Saturday, 21 January 2012 10:18

የሚያስደንቁ የሚያስደምሙ ታሪኮች

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

እፊትህ የነበረው ከወደቀ፣ አንተ ዘልለህ ቦታውን ትይዛለህ፣ የቅድም ቦታህን ከኋላህ የነበረው ዘልሎ ይተካበታል፡፡ ማለት ወታደሮቹ እየወደቁም የሰልፉ የጦር ቅርጽ አይለወጥ፡፡ የሚገጥመን ጠላት ግን እያንዳንዱ እግረኛ ወደ መሰለው እየዘለለ ስለሚዋጋ ብዙ ቢገድልም ለውጊያው ውጤት ያን ያህል ልዩነት አያመጣም፡፡

የተከበራችሁ አንባብያን

እነሆ በረከት!

አንድ

George Bernard Shaw

ሰውየው Irish ነው፡፡ በወጣትነቱ እንዲህ እንዲህ ብሎ ፎክሮ ተነሳ፡፡ “England conquered Ireland. I shall have to march to London and conquer the English with my pen” ረዥም አመታት እና ብዙ ድህነትና ችግር ካሳለፈ በኋላ፣ እውነትም እንግሊዞች ከሼክስፒር ቀጥሎ ታላቁ ፀሐፌ ተውኔት በርናርድ ሾው መሆኑን አመኑለት፡፡ እሱ ግን ከሼክስፒር መብለጡን ደጋግሞ አረጋግጦላቸዋል፡፡ ሼክስፒር የተውኔትን ጥበብ አልቻለበትም፣ discipline ይጐድለዋል፣ ዝርክርክር ነው ይላል በርናርድ ሾው፡፡

ሾው ለንደን ሲገባ ለብሷት የነበረውን ሱፍ ሙሉ ልብስ ዘጠኝ አመት ሙሉ ያለ ቅያሪ ለበሳት (ድህነትን ያን ያህል ችሎ ነው እንግዲህ እንግሊዞችን የማረካቸው፡፡ አንድ ቀን በብዙ ጋዜጠኞች ተከብቦ (በአዲስ ሱፍ ልብስ አጊጦ) ያቺን ያገለገለችውን ሱሪ ዘርግቶ እያሳያቸው “እንደምታዩት፣ ዘጠኝ አመት ቁጭ ብዬ ስጽፍ ነው እቺ ሱሪ የቅልጥሞቼን ቅርጽ የያዘችው፡፡ የናንተ የማናችሁም ሱሪ ግን ቢታይ የቅልጥማችሁን ቅርጽ አያሳይም፡፡ ያው እንደናንተው አምሮ በፋብሪካ አንድ አይነት ሆኖ የተመረተ ነው!” እንግሊዞቹ እንዲህ ሲወርድባቸው ይወዱታል፣ ያደንቁታል፡፡

Saint Joan የሚባለው ትራጀዲ የስራዎቹ ሁሉ ቁንጮ ነው ይባላል፡፡ የእውነት ታሪክ ነው፡፡ የአስራ ሰባት አመት ድንግል፣ ቅዱስ ሚካል እና እምዬ ማርያም በራእይ ድምፃቸው አመራር እየሰጡዋት የፍራንስን ሰራዊት እየመራች እጦር ሜዳ ተሰልፋ እየተዋጋች፣ እንግሊዞች ሲገዙት የነበረውን የፈረንሳይ ሰሜናዊ ክፍል ነፃ አወጣች፡፡

የሰላም ድርድር ሲደረግ ግን ፈረንሳዮቹ ያችን ነፃ አውጭ ድንግል መሪያቸውን ለእንግሊዞቹ ሸጡዋት፡፡ እንግሊዞቹም አጋንንት አድረውባት እያስዋሹዋት ነው እንጂ ቅዱሳኑ እየመከሩዋት አይደለም ብለው ፈርደው በእሳት አቃጠሉዋት፡፡

Saint Joan ካቶሊካዊት ናት፡፡ ሾው ግን ፕሮቴስታንት ሆኖም ድንግሊቱ የጦር መሪ እውነተኛ ቅድስት ናት ብሎ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ሃያስያን “ተውኔትህን አይተን ለምን ካቶሊክ አትሆንም” ብለው ጠየቁት፡፡

“እሱስ እውነታችሁን ነበር” አላቸው በርናርድ ሾው “ግን እነሱ አንድ ጳጳስ ብቻ እንጂ ሁለት ጳጳስ አይቀበሉም ብዬ ተውኩት”

ይኸውላችሁ የክርስትያን ትህትና፣ በርናርድ ሾው ሲላበሰው!

