Saturday, 25 February 2012 13:08

ደራሲም ማረግ ይችላል!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

(“ረ” ይጠብቃል)

መንገድ ሳይሄዱት ነው (እ)ሚኬድ

ሞት ሳይሞቱት ነው (እ)ሚለመድ

እንርገጠው እንጂ አፈሩን፣ ከቶ አፈር መሆን አይቀርም

አመነ ወይ አላመነም፣ ሁሌ ቤቱ አንድ ነው መቼም!

“… ከዚያች ካልታወቀች አገር ዐይነ - ሥጋችን ካላያት

የሄደባት መንገደኛ፣ ከቶም ካልተመለሰባት …”

እንዳለው ነው ልዑል ሐምሌት፡፡

የካቲት ስንቱን ያጨቀች

ይኸው አንተምጋ ደረሰች፡፡

ከአድዋ እስከዛሬ ተጓዘች፡፡

ላንተም ከረጢት አበጀች፡፡

የዐርበኞች መስዋዕት ዕለት

የሥጋህ ስንብት ቀን ናት፡፡

በእርግጥ ታውቃለህ ብዙ ሞት

የብዕር መስዋዕት ሌላ፣ ሲወርስ ምድራዊቱን ገነት!

አካለ - ሥጋህን ነው እንጂ፣ መቼስ ብዕርክን አንሸሽም

ፍትሀት ቀለምን አይፈታም፣ ወርቅ - ጣትክን አያገኝም፡፡

አይን አያየው የለው መቼስ፣ መጣሁ፣ አስተዋልኩ፣ አመንሁ

የዛሬው አዲስ ትርዒት ነው፣ ደጅ - ሲላም አርፈህ አየሁ

ስምህ ተመችቷቸው ነው፣ ስብሃት - ለአብ ሲሉም ሰማሁ?

ሥላሴ ፊት ተኛህሳ፣ አይቼህ አላቀው ሥፍራ

ሲመኙልህ ሠፊ ዳራ -

ለምለም ቦታ እረፍ ሲሉህ፣ ከሰማዕታቱ ተራ፡፡

ዛሬ ገና ትዕግሥትህን አደነኩት ቀናሁብህ

ተኝተህ የመስማት ጥበብ፣ ለካ ልዩ ክህሎት አለህ!

እኛማ ልዩ መላ አለን - ዛሬም ይኸው ካንተ ተማርን

ቆመን የማንችለውን ተኝተን እናደምጣለን፡፡

በህይወት የማይገባንን ሞተን እንረዳለን!!

አንዳንደችማ ገና

የርሳስህን ቅድስና

የብዕርክን ልዕልና

መስክረው አያውቁምና፤

ዛሬ በፍፃሜህ ዕለት፣ ሬሣህ ገዛቸው ግና!

አየሁት፡፡

ካንተ ሬሣህ ማስፈራቱን

አገሩ እጅ መንሳቱን

ዛሬ ልብ አልኩት የልቤን፡፡

ተወልዶ የማያሸንፍ የማይቀናው ሰው እንዳለ

እንዳንተ ራሱን ሆኖ ሞቶ ‘ሚያሸንፍም አለ!!

ምንም  ህይወት ባይመቸው፣ እንደሰው አልሆነም ቢባል

እንዲህ የማታ ማታ፣ ደራሲም ማረግ ይችላል … (“ረ” ይጠብቃል)

አሻራው ለምድር ትቶ፣ ደራሲ ማረግ ይችላል!!

የካቲት 12,2004

(ለስብሃት ገ/እግዚአብሔር)

 

 

Read 2266 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:13