በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለውጥን በአብዮት መንገድ ለመምራት የተደረጉ የቆዩ ጥረቶች፣ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የጎደላቸው በመሆኑ ህዝባዊ ቅሬታዎችን በዘላቂነት መፍታት አለመቻላቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንደሻው ጣሰው ገለጹ። ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በማርክሲስት አስተሳሰቦች ላይ ብቻ ተመስርተው የቆዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህንን የታሪክ ክፍተት ለማረም የለውጡ መንግስት ካለፉት በጎ እሴቶች ላይ በመደመር ወደ አንድነት፣ የጋራ አስተሳሰብና የሪፎርም አሰራር የሚያስገባ አዲስ የፖለቲካ ስትራቴጂ ይዞ መምጣቱን አስረድተዋል።
ይህ አዲሱ የመንግስት የፖለቲካ እይታ በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የተገነባ ሲሆን፣ እነሱም፦ የአሰባሳቢነትና የጋራ ትርክት እሳቤ፣ ሀገራዊ ምክክር፣ የትውልድና የሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ግንባታ እይታ ለውጥ ናቸው። በዚህም መሰረት ነጠላ ትረካዎችን ወደ ጎን በመተው በጋራ እሴቶች ላይ መስራት፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ስራዎች ማገዝ፣ ነባር ስርዓቶችን ከማፍረስ ይልቅ በጎ ተሞክሮዎችን ማሳደግ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ባለፈ ወደ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ዘርፎች ማስፋፋት ተችሏል።
ይህንን የተጀመረውን የሪፎርም ጉዞ ይበልጥ ለማስቀጠል የዜጎችን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ የስርዓት ግንባታን ማረጋገጥና የትውልድ ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል። በሆሳዕና ከተማ "ከአደረጃጀት ሽግግር ወደ ልማት ማዕከል" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ አደረጃጀት እንዲመሰረት ስላደረጉ ታሪካዊ ምክንያቶች፣ ስለተመዘገቡ ስኬቶችና ክልሉን የልማትና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ በተቀመጡ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ምሁራን በሰፊው ተወያይተዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

