Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 February 2012 11:21

“ቅርስን ጠብቆ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይቻላል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የጐንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ጌትነት አማረ በዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር፣ በእንግዶች አቀባበል፣ በቱሪዝም፣ ስለ ኢንቨስትመንት እና ቅርስ ጥበቃ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በውጭ ሀገራት የሚገኙ ተወላጆቿ እስካሁን ለጐንደር ምን አደረጉ?

ባለፈው መንግስት በተደረገው ጭፍጨፋ በርካታ ወጣቶች በሱዳን አድርገው ወደ እስራኤልና አውስትራሊያን ጨምሮ አሜሪካና አውሮፓ ተሻግረዋል፡ አብዛኞቹ የወጡት በደርግ ጊዜ ነው፡፡ የሰሜን ጐንደር ዞንም ጐንደር ከተማም ብዙ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ውጭ ሀገር ሄደዋል፤ ዲያስፖራ ናቸው፡፡ እነዚህ ወንድሞች እህቶቻችን በሚፈለገው መጠን ኢንቨስት አደረጉ ማለት ባይቻልም አሁን ምቹ ፖሊሲ አለ፡፡ እነሱና ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጐችም ጭምር ጐንደር በአገልግሎት መስጫ ዘርፍ፣ በፋብሪካ… መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፡፡ ኢንቨስትመንቱ እየጨመረ ነው፡፡ በስፋት በአገልግሎት መስጫ ላይ እየተሰማሩ ነው፡፡ በተለይ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ብዙ የሥራ እድል የሚከፍቱ እንዲጨምሩ እናበረታታለን፡፡

ከተማዋ ጐንደር ልጆቿን ለመሰብሰብ ምን አደረገች?

አካባቢው እንዲለማ ከምናደርጋቸው ነገሮች አንዱ የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ የቢሮክራሲውን ማነቆ በማስወገድ አገልግሎቱን ፈጣን እና መሠረተ ልማት የተሟላለት እያደረግን ነው፡፡ እንደ ጥምቀት በመሰሉ መልካም አጋጣሚዎች ደግሞ መጥተው እንዲያለሙ እየቀሰቀስን ነው፡፡ በአካል ከምናናግረው በተጨማሪ በራሪ ጽሑፎች አዘጋጅተናል፡፡

የጐንደር ከተማ ዋነኛ የኢንቨስትመንት አማራጮች ምንድናቸው? ችግሮቹስ?

እድገት ተኮር እና የሥራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ብረታብረት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ በከተማዋ ብዙ የቱሪዝም አማራጮች ስላሉ የአገልግሎት ሴክተሮችም እንደ አማራጭ ይጠቀሳሉ፡፡

በቂ መሬት እና መሠረተ ልማት አላችሁ?

የትም ቦታ የመሬት እጥረት አለ፡፡ ከተማ አካባቢ መልሶ ማልማት እያደረግን ነው፡፡ ቤቶች ሽቅብ እንዲያድጉ እያደረግን ነው፤ የፋሲል ግቢን ታሪካዊነት ባገናዘበ መልኩ፡፡ የቅርስ ከተማዎች ቅርስን በጠበቀ መልኩ መገንባት የሚቻልበት ነው፡ለዚህም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አስጠንተናል፤ ፒያሳና አራዳ ላይ በጐን የሚሰፋባቸው አካባቢዎች ደግሞ ኢንዱስትሪ ዞን አለ፡፡ አስተዳደሩ ዘንድሮ ብቻ ለኢንቨስትመንት 112 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል፡ የከተማዋ መንገድም በአስፓልትና በኮብልስቶን እየተሸፈነ ነው፡፡ ስልክና መንገድ ለዚህ ዞን ተሟልቷል፡፡ ውሃ ግን በከተማዋም እጥረት አለ የቆየ ችግር ነው፡፡ አቅርቦት ከአመት ዓመት እየተሻሻለ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት አለ፡፡ የሕዝብ ብዛትም ከአመት አመት እየጨመረ ነው፡፡ የአንገረብ ግድብ ከተሠራ በኋላ ችግሩን እየቀረፈ ነው፡፡ ደለልም ደግሞ እያስቸገረ ነው፡፡ የከርሰምድር ውሃም እየተጠቀምን ነው፡ በደምቢያ ወረዳ ደግሞ ባለፈው ዓመት ተጨማሪ ጉድጓዶች አስቆፍረናል፡፡ ለአስር ዓመት ያገለግላል፡ 350 ሚሊዮን ብር ያስፈልገዋል፡፡ ዘንድሮ 100 ሚሊየን ብር ወጥቷል፡፡

ለጥምቀት ዓውዳመት ከተማዋ እንግዶቿን ለማስተናገድ ነዋሪዎቿን ውሃ አስጠምታለች የሚል ቅሬታ ይሰማል…

እጥረቱ አለ፡፡ እንደዛ ለማለት ግን ያስቸግራል፡ አጠቃላይ እጥረቱ የሚፈጥረው ችግር አለ፡፡ ሆኖም ለሆቴሎችና እንግዳ ማረፊያዎች ሲባል፣ የከተማው ሕዝብ ተለይቶ የተቸገረበት አይደለም፡፡ የውሃ ቦርድን እኔ ስለምመራው ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ አውቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ ነዋሪዎቿ ተጠምተዋል የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው፡፡

በከተማዋ ምን ያህል ኢንቨስትመንት በምን ያህል ጊዜ መጣ?

