Tuesday, 02 June 2026 00:00

የቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ለኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት መልዕክት

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የዘንድሮውን የ7ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የሚያስችለኝን ዕድል አግኝቼ ነበር። እናም በግልና የተለያዩ ተቋማትን ወክለን የመጣን የአገር ውስጥ ታዛቢ ቡድን አባላት ምርጫውን ለመታዘብ ከመጡ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ የታዛቢ ቡድን አባላት ጋር በስካይ ላይት ሆቴል የትውውቅና ሰፋ ያለ የጋራ ውይይት አድርገን ነበር።
በዚህ ውይይት ላይም የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪና የቀድሞ የኡጋንዳ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር ዋንዲራ ካዚብዌ በምክር መልኩ ለወጣቶች ያነሱት ሐሳብ ቀልቤን ገዛው። እናም ከእኚህ ጉምቱ ፖለቲከኛ አፍሪካዊ እናት ከሐሳባቸው ጥቂት ሰበዞችን ለመምዘዝ ወደድኹ።
በአገራቸው ኡጋንዳ ፖለቲካ ውስጥ የሴቶችን/የእናቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ትርጉም ባለው መንገድ በመቀየር ጉልህ አሻራ ያኖሩት የህክምና ሳይንስን ከሥነ-መንግሥት ትምህርት ጋር ያጣጣሙ እኚህ አፍሪካዊ ምሁር እናት በውይይታችን መካከል እንዲህ አሉን።
"When women lead, even water climbs uphill."
"ሴቶች ሲመሩ ውኃ ሳይቀር እንኳን ሽቅብ ይፈሳል፤" የሚል አፍሪካዊ አባባል አለ።
መቼም ለዚህ አባባል እናንት ኢትዮጵያውያን ሕያው ምስክሮች ናችሁ። ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ፣ የዐድዋውን ጦርነት በሴትነት ብልሃት ከመሩት እቴጌ ጣይቱ ድረስ የአገራችሁ የፖለቲካ ታሪክ በሴቶች ጉልህ ተሳትፎና አሻራ የደመቀ ነው። በእውነት በእነዚህ ጀግኖች እናቶቻችሁ ታሪክ ልትኮሩ፤ ልትደነቁ ይገባችኋል።
ዶ/ር ካዚብዌ ቁጭት በቀላቀለ ስሜት ያነሱትን ሌላኛው የሐሳባቸውን ሰበዝ ለዚህች አጭር ማስታወሻ መደምደሚያ ይሆነኝ ዘንድ መረጥኩት።
እኛ አፍሪካውያን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደ ሸቀጥ ዕቃ ሙሉ በሙሉ ከምዕራቡ ዓለም ለማስገባት የምናደርገውን ልፋት ቆም ብለን መፈተሽ ይገባናል። ከሌሎች የምንቀበለውን ያህል እኛ አፍሪካውያን ለተቀረው ዓለም ልንሰጠው የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉን።
አፍሪካ ለሺህ ዓመታት የቆየ የራሷ የሆነ ግዙፍ ታሪክ፤ ገናና ሥልጣኔ፤ በዘመናት ተፈትኖ ያለፈ የዳበረ ባህላዊ የፖለቲካ ሥርዓት ያላት አህጉር ናት። እናንት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ የአኅጉራችን የአፍሪካ የሺህ ዘመናት ታሪክና ባህል ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳላችሁ።
ከአክሱም ገናና ሥልጣኔ የቅኝ ገዢዎችንና የተስፋፊዎችን ቅስም እስካንኮታኮተው የዐድዋ ድል ድረስ አኩሪ ታሪክ ያላችሁ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ። አብዛኛው የታሪካችሁ ምዕራፍ ሲገለጽም- የአንድነትን፤ የኅብረትን ኃይል ቀድሞ የተረዳችሁ ጠቢባን ሕዝቦች መሆናችሁን ነው የሚመስክረው። እናም ዛሬ ልዩነታችሁን በማጥበብ አንድነታችሁን አጠናከሩ፤ ኅብረታችሁን አጎልብቱ። አንድነት ኃይል ነው!!
ኢትዮጵያ በመከፋፈል ሳይሆን በአንድነት የደመቀ፤ በጦርነት ሳይሆን በሰላም ያሸበረቀ፤ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር የተዋበ አፍሪካዊ ተምሳሌትነቷንና እናትነቷን ያስመሰከረች አገር ሆና እንድትቀጥል ነው ምኞታችን፤ ተስፋችንና ጸሎታችን።
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ፤ አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ አበው፤ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት- ኢትዮጵያውያን እናቶች ይጸልዩልኛል፤ የእናቶቼ ጸሎታቸውና ምርቃታቸው ያግዘኛል፤ ጉልበት ይሆነኛል። የሚል ቃልን አብዝተን ከአንደበታቸው አንሰማ ነበር። ዛሬስ...?!
ታላቁ መጽሐፍ፤ "የእናት ምርቃት ቤትን ያጸናል፤" እንዲል በእናቶቻችን ምርቃትና ጸሎት የሁላችን ቤት የሆነች ኢትዮጵያ፤ አፍሪካ የአንድነት መሠረቷ ጸንቶና ሰላሟ ተጠብቆ በአንድነት ጸንታ ትኖር ዘንድ በመመኘት ልሰናበት።
ሰላም!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
Read 830 times