድ ሙሳ የ25 ዓመት ወጣት አርሶ አደር ሲሆን፤ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በኮምቦልቻ ወረዳ በኤጉ ቀበሌ የገንደዋሬ መንደር ነዋሪ ነው፡፡ ጀማል በመንደራቸው የነበረውን ከፍተኛ የውሃ እጦትና ችግር በምሬት ያስታውሳል፡፡ የዚህ መንደር ነዋሪዎች እንደ አንድ ቤተሰብ ነው የምንተያየው፤ ስለዚህ አንጋባም፡፡ ድሮ ጋብቻ የምንመሠርተው ከሌላ መንደር ጋ ነበር፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት በከፍተኛ የውሃ እጥረት ስንሰቃይ ነበር፡፡ በባህላችን ውሃ ፈልጐ መቅዳት የሴቶች ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ የሌላ መንደር ሴቶች ለማግባት ስንጠይቅ “ልጆቻችን ውሃ ፍለጋ በጭለማ ሲንከራተቱ በአውሬ ሊበሉ ይችላሉ፤ ዳገት ወጥተው ቁልቁለት ወርደው ከሩቅ ስፍራ ውሃ ሲፈልጉና ሲያመላልሱ ይጐዳሉ፤ …” በማለት የጋብቻ ጥያቄውን ስለማይቀበሉ እንደ አንድ ቤተሰብ የምንተያየው ነዋሪዎች፤ እርስ በርስ ለመጋባት ተገድደን ነበር ያለው ጀማል፤ “አሁን አክሽን ኤድ፣ ንፁህ ውሃ በመንደራችን ስላወጣልን እንቢ ሊሉ አይችሉም፡፡

ገና የጋብቻ ጥያቄ ሳናቀርብ፣ ፍላጐት እንዳለን ሲረዱ ዝምድና እንድንፈጥር ያግባቡናል፡፡ ዕድሜ ለአክሽን ኤድ” በማለት አስረድቷል፡፡ ወ/ሮ ከዶ ኢብሮ የዚሁ መንደር ነዋሪ ሲሆኑ፤ የስምንት ልጆች እናት ነበሩ፡፡ በተለያዩ በሽታዎች ሰባቱን ሞት ነጥቋቸው አሁን አንድ ልጅ ብቻ እንደቀረቻቸው በሃዘን ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ ከዶ የነበረባቸውን የውሃ ችግር በምሬት ይናገራሉ፡፡ ውሃ የሚቀዱበት ወንዝ ወይም ምንጭ በአካባቢው የለም፡፡ ውሃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም የመንደሩ ነዋሪዎች እንደሰማይ ርቋቸው እንደነበር ስታውሳሉ፡፡ ውሃ የሚቀዱት፤ በስርቆት ነበር - ግለሰቦች ካስቆፈሩት ኩሬ፡፡ የመንደሩ ሴቶች ከሌሊቱ ዘጠኝና አስር ሰዓት ተነስተውና ሁለት ሰዓት ያህል ረዥም ርቀት ተጉዘው ኩሬው ጋ ይደርሳሉ፡፡ እንደ ነሱው ለስርቆት ቀድመዋቸው የደረሱ የሌላ መንደር ሴቶች ካሉ እነሱ እስኪቀዱ ድረስ መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ተራቸው ደርሶ ወደ ኩሬው ሲገቡ፣ ውሃው አልቆ በጀርም፣ በባክቴሪያና በነፍሳት የተሞላ ድፍርስና ጭቃ ውሃ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በነፍሳትና በጭቃ የተሞላውን ውሃ በልብሳቸው እያጣሩ ወደ ቤት ቢወስዱም ብዙ ጊዜ የልጆቻቸው ሆድ እየተነፋና እየተቆዘረ እንደሚታመሙ ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወረፋ ሲጠብቁ ይነጋባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የኩሬው ባለቤት ደርሶ ጀሪካኖቻቸውን በጫንጫ (ከገበሬው እጅ የማይጠፋ መገልገያና መከላከያ መሳሪያ) ስለሚበሳሳው ሳይቀዱ እያዘኑ የሚመለሱበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ - ወ/ሮ ከዶ፡፡ በሌሊት ተነስተው ውሃ ለመስረቅ ሲጓዙ፣ የተለያዩ አደጋዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥማቸው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የዚሁ መንደር ነዋሪ ወ/ሮ ከሚያ ኢብራሂም ናቸው፡፡ ወ/ሮ ከሚያ፣ አምና አንዲት ሴት ከኩሬው ውሃ ስትቀዳ አዳልጧት ኩሬው ውስጥ በመግባቷ ድርጊታቸው የስርቆት ቢሆንም ነፍሷን ለማዳን ተጯጯሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች ደርሰው ከኩሬው አውጥተዋትና ሐኪም ቤት ወስደው ነፍሷ ቢተርፍም እስካሁን ድረስ በደንብ ያለመዳኗን ተናግረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ሌሊት ሲጓዙ አውሬ እንደሚተናኮላቸው የጠቀሱት ወ/ሮ ከሚያ፤ አንድ ቀን የሆነው ግን ምንጊዜም አይረሳቸውም፡፡ እንደተለመደው በቡድን ሆነው በጭለማ ሲጓዙ የጅብ መንጋ ከበባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ባለ ኃይላቸው በአቅራቢያቸው ወደነበረ ት/ቤት ሮጠው አንዱን ክፍል በርግደው በመግባት፣ ነፍሳቸውን እንዳተረፉ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጅቦች ውሃ ስለማያገኙ፣ ሲጠማቸው ኩሬውን ከበው ይቀመጣሉ፡፡ ውሃ ካልጠጡ ስለማይሄዱ መጀመሪያ ቀድተው እነሱን አጠጥተው፣ ጅቦቹ ሲሄዱ ለራሳቸው እንደሚቀዱ ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ ከዶና ወ/ሮ ከሚያ እንዲሁም በጀሪካኖቻቸው ውሃ ሲቀዱ ያገኘናቸው የመንደሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ደስታ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ጉድጓዱ ተቆፍሮ አገልግሎት ከጀመረ ጊዜው አጭር  ቢሆንም፣ አክሽን ኤድ ለዘመናት የዘለቀ የውሃ ጥማታቸውን ተገንዝቦ ረዥም መንገድ ሄደው ሳይደክሙና ሳይሳቀቁ በመንደራቸው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ስላቀረበላቸው ምሥጋናቸው ወደር እንደሌለው ገልፀዋል፡፡ በገንደዋሬ ከፍተኛ የውሃ ችግር እንደነበር የኮምቦልቻ ከተማ የአክሽን ኤድ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ የሺጥላ ዓለሙም ይመሰክራሉ፡፡ “ኤጉ ቀበሌ በተለይም ገንደዋሬ ከአንድ፣ ሁለትና ሦስት ዓመት በፊት ከፍተኛ የውሃ ችግር ነበረበት፡፡የአካባቢው ሕዝብ ሁሉ የጉድጓድ ውሃ ሲጠጣ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ሕፃናት በንጽህና ጉድለት በተለይም በምግብ እጥረት በጣም ይጐዱ ነበር፡፡ የውሃ ፕሮጀክቱን በስፋት ለመሥራት ስናስብ፣ ዋነኛው ዓላማ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘውን የሕፃናት ጉዳት ለመቅረፍ ታስቦ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ያለባቸውን የውሃ ችግር እንድንቀርፍላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አሁን