Saturday, 07 April 2012 08:48

ለዚህ ትህትና ሆሳዕና በአርያም

Written by  ሳባውዲን ኑር
Rate this item
(0 votes)

‘የአህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት አመድ’ ( በሞቴ አልጋ ላይ ማን አውጥቶት ?) ‘ለአህያ ማር አይጥማትም’ ( በስንት ማንኪያ ማር ተሞከረች?) ‘የተናቀ ከተማ በአህያ ይወረራል’ (በታሪክ ተዘግቦ ከሆነ ስሙ ይነገረን) …. ወዘተ በምድረ አበሻ የተነገሩ አህያን አመካኝቶ ለመዝለፍ የተፈለገን ሰውን ክብር ለመንካት ከተተረቱ በርካታ ሥነ ቃሎችን መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ያገሬ ሰው ‘አህያ’ ብሎ ሲሳደብ ጥቃት የማይገባው፣ ሲበደል ምላሽ የማይሰጥ፣ ክብረ በላ ደነዝ …. ለማለት ነው ፡፡ በጥንቶች የይሁዳ ግዛቶችም ለአህያ የነበረው አመለካከት ያው በንቀት ላይ የተመሰረተ ነበር ማለት ይቻላል ፡፡ ‘የጽዮን ልጅ ሆይ! እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወዳንቺ ይመጣል፡፡’ እንዲል ነቢዩ ኢሳያስ፤ ትሁት የሆነው ንጉሥ በፈረስና ፈረሰኞች ታጅቦ በሰረገላ ሳይሆን በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከደብረ ዘይት እስከ ኢየሩሳሌም በመምጣቱ ውስጥ አህያ በአካባቢው የነበራትን ሥፍራ ማየት ይቻላል ፡፡

በሰውኛ ሲታሰብ ስትለፋ ውላ ምሷ ዱላና ገለባ፤ ፍዳዋን ስታይ ኖራ ስታረጅ ቀርቶ በቁሟ የአራዊት ሲሳይ የምትሆን ይህች ፍጥረት፤ በአለም መንፈሳዊ ታሪክ ውስጥ ላንዲት አፍታ እንኳ ልታስበው ቀርቶ ከቶ ልትገምተው የማትችለው ነገር ተፈጸመባት፡፡  የደመና አክናፍ የ’ሳት ሰረገላ የሚያንስበት ፈጣሪ በእርስዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ከበረባት፡፡

ዳውላና የነጋድራሶችን ሸቀጥ ተሸክማ አገር ‘ላገር የምትኩዋትን ይህች እንስሳ፤ ለቅጽበት ‘ሳተ መለኰት ዙፋኑ ያደርገኛል ብላ ልታስብ ቀርቶ ልትቃዥ አትችልም ነበር ግን ሆነ ፡፡ ክብሩን በእርስዋ ሲገልጽ ዛሬ የመጀመሪያው አልነበረም፤ በብሉይ ዘመን የእግዚያብሔር ሰው በዓለም እግዚያብሔር ፈፅሞ የማይፈቅደውን ድርጊት ሊፈፅም ህዝቡን ያለጥፋቱ ሊረግም በእንስሳይቱ ጀርባ ላይ ሆኖ ጉዞ ጀመረ፡፡ ሲሔድባት ቆይቶ የእንስሳይቱ ጉዞ ድንገት ተገታ፡፡ ቆመች፡፡ በለዓም በሁኔታዋ ተበሳጭቶ ትሔድለት ዘንድ ቀጠቀጣት፡፡ይሄኔ አህያይቱ በሰው አንደበት ተናገረችው፡፡ “ስለምን ያለጥፋቴ ትደበድበኛለህ፤ ሰይፈ ነበልባል ይዞ ከፊቴ የቆመው አይታይህም?” አለችው፤ ያ! የእግዚያብሔር መልዐክ ለእንስሳይቱ እንጂ ለበለዓም አልታየም ነበር፡፡ ፈጣሪ በእንስሳቱ በኩል ለበለዓም ሊል የፈቀደው ነገር ነበርና እንስሳይቱን አከበራት፡፡

