Tuesday, 13 October 2026 06:35

የመንግሥት ኃይሎች ወደ አኽሱም፣ ዛላንበሳና ሸራሮ እየገሰገሱ መሆኑ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(2 votes)
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ የሰላም ኃይል ጋር በመሆን ወደ አኽሱም፣ ሸራሮ፣ ዛላንበሳ እና ኢሮብ እየገሰገሱ መሆናቸው ተገለጸ።
የትግራይ የሰላም ኃይል ቃል አቀባይ ኮለኔል ሰሎሞን ኃይለማሪያም በሰጡት መግለጫ፤ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የተሰማራው ኃይል ዓዲ ዳዕሮ፣ ዓዲ ነብሪኢድ እና ዓዲ ሃገራይን ነፃ በማውጣት ወደ ሸራሮ በመገስገስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በተጨማሪም ሰለኽለኻንና ውቕሮ ማራይን ነፃ ያወጣው ስብስብ ወደ አኽሱም ከተማ እየተጠጋ ሲሆን፣ በታንቤን በኩል የተሰማራው ኃይል ደግሞ ወደ ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኙት ራማ እና ጭላ አካባቢዎችን እያቀና ነው። በምስራቅ ትግራይ ያለው ሰራዊትም እንዲሁ ወደ ጉሎመኸዳ፣ ዛላንበሳ እና ኢሮብ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል።
በሌላ በኩል፣ የመከላከያ ሠራዊትና አጋሩ የሰላም ኃይል ስልታዊ የነበረችውን የዓድዋ ከተማን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) የከተማዋን ነዋሪዎች ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የፌዴራል ኃይሎች ወደ ዓድዋ ሲገቡ ከህወሓት ወታደሮች ምንም ዓይነት ፍልሚያ ወይም መከላከል አልገጠማቸውም። የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን ለቀው የወጡት ቀደም ብሎ በመሆኑና በኃይሎቹ መውጣት እና መግባት መካከል የጊዜ ክፍተት በመፈጠሩ፣ በአድዋ ሆስፒታል እና በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላይ የዘረፋ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የከተማዋ ነዋሪዎች የመንግሥት ወታደሮች ቢገቡም ገና ሙሉ በሙሉ ባለመረጋጋቱ ምክንያት በስጋት ሳቢያ መንገዶች ባዶ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም በአድዋ ከተማ የሚገኝ አንድ ሆቴል በድሮን ጥቃት ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ኤሲኤልኢዲ (ACLED) የተባለው የጥናት ቡድን ማስታወቁ ይታወሳል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 10217 times