Saturday, 28 January 2012 11:51

“አገርም እንደ ሰው” Great Britain

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

የተከበራችሁ አንባብያን:-

England, my England,

What have I done for you?

What is there I would not do,

England my own? (Anonymous.)

“ወይ አዲስ አበባ፣ ወይ አራዳ ሆይ!

አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ?”

(መንግስቱ ለማ)

አንድ

በመጀመርያ ኢንግላንድ ብቻ ነበረች፡፡ በኋላ በጦር ሀይል (እና በዲፕሎማሲ) ተራ በተራ Scotland, Wales እና Southern Ireland ገበሩላትና The United Kingdom ሆነች፡፡ለማሳጠር ያህል እንግሊዝ እንበላትና፣ የተፃፈ ህገ መንግስት የላትም፡፡ ነገስታትዋ አስቀድሞ “I rule by Divine Right!” የሚሉ ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ፡፡ በኋላ ግን ፓርላማ “ንጉስ ያስተዳድራል፡፡ የሀገር ሉአላዊነት ጉዳዮችን በተመለከተ ግን ወሳኙ ፓርላማ ነው፣ ንጉስ የፓርላማን ውሳኔ ይፈፅማል”

ፍጥጫው ካንድ ንጉስ ወደ ቀጣዩ እየተወረሰ እየተባባሰ ሄዶ፣ ቻርልስ ቀዳማዊ ዘንድ ሲደርስ ፓርላማና ንጉስ ጦርነት ከፈቱ፡፡ Oliver Cromwell የተባለው ድንቅዬ ጄኔራል የንጉሱን ሰራዊት ባጭር ጊዜ “ድባቅ መታው!”ንጉስ ቻርልስ ተማረከ፡፡ የህዝብ ደም በማፋሰሱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ቦታው The Tower (ነገስታቱ የፈረዱባቸው መሳፍንት ወይም መኳንንት የሚታሰሩበትና፣ ሞት ከተፈረደባቸው አንገታቸው በመጥረቢያ የሚቀላበት!)

ንጉስ ቻርልስ ማለዳ ተነስቶ ጭንቅላቱ ሊቆረጥ ወደ ታወር ለመራመድ ሲለብስ፣ አልባሹን “አንድ ሌላ ሸሚዝ ደርብልኝ፡፡ ምናልባት ብርዱ ቢያንቀጠቅጠኝ ሞት ፈርቼ እንዳይመስላቸው” አለው፡፡ በኋላ ህዝቡ ይህን ሲሰማ፣ ንጉሱን ያን ያህል እንዳልጠመደው አሁን አደነቀው፣ ወደደው! (እንግሊዝም እንኳ ቢሆን ቅሉ፣ ተራ ህዝብ ማለት እንደዚህ በጥቂቱ የሚያሞኙት የዋህ መንጋ ነው፣ ለፖለቲካዉ ሽንገላ ሳያውቅ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ)

ለማንኛውም፣ ንጉሱ ስርአቱ እንደሚያዝዘው ፊቱ በጥቁር ሻሽ ተሸፍኖ (አይኖቹ ግን በሁለት ቀዳዳ እጆች የሚሰሩትን ያያሉ) አንገቱን ሊቆርጠው የሚጠብቀውን ግዙፍ ጡንቸኛ ጐረምሳ “ግዴታ ሆኖብህ ለምትቆርጠው አንገት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይቅር ብዬሃለሁ” ይለውና፣ እግራቸው አጠገብ ወደሚጠብቀው ግንድ ወርዶ ተንበርክኮ፣ አንገቱን ለመጥረቢያው አስተካከለ፡፡

የንጉስ ቻርልስ ጭንቅላት ወደዚያ ተሽቀንጥሮ ከወደቀ በኋላ ለብዙ ደቂቃዎች ሲያወራ፣ ተደብቆ የነበረ የመንግስት ምስጢር አንድ በአንድ ዘከዘከ፣ የአንዳንድ ልዑላን፣ መሳፍንት፣ መኳንንት እና ሚኒስትሮች ስም እየጠራ! (ይላሉ እንግዲህ እንግሊዞች ሲቀልዱ!)