ጢባርዮስ ቄሳር የሕዝብና የንብረት ቆጠራ ሊያደርግ አገሩን በሙሉ ወደ ቤተልሔም ጠራ፡፡ እንግዳ መቀበያዎት በሙሉ ከየአገሩ በተሰበሰቡ ተቆጣሪዎች በመያዛቸው፣ ማሪያምና ዮሴፍ ከቤተልሔም ነዋሪዎች በአንዱ ሰው ቤት ግርግም ገለባ ጐዝጉዘው ሰውነታቸውን ማሳረፍ ነበረባቸውና ጋደም አሉ፡፡ ብርዱ ቆዳን ስርስሮ አንጀት ውስጥ የሚገባ ዓይነት ነው፡፡ ድንገት ማርያም በምጥ ተያዘች፡፡ የበኩር ልጅዋንም ወለደች፡፡ እረኞች ውዳሴ አቀረቡ፡፡ መላዕክት ዘመሩ፡፡ አህያይቱን ጨምሮ በግርግም የነበሩቱ እንስሳት ሙቅ ትንፋሻቸውን እያመነጩ ህፃኑን ሊንከባከቡት ሞከሩ፡፡ በዚህ ሰዓት የቤተልሔም በርካታ ቪላዎችና የእንግዳ ማረፊያዎች በግንዲላ ፍም ደምቀው፣ ነዋሪዎቻቸውንና እንግዶቻቸውን ለእንቅልፍ ያባብላሉ ፡፡ ክርስቶስ ግን በእንስሳት ታጅቦ በእናቱ ማርያምና ዮሴፍ እቅፍ  በመላዕክት መልካም ምኞት በእረኞች ዘፈን ውስጥ በግርግም ከበረ ፡፡

ክርስቶስ በተመለሰባቸውና በኖረባቸው ጊዜያት ሁሉ ከምንም በላይ ትህትናን፣ ዝቅ በማለት ውስጥ ያለውን ክብርና በረከት ሲያስተምርና በተግባርም ሲያሳይ ኖሯል፡፡ ሆሳዕናም አንዱ ማስተማሪያው ነበር ፡፡ ስመ ገናና ነው፡፡ ህዝቡም ሆነ ሮማውያኑ ቅኝ ገዢዎች ስለእርሱ ያላቸው ግንዛቤ የተምታታና ግልፅ ያለ ባይሆንም እጅግ ክብር ይሰጡት ነበር ፡፡ ድውያንን ፈውሷል፤ አንካሶችን አስዘልሏል፤ ከበረከቱ መና ብዙዎችን መግቧል፡፡ በድንቅ  ትምህርቱ የሺዎችን አፍ አስከፍቷል፡፡ እንደሰው ቢታሰብ እንኳ ይህ ሰው በወርቅ የተንቆጠቆጡ ሰረገላዎች፣ በክብር ያጌጡ ጋሻ ጃግሬዎች ለንጉሥ የሚገባ የሠራዊት ሰልፍ ሲያንስበት ነው፤ ሊያውም የአባቱ የዳዊት ዙፋን ወደነበረበት ኢየሩሳሌም ሲገባ ግና ይህ ሁሉ ክብሩ በውርንጫ ጀርባ በህፃናት አጀብ ሆኖ እንዳይሔድ የሚከለክለው አልነበረም ፡፡

እርሱ በውርንጫዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባው የባለሰረገላዎችን ክብር ሊያዋርድ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ በምድር ላይ በቆየባቸው ሰላሳ ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ውስጥ ማንንም አዋርዶ አያውቅም፡፡ ብዙዎችን ከትዕቢት ባርነት ነፃ ሊያወጣ ሲል ያደረገው ነው ፡፡ በክብር ደመና የሚመላለስ ንጉሥ እኛ በምንንቃት ፍጡር ላይ ተቀምጦ መሔዱ፣ ቁሳዊ የሐብት ቁልል ብቻ ኖሮን ትህትና ለጐደለን ሁሉ መልዕክቱ ግልፅ ነው፡፡

ከምንም በላይ የልብን ውስጥ ክብርና ልዕልና እንድናስቀድም እጅግ ትሁት በሆነ መንገድ ተናገረ፡፡ ‘ከናንተ መካከል አንድ ስንኳ ንፁህ ቢኖር እርሱ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውባት!’ ብሎ ፍትህ ከመስጠት በላይ ልዕልና የታል? የሰዎችን ልጆች ኃጢያት ሊመዘግብ ከተገባ እርሱ ፈጣሪ ነውና ከፈሪሳውያኑ ይልቅ ለህጉ ቀናዒ ነው፡፡ በአደባባይ እየተመፃደቁ ድንጋይ ያነሱባት ሁሉም እንደርስዋ በድንጋይ ተወግረው ሊሞቱ ይገባቸው የነበሩ ናቸው ፡፡ ‘አንቺ ሴት ሒጂ ዳግመኛም ኃጢያት አትስሪ!’ አላት፡፡ ንጽህና ድንጋይ ካስነሳ ድንጋይ ሊያነሳባት ይገባ የነበረው እርሱ ብቻ ነበር ግን አላነሳባትም “ሒጂ!” አላት፡፡ ይህች ሴት ካላበደች ዳግም ያንን ኃጥያት ታደርገዋለች? ፈጽሞ! ድንጋይ ማንሳት ሲችል ድንጋይ ያላነሳ ትሁት! እርሱ ለድንጋይ አልመጣማ ፡፡

