Saturday, 26 May 2012 10:50

ሌላኛው ቤታችን

Written by  ተስፋዬ ዓለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

ይህም የእኛ ቤት ነውና የእኛ ቤት ብየዋለሁ፡፡ በቀኑ ውስጥ ካሉት ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን እዚህ እናሳልፋለን፡፡ እንግዲህ የመኖሪያ ቤት የተከራየነው ከቀኑ ለሚተርፈን አንድ ሶስተኛ ሰዓት መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም እያወቁ እንኳን አከራዮቻቸችን አስተያየት አያደርጉልንም፡፡ የጋዝ ዋጋ ጨመረ፣ የሸቀጦች ዋጋ ናረ ፣ ኑሮ ተወደደ፣ ምናምን. . . ምናምን፤ የቤት ኪራይ ዋጋ ለመጨመር ሰበባ ሰበብ ናቸው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ግን የእኛው ቤት ያልኩትን ሌላኛውን ቤታችንን ላስተዋውቃችሁ፡፡ ኪራይ አንከፍልበትም በቀኑ ውስጥ ካሉቱ ከሃያ አራቱ ሰዓት ውስጥ ግን የክፍል ውስጥ ትምህርት ከሌለን በስተቀር የማንለየውን ቤታችን ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ አንገብጋቢ እና አጣዳፊ ስራ ሲኖር ሃያ አራቱንም ሰዓት እዚሁ ማሳለፍ ግድ ይላል-ከድህር ምረቃ ቤተ መፅሀፍ፡ቤተመፃህፍታችን እጅግ ብዙ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለእኛ ከማንበቢያና ከንባብ ክፍልም በላይ ነው፡፡ የእንግሊዝኛው Home sweet home የሚለው አባባል በደንብ ይገልፀዋል፡፡

እኛም በሃገርኛው ዘፈን “ቤቴ ጌጤ” ብለን አያንሰውም፡፡ ቤተመፅሃፋችን ዝም ያለ ነው፡፡ ዝምታውን የምታገኙት ግን በሩን ስታልፉ ነው፡፡ በሩን አልፋችሁ እስክትገቡ  በዙሪያው ካሉ የመማሪያ ክፍሎች የወጡ፤ ወይ መምህራቸውን የሚጠብቁቱ በጥንድ እና በቡድን  እየሆኑ ተማሪዎች በሚያነሷቸው ውይይቶች እና ክርክሮች፣ ወይም ደግሞ ወደሮአቸው በሚወጡ እና በሚገቡ መምህራን ወይም መምህራኖቻቸውን ፈልገው እዛው አካባቢ ውርውር በሚሉ እና በሚያንዣቡቡ ተማሪዎች፤  ከዚሁ ቤተመፅሃፍ ስልክ ለመመለስ በሚጣደፉ ተማሪዎች ውጫዊው ፀጥታ ይረበሻል፡፡ ይህ ረብሻ ግን ልክ የቤተመፅሃፉን የመግቢያ በር እንዳለፋችሁ ከጀርባችሁ ይቀራል፡፡ ከመግባታችን በፊት ግን በሩ ላይ እንደቆምን አንዴ ቀና እንበል፤  ከበሩ አናት አንድ ነገር እናስተውላለን፤ ትልቅ የግድግዳ ሰዓት፡፡ በመጀመሪያ ይህ ሰዓት በአግባቡ ዘጠና ዲግሪውን ጠብቆ አልተሰቀለም ሲቀጥልም ይህ ሰዓት የሚቆጠረው ሁልግዜም 7፡15 አለፍ ብሎ ነው፡፡ ጠዋትም፣ ማታም፣ ቀንም፣ ሌሊትም ሁሌም በዚህ ሰዓት አቆጣጠር ሰዓቱ ዝንፍ አይልም - ምንጊዜም ያው 7፡15 አለፍ እንዳለ ነው፡፡ ማንም ተመልክቶት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ መኖሩንስ ማን አውቆ!  