ኢንቨስትመንት አዋጅ ከወጣ ከ1985 ጀምሮ፣ በተለይ ከ1990 ወዲህ 670 ተቋማት ሥራ ጀምረዋል፡በዘንድሮ አምስት ወራት ብቻ አርባ ያህል ባለሀብቶች ቦታ ወስደዋል፡፡ ወደ ግንባታ ለመግባት እየተንደረደሩ ነው፡፡

ኢንቨስትመንት ታሪካዊ ቅርሶችን እንዳያጠፋ፤ በቅርስ ጥበቃ ኢንቨስትመንቱም እንዳይቀር ምን እየተሰራ ነው?

ታሪካዊ ቅርስን በጠበቀ መልኩ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይቻላል፡፡ ለዚህ በባለሙያ ጥናት እንደገፋለን፡የኢንዱስትሪ ዞኖች አሉ፡፡ ፋሲል ግቢ፣ ቁስቋም፣ ደብረብርሃን ሥላሴና ሌሎችም የታሪካዊ ቅርስ አካባቢዎች ቅርስ የጠበቀ ኢንቨስትመንት አለ፡፡ ቅርሱንም ኢንቨስትመንቱንም የሚያስታርቅ ሥራ እየሰራን ስለሆነ ችግር ነው ብዬ አልወስደውም፡፡ ለምሣሌ በዣን ተከል ዋርካ አካባቢ በሶስት ሚሊዬን ብር መናፈሻና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጥ ተቋም እየገነባን ነው፡፡

የጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያመጣው ለውጥ አለ?

በዚህ መልኩ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ ለዚህ የመረጥነው ጥርን ነው፡፡ በወሩ ከጥምቀት ጋር በተያያዘ በርካታ ቱሪስቶች ይመጣሉ፡፡ የቱሪስቱን ቁጥር ብቻ ሳይሆን የቆይታ ጊዜውን ማራዘም እንፈልጋለን፡፡ ቆይታ የሚራዘመው ከተማችንን በደንብ መሸጥና ማስተዋወቅ ስንችል እና ገጽታ ስንገነባ ነው፡፡ ይህም ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ኢንቨስትመንትም ይስባል፡፡ ጐንደር በዚህ ወቅት የሆቴል አልጋ የማይገኝበት መሆኑ በራሱ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያጐላዋል፡፡ ይህም የቱሪስት ቁጥር በመጨመሩ የተገኘ ነው፡፡

በጥምቀት ሰሞን የሀገር ጐብኚው ቁጥር እንደሚጨምር በጥናት አረጋግጠናል፡ የሆቴል ቁጥር ቢጨምርም ፍላጐትም ጨምሮአል፡፡ በውጭ መገናኛ ብዙሃን ተጠቅሞ የጐብኚዎችን ቁጥር ስለመጨመር አስባችሁበት ታውቃላችሁ?

በውጭ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች አሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ባለፈው ዓመት “ቪዝት ቱ ኢትዮጵያ” የተባለ ዓለምአቀፍ ተቋም ትልቅ ድጋፍ አድርጐልናል፡፡ በጋራ ሰርተናል ከነሱ ጋር፡፡

ባለፈው ዓመት ምን ያህል ጐብኚዎች ጐንደርን ጐበኙ?

የየወሩን ለመናገር ቢቸግረኝም ወደ 5670 ጐብኚዎች ነበሩ፤ በጥር ወር ብቻ፡፡ የዓመቱ ከ60ሺህ እስከ 70ሺህ ይሆናል፡፡ የመጡትም ከአሜሪካ፣ ከስፔን፣ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመን እስራኤልና ሌሎችም ሀገሮች ነው፡፡ የስፔኖች ከሕዳር ጀምሮ ነው ቁጥሩ የሚጨምረው፡፡ ስለዚህ የባለፈው ዓመት “የጥምቀት በጐንደር” ብሔራዊ ትዕይንት የዘንድሮን ጐብኚዎችን ቁጥር ጨምሯል፡፡ በበዓሉ ወቅት የቅንጅት ችግር ታይቷል ይባላል… ሃላፊዎች እርስ በእርስ አይናበቡም ወዘተ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡

እንደዚህ አይነት ትልቅ ዝግጅቶች ሲኖሩ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ሆኖም ከአምናው ዘንድሮ አሻሽለናል፡፡ ችግሮች አይኖሩም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡

 

 

Read 2917 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:27