Tuesday, 26 May 2026 08:24

ሞሮኮ በዓለም ትልቁን ስታዲየም እየገነባች ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)
ሞሮኮ እ.ኤ.አ. በ2030 ለምታስተናግደው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ማዘጋጃ ይሆን ዘንድ፣ 115,000 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለውን ግዙፉን የሀሰን ሁለተኛ ስታዲየም እ.ኤ.አ. እስከ 2027 ማጠናቀቂያ ድረስ ለመጨረስ ማቀዷን አስታወቀች። በካዛብላንካ አቅራቢያ እየተገነባ ያለው ይህ ስታዲየም ሲጠናቀቅ በዓለም ላይ ትልቁ የእግር ኳስ ስታዲየም እንደሚሆን ይጠበቃል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚከታተሉት ባለስልጣን ያሲር ሱሲ እንደገለጹት፣ ስራው በተጀመረ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ የስታዲየሙ 30% ያህሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከተመልካች መቀመጫዎች መካከልም 40% ያህሉ ተገንብተዋል። የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ለማሳካት ሰራተኞች በቀን በሶስት ፈረቃ የ24 ሰዓት ሙሉ ስራ እየሰሩ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ስታዲየሙ ሞሮኮ ከስፔን እና ከፖርቹጋል ጋር በጋራ ከምታስተናግደው የ2030 የፊፋ ዓለም ዋንጫ በፊት ካቀረበቻቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ፊፋ የፍጻሜው ጨዋታ የት እንደሚካሄድ እስካሁን ያልወሰነ ሲሆን፣ ሞሮኮ እንደ ሳንቲያጎ በርናባው እና ካምፕ ኑ ካሉ የስፔን ስታዲየሞች ጋር ከፍተኛ ፉክክር እያደረገች ትገኛለች።
የሞሮኮን ባህል በሚያንጸባርቅ ድንኳን መሰል ጣሪያ የተቀረጸው ይህ ግዙፍ ግንባታ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ እንደሚፈጅ የተገመተ ሲሆን፣ በአዳዲስ አውራ ጎዳናዎችና በባቡር ጣቢያ አማካኝነት ከካዛብላንካ ጋር እንደሚገናኝ ታውቋል።
Great Africa-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 1011 times