ሁለት እርስ በርስ የሚናበቡ የእስክስታ አዋቂዎች አንድ ላይ ሲጨፍሩ፣ ትዕይንቱን አይቶ የማይመሰጥ ማን አለ? ውበቱ እያንዳንዳቸው በተናጠል ባላቸው ችሎታ ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴ አንብቦ፣ ምቱን ጠብቆ፣ አብረው በሚፈጥሩት ቅንጅት ውስጥ ነው።
ዲሞክራሲም ልክ እንደዚያው ነው። መሪውና ሕዝቡ መደማመጥ፣ መከባበርና መናበብ ይጠይቃል። አንዱ ብቻ ምቱን ቢያውቅ፣ ጭፈራው አይዋሃድም።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ዲሞክራሲን እውን ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ይመስለኛል። መሪው «ዲሞክራት ልሁን» ቢል እንኳ፣ በማኅበረሰባችን ውስጥ ሥር የሰደደው አምባገነናዊ አስተሳሰብ፣ ልዩነትን የመቀበል ችግርና መብትን ከግዴታ ጋር አያይዞ የመረዳት ክፍተት እንቅፋት ይሆናሉ።
ዲሞክራሲ መብታችንን መጠየቅ ብቻ አይደለም፤ ግዴታችንንም መወጣት ነው። ሐሳባችን እንዲሰማ ስንፈልግ፣ የሌላውንም ሐሳብ ማዳመጥ፤ መብታችን እንዲከበር ስንጠይቅ፣ የሌላውንም መብት ማክበር መቻል አለብን።
ሐሳባችንን በነፃነት፣ በጨዋነትና በተጠያቂነት መግለጽም የዲሞክራሲ አካል ነው።
መቃወም ጠላትነት አይደለም፤ መለያየትም መጠላላት መሆን የለበትም። ሐሳብን መሞገት እንጂ፣ ሰውን ማዋረድ የውይይታችን ባህል መሆን አይገባውም።
እነዚህን እሴቶች በማኅበረሰባችን ውስጥ ለማስረጽ ጊዜ፣ ትምህርት፣ መልካም አርአያና ተከታታይ ልምምድ ያስፈልጋል።
ዲሞክራሲ በአዋጅ ብቻ አይገነባም።
በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታና በዕለት ተዕለት ግንኙነታችን ውስጥ እየተለማመድነው የሚያድግ ባህል ነው። የጋራ ምታችንን የምናገኘውም ሆነ አብረን መደነስ የምንችለው እርስ በርስ መደማመጥ ስንጀምር ነው።
Yordanos Goushe
Published in
ነፃ አስተያየት

