ደብረ ብርሃን የሚገኘው ኃይሌ ማናስ አካዳሚ በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ያስፈተናቸውን 43 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ (100%) በማሳለፍ ድንቅ ስኬት አስመዝግቧል። ከተፈታኞቹ መካከል 30 የሚኾኑት ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት በማምጣት አብነታዊነታቸውን ያሳዩ ሲሆን፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ናትናኤል ክንደዓለም 570 ነጥብ 25 በማስመዝገብ የአካዳሚው ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል። በሴት ተፈታኞች በኩል ደግሞ ሻሎም ከፈለኝ 548 ነጥብ 83 በማምጣት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
ይህ አስደናቂ ውጤት ያስመዘገበው ተቋም 38 ተማሪዎችን (88%) ለውጭ ሀገራት ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ማብቃቱን የገለጹት የአካዳሚው ምክትል ዳይሬክተር ተስፋዬ ክፍሌ ናቸው። በ2013 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር የጀመረው እና ላለፉት ሁለት ዓመታትም መቶ በመቶ የማሳለፍ ታሪክ ያለው ይህ አካዳሚ፣ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ባስፈተናቸው ተማሪዎች ያስመዘገበው ይህ ድል የትምህርት ጥራቱን በድጋሚ ያረጋገጠበት ሆኗል።
አሚኮ-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