ከዚህ ፕሮጄክት የሚጠቀሙ ሰዎች ለቤት የሚቀዱት ውሃ፣ ለከብቱም ለመስኖም የሚጠቀሙበት ያገኙትን ውሃ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ መጥቼ ቆሻሻ የኩሬ ውሃ ሲቀዱ አየሁ፡፡ “ይህን ውሃ ለማነው የምታጠጡት?” ስላቸው “ገና የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናትምኮ ይህንኑ ነው የሚጠጡት” የሚል መልስ ነበር የተሰጠኝ፡፡ ዚህ የተነሳ ችግሩ አሳሳቢ ስለነበር፣ በጀት አፈላልገንና ከወረዳው ውሃ ቢሮ ጋር በመተባበር ከ45 እስከ 60 ሜትር በመሳሪያ የተቆፈሩ አምስት ጥልቅ ጉድጓዶችና አራት የቦኖ ማከፋፈያዎች ሠርተናል፡፡ ለአንዱ ጥልቅ ጉድጓድ ወደ 255ሺ ብር፣ ለአምስት 1ሚ 275 ሺ ብር ያህል ወጥቷል፡፡ ለአራቱ ማከፋፈያዎች ደግሞ 140ሺህ ያህል ብር በአጠቃላይ 1 415.000 ያህል ብር ወጥቷል፡፡ እነዚህ ጉድጓዶች ለምን ያህል ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣሉ?የቀበሌው ነዋሪ ብዙ ነው፡፡ ለምን ያህል ሕዝብ አገልግሎት እንደሚሰጡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በቀበሌው፣ 2ሺህ ያህል አባወራዎች የሚኖሩ ይመስለኛል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ተሳትፎ ምን ያህል ነበር?ጉድጓዶቹ የሚቆፈሩት በመሳሪያ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ኅብረተሰቡ አይሳተፍም፡፡ ሕዝቡ ቆርቆሮ ገዝቶ ማከፋፈያዎቹን ያጥራል፤ የውሃውን አጠቃቀም ኮሚቴ መርጦ ይቆጣጠራል፣ ለተመረጡ የኮሚቴ አባላት ያርሳል፤ ለምሳሌ፣ አንዱ ማከፋፈያ ተሰጥቆ ነበር፡፡ ራሳቸው ሲሚንቶ ገዝተው ግን በኛ ቀጥረው አሠርተዋል፡፡ አሁን እንግዲህ የቀበሌው ነዋሪ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አግኝቷል ማለት እንችላለን፡፡ ጉዳቱ ዳውኢቲ ጅሬኛ (ታዳጊ የኑሮ መስተዋት)፤ የገንደዋሬ ሴቶች ራሳቸውንና አኗኗራቸውን መለስ ብለው ለማየት “የሕይወት መስተዋት” እንዲሉ ያወጡት ስም ነው፡፡ ይህ እርስ - በርስ የመማማሪያ መድረክ ሪፍሌክት (reflect) ይባላል፡፡ መምህርት የሺእመቤት እምሩ፤ በኤጉ ቀበሌ የኢራምቤዬ 1ኛ ደረጃ (1-4) ት/ቤት የቋንቋ አስተማሪ ስትሆን፤ የመንደሩ የሪፍሌክት አመቻች (ፋሲሊቴተር) ናት፡፡ አመቻች የሆነችው ደግሞ አክሽን ኤድ በሰጣት ሥልጠና ነው፡፡ በዚህ ዘዴ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን አንድ ላይ በመሰብሰብ የቤታቸውንና የመንደራቸውን ዋና ዋና ችግሮች አንድ በአንድ እየነቀሱ በመወያየት ማስወገድና ማሻሻል በሚችሉባቸው ዘዴዎች ላይ ይነጋገራሉ፡፡ ሌላው የሪፍሌክት ዓላማ መሃይምነትን መቀነስ ነው - ያልተማሩ ሴቶች መሠረታዊ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ፡፡ የሺእመቤት ሥራ የጀመረችው 28 ሴቶችን በማደራጀት ነበር፡፡ ቀደም ሲል ሴቶቹ ይተዳዳሩ የነበሩት እንጨት በመሸጥ ነበር፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ቅዳሜና እሁድ ይወያያሉ፡፡ የሺእመቤት፣ የእንጨት ንግድ የደን መጨፍጨፍ የአካባቢ መራቆት፣ የከባቢ አየር ለውጥ በረሃማነት፣ የዝናብ መጥፋት የመሳሰሉ በርካታ ጉዳቶች እንደሚያስከትል አስተማረቻቸው፡፡ ሴቶቹም የማያውቁትን እውነት ሰሙ፡፡ በድርጊታቸውም በራሳቸው፣ በልጆቻቸውና በአገር ላይ ጉዳት እየፈፀሙ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ ስለዚህ የእንጨት ንግድ እርግፍ አድርገው ለመተው ተስማሙ፡፡የእንጨት ንግዱን ከተው ገቢያቸውን በምን ይደጉማሉ? እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ ፋሲሊቴተሯ በእንጨት ምትክ ፍየል፣ እንቁላል፣ ላም፣ ቡና፣ መነገድ እንደሚችሉ መከረቻቸው፡፡ እነሱም ምክሯን ተቀብለው በተለያየ ንግድ ተሠማሩ፡፡ ሱቅም የከፈቱ እንዳሉ ሰምተናል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ወር ሙሉ የተወያዩት በዋነኛ የጋራ ችግራቸው በውሃ ላይ ነበር፡፡ በኅዳር ውይይት ጀምረው ሳያስቡት በአራት ወራት ውስጥ ንፁህ ውሃ በማግኘታቸው በጣም መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ስለኑሮአቸው ስለሚደርስባቸው ጉዳትና በደል፣ ስለቤተሰባቸው ስለጐጂ ባህል፣ ስለቤተሰብ ምጣኔ ስለንጽህና አጠባበቅ በተለይም ስለ ሽንት ቤት ችግር በአጠቃላይ በእያንዳንዷ ቤት ስላለው ችግር እየተወያዩ ነው፡፡ ውይይቱን ሲጀምሩ ሽንት ቤት ያለው አልነበረም፤ አሁን ግን 28ቱ ሽንት ቤት 11 ማዕድ ቤት (ኩሺና) መስራታቸውን፤ 70 ሴቶች የቤተሰብ ምጣኔ እየተጠቀሙ መሆኑን፤ የተሳታፊ ሴቶች ቁጥር 37 መድረሱን አብዛኞቹ ሴቶች መጻፍና ማንበብ መቻላቸውንና በአጠቃላይ የሁሉም ሴቶች ሕይወት  እየተለወጠና እየተሻሻለ መሆኑን የሺእመቤት አስረድታለች፡፡ “ካሁን ቀደም አውቀት አልነበረንም፤ አዕምሯችንን አንጠቀምበትም ነበር፡፡ ዕቅድ አልነበረንም፡፡ ስናደርግ የቆየነው ያለንን መጨረስ ብቻ ነበር፡፡ ከተደራጀን በኋላ እየተገናኘን ስንነጋገር የነበረው ስለቤታችን ገቢና ወጪ እያነፃፀርን ነበር፡፡ ገቢያችን ትንሽ ወጪያችን ብዙ ሆኖ አገኘነው፡፡ “ስለዚህ ያለንን ጉልበት ተጠቅመን ይህን ችግር መለወጥ እንችላለን፡፡ ወደፊት ደግሞ አቅማችን በደከመበት ቦታ የሚረዳን አናጣም ብለን እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ ሽንት ቤት መቆፈሪያ ቦታ ያለን ሰዎች ቆፍረን እየተጠቀምን ነው፡፡ ቦታቸው ድንጋያማ በመሆኑ መቆፈር ያልቻሉም አሉ፡፡ “ድሮ እንኖር የነበረው ከከብቶች ጋር በአንድ ቤት ነበር፡፡ ምግብ የማበስለውም እዚያው ነበር፡፡ አሁን ግን ኩሺና ስለሰራሁ ምግብ የምሠራው በሌላ ክፍል ነው፡፡ ለከብቶችም ቤት ለመሥራት ቦታ አዘጋጅቻለሁ፡፡ እኔ አሁን የምተዳደረው በፍየል ንግድ ነው፡፡ ከሳ ያሉ ፍየሎች ገዝቼ አድልቤ እሸጣለሁ፡፡ ሌላ ደግሞ ገዝቼ አደልባለሁ፤ በዚህ ዓይነት ገቢዬን እያሻሻልኩ ነው፡፡ አሁን በትርፉ የገዛኋቸው ሁለት ወጠጤና አንዲት ሴት ፍየል አሉኝ፡፡ ውይይት ከጀመርን ወዲህ ተለውጠናል፡፡ ሴት መለወጥ እንደምትችል አምኛለሁ፡፡ ብዙ የማኅበራችን አባላትም እየተለወጡ ነው፡፡ ከውይይቱ ባገኘነው ብርሃን እየተንቀሳቀስን ነው” ያለችው የውይይቱ ቡድን አባል ወ/ሮ ሞሚና ኢብሮ ናት፡፡ “በፊት ተጨማሪ ሥራ አንሠራም ነበር፡፡ ያመረትነውን ይዘን ወደ ገበያ እንሄድና ግማሹን አስፈጭተን ግማሹን እንሸጣለን፡፡ መሰባሰብ ከጀመርን ወዲህ ግን፣ ዝም ብለን አይደለም የምንሸጠው፤ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘን ነው፡፡ ድሮ የወንድ እጅ ጠብቀን ነበር የምንኖረው፡፡ አሁን ግን በምናገኘው ትርፍ ለልጆቻችንና ለባሎቻችን አንዳንድ ነገሮች እንገዛለን፡፡ ባሎቻችንም ለውጣችንን በማየት አሁን አሁን እነሱም ትምህርት እየፈለጉ ነው፤ አንዳንዶቹ መሰባሰብ ጀምረዋል” ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ዙልፋ ሁሴን ናቸው፡፡ “በጋብቻ ላይ ጋብቻ ለማስቀረት ችለናል”ቄሬንሳ ቀ.ገ.ማ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ በትዳር ላይ ትዳር እንጥል መቁረጥ የመሳሰሉ ጐጂ ባህሎችን ለመከላከል በማኅበር የተደራጁ ሴቶች የሚንቀሳቀሱበት ቀበሌ ነው፡፡ “አንዲት ሴት ስትገረዝ ደሟ ለረዥም ጊዜ እየፈሰሰ ትሰቃያለች፡፡ ስትወልድም ሦስትና አራት ጊዜ በምላጭ የምትቆረጥበት ጊዜ ነበር፡፡ በትዳር ላይ ያሉ የተገረዙ ሴቶች በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ይቸገራሉ” ያሉት ጐጂ ባህሎች ለመከላከል የተቋቋመው የማኅበር ም/ሊቀመንበር ወ/ሮ ቀመሮ ኡስማን ናቸው፡፡ ጐጂ ባህሎች በአካባቢው ምን ያህል ተቀርፈዋል?በአሁኑ ጊዜ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ለማስቀረት ችለናል፡፡ ግርዛትን በተመለከተ ቀደም ሲል ወደ ሌላ ቦታ እየወሰዱ የሚያስገርዙ ሰዎች እንኳ ትተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሳይገረዙ ያገቡ ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶች አሉ፤ ከመገረዝ ዕድሜ ያለፋቸውም ሴቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች በመነሳት በአካባቢው ጐጂ ባህል አስቀርተናል ማለት እንችላለን፡፡ ጐጂ ባህል ለማስቀረት ምን ሠራችሁ? ኅብረተሰቡ እንዴት ተቀበላችሁ?በየመንደሩ አንዳንድ ሴቶች አሳምነን አስቀምጠናል፡፡ እነሱ በሰፈራቸው የሚፈፀመውን ነገር ይጠቁሙናል፡፡ ድሮ ያልተገረዘች ሴት የሚያገባት የለም፤ ብትሰግድም እርኩስ ነገር ይዛ ስለሆነ ፀሎቷ ተቀባይነት የለውም ሲባል ነው የምናውቀው፡፡ የሃይማኖት አባቶችን ቀርበን ስለ ሴት ልጅ ግርዛት ስንጠይቅ፣ ከሃይማኖት ረገድ ብትገረዝም ባትገረዝ ጉዳት የለውም አሉን፡፡ ሰለዚህ የሴት ልጅ ግርዛት በሕግ የተከለከለ ከሆነ በሃይማኖትም ጉዳት እንደሌለው ከታወቀ ለምን አይቀርም? በማለት ሕዝቡን አስተማርን፡፡ ሌላ ደግሞ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወርን ልጃገረዶችንና ሕፃናት ሴቶችን በማደራጀት ይኼ ነገር