Thursday, 04 June 2026 10:56

ዚምባብዌና 4 ሀገራት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ወንበርን ተቀዳጁ፤ ጀርመን ሳይሳካላት ቀርቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዚምባብዌ፣ ኦስትሪያ፣ ኪርጊዝስታን፣ ፖርቹጋል፣ እንዲሁም ትሪኒዳድ እና ቶቤጎን ከጥር 1 ቀን 2027 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆኑ አባላት አድርጎ መርጧል። በዚህ ብርቱ ፉክክር በተስተዋለበት ታሪካዊ ምርጫ ወቅት መቀመጫውን ለማግኘት ከፍተኛ ቅስቀሳ ስታደርግ የነበረችው ጀርመን በቂ ድምፅ ሳታገኝ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች። በተመሳሳይ በእስያ-ፓስፊክ ቡድን ስር በፊሊፒንስ እና በኪርጊዝስታን መካከል የተደረገው ፍልሚያ እስከ አራት ዙር የዘለቀ ሲሆን፥ በመጨረሻም ኪርጊዝስታን ፓኪስታንን ለመተካት የሚያስችላትን የመጀመሪያውን ታሪካዊ ድል አረጋግጣለች።
ማዕቀብ የመጣልና የኃይል እርምጃ የመፍቀድ ሕጋዊ ሥልጣን ያለው ይህ የ15 አባላት ምክር ቤት፥ አምስት ቋሚ አባላትና በየዓመቱ አምስቱ እየተቀያየሩ የሚመረጡ 10 ቋሚ ያልሆኑ አባላት አሉት። በዚህም መሠረት አዲሶቹ ተመራጮች ሶማሊያን፣ ፓናማን፣ ዴንማርክንና ግሪክን የሚተኩ ሲሆን፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ላይቤሪያ ደግሞ እስከ 2027 ማብቂያ ድረስ በምክር ቤቱ መቆየታቸውን ይቀጥላሉ። በሌላ በኩል የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የባንግላዲሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሊሉር ራህማንን በመስከረም ወር ለሚጀምረው ለ81ኛው የጉባኤው ክፍለ-ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ታውቋል።
Read 10090 times