ሁለት

እዚህ ላይ ያቺ አዝማሪው ምርጥ ልጅዋ Shakespear (ጦር ነቅንቅ) ሲያሞግሳት This scepterd Isle የሚላት (ይህች ሉአላዊት ደሴት) ለአለም ካበረከተቻቸው ፀጋዎች አሁን ትዝ የሚሉኝን ብቻ ላንሳላችሁና:-

Foot ball. እነ Arsenal, Chelsea, Milano, ወዘተ ብቻ ሳይሆኑ፣ አብዛኛው ሰውነቱ ጤነኛ የሆነ የማንም አገር ልጅ የሚጫወተው Sport! የሚነጥር ኳስ የሚገዛላቸው ያጡ ልጆች እንኳ በድሪቶ ጨርቅ ኳስ ሰፍተው፣ በድንጋይ ጐል ሰርተው የሚጫወቱት! Rugby አለላችሁ ደግሞ፣ American foot ball የሚሉት (Rugby ግን ጨዋታው የተፈጠረባት የኢንግላንድ ከተማ ናት)

The English Language የአለም ዲፕሎማቶች፣ መንግስታት፣ ሳይንቲስቶች፣ ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ አየር መንገዶች፣ international “ሸሌዎች” ሳይቀሩ በየቅላፄያቸው የሚናገሩት (እየተንተባተቡም ቢሆን!)

የወንዶች ሙሉ ልብስ (ማለት ከካልሲና ጫማ አንስቶ እስከ ሸሚዝ፣ ክራባት፣ ሰደርያ፣ ሱሪ ድረስ) የያንዳንዱ አገር ሰዎች ያገርን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ለማክበር ሲሉ፣ በበአል ቀን ከሚለብሱት የአክብሮት ልብስ በስተቀር፡፡ (አሁንም ቢሆን ሰፊው ህዝብ ያሳዩትን fashion እየተከተለ ነው እንጂ፣ ከአፍ መክፈቻ ቋንቋው ሌላ ለማወቅ የኑሮው ውጣ ውረድ አያስችለውም)

በሰው ዝርያ ታሪክ ከፊውዳሊዝም ዘመን የሚቀጥለው ስርአተ ማህበር (Capitalism) ከIndustrial production (ማምረት) ጋር ተቆራኝቶ ብቅ ያለው እንግሊዝ አገር ነበር፡፡ ከዚህ ጋር steam engine ተፈጥሮ፣ በየብስ ከሰረገላ ወደ ባቡር ጉዞ፣ በባህር ደግሞ ነፋስ ከሚያንሳፍፈው ዘገምተኛ መርከብ የውሀ እንፋሎት ወደሚነዳው ፈጣን መርከብ ተሸጋገረ፡፡ በለንደንና በኒውዮርክ መካከል የሚመላለሱት The Queen Mary እና The Queen Elizabeth መርከቦች ባለ ብዙ ፎቅ ህንፃዎች ከመሆናቸው ጋር፣ ከማጅራት መቺ በቀር ምንም የማይጐድላቸው ራሳቸውን የቻሉ ከተማዎች ነበሩ፡፡

(ከዚህ ጋር እንግዲህ የሃይማኖት ሰባኪዎች “እዩኝ እዩኝን ያበዛች ደብቁኝ ደብቁኝን አመጣች”) የሚባለውን ስነ-አእምሮአዊ ሀቅ ለማስተማር ይጠቀሙባታል:-

አንዲት “ቢጠሩዋት የማትሰማ” ባለፀጋ ሴትዮ በግራ ክንዷ (ከመዳፍ እስከ ክርን) አልማዝና ወርቅ በፀሀይ እያንፀባረቁ አይን እየሳቡ፣ ወደ መርከብ ለማውጣት ተጓዦች የሚደገፏትን ረዥም ጣውላ ተደግፌ እወጣለሁ ስትል፣ አንዱ ሞጭላፋ ጭልፊት ሌባ በያዘው ቆንጨራ ክንዷን ቆረጠና፣ እሷ ደሟ ሲጐርፍ እሱ ያን ሁሉ ክቡር ድንጋይ ይዞ ሮጦ እንደ ቅብብሎሽ ዱላ ለግብር አበሩ አቀብሎት እሱ መንገዱን ቀየሰ፡፡ ሁለቱ በለስ የቀናቸው ዘራፊዎች ያንን treasure እና ያንን የሰው ክንድ እንደ ተራ እቃ በፌስታል አንጠልጥለው ወዳልታወቀ አድራሻ ቀየሱ ይባላል እላችኋለሁ፡፡