…George Bernard Shaw እንግሊዞች ላይ እንዲህ ሲፈነጭባቸው፣ Opera መድረክ ላይ Madame Melba የምትባል በጣም የተዋበች ሴትዮ እጅግ ታስደስታቸው ነበር  (ሌላውን ኤውሮፓ ጭምር!) ተወልዳ ያደገችው Melbourne, Australia ስለሆነ፣ ለከተማዋ ክብር ብላ ነው ማዳም ሜልባ የሚል የመድረክ ስም የመረጠችው፡፡

አንድ ቀን ማዳም ሜልባ ፂማሙን ፉንጋውን በርናርድ ሾው አገኘችውና፤

“ለሁለታችንም የሚበጅ ሀሳብ ላቅርብልዎ?” አለችው፡፡

“መልካም፡፡ ልስማዋ”

“ተስማምተን ልጅ ብንወልድ፣ የኔን ውበትና የርስዎን ብርሃን አእምሮ ሲወርስ፣ ምን ያህል ድንቅና ብርቅዬ ሰው እንደሚሆን ይታይዎታል”

“አዎን ይታየኛል” አላት በርናርድ ሾው “ግን ምናልባት የኔን ውበትና የርስዎን አእምሮ ይዞ ቢወጣስ?”

ሁለት

…በዚያን ወቅት ከበርናርድ ሾው እና ከማዳም ሜልባ እኩል ኤውሮፓ ውስጥ ዝናው የተናኘው Bergson የሚባል ፈረንሳዊ ፈላስፋ ነበር፡፡ ስራዎቹ ሲነበቡ፣ Original (ፈር ቀዳጅ?) ፍልስፍና፣ የአፃፃፍ ዘዴያቸው (Style) ግን እጅግ በጣም የሚጥምና የሚመስጥ Prose - poetry ነው፡፡

እያንዳንዳችን የህይወት እመርታ ነን (ይላል ቤርግሶን) ጠቅላላ ኑሮዋችንን ስንመለከተው በአንድ ሰው የእግር ጉዞ ልንመስለው እንችላለን፡፡ እኔ ስወለድ የህይወት እግር አንድ ዱካ (ኮቴ) ነኝ፡፡ አባቴ ቀዳሚ ዱካ ነበር፣ ልጄ ተከታይ ዱካ ይሆናል፣ የሱ ልጅም ቀጣዩ ይሆናል፣ እያለ ይቀጥላል፡፡ የህይወት እመርታ (élan vital)

አንድ ጊዜ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር ቤርግሶን ወደ ለንደን መጥቶ አዳራሽ ውስጥ ስለ ፍልስፍናው የገለፃ ንግግር እንዲያደርግና፣ ሲጨርስ ደግሞ የጥያቄና መልስ፣ የውይይት ሰአት እንዲያስከትል ጋብዙት፡፡

አዳራሹ ሞልቶ፣ መቆምያ ስፍራው እንኳ ተጨናንቋል፡፡ ቤርግሶን ንግግሩን ሊያቀርብ ገና ከወንበሩ ሊነሳ ሲል ሳይታሰብ ድንገት Bernard Shaw ገብቶ ቤርግሶን ሊቆምበት ወደ ነበረው መድረክ ቀድሞት ወጣ፡፡ እና “Ladies and gentlemen”  ብሎ ንግግር ጀመረ “ከሚስተር ቤርግሶንን ፍልስፍና ጋር ላስተዋውቃችሁ መጥቻለሁ” ብሎ ገለፃውን ቀጠለ፡፡

ቤርግሶን ሚስተር ሾው ልክ ስላልመሰሉት ተቃውሞውን ለመግለጽ “Mais non! Pas du tout! “እንደሱ አይደለም!” ኧረ በጭራሽ! ማለት ሲጀምር

