Wednesday, 29 July 2026 19:32

"እኛ የታሪክ መጀመሪያም መጨረሻም አይደለንም"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የቀደሙት ትውልዶች የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያከማቹትን ጥበብ እንደ ዋጋ ቢስ ማየት ታሪክንና ልምድን መናቅ እንደሆነ ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሀይሌ ገሪማ በአንድ ፖድካስት ላይ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ አሳሰቡ።

ከአያቶችና ከአባቶች ስኬትም ሆነ ስህተት ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን፣ የነበሩ ጥፋቶችን እንደ አዲስ እንድንደግማቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም ሁሉንም ነገር በራሳችን እውቀት ብቻ ለመለካት መሞከር የትዕቢት እና የትዕግስት ማጣት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

"እኛ የታሪክ መጀመሪያም መጨረሻም አይደለንም" የሚሉት ሀይሌ ገሪማ፣ እውነተኛ እድገት ሊመጣ የሚችለው በቀደሙት ትውልዶች ጠንካራ መሰረት ላይ አዲስና የተሻለ ነገር መገንባት ሲቻል ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል። ትውልድ አልፎ ትውልድ እንደሚተካ በማስታወስ፣ ያለፉትን አባቶች ጥበብና ታሪክ ረስቶ መሄድ ለሀገር እድገት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን በውይይታቸው ላይ አንስተዋል።

ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለመለወጥ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት እና በማህበራዊ ሚዲያ የትውልዶችን ውይይት ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል። የታሪክ አወንታዊ እሴቶችን ለወጣቱ ትውልድ ማሳየትና ከቀድሞ ልምዶች መማር ለወደፊቱ የተሻለ ሀገር ለመገንባት ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን የፊልም ባለሙያው አሳስበዋል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 4604 times