ከጥንታዊት Athens ወዲህ በታሪክ ተደግሞ የማያውቅ Parliament እና Mute-party political system. ዛሬ ከሰሜን ኮሪያ ጉረኛ መንግስት በስተቀር የአለም ነገስታት ሁሉ መመሪያችን ነው ብለው የሚያውጁት ነው (አንዳንዶቹ ጭልጥ አርገው እየዋሹ መሆናቸው “ያደባባይ ምስጢር” መሆኑን አለም በሙሉ የሚያውቀው መሆኑን እነሱ ራሳቸውም የሚያውቁት ቢሆንም ቅሉ!)

ይህስ ከምን ይመነጫል? ብለን ብንጠይቅ፣ “እንካ በእንካ” የሚባለውን ጥበብ ተፈጥሮ ያደለችው ህዝብ በመሆናቸው ነው፡፡ Give and take ይሉታል፣ ወይም To have a sense of compromise.

ሶስት

The sun never set on the British Empire ይባል ነበር፤ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን፡፡ እውነት ነበር! ለምሳሌ ኦስትሬሊያ ላይ ቢጨልም እንኳ፣ ሰሜን አርጀንቲና ጫፍ ላይ ያሉት Falkland Islands ላይ ፀሀይዋ እየታየች እየተሞቀች ነው፡፡ ናይጀርያ ላይ ጠልቃ ህዝቡ ቢጠቁር እንኳ፣ ሆንግኮንግ ላይ እያበራች ህዝቡ ነጭና ቢጫ ነው፡፡

በነገራችን ላይ Roman Empire ማንም የውጭ ጠላት ሊጋጨው ሳይደፍር ሁለት ሺ አመት ፀንቶ ኖረ ብለናል፡፡ ሜዲቴራንያን ባህር ዙርያ የሚኖሩት ህዝቦች ሁሉ ባለ ሙሉ መብት ሮማዊያን ዜጋዎች ሆነው፡፡ Pax Romana ይሉት ነበር! (የሮማ ሰላም)

British Empire ደግሞ አራት መቶ አመት ያህል የአለምን አንድ አራተኛ ህዝብ ስታስተዳድር Pax Britannica ይሉት ነበር (የብሪታንያ ሰላም) ለመሆኑ በዚህ በኩል የሮማ ግዛትን የቆዳ ስፋት በሁለት ሺ አመት ብናባዛውና በህዝቦቹ ብዛት ብናካፍለው፣ በዚያ በኩል ደግሞ የብሪታንያ ግዛትን የቆዳ ስፋት በአራት መቶ አመት ብናባዛውና በህዝቦቿ ብዛት ብናካፍለው፣ የትኛቸው ይበልጥ ይሆን? (ጮካ ፀሀፊ ፍርዱን ለአንባቢያን ይተውላቸዋል፣ መደበርያ እንዲሆናቸው)፡፡ “መደበር መደበር፣ አሁንም መደበር!” ጓድ ፀሀፊያችሁ፡፡

አራት

ስለ ኤምፓየር ስንተርክ “እንግሊዝ” የሚለው ቃል የሚወክለው መሳፍንቱን፣ መኳንንቱን፣ እና የናጠጠ business man የሚባለውን ነው እንጂ፣ በምንም መስፈርት ቢመዘን ተራው ህዝብ ከቁጥር አይገባም፡፡ እነሆ የኤምፓየር ሰው ለናሙና ያህል:-

Keep a stiff upper lip ይላል እንግሊዝ፣ ወንድ ልጁን በብሪታንያዊ ባህሪ አርአያ ሲቀርፀው፡፡ ማለትም ውስጣችን በእፍረት ወይም በፍርሀት እየተሸማቀቀ ቢሆንም፣ የውጭ ገፅታችን ግን እንደ ኩሬ ውሀ የረጋ ፀጥታ የሞላው መስሎ መታየት አለበት፣ ምንም ቢመጣ ማንም ቢመጣ አንረበሽም፡፡ “ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ!”