“My dear Mr.Bergson,” አለው በርናርድ ሾው “Do let me continue. I understand your philosophy much more than you do” ብሎ ዝም አሰኘውና ቀጠለ፡፡ (ወዳጄ ሚስተር ቤርግሶን፣ ልቀጥል ፍቀድልኝ፡፡ ፍልስፍናህ ላንተ ከገባህ የበለጠ ገብቶኛል፡፡)

እና በርናርድ ሾው ከአንድ ሰአት በላይ ተናገረ፡፡ ሲጨርስ፣ ቤርግሶንን ይሁን ታዳሚውን ህዝብ ይሁን ደህና ሁኑ እንኳ ሳይል ወጥቶ ሄደ፣ አቶ ሳይጠሩት ከተፍ ሳይበደሩት ጤፍ!!

ሶስት

መገረማችንን ስንቀጥል ወደ ጥንታዊ ታሪክ ጐራ እንላለን፡፡ The Roman Empire ከአንዲት የወንዝ ዳር መንደር (Roma የምትባል) ተነስቶ፣ Mediterranean Sea ዙሪያ ያሉትን አገሮች ሁሉ ጠቅልሎ፣ ሁለት ሺ አመት ሙሉ ማንም የውጭ ጠላት ሳይደፍረው፣ ህዝቦች ሁሉ Pax Romana (የሮማ ሰላም) ጃንጥላ ስር ተጠልለው በሰላም ይኖሩ ነበር፡፡

እንደ ሌሎች ታላቅ ስልጣኔዎች፣ የሮማ ከተማ ግንባታም መነሻ Legend አለው፣ ህዝቦቹ እውነት ነው ብለው የሚያምኑት፡፡

Romus እና Remulus የሚባሉ ወንድማማች ነበሩ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን Tiber ወንዝ ዳር ከተማ ገነቡ፡፡ ስንትና ስንት ወራት ብዙ ብዙ ከለፉ በኋላ፣ ተግባራቸውን በመፈፀማቸው የደስ ደስ እየታዘዙዋቸው ለደከሙት ያገር ልጆች ሁሉ ግብር ጣሉ፡፡

ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲዘፍኑ ሲጨፍሩ ውለው ሁሉም ሞቅ አላቸው፡፡

በተይ ሬሙሉስ ሰከረ፡፡ ተነሳና “አሁን እንግዲህ ሮሙስ ማንም የማይደፍረው ከተማ ሰራሁ ብለህ ሞተሀል፡፡ በል ይኸውልህ ካቡን ጥሼ ስገባ” አለ በካቡ ዘልሎ ገባ፡፡

ይህን ጊዜ ሮሙስ በደም ፍላት ዘልሎ እየተነሳ “ሮማን ጥሶ የገባ፣ በራሱ ሞት ፈረደ” ብሎ ወንድሙን ሰየፈው …

…ለመሆኑ ሮማን እንደዚህ ታላቅ ለመሆን ያበቃት ምስጢሩ ምንድነው? እንደ  እንቆቅልሽ አይነት ጠባይ ያለው መልስ እናገኛለን፡፡ ማለቴ ፈልገን ፈልገን አጥተነው ምስጢሩ ከተነገረን በኋላ “ውይ ይህን ያህል ቀላል ነበር” እንላለን፡፡ ሁለት ቀላል የመሰለ ብልሀት ሲያብር፣ ያልታሰበ ትልቅ ዘላቂ ውጤት ያስገኛል፡፡

ብልሀት አንድ፣ የሮማ እግረኛ ወታደር አሰላለፍ ነበር፡፡ ሲታይ መልኩ የጦር ጫፍን ያስታውሳል፡፡ የመጀመሪያው ወታደር የጦሩ ጫፍ ነው፡፡ ከኋላው ሁለት ወታደር፣ ከነሱ ኋላ ሶስት ወታደር፣ እንዲህ እያሉ ይበዛሉ፡፡

እፊትህ የነበረው ከወደቀ፣ አንተ ዘልለህ ቦታውን ትይዛለህ፣ የቅድም ቦታህን ከኋላህ የነበረው ዘልሎ ይተካበታል፡፡ ማለት ወታደሮቹ እየወደቁም የሰልፉ የጦር ቅርጽ አይለወጥ፡፡