ከደብረዘይት ወደ ኢየሩሳሌም በውርንጫ የሚያደርገውን  ጉዞ ከመጀመሩ አስቀድሞ ኢያሪኮ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ኢያሪኮ ቀራጩ ዘኪዮስ ቤት፡፡ ከነደቀ መዛሙርቱ ሲስተናገድ ውሎ ነው አመሻሽ ላይ ጉዞ የጀመረው፡፡ ማንም የማይጠጋው፣ ፍቅር የተነሳው፣ ሕዝብ የጠላው፣ እርሱም ሕዝቡን የጠላው ቀራጩ ዘኪዎስን “ዛሬ ካንተ ጋር ነኝ!” አለው፡፡ ሕዝቡም ‘ይሄ ከሃጢያተኛ ጋር የሚውል ሃጥያተኛ ነው!’ አለና ተግተልትሎ ሊያየው እንዳልወጣ ትቶት ቤቱ ተከተተ ፡፡ ፍቅርን አይቶ የማያውቀው ዘኪዎስ ባጋጠመው ነገር ተደነቀ፡፡ ጉድጓዱን በፍቅር የሞላለት መሲህ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታና ትዕዛዝ ከቤቱ ጣሪያ ሥር አርፏል፡፡

‘ከዚህ ፍቅር በኋላ  በግፍ ያከማቸሁት ወርቅና ዲናር ለምኔ?’ አለ ዘኪዎስ፡፡ የህዝቡን ወርቅ ለህዝቡ አለና ጐዳና ላይ አውጥቶ በተነው፡፡ መሲሁ በትህትናና በፍቅሩ የዘኪዎስን ደዌ ፈወሰ፡፡ ከዘኪዎስ ቤት ጣሪያ ሥር ውሎ መባውን እየቆረ ወይኑን አብሮት እየጠጣ ልዑሉ ከበረ፡፡ ለእርሱ ክብር ማለት የተናቁትን ማክበር ነውና!

ክርስቶስ በሁሉም ትምህርቶቹና ድርጊቶቹ ትህትናን ከፍ ከፍ ያደረገ መምህር ነበር፡፡ ይህ ትህትናው እስከ መጨረሻዋ እራት ማለትም እስከ ጸሎት ሐሙስ አልፎም እስከ ጌቴ ሰማኒ ድረስ ዘልቋል፡፡ ዝቅ ብሎ የተማሪዎቹን እግር እስከማጠብ…የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው እስከማለት ፡፡

የሆሳዕናዋ ውርንጫ ነገር ሌላም የሚያሳስበን ነገር አለ፡፡ እጅግ የተናቀ የተዋረደና ለጉልበቱ ብቻ የሚፈለግ ፍጡር እንበል ሰው አንድ ቀን በአንዳች አጋጣሚ የመለኰቱ ክብር የሚገለጥበት  ሊሆን እንደሚችል ማስተማሪያም ነው አጋጣሚው፡፡ ምክንያቱም መሲሁ ከአባቱ ከዳዊት ምድራዊ ዙፋን ይልቅ የመጣበትን የትህትና መንገድ ለማሳካት ስሙር ሆነው ካገኛቸው ፍጥረታትና ሰዎች መካከል የቤተ ፋጌዋ ውርንጫ አንዷ ናትና ፡፡

መለከት ባይነፋለትም በተንቀጠቀጠ የክብር ሰረገላ ላይ ባይቀመጥም፣ ልባቸው ውስጥ የነገሠባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችና ህፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ፤ መጐናጸፊያዎቻቸውንና የአርዛሊባኖስና ጥድ ቅርንጫፍ እያነጠፉ የታላቅ ንጉሥ አቀባበል ከማድረግ ወደ ኋላ አላሉም ፡፡

“ለዚህ ታላቅ ትህትናህ ሆሳዕና በአርያም ምሥጋና በሠማይ!” ከማለት ያገዳቸው አንዳች የለም፡፡ ሆሳዕና በአርያም !!

 

 

 

Read 2928 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:52