Sunday, 06 May 2012 14:34

“ከ‘ብሉ ፕሪንት’ ፀሀይ ወደ ማሞቅ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለድል በዓል አደረሳችሁማ!

ስሙኝማ…መላውን እያጣ የመጣ ነገር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ይሄ ሱሪ ከቀበቶ ማኖሪያ በታች መልበስ፡፡ እንዴ… መጀመሪያ ላይ በየታክሲው ሲወጡና ሲወርዱ በአንድ እጅ ሱሪ ከፍ ያደርጉ የነበሩት እንትናዬዎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ አሁንማ…እንትናዬ የለ፣ እንትና የለ፣ ወጣት የለ፣ ቬቴራን የለ…ምን አለፋችሁ፣ ሱሪ ከቀበቶ ማሰሪያ በታች መልበስ ‘የዜግነት ግዴታ’ አይነት ነገር ልናስመስለው ምንም አልቀረን፡፡ (ልክ እንደ ‘ማንቼስተር ደርቢ’ ማለት…ቂ…ቂ….ቂ…)

እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ የማይመች ነገር ምን አለ መሰላችሁ፣ ይሄ ወጣቱን ጠቅልሎ የመኮነን ነገር፡፡ በጣም አሪፍ ሥራ እየሠሩ ያሉ፣ እውቀትን የሚያሳድዱ፡ አዳዲስ ነገር ለመፍጠር የሚሞክሩ መአት ወጣቶች አሉ፡፡ ይመቻችሁማ!

ሌሎች የትውልዱ አባላት ደግሞ መሄጃውና መድረሻው የተምታታባቸው… “እነዚህ ልጆች መጨረሻቸው ምን ይሆን!” የሚያስብሉ አሉ፡፡ እናማ ‘የቄሳርን ለቄሳር’ ማድረግ አሪፍ ነው፡፡

እናላችሁ… የሆነ የታዳጊነት ዕድሜ ወደታች እየወረደና ህጻንነት ደግሞ ገና ከማህጸን ሳይወጣ እየሆነ ነው፡፡ ልክ ነዋ… የአሥራ አራትና የአሥራ አምስት ዓመት ልጆች … አይደለም ድራፍት ምናምን… ደረቅ ቮድካ በአደባባይ የሚጠጡበት ዘመን እኮ ነው! ልክ እኮ… የከተማው ወላጆች ለረጅም ጊዜ እረፍት ጠቅልለው ወደ ሞንጎሊያና ፊጂ የሄዱ ነው የሚመስለው!

ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በአንድ ወቅት አንድ የ‘ሀይ ክላስ’ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠርታ የአሥራ አምሥት ዓመት ልጇ ሲጋራ ስታጨስ እንደተደረሰባት ሲነገራት ምን ብላ መለሰች… “እኔ ልጄን አስተምሩልኝ አልኩ እንጂ፣ ሲጋራ ማጨሷን ተቆጣጠሩልኝ አልኩ!” አለች ሲባል ሰምተናል፡፡ እመኑኝና፣ የዘንድሮ ብዙ ወላጆችን ነገር ስትሰሙ…የሴትየዋ አባባል ምንም የተጋነነ ነገር የለውም፡፡ እንደውም…እኛ ከጀርመንና ከኔዘርላንድ ምናምን “ኮረጅን” እንደምንለው ሁሉ… አለ አይደል… ዘንድሮ ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው እየኮረጁ ነው እላችኋለሁ፡፡ የምር… ዘመን እየተለወጠ ነው፡፡

እናላችሁ… ድሮ እኮ “ኸረ እባካችሁ…ይሄን ልጃችሁን አንድ በሉት…”

“ይቺ ልጅ እንዲህ መላዋን ስታጣ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ!” ምናምን ተብሎ ለወላጅ አቤቱታ ይነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ…እንዲሀ አይነት ማሳሰቢያ ምናምን አቅጣጫውን ሊቀይር ምንም አልቀረው፡፡ እናማ… ለወላጅ ሳይሆን ለልጅ ምን ‘ጥቆማ’ ሊቀርብለት ይችላል መሰላችሁ…

“አንተ፣ እኚህ አባትህን አንድ ነገር አትሏቸውም እንዴ!”

“ምነው! መጠጥ መጠጣት ጀመረ እንዴ?”

“እሱ ይሻል ነበር፡፡ ጭራሽ ሱሪያቸውን እዛ ታች አድርገው መቀመጫውን እያሳዩ መሄድ ጀመሩ!”