የሚገጥመን ጠላት ግን እያንዳንዱ እግረኛ ወደ መሰለው እየዘለለ ስለሚዋጋ ብዙ ቢገድልም ለውጊያው ውጤት ያን ያህል ልዩነት አያመጣም፡፡

ብልሀት ሁለት፣ ድል ያደረግነውን አገር እንዴት ነው የምናስተዳድረው ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል፡፡

ሊመጣብን የሚችለው ችግር፣ አገሬው ከሮማ ነፃ እንወጣለን ብሎ ያመፀ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ የዚህ አገር ሰዎች ከንግዲህ ወድያ የሮማ ዜጋዎች ናቸው፡፡ በህግ ፊት ሮማዊ ያለው መብት ሁሉ የነሱ ነው፡፡

ከመሀላቸው በቂ ፍላጐትና ችሎታ ያለው ሰው ከተገኘ፣ ልክ ሮማ ከተማ ውስጥ ከተወለደው ዜጋ እኩል Senator ሆኖ የመመረጥ እድል አለው፡፡

ለዚህ ነው ሮማ የውጪ ጠላት ሳያሰጋት ሁለት ሺ መት የኖረችው፡፡ የእርስ በርስ ስልጣን ሽሚያ ያስቸግራት ነበር እንጂ፡

ብዙ ከተማዎች ጠባቂ አድባር አለቻቸው ወይም አንድ ታቦት ነው ጠባቂያቸው፡፡ የሮማ ከተማ ጠባቂ Janus ይባላል፣ ሁለት ፊት አለው፡፡ በዚህ በኩል ፊቱን እናያለን፡፡ እልፍ ብለን ደሞ ከኋላው ምን እንደሚመስል ብንመለከት ይህም የጃኑስ ፊት ነው፡፡ ማለት ጃኑስ ሳያይህ ወደ ሮማ መግባት አትችልም፡፡ (ለሮማ መንግስት ዘላቂነት ምክንያት፣ ምናልባት ጃኑስ አንዱ (እንድያውም ዋነኛው) ቢሆንስ?

አራት

ኢጣልያ አገርን ሳንለቅ፣ በዘመናት ጉዞ ብቻ Roman Empireን አልፈን ወደ ክርስትያንዋ የባህር Empire ወደ Venice እንመጣለን፡፡ ይህ የአንዲት ወደብ መንግስት በሜዲቴራንያን ባህር ዙሪያ ያሉትን አገሮች ሁሉ ለስድስት መቶ አመት አንቀጥቅጦ ገዝቷቸዋል፡፡ ከሁሉ የሚገርመው እንቆቅልሻዊ ምስጢር ደግሞ፣ ይህን ስድስት መቶ አመት “ጥርጣሬ - ፍርሃት” የሚሉት ቅዠት ቬኒስን ራስዋን አንቀጥቅጦ ሲገዛት የኖረ መሆኑ ነው፡፡

አስተዳደራቸውን ምን አይነት ሰይጣን እንዳዋቀረው እንጃ፣ አብረውህ የሚሰሩት ሁሉ አንተ የመንግስት ጠላት መሆንህን ለማጋለጥ ታጥቀው የተነሱ ይመስልሃል፡፡ እነሱም እያንዳንዳቸው በየበኩላቸው ልክ እንዳንተው ያ ሁሉ ሰው ሊያጠፋቸው የተሰለፈ ይመስላቸዋል፡፡

ይሄ ጭጋጋም ድባብ በስራህ ቦታና ሰአት ብቻ አይደለም የሚያጠላው፡፡ በጨዋታ በመዝናኛ ቦታም፣ በፓርቲ በዳንከራ ስፍራም እያንዳንዱ ግለሰብ ሌሎቹ ከሚሸርቡበት ተንኮል ለማምለጥ መጠንቀቅ አለበት፡፡

ወደ ቤተሰብ ኑሮ ብንመጣም ያው ነው፡፡ ካናትህ በስተቀር ማንንም አታምንም፡፡ ወይ የቅርብ ዘመድህ ወይም ወንድምህ ወይም እህትህ ወይ አንዳቸው ተሻርከው ሊያጠፉህ ይችላሉ፡፡