ምናልባት ሰዓቱ ራሱ ብቻ መሰለኝ እዚህ ቦታ መኖሩን የሚያውቀው፤ ግና እሱም ቢሆን ራሱን ረስቷል፤ የጊዜ ዑደትን ልኬት የመስፈር ስራውን አቁሟል፡፡ የሰቀሉትም አንዴ እንደምንም ተንጠራርተው ከዚህ ቦታ አኑረውት ሲያበቁ በሌላ ስራ ስለተጠመዱ ረስተውታል፡፡ ያስተዋሉት ቀን የሞተ ባትሪውን ቀይረው ሰዓቱ መስራት ሲጀምር እሪ ብሎ መጮሁ አይቀርም፤ ምክንያቱም ከለመደው የሰዓት አቆጣጠር 7፡ 15 አለፍ ካለው ሊያዛንፉት ነውና፡፡  በሩን አልፋችሁ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ የዝምታው ድባብይቀበላችኋል፤ የፍተሻ ቦታው እና የቤተ መፅሃፉ የፍተሻ ሰራተኛ መጀመሪያ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ እነሱን እንዳለፋችሁ የማስታወቂያ ሰሌዳው አለ፡፡ ማስታወቂያዎቹ እንደወቅቱ ሁኔታ ቢለዋወጡም የሞባይል ስልኮቻችሁን አጥፉ ወይም ፀጥ አሰኙ (silence your mobile) የሚለው ማሳሰቢያ ግን በቋሚነት ከቦታው አይጠፋም፡፡ እልፍ እንዳልን ደግሞ አዳዲስ የመጡ መፃህፍትን የምንተዋወቅባቸው በመስተዋት የተሰሩ የመደርደሪያ ሳጥኖች እንደየወቅቱ ሁኔታ አዲስ ከገቡ መፃኅፍት ጋር ወይም ደግሞ ባዶአቸውን በተቃራኒ ከግድግዳው ተለጥፈውው አሉ፡፡  ፊት ለፊት ካለው የመስተዋት ሳጥን ጎን በኮላዥ የተሰራ የዓለም ካርታ አለ፤ ከጊዜ ብዛት ግን የተሰራበት ነገር እየረገፈ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ከትንሽ ግዜ በኋላ ይህም ካርታ ወደ ነጭ ሰሌዳነት መቀየሩ እንደማይቀር ምልክቶች እየታዩበት ነው፡፡ ወደ ውስጥ እየዘለቅን ነው፤ ከበስተቀኝ የቤተ መፅሃፉ ሰርኩሌሽን መደርደሪያ ከነመፃህፍቱ በሙሉ ግርማ ሞገሱ ቆሟል፡፡ የሰርኩሌሽን ሰራተኞቹ በየወንበራቸው ከዚሁ መደርደሪያ ስር አይጠፉም፡፡ ከፊት ለፊትም የፔሪዮዲካልስ እና የሪፈረንስ (ወቅታዊ እና ዋቢ ህትመቶች) ቢሮ አለ፤ ስንወጣም ስንገባም እንሳለመዋለን፡፡ እዚህ ጋር ቆመን ስናስተውል ቤተ መፅሀፉ የፊደል “ሀ” ቅርፅን ወደቀኝ አዙሮ ነው ተሰራው፡፡ ከበስተግራ ደግሞ የግል የጭኔዋ(ላፕቶፕ ኮምፒዩተር) ለሌላቸው