ለእንትናዬም ደግሞ ጥቆማ ሊቀርብላት ይችላል፡፡

“አንቺ እናትሽን ወይ በዘመድ አስመክሯት፣ ወይ በቄስ አስገዝቷት!”

“ምን አደረገች! ከሰው ተጣላች እንዴ?”

“ምን ከሰው ትጣላለች! መሀረብ የምታክል ቀሚስ ለብሳ በየምግብ ቤቱ እንዲህ…” ይባልና ስለ እናትየዋ አቀማመጥ ስዕላዊ መግለጫ ይቀርባል፡፡ እናላችሁ ወደፊት የልጆችን ሁኔታ ለመከታተል የወላጅ ኮሚቴ ምናምን ይቋቋም እንደነበር ሁሉ (መቼም ነገርዬው “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ…” አይደል…) ትንሽ ቆይቶ የወላጆችን ሁኔታ ለመከታተል የልጆች ኮሚቴ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

ኮሚክ እኮ ነው… የምትቀባውን ‘ሎሽን’ ስም እንኳን አንብባ የማታውቅ እንትናዬ… “በእናትህ፣ የአማርኛ መጽሐፍ ታነባለህ!” የምትልበት ዘመን ነው፡፡ “ልጄ በእንግሊዝኛ ብቻ ነው የምትነጋገረው” የሚሉ ልጆቻቸው “ኋ’ሳፕ…” “ዋው…” ምናምን ማለት ስለቻሉ ብቻ የኒውተንን አርማ የጨበጡ የሚመስላቸው ወላጆች በበዙበት ዘመን “ኸረ ወዴት እየተሄደ ነው!” ማለት ጥሩ ነው፡፡

እናላችሁ… መልክ በቅባቱም በምናምኑም እየወዛ… አለ አይደል… አእምሮ እየደበዘዘ ሲሄድ የምር ያሳስባል፡፡ እንግሊዝኛ ማወቅ አንስታይን መሆን ማለት ሳይሆን በአንድ ተጨማሪ ቋንቋ መግባባት ማወቅ ማለት ነው፡፡ አለቀ፣ ደቀቀ!

የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ ትውልዶች የሚለያዩባቸው መስመሮች እየደበዘዙ ሄደው ነገሩ “ቀላቀለውና እርጥቡን ከደረቅ…” አይነት ነገር ሲሆን… “ልብ ያለው ኅብረተሰብ ልብ ያድርግ” የሚባልበት ጊዜ ነው፡፡ ሲክስቲ ምናምን ደፍነው… ሱሪ ከቀበቶ መዋያ በታች… ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው!

ምን ይገርምሀል አትሉኝም… ‘መቀመጫ’ ማሳየት ምን የሚሉት ‘ግሎባላይዜሽን’ ነው? የፒካሶ ‘አብስትራክት አርት’ ነው!… የባዮሎጂ ‘ሜክአፕ ክላስ’ ነው!…ወይስ “ከዚህ አቅጣጫ ልክ እንደ ዝንጀሮዋ ነን” ለማለት ነው!

ደግሞላችሁ… ሌላ ይሄ ‘ትልልቁ ሰው’ ከአሁኑ ትውልድ ልምድ እየቀሰመበት ያለ የሚመስል ነገር አለላችሁ… ይሄ የተበጫጨቀ ጂንስ መልበስ! በዛ ሰሞን አንድ ‘ቬቴራን’ ከኢራቅ የፈንጂ ቀጠና ተቆፍሮ የወጣ የሚመስል፣ ከጨርቁ ይልቅ ቀዳዳው የሚበዛ ጂንስ ለብሰው የፒያሳ ሰው ዘወር እያለ ሲዘባበትባቸው ስታዩ የምር እንዴት ይደብር ነበር መሰላችሁ!

ደግሞላችሁ…ይቺን ‘ቆራጣ ሱሪ’ በሚያንዘፈዝፈው ብርድ ለብሰው “ቀይ ምንጣፍ አንጥፉልኝ…” ለማለት የሚቃጣቸው በዝተውላችኋል፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ይቺ ስንጥር የመሳሰለች እግራችን መጋለጧ! አንዳንዶቻችንማ ልክ የቻርሊ ቻፕሊን ፊልም ልንሠራ ልምምድ ላይ ያለን ነው የሚመለስለው፡፡ (በቀደም ሚኒባስ ውስጥ ያየነው ከአንዲት እንትናዬ ጋር የነበረ የዘመኑ አራዳ የሸለለው እንዴት ሆኖ መሰላችሁ… ስቲኪኒውን ጸጉሩ ላይ ሰክቶ! ቂ…ቂ…ቂ… በዚህ በቅብ አራድነትማ…የሆነ ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ ማዘጋጀት አለብን፡፡)