የዚህ ሁሉ ፍርሃት ምንጭ “ምስጢራዊው ክስ ነው፡፡ ዘግናኝ ነገር!  ማንም ዜጋ የሌላውን ሰው ስምና አድራሻ ጽፎ፣ እንዲህ እንዲህ አይነት ቃላት (ተከሳሽን የሚኮንኑ) በእንትና ፊት ለእንቶኔ ሲነግረው ሰምቻለሁ፡፡ በቃ፡፡

ከሳሽ ስሙን መንገር የለበትም “ለሀገር ተቆርቋሪ” ብሎ ወረቀቱን ወደሚመለከተው መስሪያ ቤት ይልካል፡፡ ተከሳሽ ይታሰራል፡፡ እስራቱ እድሜ ይፍታህ ነው፡፡ እስረኛው ማን እንደከሰሰው እንኳ ስለማያውቅ፣ በቀን ውሎው የሚያገኛቸውን ሰዎች ሁሉ አንድ በአንድ ሲጠረጥር ይኖራታል፡፡ ከእናቱ በስተቀር ማንም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ ምስኪን እስረኛ ምናልባት የገዛ እናቱንም ሊጠረጥራት ይችላል፡፡

ተራው ዜጋ ብቻ አይደለም ሰውን ሁሉ የሚጠረጥረው፡፡ ባለስልጣናቱ ራሳቸው እርስ በርስ ሲጠራጠሩ ሲፈሩ ነው የሚኖሩት፡፡ ሹመቱ “Dodge” የሚባለው ዋናው ገዢ እንኳ ጥርጣሬ ሲያብላላው ይኖራል፡፡

እንዲያም ሆኖ Venician Empire ፀንቶ በኖረባቸው ዘመናት ሃያ ትውልድ ሲጋባና ሲራባ ኖሮባታል፣ በዚህ በኩነኔ ውስጥ፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት አሜን፡፡

አምስት

አረቦች ነዳጅ እየሸጡ መበልፀግ ካመጡ ወዲህ ተለወጡ (ተበላሹ የሚሉ ወገኖችም አሉ) እንጂ፣ ከዚያ በፊት እጅግ የሚያስገርሙና የሚደነቁ ህዝብ ነበሩ፡፡ ማህበራዊ ስርአታቸው በጐሳ እና በነገድ የተዋቀረ ነበር፡፡ (እንደ ሱማሌዎቻችን)

በዚያ በምድረ በዳ ውስጥ ህዝቦቹ የሚኖሩት ውሃ ጉድጓዶች ዙሪያ መንደር ሰርተው ነው፡፡ ዙሪያውን ሳርና እጽዋት፣ እና ረዣዥሞች የቴምር ዛፎች ይገኛሉ፡፡ ለህዝቦቹ የሚበቁ ውሃ ጉድጓዶች ባለመኖራቸው፣ ጐሳ ለጐሳ ውጊያ ይበዛል፡፡

ከአስደሳች ባህላቸው አንዲትዋን ጐን እንመልከት፡፡ አንድ ሰው መንገድ ጠፍቶት ወይም ስንቅ አልቆበት መጥቶ “የመሸብኝ እንግዳ አሳድሩኝ” ሲላቸው፣ ወድያው ተቀብለው፣ ለእግሩ መታጠብያ ውሃ አቅርበው፣ እራት አብልተው፣ የሚተኛበትን ቦታ አሳይተው፣ ማን ነህ ከየት መጣህ ሳይሉ ሶስት ቀን ያስተናግዱታል፡፡

አመስግኖ ሊሰናበት ሲል ነው ማንነቱ የሚጠየቀው፡፡ እንግዳና አስተናጋጅ የጐሳ ስም ይለዋወጣሉ፡፡ የአንድ ጐሳ ሰዎች ሆነው የተገኙ እንደሆነ፣ እና እንግዳው ጉዞውን ለመቀጠል በቂ አቅም ገና ያላጠራቀመ ከሆነ፣ መስተንግዶው ሊቀጥል ይችላል፡፡

የጠላት ጐሳዎች አባላት ሆነው ከተገኙ ግን፣ አስተናጋጅ “በአንድ ሰአት ውስጥ ከዚህ ርቀህ ካልጠፋህ ደምህ ደመ ከልብ ነው ” ብሎ ያባርረዋል፡፡