ታላቅዋ ብሪታንያ ያን ሁሉ ሲሳይ ለአለም ስታበረክት Butler የሚባለውን የተከበረ profession (ሙያ) ግን የማንም አገር ሀብታም import ሊያረገው አልቻለም፡፡

Milord (My Lord) የሚዘዋወሩት Rolls Royce መኪናቸውን በትለራቸው እየሾፈረው ነው፡፡ ሮልስ ሮይስ እንደ ማንም መኪና (Cadillac ራሱ ሳይቀር!) በፋብሪካ mass produced አይሆንም፡፡ ሁለመናው (ከመስተዋቶቹ በስተቀር) ብዙ ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች በእጃቸው የሚቀርፁት ነው፤ በልዩ ጥንቃቄ፡፡ሮልስ ሮይስ ሄደው መርጠው ገዝተው የሚነዱት ready made እቃ አይደለም፡፡ ዋናው መስሪያ ቤት ሄደው፣ በቅድምያ ከፍለው፣ የሁለት አመት ወረፋ ጠብቀው፣ ጊዜው ሲደርስ መኪናውን በትለርዎ እየነዳ እመኖርያዎ ጊቢ ድረስ ያመጣልዎታል፡፡ ሮልስ ሮይስ ጋራዥ የሚሉት ቦታ ድርሽ አይልም፡፡ ሊበላሽ አይችልማ! “Never in the history!” በአዲስ አበባ እንግሊዝኛ፡፡ መቸስ የሰው ስራ ነውና፣ የቅዠት ያህል የራቀ ምናልባት ቢያጋጥምና ብልሽት ቢደርስበት እንኳ፣ የሾፌር-በትለራችን አእምሮ ነው ጋራዡ!

በትለር አርባ ክፍል ያለውን የጌታውን መለስተኛ ቤተ መንግስት ቁልፎች በኪሱ ይይዛል፡፡ በክብ ሰፊ ቁልፍ መያዣው (ግማሽ ኪሎ ያህል ሳይካበድ ይቀራል?) የጠረጴዛና የቁምሳጥን መሳብያዎች ቁልፎችም በእጁ ናቸው፡፡ ሚሎርድ ምንም ቢመጣ እንደማይረበሹ፣ እና ከበትለራቸው ጋር ያላቸውን የሁነኛ አገልጋይ እና የጌታ የቅርብ ግንኙነት ምንም ቢሆን የማይለወጥ መሆኑን የምታሳይ አጭርዬ ታሪክ እቻትና:-ሰንበት ረፋድ ላይ ሚሎርድ ከቁርስ በኋላ የጓሮ አትክልታቸውን እየኮተኮቱ እያለ፣ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፡፡ እጅ ከነሳ በኋላ ትንፋሽ እያጠረው:-

“ሚሎርድ! Good morning. A train just ran over your butler!”

“Oh dear, how unfortunate!” አሉ ሚሎርድ “Please send me the half that has got my keys.”

በትለር ስለሚባለው ተቋም የመጨረሻ ነጥብ፣ የሚከተለው እንግሊዛዊ ሀቅ ነው፡፡ ሚሎርድ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ካላሰቡ በስተቀር፣ በምቾታቸው እየተንፈላሰሱ ለመኖር ማሰብ እንኳ አይኖርባቸውም፡፡ በትለራቸው ያስብላቸዋል፡፡

በትለርና ሮልስ ሮይስ ለሦስት አራት ትውልድ ተደናቅፎ የማያውቅ የተሚላ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

ይህን አሳምረው የሚያውቁት ሚሎርድ ደግሞ የበትለራቸውን የበህር ልጅ ዋነኛ በተባሉት ትምህርት ቤቶች እየከፈለ ያስተምረዋል፡፡

ከዚህም ጋር ሮልስ ሮይሳቸውን የመንዳትና መጠገንን ጥበብ እየተካነበት ይገኛል…

 

 

Read 1920 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 11:56