በሃይማኖት የተከለከለ ግዴታ አይደለም ብላችሁ እንቢ በሉ፤ በአሁኑ ወቅት ፍ/ቤት አካባቢ ሴቶች በዝተው የሚታዩት ያለ ዕድሜ እያገቡ፣ በትዳር ውስጥ በሚፈጠር ችግር ነው፡፡ የተገረዙ ሴቶች ወሲብ ሲፈጽሙ ስለማይጣጣሙም ችግር ይፈጠራል፡፡ በዚህ የተነሳ ለፍቺ ወደ ፍ/ቤት ስለሚሄዱ ነው እዚያ አካባቢ የሴቶች ቁጥር የበዛው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ተገንዝባችሁ ቤተሰቦቻችሁ እንኳ ቢያስገድዷችሁ እንቢ በሏቸው እያልን እናስተምራለን፤ እንመክራለን፡፡ እነሱ በሚገባ ረድተውናል፡፡ ልጆቻቸውን ማስገረዝ የፈለጉ ሰዎች ሊቀመንበሯ የራሷን ልጅ አስገርዛ እኛን ትከለክላለች በማለት ግርዛት ወዳልተከለከለበት አካባቢ ሲወስዱ ተይዘው ስድስት ልጆች ሰለባ ከመሆን አድነናል፡፡ የእኔ ልጅ ያቻትና አልተገረዘችም፡፡ ያለመገረዟን ለማረጋገጥ ከተማ ወስጃት ከሐኪም ቤት ማስረጃም አምጥቻለሁ፡፡ ብሞት እንኳ እንዳይገርዟት ረግሜ ነው የምሞተው፡የድርጊቱ ፈፃሚዎች ወንዶች ናቸው፡፡ እንዴት ተቀበሉዋችሁ?ስለ ጉዳቱ ካስረዳናቸው በኋላ የተገረዘች ሴት ያገቡ ወንዶች እየተቆጩ ነው ያሉት፡፡ ወደ ኋላ መመለስ ቢቻል ያልተገረዘች ሴት ነበር የምናገባው ይላሉ፡፡ ትምህርቱ የገባቸውና ያላገቡ ወንዶች ደግሞ የተገረዘች ሴት በፍፁም አናገባም፤ ይህን ትምህርት አሁን ያስፋፋው አክሽን ኤድ እስካሁን የት ነበር? እያሉ ነው፡፡ ያለ ዕድሜ ሊዳሩ የነበሩ ስድስት ታዳጊዎችም አድነናል፡፡ አክሽን ኤድ ምን አስተማራችሁ?

 

ስለ ጐጂ ባህላዊ ድርጊት ድሮ ቀበሌ ስንሰራም እናውቃለን፡፡ ያኔ አምስት ነበርን፡፡ አሁን አክሽን ኤድ ሰባት ሴቶች አንድ የአገር ሽማግሌና አንድ የሃይማኖት አባት በአጠቃላይ ዘጠኝ ሰዎች አሠለጠነ፡፡ ሁላችንም በትብብር ስለምንሠራ የሠለጠንበትን ትምህርት ተግባራዊ ስላደረግን ነው ለውጥ የመጣው ያሉት ደግሞ የማኅበሩ ሊቀመንበር ወ/ሮ ቀመሮ አሊሽ ናቸው፡፡ እናንተ ሕዝቡን በማስተማርና በመለወጥ ነው ጊዜያችሁን የምታሳልፉት፡፡ መተዳደሪያችሁ ምንድነው?

አክሽን ኤድ ከሁለት ዓመት በፊት ለሰባታችንም አንድ አንድ ሺህ ብር መድቦ በዚያ ገንዘብ ፍየሎች ገዝተናል፡፡ ዛሬ በእያንዳንዳችን ቤት ሰባትና ስምንት ፍየሎች አሉን፡፡ ስለዚህ አክሽን ኤድ ደሞዝ እንደከፈለን ነው የምናስበው፡፡ በቀበሌም የሚደረግልን ድጋፍ አለ፡፡ ድሮ ለሥራ ስወጣ ባለቤቴ ዝም ብዬ የምዞር ይመስለዋል በማለት እፈራ ነበር፡፡ ፍየሎቹን ከገዛሁ በኋላ ግን ኩራት ተሰምቶኛል፡፡ አሁን ኮምቦልቻም ስጠራ ያለፍርሃት እሄዳለሁ፡፡ ስለዚህ ለተደረገልን ድጋፍ በጣም እናመሰግናለን፡፡ አክሽን ኤድን የምናመሰግንበት ሌላው ምክንያት የሃይማኖት አባቶችና የቀበሌ አመራሮች አብረውን እንዲሰለጥኑ በማድረጉ ነው፡ እነዚህ ክፍሎች ከእኛ ጋር ተቀናጅተው ባይሠሩ ኖሮ አሁን የተገኘው ለውጥ ላይመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለን፡፡ ከዋናዎቹ ሰዎች ጋር በመሥራታችን ውጤታማ ስለሆን በጣም እናመሰግናለን ብለዋል ወ/ሮ ቀመሮ አሊሽ፡፡

 

 

Read 2389 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 16:14