ተማሪዎች የተዘጋጁ የዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ፤ ሁሌም ማለት ይቻላል እነዚህ ኮምፒዩተሮች ቢዚ ናቸው-ስራ ይበዛባቸዋል፡፡ በዚሁ ወደ ግራ ስንዘልቅ የመፅሃፍ መደርደሪያዎች ከተለያዩ የምርምር ህትመቶች እና እድሜ ጠገብ መፃህፍቶቻቸው ጋር አሉ፡፡ ከነዚህ መደርደሪያዎች ፊት ለፊት ሁለት ረጃጅም ጠረጴዛዎች ወደ ግድግዳው ጠጋ ብለው ከእነወንበሮቻቸው ተሰድረዋል፡፡ እነዚህ ጠረጴዛዎች ለግድግዳው ቅርብ ናቸው፡፡ ዋነኛ ግልጋሎታቸው ለእንደኔ አይነቱ ከድሃ ከፍ ከሃብታም ዝቅ ላልነው ጭኔዋ ኖሮን ግን ባትሪዎቻችን ደከም ላሉብኑ ሁነኛ እና ተመራጭ ስፍራዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በግድግዳው ላይ የተሰኩ ሶኬቶች ለላፕቶፖቻችን የኤሌክትሪክ ሃይል በቀጥታ ለማግኘት የሚያስችለን ስፍራ በመሆኑ ነው፡፡  እዚሁ ጋ ከበስተግራ ከግድግዳው ጋር ተያይዘው በጣውላ የተሰሩ ለግል ማንበቢያነት የተዘጋጁ ክፍሎች አሉ፤ የተወሰኑቱ ሶኬት አላቸው፡፡ ወደ ቤተመፅሀፉ በስተቀኝ በኩል ስንመላለስ፤ ሠልፋቸውን ጠብቀው የተሰደሩ ስድስት ምሰሶዎች አሉ፤ እነዚህን ምሰሶዎች ከማለፋችን በፊት፣ ምሰሶዎቹ ጋር እንደቆምን ከጀርባ ወቅታዊ ህትመቶች የሚቀመጡበት መደርደሪያዎች፣ ከምሰሶዎቹ ፊት ለፊት ደግሞ ለእነዚሁ ፅሁፎች፣ ጋዜጦች እና መፅሄቶች ማንበቢያ የተዘጋጁ ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች አሉ፡፡ ከግድግዳው በስተቀኝ ከግድግዳው ጋር ተለጥፈው እንደ በስተግራው የግድግዳ ክፍል ሁሉ ለግል ንባብ የተዘጋጁ የጣውላ ክፍሎች ከጠርዝ እስከ ጠርዝ ከአናታቸው ቁጥሮቻቸው ተለጥፎ ተሰልፈዋል፡፡ወደእነዚሁክፍሎችጠጋብለውግድግዳውን ተጎራብተው ሁለት ሰፋፊ ጠረጴዛዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጠረጴዛዎችም ከበስተግራ በኩል እንዳሉቱ ዋነኛ ግልጋሎታቸው ከላይ እንደገለፅኩት ለእንደኔ አይነቱ የጭኔዎቻችን ባትሪዎቻችን ደከም ላሉብኑ ነው፡፡ እነዚህን እና የተወሰኑ ሶኬት ያላቸውን ለግል ማጥኛነት የተዘጋጁ ክፍሎችን ለማግኘት ምንግዜም ቀድሞ መገኘት ግድ ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች የሁሉም ተማሪ ምርጫዎች ናቸው፡፡ መብራት ፈላጊው ብዙ ነው፤ ስለዚህም እነዚህ ቦታዎች ምንግዜም ይያዛሉ፡፡ በቤተመፅሃፉ ግድግዳዎች ላይ በተለይም ሶኬቶች አካባቢ “እባካችሁ፣ በኤለክትሪክ ባለሙዎች ከተዘረጋው በስተቀር በመተላለፊያዎች እና ከክፍል ወደ ክፍል የኤሌክትሪክ ገመዶችን አትዘርጉ፡፡” የሚል ማሳሰቢያ ተለጥፏል፤ ግና እነዚህን አካባቢዎች ስታስተውሉ የኔትወርክ ዝርጋታ ባለሙያዎች ፍቱት ቢባሉ አቅጣጫውን ማግኘት በሚቸግራቸው መልኩ ሶኬቶች ተጠላልፈው ተዘርግተው የማይገጥሟችሁ ቀናት ከስንት አንድ ነው፡፡ ተማሪው በራሱ ለሶኬት እጥረቱ የሰጠው መፍትሄ ነው፤ ማከፋፈያ ከቤቱ ይዞ ይመጣል፡፡  ከመግቢያው በር ጀምሮ የሞባይል ስልኮቻችሁን አጥፉ ወይም ፀጥ አሰኙ (silence your mobile) የሚለው ማሳሰቢያ የቡድን ውይይት አይፈቀድም ከሚለው አባሪ ጋር በቤተ መፅሃፉ የውስጥ ክፍል የተለያዩ ቦታዎች ተለጥፈዋል፡፡ ተማሪዎች ግን በጥንድ እና ቁጥሩ ከሶስት ባልበለጠ ቡድን እየተደራጁ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ስራቸውን ይሰራሉ፣ ይቀላለዳሉ፤ ባስ ሲልም የታፈነ ሳቅ ይስቃሉ፡፡ ከንባብ በተጓደኝ ይህ ቤተ መፅሀፍ የተማሪው ዋነኛ የኢንተርኔት መጠቀሚያ ቦታ ነው(ጥቂት የተማሪ ሃብታሞች ግን ከእኛ ጋር መጋፋት ስለማይፈልጉ ከቤታቸው ሆነው ሲዲኤምኤ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡) እናም ተማሪዎች፣ የሚያዩት ድረ - ገፅ ላይ ያነበቡት ወይም የሰሙት፤ ካስገረማቸው ወይም ካስደነገጣቸው ወይም ደግሞ የሆነ አዲስ ስሜት ከፈጠረባቸው ብዙውን ግዜ ተጠጋግተው ስለሚቀመጡ አንዱ ላንዱ ይነግረው እና የውይይት ርእስ ይሆናል፡፡ ውይይቱ እዚያው ይጀመርና ለቡናና ለሻይ  አብሮ ከተማሪው ጋር ይወጣል፡፡ የስልኩም ነገር በጣም ነው የሚነገር፤ ድካም እና መሰላቸትን ያስረሳል፤ ዘና ደርጋል፡፡ በተለይም የሃብታም ቁም ሳጥን በሚያክሉት የግል የጥናት ክፍሎች ውስጥ ለሚያነቡት ውጭኛው የቤተ መፅሃፉ ክፍል እንዳለም ትዝ የሚላቸው አይመስለኝም፡፡ በራቸውን ከውስጥ ዘግተው ሙሉ ሃሳባቸውን በሚያነቡት ወይም በሚሰሩት ዙሪያ ብቻ ስለሚሆን ስልካቸው ሲጠራ፣ ብቻቸውን እንደሆኑ ስለሚሰማቸው የስልክ ጥሪዋቻቸውን ይመልሳሉ “የት ነህ? እኔ አሁን ፖስት ግራጁዬት ነኝ ስወጣ ልደውል?” ወይም ደግሞ  የሚወጡበትን ሰዓት ይናገሩና “በቃ በዚህ ሰዓት እዚህ ቦታ እንገናኝ” አጣዳፊ ሲሆን ደግሞ “ጠብቀኝ፣ ጠብቀኝ አሁኑኑ እመጣለሁ. . . “ ሌላም ሌላም… የድምፃቸው መጉላት አይታወቃቸውም፤ ዘና ብለው ያናግራሉ፡፡ ንዴ እንዲሁ  የመመረቂያ ስራውን ለማጠናቀቅ ከእነዚሁ ክፍሎች የመሸገ ተማሪን ሁኔታ ላውሳችሁ፡፡ እንደተጣደፈ ከአነጋገሩ ያስታውቃል፡፡ ስልኩ ጠራ፤ ድምፁን ዝቅ ማድረግ አልቻለም፡፡ የደወሉለት የመመረቂያ ፅሁፉ አማካሪ መምህሩ ነበሩ “ዶክተር፣ እዚሁ ከእርሶ ቢሮ ስር. . .  ፖስት ላይብረሪ ነኝ፡፡ ትንሽ ጊዜ. . . እሺ. . .እሺ  አስተካክል ያሉኝን እየጨረስኩ ነው፣ . . . ተበላሽቶብኝ እኮ ነው. . . በድጋሚ እየሰራሁ ነው፡፡ ትንሽ ግዜ አስራ አምስት ደቂቃ ብቻ” ስልኩ ተዘጋ፡፡ የተሳቀው ሳቅ መቼም አይደገም ፡፡ ይህ ተማሪ ግን አይደለም እንዳለው በአስራ አምስት ደቂቃ… እኔ በቆየሁባቸው ሁለት ሰዓታት ውስጥ ከዚህች ክፍል ብቅ አላለለም፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ምናልባትም መረበሻቸው የሚታወቃቸው የውጭኛው የቤተመፅሃፍ ተጠቃሚ አንዴ በህብረት ሲስቅ ነው፡፡ ብልጦቹና ያሉበትን ያልረሱቱ ጎላ ባለ የሹክሹክታ ድምፅ ከላይኞቹ ባልተለየ መልኩ ጥሪያቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ የሞባይል ስልኮቻችሁን አጥፉ ወይም ፀጥ አሰኙ (silence your mobile) የሚለውን ማሳሰቢያ ተዉት፤ መቼም፣ መቼም ቢሆን ተከብሮ አያውቅም፡፡ የስልኮች የጥሪ አይነት ይሰማል፡፡ የጠራው ስልክ፣ እዛው በሹክሹክታ በአጭሩ ሲመለስም ትሰማላችሁ፡፡ በሹክሹክታ በአጭሩ ሊመለሱ የማይችሉቱን ደግሞ ስልኩ ጥሪውን ሳያቆም፤ ከመዘጋቱ በፊት ለመመለስ ያለው ጥድፊያ ፈገግ ያሰኛችኋል፤ በተለይ ከመውጫው ቦታ ፍተሻው ላይ “ሀሎ ሀሎ ፖስት ነኝ” “ላይብራሪ፣ ላይብራሪ፣  ላይብራሪ” በሹክሹክታ ስልኩ እንዳይዘጋ ለማቆየት፤ በጣም የተጣደፈው ገፍትሮአችሁ ሊሄድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ስልኩ ከመዝጋቱ በፊት መመለስ አለበት፡፡ ማን ያውቃል? ይህን ስልክ አለመመለስ፤ ከሚስት፣ ከፍቅረኛ ከስራ ሃላፊ ወይም ደግሞ ከራሱ ከስራ ጋርም ሊያቆራርጥ ይችላልና፡፡ እናም ይህን ስልኩን ለመመለስ አ . . .ቤ. . . ት. . . ጥድፊያ፡፡ እዚህ ጋር ግን ጉዳያቸውን በአጭር መልዕክት በፀጥታ የሚተኩሱ ስልጡኖችም አሉ፡፡አብዛኛውን ግዜ ከግል የጥናት ክፍሎች ውስጥ የሚያነቡ ተማሪዎች የሚገቡት ከጓደኞቻቸው ጋር ነው፡፡ ሲደክማቸው አንዱ አንዱን  ነጥብ ሊያስቆጥር በሚችልበት ሁኔታ ከጓደኛው ላይ ነገር ጣል ያደርግበታል፡፡ ፈጣን ወይም ደግሞ ያደባ፣ የሰባ የዘገየ የመልስ ምት አይቀርም፡፡ አእምሮ ሲሰላች ለቡና ከመውጣት በፊት ዘና የሚባልበት የመጀመሪያው መንገድ ነው፡፡ ሁኔታው በጣም አስቂኝ በመሆኑ ወይ የታፈነ አለያም የፈነዳ ሳቅ ቡፍ ይላል፡፡ ይሄኔ ወይ ከግራ ወይ ከቀኝ ወይም ደግሞ ከሁለቱም በኩል ክፍሎቹን የሚለያቸው የጋራ የጣውላ ግድግዳ ይቆረቆራል፡፡ መልዕክቱ “ረበሽከኝ እባክህ ድምፅህን ቀንስልኝ፣  ረብሻህን አቁምልኝ” ማለት ነው፡፡ እነዚህ የጥናት ክፍሎች ውስጥ ምስጢራዊ ነገሮችን ለመስራት ያመቻሉ፡፡  ግን ምስጢር ነውና አልነግራችሁም፡፡ አዳር የሚያነቡ ጓደኞቼ የተለየ ገጠመኝ ቢነግሩኝም እኔ እስከአሁን ብዙ የተለየ ነገር አልገጠመኝም፡፡ አንድ በጣም ያለዘብኩትን እና ያጠየምኩትን የራሴን ገጠመኝ ላጋራችሁ፡፡ ከአንደኛው ክፍል ውስጥ ከጓደኞቼ ጋር አድፍጠን ስራችንን እየሰራን ነው፡፡ አጎራባቾቻችን ሴቶች ነበሩ፤ ሳቅ በሳቅ ሆኑብን አላቋረጠም በሹክሹክታ ታጅቦ ዘለግ ያለ ሳቅ ተደጋገመ፡፡ ትኩረት ፍለጋ ነው፡፡ እንተዋቸው አልን ግን የሚተዉ አልሆኑም፤ ሳቁም ወሬውም ጨመረ፡፡ ቢቀርብንስ? አላርፍ አልንና “ወይ ሳቁን አጋሩን አለያ አትረብሹን” የምትል ወረቀት ፅፈን ወደ እነሱ ክፍል በአናት ወረወርን፡፡ ያችው ወረቀት ከጀርባዋ የእነሱን ምላሽ አመጣች፡፡ “በአካል ይሻላል፤ በመልክት አይሆንም” የሚል ነበር፡፡ የደብዳቤው ምልልስ ላልተወሰነ ግዜ ቀጥሎ የተባባልነውን ተባባልን፡፡ ኦ. . . .ሆ. . . .ይ. . . .!!! ድፍረታቸው አስገርሞን እኛም በተራችን በጣም ተሳሳቅን፡፡  ብንገናኝስ ምን ይሉን ይሆን ብለን ስናስብ ግን ተሳቀቅን፡፡ ከእነዚህ የንባብ ክፍሎች እንደወጣችሁ የምታገኙት የቆዩ መፃህፍትን እና የምርምር ህትመቶችን የያዙ መደርደሪያዎች በመስመር ተሰድረው ነው፡፡ ብዙውን ግዜ ተማሪው  አይጠቀማቸውም፡፡ እነዚህን ጎግል የተካቸው ይመስለኛል፡፡

 

በአንድ ጠቅታ (ክሊክ) ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ከሚገኙ የመረጃ ምንጮች አፈላልጎ ያለምንም ብድግ ቁጭ የሚፈለገውን መረጃ በየኮምፒዩተሮቻቸን መስኮት ከተፍ ያደርጋል፡፡ ከተፎው ጎግል! ወደ መግቢያችን ጋር ልመልሳችሁ እና ከሁለቱ አዳዲስ የገቡ መፃህፍት ማስተዋወቂያ የመስተዋት ሳጥኖች መካከል በፊደል ተራ የተዘጋጁ የመፅሃፍት ማውጫ የካታሎግ ሳጥኖች ጋር ልውሰዳችሁ፡፡ ማውጫዎቹን ስትመለከቱ ግን እጅግ በጣም ትገረማላችሁ፡፡ ዓለም በሰለጠነበት፤ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ስራ ባቀለለበት እና ነገሮችን ባቀላጠፈበት በዚህ ዘመን የካታሎግ ሲስተሙ ለኢምፔሪያሊዝም ጫና አልሸነፍም፤ ለባህል ወረራው አልረታም በማለት ዛሬም እንደ ድሮው ነው፤ የተቀየረ ነገር