…አረቦች ውጭ አገር ሲኖሩስ እንዴት ያለ ገጽታ ያሳያሉ? የዛሬን እንጃ፡፡ በጃንሆይ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በጋሪ በምንመላለስበት ወቅት፣ ሱቆች ሁሉ “አረብ ቤት” ነበሩ፡፡

(ባለፀጋዎች ግን አርመን ወይም ግሪክ ሱቅ ሄደው ይገበያሉ) እዚህ ጽሑፍ ውስጥ አረብ ማለት የየመን ሰው ነው፡፡

የመኒዎቹ ከሀበሻ ጋር በጣም ይግባባሉ፣ ሲቀልዱብን ደግሞ ከልብ እንስቃለን፡፡ ጥቂት ናሙናዎች እኚውላችሁ፡፡ (ሀበሻ ግን በስማቸው አይጠራቸውም፡፡ “አረብ” ናቸው በቃ፡፡

ሀ) አንዱ አረብ ሱቁ ጽዳት ስለጐደለው ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሷል፡፡ ዳኛው “አረብ” አሉት “ሱቅህ እንዳይዘጋብህ ተጠንቀቅ፡፡ ቆሻሻ ከመሆኑ የተነሳ በየማእዘኑ ሸረሪት አድርቶበታል”

“ያ ዳንያ” አላቸው አረቡ “ምን አይነት ሸረሪት” በጣቱ እያመለከተ “ይህ አይነት ሸረሪት ወይስ ሌላ አይነት?”

ለ) አረብ ቤት ጐን ሻይ ቤት አለ፣ የአረቡ ሀበሻ ሚስት ናት ባለ ሻይ ቤትዋ፡፡ ለሁለቱም የሚላላክ ጉራጌ ልጅ ቀጥረዋል፡፡ (በኋላ አረቡ አገሩ ሲገባ ሱቁን ያ ተላላኪ ልጅ ይወርሰውና “ጉራጌ ሱቅ” ይሆናል)

ሌላው አረብ ተከሳሽ ሆኖ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ እሱ ነው ከሳሽ፡፡ ተከሳሽ ጐረቤቱ የሆነ ጠብደል ሀበሻ ጐረምሳ

ዳኛው “አረብ፣ ተከሳሽ ምን በደለኝ ነው ምትለው?” አሉት፡፡

አረብ “አላህ ያውቃል፣ እሱ ያውቃል፣ አና ያውቃል”

ዳኛ “ዱቤ ወስዶ አልከፍል አለ?”

አረብ “አላህ ያውቃል፣ እሱ ያውቃል፣ አና ያውቃል”

ዳኛ “ደበደበህ?”

አረብ “አላህ ያውቃል፣ እሱ ያውቃል፣ አና ያውቃል”

ዳኛ (እየተናደዱ) “ምን ይለፋደዳል?! አስገድዶ ደፈረህ እንዴ?”

አረብ ”አላህ ያውቃል፤ እሱ ያውቃል፣ አና ያውቃል፣ ኢንታ ያውቃል”

የመኒዎቹ ሳይሆኑ ሌሎቹ አረቦች ምን ይላሉ? “እባብና ሀበሻ አብረው ብታገኝ፣ አስቀድመህ ሀበሻውን ግደል” (“ምን ያህል ቢፈሩን ነው፣ ጃል?” ይላል ቆፍጣናው አይበገሬ ሀበሻ)

ሐ. ሱቅ ወይም ፍርድ ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም የመኒ ወዳጆቻችንን የምናገኛቸው፡፡ ጐዳናም ያገናኘናል፡፡

አረቡ አራት ኪሎ ቆሞ ወደ ስድስት ኪሎ የሚወስደውን ጋሪ ይጠብቃል፡፡ ባለጋሪ “ወዴት ነው፣ አረብ?”

አረብ “ወደ አባትህ ቤት”

ባለጋሪ (ለመሳቅ እየተዘጋጀ) “የት ነው እሱ ደሞ?”

