Wednesday, 21 October 2026 06:58

የአብርሀም ጩኸት ለምን አልሰማን አለ ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)
አንዳንዴ ሕይወት አድሏዊም ፣ ኢ-ፍትሐዊም ናት ። ደራሲ ፣ አዘጋጅና ተዋናይ አብርሀም ቀናው የስራው ተቆጥሮለት ቢሆን ህመሙ ላይባባስ ፣ ተባብሶ ቢገኝም የማንንም ፊት ሳያይ ራሱን ችሎ ሊታከም ይችል ነበር ። ግን እንዳልኳችሁ ነው። ለአብርሀም ሕይወት አልቀናችውም። አብርሀም በኪነጥበቡ ሜዳ ብዙ ሰርቷል። በተለይ 90ዎቹ ላይ በሬዲዮ ፣ በቴሌቪዥን ፣ በፊልም ፣ በመድረክ ድራማና ፊልሞች በድርሰት ፣ በዝግጅት ፣ በትወና ጎልቶ የታየ ከያኒ ነበረ ። እስከማውቀው አብርሀም አግኝቶ ያባከነ አይደለም ። የባከነም አይደለም ። አብርሀም ከመስራትና ከመኖር ውጭ የምንም ሱስ የለበትም ። በሱሱ የተነሳ የባከነና ያባከነ አልነበረም ። አብርሀም በጤናውም ጊዜ እንዲሁ ርግት ፣ ቅዝቅዝ ያለ ነው ። ልታይና ልሰማ አይልም።
አርቲስቱን ጠልፈው የሚጥሉት ብዙ መሰናክሎች አብርሀም የሉበትም። በማውቀው ልክ "አብርሀም እንዲህ አደረገኝ" ሲባል ሰምቼ አላውቅም። በስራ ፣ በትጋት ፣ በጥረት ነው የሚታወቀው። እንደ ስራው ፣ ትጋቱ ፣ ጥረቱ ግን አልተከፈለውም። እድል በሉት እጣፈንታ አላውቅም። ገታራ ነው። ቀጥተኛ ነው። ሀቀኛ ነው። አብርሀም የቀማው ያለ አይመስለኝም። ካለም " ጉድለቱ " እሱ ይመስለኛል። አብርሀም ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል የጤና እክል ገጥሞት ደጋግሞ " እባካችሁ አግዙኝ " ብሎ በድፍረት ተናገረ። በጉብዝናው ወራት ከሰው የሚጠይቅ አልነበረም። እንዲህ እንደምታዩት ስትር ፣ ኮስተር እንዳለ ነው ሕይወቱን ያሳለፈው። ሕይወት እንዲህ ናት። አብርሀም አሁንም ሀሳቡና አቅሙ እንዳለ ነው። ግን ነገሮች አልተገጣጠሙለትም። ለገጠመው የጤና ፣ የኢኮኖሚና የኑሮ እክል " የወገን ያለህ ! " እያለ ነው። እንዲህ ሊልና ሊሆን አይገባውም ነበረ። ልብ ያማል። አብርሀም ከባህሪው ወጥቶ ጮክ ብሎ " ድረሱልኝ ! " ሲል ጠየቀን። እስካሁን አልሰማነውም። ወይም በደንብ አልሰማነውም። እስቲ ከልባችን እንስማው።
#SHARE በማድረግ መልዕክቱን ለሚመለከተው ያድርሱ።
Tewodros Teklearegay-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 21319 times