የለውም፡፡ የምትፈልጉትን መፅሃፍ ለማግኘት እነዚህ ሳጥኖች ጋር ሄዳችሁ ደራሲውን፣ ርዕሱን እና ቁጥሩን ፅፋችሁ ለቤተ መፅሃፉ የሰርኩሌሽን ሰራተኛ መስጠት ይጠበቅባችኋል፡፡ ተጨማሪው ችግር ግን እነዚህ የካታሎግ ካርዶቹ ከቆይታ ብዛት አርጅተዋል፣ ነትበዋል፣ የተወሰኑቱ ተቀደዋል፤ ብዙዎቹ ደግሞ መቀደድ ጀምረዋል፡፡ መተካካትን የፈለጉ የሳጥን ውስጥ ቆይታቸው የሰለቻቸው ይመስላል፡፡  በዚህ ቤተመፅሀፍ ውስጥ ሁሉም ተማሪ በራሱ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ ማንም ለማንም ግድ የለውም፡፡ የሁሉም ተማሪ ሃሳቡም፣ ካራማውም፣ ቆሌውም ከራሱ እና እየሰራ ካለው ስራ ጋር ብቻ ነው፡፡ መምህራኖቻችን በቀነ ገደብ የሚሰጡን ስራዎች በተያዘላቸው ቀን እና ሰዓት ማለቅ አለባቸው፡፡ ለሌላ ጉዳይ ግዜም ቦታም አይኖርም፡፡ ጥድፊያ እና ውጥረት ነው፡፡ ቀኑ አልበቃ ሲልም ስራቸውን ወደ ሌሊት የሚያሻግሩም አሉ፡፡ እናም ከቤተመፅሀፍ አእምሮ ደክሞ እረፍት እስኪፈልግ ድረስ ማንም ማንንም ማናገር፣ ማየትም እንኳ ላይፈልግ ይችላል፤ ደግሞም አይፈልግም፡፡ ግን አሉን አንዳንድ (please pay attention) “እባካችሁ እዩን” ብያቸዋለሁ፡፡ ሆነ ብለው፣ አስበው፣ አቅደው እና ተዘጋጅተው (አቃቤ ህግ ወንጀልን ከፍ አድርጎ በጥፋተኝነትን ማስቀጣት ሲፈልግ የሚጠቀምባቸው ቃላት ናቸው) አትኩሮት መሳብ የሚፈልጉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ሲፈልጉ ከግል የጥናት ክፍል ውስጥ አለያም ከውጭኛው የቤተ መፅሀፉ ክፍል ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ በሰባሰበቡ ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ ሻቸውም ቀጥታ ይመጡ እና በጣም ተራ እና ቀላል የሆነ ነገር እንዲተባበሩዋቸው በፈገግታ እየተቅለሰለሱ ይጠይቁዎታል፡፡ አቀራረባቸው አያስከፋም፤ እንዲያውም እየረበሹም ቢሆን ፈገግ ያሰኛል፡፡ እስኪ ይሁና፡፡ የላይኛዋን የክስነጥቤን እዚህ ጋር ያዙልኝ፡፡ በትምህርት ዓለም የተማሪው አይነት ብዙ ነው፡፡ ለዛሬ ግን ሶስት ምድብ ላስተዋውቃችሁ፡፡ የምድቡ አከፋፈል መሰረት ያደረገው የተማሪዎቹን የቤተመፅሃፍት የመጠቀሚያ የፈረቃ ሰዓት ነው፡፡ ምድብ አንድ ብዙው ተማሪ የሚካተትበት የቀን ምድብ ሲሆን አስራ አንድ ወይም አስራ ሁለት ግፋ ቢል እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ነው ቆይታቸው፡፡ ምድብ ሁለት