አረብ “እናትክ ቤት አጠገብ” (የጳጳሱን ግቢ እና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ማለቱ ነው)

መ. አረብ አገሮች ጦር ሀይሎቻቸውን አስተባብረው እስራኤልን ወረሩዋት፡፡ አንድ አይናው ጄኔራል ሞሼዳያን ስድስት ቀን ብቻ በወሰደ ውጊያ “ድባቅ መታቸው”

በዚያ ሰሞን የአዲስ አበባ ሰዎች በአብዛኛው ወሬያቸው ስለዚህ ጦርነት ነበር፡፡ የመኒዎቻችን በጣም አዝነውም ተናደውም ነበር፡፡

አንዲት ሀበሻ  ገበያተኛ ሱቅ መጣችና “አረብ” ብላ ጮኸችበት “የእስራኤል ሸሚዝ አለህ?”

“ኡሱ የለም!” አላት እየገላመጣት “እናትሽን በጉልበት ደፍሮ ያስረገዛት የጣልያን ሸሚዝ አለ”

(ሴትዮዋ ክፉ ከይሲ ናት ወይስ ምን? ቢባል፣ እኔ በበኩሌ ስገምት፣ እንደኔ ብልጥ የለም የምትል የመጨረሻ ደደብ ሀበሻ ናት)

ስድስት

አንዲት ባለፀጋ ሴትዮ አጥር ግቢያቸው ዘንድ ቆመዋል፡፡ አንድ ኮሳሳ የቆሎ ተማሪ አጠገባቸው መጥቶ፣ ወደ ውስጥ በኩል “በእንተ ስማ ለማርያም! ቁራሽ ጣሉልኝ ፃድቃኖቼ!” ብሎ አዜመ፡፡

“ርቦሀል?” አሉት

“አዎን እመቤትዬ”

“በጣም ነው የራበህ”

“በጣም!”

“አሁን ራቡ ሙርሙር እያደረገህ ነው?”

“አዎን እመቤትዬ!”

“በል እለፍ” ብለውት ገብተው በራቸውን ዘጉ፡፡

(ለምን እንዲህ መረመሩት ይሆን? እሳቸውስ ያውቁ ይሆን?)

ሰባት

የጊቢ አንበሶችን የሚመግባቸውና እስር ቤታቸውን የሚጠርግላቸው አንድ ሰውዬ ነበረ፡፡ ጃንሆይ ከሌሎቹ አብልጠው የሚወዱት መኩሪያ የሚሉትን ትልቅዬ፣ ባለጥቁር ጐፈር ኰርማ ነበር፡፡

አንበሳ ጠባቂው “መኩሪያና እኔ’ኮ ጓደኛሞች ነን፡፡ እዩን!” ይልና አንገቱን ያቅፈዋል፡፡

ጎብኚዎቹ ሁልጊዜ “ተው ይህን አውሬ አትዳፈረው” ይሉታል አልሰማቸውም፣ መተቃቀፉን ቀጠለበት፡፡

አንድ ጎደሎ ቀን አቅፎት ሲመካበት ቆየና፣ መኩሪያ ሆዬ ምን እንደነካው እንጃ፣ እያዩት ጠባቂውን ይበላው ጀመር! ሰውየው በድንጋጤ ሲጮህ፣ ምክር ለጋሾቹ ሀበሾች “አላልንህም?” አሉት እየተቀባበሉ “አንድ ቀን ይበላሀል አላልንህም? የሰው ምክር  ብትሰማ ምን ነበረበት?”

ነብስ ይማር! ሰአሊ ለነ ቅድስት አሜን፡፡

ስምንት

አንዲት አሜሪካዊት ነበረች፣ እዚህ አገር የምትኖር፡፡ ሀይቅ ውስጥ የሚኖር አንድ አዞ አለመደች፡፡ በየቀኑ ረፋድ ላይ እየመጣች ስጋ ታጐርሰዋለች፡፡ እየተቀራረቡ ጓደኝነት አበጁ፡፡ ሴትዮዋ ወደ ውሀው ትገባና አንገቱን አቅፋ ታጐርሰዋለች፡፡

አንድ ጎደሎ ነጃሳ ቀን፣ አቅፋ እያዋራችው እያጐረሰችው ቆይታ፣ ድንገት በእግርዋ እየጐተተ ወደ ሀይቁ ወሰዳትና ሲበላት፣ እየጮኸች “ፎቶ አንሱኝና ወደ ቤቶቼ ላኩልኝ” አለች፡፡

ነብር ይማር! ሰአሊ ለነ ቅድስት አሜን፡፡

እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

 

 

Read 2472 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:22