"ኡ..ሊ..ሴ" በሚለው ዘፈኗ የምናውቃት ደቡብ አፍሪካዊቷ ብሬንዳ ፋሲ አፍሪካዊቷ ማዶና እስከመባል ደርሳ ነበር። በ2004 ዜና እረፍቷ ሲሰማ ገና 39 አመቷ ነበር። የሞቷ ምክኒያት ደግሞ አብዝታ የወሰደችው ኮኬይን የተባለ እፅ ነበር...
እስከ ቅርብ ጊዜ ኮኬይን እንዲሁም ሌሎች በደምስር የሚወሰዱ ከባባድ እፆች በሀገራችን የሌሉ ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን በሀገራችን የተሰራ ጥናት አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ4000 በላይ ከባድ እፆች የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳሉ ያሳያል። ኮኬይን በከፍተኛ ደረጃ ሱስ የሚያሲዝ በመሆኑ አንድ ጊዜ የሞከሩት ሰዎች ወዲያውኑ ሊቋቋሙት የማይችሉት ሱስ ይሆንባቸዋል። ለማቆም ቢፈልጉ እንኳ እገዛ የት ማግኘት እንዳለባቸው ስለማያውቁ የስቃይ ህይወት ይገፋሉ።
የሱስ ህክምና በጳውሎስ፣ አማኑኤል፣ ዘውዲቱ እንዲሁም በግል የአእምሮ ተቋማት ይሰጣል።
ልጅ እያለን "ኡ..ሊ..ሴ" የምንለው የብሬንዳ ፋሲ Vulindlela መንገድ ክፈቱ እንደማለት ነው። እሷ አልፋለች ነገር ግን በኮኬይን እና ሌሎች ሱሶች ምክኒያት እየተቸገሩ ያሉ ሰዎችን የህክምና አማራጮቹን በመጠቆም መንገድ ልናሳያቸው እንችላለን።
ሱስ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ሀይማኖት የማይለይ የሚታከም የአእምሮ ህመም ነው።
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ኪነ-ጥበባዊ ዜና