ደግሞ የተማሪው ቁጥር እምብዛም ሆነው የምሽት (የአምሺው) ምድብ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ያመሻሉ፤ ግፋ ቢል እስከ ሶስት በጣም ከቆዩ እስከ አራት ሰዓት፡፡ ሶስተኛው ምድብ ግን የአዳሪው ምድብ ነው፡፡ እነዚህ ብዙውን ግዜ ወደ ቤተመፅሃፉ የሚመጡት የቀኑ ብርሃን ደንገዝገዝ ሲል እና የምሽት ምድቦች ቦታውን ሲለቁ ነው፡፡ በአግባቡ ስራን በአትኩሮት ለመስራት ያስችላል ይላሉ - የማደራቸውን ምክንያት እና የአዳርን ጥቅም ሲገልፁ፡፡ የቀኑ ግዜ አልበቃ ብሎአቸው ሌሊት አዳር የሚሰሩ እንዳሉ ከላይ የጠቆምኳችሁን አስታወሱልኝ፡፡ ነገርየው እወነት ነው፤ ግን ከአዳሪ ተማሪዎች ጋር ስናወራ የአዳራቸው ምክንያት ግርም ይላል፤ ዋነኛ ምክንያታቸው ላይፉን ለማየት ነው፡፡ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ለማየት እና የጓደኛ ግፊት፡፡ እነዚህ ተማሪዎች እንደነገሩኝ፤ ሌሊቱን ከሚሰሩበት የማይሰሩበት ሰዓት ይበዛል፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ ለቡና ሻይ ይወጣል፡፡ የነፋሻ ሌሊቶች ሽርሽር ይደረጋል፡፡ ከካፌዎቹም ኬክ እና ሳንዱች ከወሬ ጋር በቡና ይወራረዳሉ (እነዚህ ካፌዎች በስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ ያሉ እስከ እኩለ ሌሊት አገልግሎት የሚሰጡ ካፌዎች ናቸው)፡፡ ከካፌ መልስ የኢንተርኔቱ ፍጥነት በጣም ስለሚመች ፌስ ቡክ ይከፈትና ከሩቅ ሀገር ወዳጅ ጋር ቻት ይደረጋል፡፡ ሙዚቃና ፊልም ይወርዳል (Download ይደረጋል) ከስምንትና ዘጠኝ ሰዓት በኋላ እንቅልፍ ስለሚያስቸግር ከየወንበሩ ላይ ላፕቶፕን አጥፍቶ ወይ ደግሞ ከግል የማንበቢያ ክፍል ተገብቶ ኩሼ (ይተኛል)፡፡ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ሲሆን ቤተመፅሃፉ የቀኑን ስራውን ያቆማል፡፡ የተኛው እየተቀሰቀሰ ይወጣል፡፡ሰማይ ፈገግ እስኪል ቅድም ካፌ ተጀምሮ የተቋረጠው ወሬ ለጀንበር መቀበያነት ከቤተመፅሃፉ ውጭ አሁን ይቀጥላል፡፡ ራቅ ያሉቱ ወደ ቤት ለመሄድ ታክሲም ስለማይገኝ፣ የቅርቦቹም ቢሆኑ ወደ ቤት ለመሄድ ሰዓቱ አጉለኛ ስለሚሆንባቸው፣ እዛው በተሰበሰቡበት ጀንበሯን እንዲህ ይቀበሏታል፡፡ የሌሊት ምድብ ጨዋታ ይህን ይመስላል፡፡ ለእነዚህ ተማሪዎች ቀኑ በመኝታ ያልፋል፡፡

 

 

 

Read 1827 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 11:07