ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ወርደው ወደ 4ተኛ ክፍለጦር ሲሄዱ "በዚህች ነው የምሄደው!?!" ያሏት ቮልስ ዋገን መኪና በፎቶው የምትታየው ነች።
ይህች መኪና የጄኔራል ሉሉ እንግሪዳ ነበረች። እሳቸው ማለት የንጉሱ የጦር መኮንንና ታማኝ ሾፌራቸውም ነበሩ። የጄኔራሉ ባለቤት ወ/ሮ አጸደ ኃ/ሚካኤል እንደተናገሩት "መኪናዋ በ12 ሺህ ብር ነው የተገዛችው!" ከሴፌሪያ፣ ያውም በብድር።
እንግዲህ በእዚህች መኪና ነበር መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ/ም ንጉሱ የተወሰዱት።
መኪናዋ ግዳጇን ጨርሳ ወደቤቷ ከተመለሰች በኋላ ጄኔራል ሉሉ ጋ ሰው ተልኮ "እርሶም፣ መኪናዎም ይፈለጋሉ!" ተባሉ። ጄኔራሉ መኪናዋን አስነስተው ጥሪ ወዳደረገላቸው አካል ቀረቡ። ጄኔራል ሉሉ እና መኪናዋም ታሰሩ። ጄኔራሉ ለ8 አመት ታስረው ነው የተፈቱት። መኪናዋ ግን ከ18 ዓመታት በላይ ለባለቤቶቹ አትመለስም ከተባለች በኋላ የጄኔራሉ ባለቤት ወ/ሮ አጸደ ተሟግተው ነው ያስመለሷት።
ወ/ሮ አጸደ ባለቤታቸው ጄኔራል ሉሉ ቮልሷ ከእስር ተፈታ ሳያዩዋት በማረፋቸው ይቆጫቸዋል። "ጥቂት ጊዜ ቢሰነብት ያያት ነበር!" ሲሉ ይናገራሉ።
እንግዲህ መኪናዋ እስካሁን አለች። እንደውም ከቅርብ አመታት በፊት መቶ ስልሳ (160) ቮልሶች ብቻ በተካፈሉበት "የቮልሶች አውደ ርዕይ" ላይ ተካፍላ ነበር። ታሪክ ተጽፎባታልና የብዙዎችን አይን ስባ ነበር።
በነገራችን ላይ የተለያዩ ሰዎች 'መኪናዋን ሽጡልኝ' እያሉ ወ/ሮ አጸደን ይጠይቋቸዋል። መልሳቸው "ታሪክንማ አልሸጥም!" የሚል ነው።
ለምን እንደሆነ አላውቅም ይህቺ መኪና በክብር በሙዚየም ብትቀመጥ ጥሩ ይመስለኛል!
እስቲ ሀሳብ ስጡበት።
ውድነህ ክፍሌ-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

