በኢትዮጵያ የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ 25 የኅብረቱ አባል አገራት ኤምባሲዎች (የጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ) እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት አባል ያልሆኑት ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊትዘርላንድ በጋራ በመሆን ስለ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ መግለጫ አውጥተዋል። በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ በበጎ እንደሚቀበሉ የገለጹት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎቹ፤ ለሂደቱ ስኬት አስተዋጽዖ ላበረከቱት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለምርጫ ሠራተኞች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለዕጩዎች እና ለሲቪል ማኅበራት ተዋናዮች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎችን ሚና በማድነቅ የዘገባዎቻቸውን ውጤት በጉጉት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
ይህ የጋራ መግለጫ ምርጫው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን የወጣ ሲሆን፣ በትናንታው ዕለት በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ያልተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች በሙሉ ድምጽ የመስጠት “ዕድል ይሰጣቸዋል” የሚል ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸውም አመልክተዋል። ዲፕሎማቶቹ በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም ዜጎች በምርጫው የመሳተፍ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ በማሳሰብ፣ ምርጫ ባልተካሄዱባቸው አካባቢዎች ሂደቱ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