እናማ… አዳዲስ የአስተራረስ፣ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ዘዴዎች ከማየት ይልቅ አዳዲስ ‘አራድነት’ ማየት እየለመደብን መጥቷል፡፡ ይሄ የሰውነት ክፍሎችን ‘ዲክላሲፋይ’ ማድረግ ሲጀመር (ቂ…ቂ…ቂ…) መጀመሪያ ‘ብሬስት’ ምናምን ሲታይ “ጉድ!” አልን፡፡ “ኧረ ምን ዘመን መጣ!” ተባለ፡፡

ከዚያ ደግሞ ቀጠለላችሁና እምብርት ታየ፡፡ “ኽረ ይሄ ነገር ወዴት እየሄደ ነው!” ተባለ፡፡

አሁን ደግሞ ‘መቀመጫ’ ማሳየት እየበዛ ሄዶ “ምን አዲስ ነገር አለና ነው!” ሊያሰኝ ምንም አልቀረው፡፡

እናላችሁ… ያኔ ነገርዬው ‘እምብርት ክልል’ ሲደርስ እኮ “ይሄ ነገር ከራዳር ሊወጣ ነው እንዴ!” ምናምን ብለን ነበር፡፡ (ስሙኝማ…ነገርዬው ‘ቀይ መብራት ጥሶ’ ሌላውን ገና ‘ዲክላሲፋይድ’ ያልሆነውን የአካል ክፍል በአካልና በሥጋ ባናየውም… አለ አይደል… በስስ ነጭ ሱሪ በኩል ‘ብሉ ፕሪንቱን’ አይተነዋላ! ቂ…ቂ…ቂ…)

በነገራችን ላይ እነኚህ በሁሉ በኩል እየኮረጅናቸው ባሉ አገሮች እኮ ሁሉም ነገር “እንደ ፍጥርጥራቸው” ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ እንደፈለጉ መልበስ የግለሰቡ ምርጫ ቢሆንም የሌላውን ኅብረተሰብ መብት መጠበቅም ያስፈልጋል፡፡ እናማ… ይሄ ምኑንም ምናምኑንም የአካል ክፍል ማሳየትና አንዳንዱንም በደብዛዛው ‘ያለበትን መጠቆም’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ኅብረተሰቡን የሚያስቀይም ከሆነ ያስጠይቃል፡፡ ‘ኢንዴሰንት ኤክስፖዠር’ ምናምን የሚሉት ኅብረተሰቡን ልቅ ከሆኑ ምኑንም ምናኑንም ለኤግዚቢሽን የማቅረብ ነገርን የሚከላከል ህግ አላቸው፡፡

እናላችሁ… ዓለም ‘የእኔ የሆነ ነገር ሁሉ የእኔ’ እያለ ዕድሜ ልካቸውን ኖረው ወልደው የከበዱ ሰዎችን “ወደ አገራችሁ ሂድሉን” በሚሉበት ዘመን… ራስን አለማወቅ ያሳዝናል፡፡ አሁን ለምሳሌ ባንዲራ በባርኔጣ ወይም በሻርፕ መልክ የሚያደርጉ አሉ አይደል…እናማ ምን መሰላችሁ… ብዙዎቹ የአገር ፍቅር አቃጥሏቸው ምናምን ሳይሆን የ‘ራስታነት’ ጉዳይ ነው፡፡ (ነገሩ ሁሉ እኛ ዘንድ ሲሆን ቀሺም የሚሆንበት… ዞሮ ሲመጣ ደግሞ አሪፍ የሚሆንበት እርግማን መቼ እንደሚቀርልን አንድዬ ይወቀው!)

እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ዳያስፖራዎች በተሰበሰባችሁ ቁጥር እኛን የመሞለጭ ስለት አለባችሁ እንዴ! ግራ ገባና… እዚህ አገር ‘የተትረፈረፈ ምርት’ ያለበት፣ እጥረት የሚባል ነገር የማይታይበት፣ ታክስ ምናምን የማይጨመርበት ነገር ቢኖር ‘እኛን መሞለጭ’ በቻ ነው፡፡ እናማ… የቤታችን ትከሻችንን አጉብጦታል… እናንተም ተጨመራችሁ! “ሰነፎች ናቸው” “ሥራ አይወዱም” ምናምን እያላችሁ… አትነካኩና! አለበለዛ… “ተንከባከቡን፣” “እዛ በለመድነው ኑሮ ደረጃ እዚህም ይመቻችልን” ምናምን እያላችሁ በሞራላችን ላይ ‘ቺካጎ ቡልስ’ ምናምን ነገር አትሁኑብና! እኛ ጥሩ ኑሮ አይወድልንም! አለበለዛ… ዲ.ሲ. ውስጥ አሥራ ዘጠነኛው መንገድ ያለው ህንጻ አራተኛ ፎቅ ላይ በአደራ አስቀምጣችሁ የመጣችኋትን መወልወያ ፎቶግራፍ ዩ ቲዩብ ላይ ለቀን ጉድ እንዳትሆኑ፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ለእናንተማ አናንስም!

ደግሞ… አለ አይደል… እስቲ “የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት ስጡን”፣ “መኪና ያለቀረጥ ለማስገባት ይፈቀድልን” ምናምን አይነት “ከራስ በላይ ነፋስ…” ነገር ደግሞ ትንሽ አለፍ ብላችሁ አንዳንዴ “ለወጣቱ የሥራ መስክ ይፈጠርለት…” “ለህዝቡ ንጹህ የመጠጥ ውሀ ይቅረብለት…” ምናምን እያላችሁ ስለ አገር ጠይቁ እስቲ! እናላችሁ…ቴክኖሎጂውም ምኑም እኛ ዘንድ ሲመጣ ለእውቀት መሆኑ ቀርቶ ሲባክን ያሳዝናችኋል፡፡ አሁን ይሄ ፌስቡክ የሚሉት ነገር… አለ አይደል…በደንብ ለሚጠቀሙበት አሪፍ የመረጃና የእውቀት ምንጭ ነው፡፡ ግን በሚያሳዝን መልኩ እዚህ አገር ብዙዎች እየተለዋወጡ ያሉትን ነገር ስትሰሙ… ተሰፋ ያስቆርጣችኋል፡፡

የጭሶቹን ቋንቋ ለመጠቀም… ፌስ ቡክ ‘እውቀት መጥበሻ’ ሳይሆን የእንትናዬና የእንትና ‘መጣበሻ’ ሆኖላችኋል፡፡ (በነገራችን ላይ ባል መፈለጊያ ድረ ገጾችን ባለትዳር የሀበሻ ሴቶች ሞልተዋቸዋል ይባላል፡፡

ምን ይገርማል… እዚቹ ከተማም እኮ እነኚህ የሸለሉ መዝናኛ ቦታዎች… “እንትና እኮ የእንትናን ሚስት አወጣት…” መባባል ልክ “በባዶ እጁ አምስት የግራዚያኒ ወታደሮችን ማረከ…” አይነት ጀግንነት ሆኗል እየተባለ ነው፡፡

ይቺ ‘በዛኛው ጥግ’ እየተፈጠረች ስላለች ከተማማ አንድ ቀን በደንብ እናወራባታለን!!)

በዛ ሰሞን መሀል ከተማ አንድ ሸላይ ጎረምሳ ጸጉሩን ቁንጮ አድርጎ አየሁና…መቼም ውሸት ምን ያደርጋል…ምን አሰብኩ መሰላችሁ… “ደግሞ የትኛው ራፐር ቁንጮ ሆኖ ይሆን!” ልክ ነዋ! ይኸው የእኛው የሆነ ንቅሳት እንዳልተዘበተበት ከስንት ዘመን በኋላ ዞሮ ሲመጣ ሰዉ ሰውነቱ ላይ መነቀሻ ቦታ እየጠፋው አይደል! (አንዳንድ እንትናዬዎች…ስንት መነቀሻ ቦታ እያለ ምነዋ!)

እናላችሁ… ይሄ ሱሪ ከቀበቶ በታች መልበስ የትውልድ ድንበር ጥሶ መካሪና ተመካሪ ሲደበላለቅ አሪፍ አይደለም፡፡

ነገሩ ሁሉ በዚህ ከቀጠለ አሁን በ‘ብሉ ፕሪንት’ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ ‘አገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው’ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ እናማ… ለአንዳንድ ነገሮች ከ‘ብሉ ፕሪንት’ ፀሀይ ወደ ማሞቅ… አሪፍ ሽግግር አይሆንም፡፡

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 2789 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:38