Saturday, 23 May 2026 18:18

ከኡጋንዳ መንደር እስከ ዓለም ዋንጫ መድረክ፡ የ«ጌቶ ኪድስ» እና የሻኪራ አስደናቂ ታሪክ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ራሳቸውን «ጌቶ ኪድስ» እያሉ የሚጠሩትና በኡጋንዳ ካትዊ ከተሰኘ የድሆች ሰፈር የወጡት ታዳጊ ዳንሰኞች፣ የዘመናት ትልቅ ህልማቸው ዕውን ሆኗል። ለዚህ አስደናቂ ስኬት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነችው ኮሎምቢያዊቷ ድምፃዊት ሻኪራ ትልቁን ምስጋና ትወስዳለች። ድምፃዊቷ ታዳጊዎቹ በ2026 በምዕራብ ንፍቀ ክበብ (አሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ) በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የእረፍት ሰዓት የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ አብረዋት መድረክ እንዲጋሩ በይፋ ግብዣ አቅርባላቸዋለች።
ሻኪራ በማህበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልዕክት፣ በኡጋንዳ የሚገኙትን የጌቶ ኪድስ የዳንስ ትርኢቶች በሙሉ ተከታትላ እጅግ መገረሟንና መደሰቷን ገልጻለች። በአለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወነው ይህ ታላቅ የእረፍት ሰዓት የሙዚቃ ትርኢት ጁላይ 19 ቀን 2026 ዓ.ም በኒውጀርሲ በሚገኘው ሜት ላይፍ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን፣ በዕለቱ ከሻኪራ በተጨማሪ እንደ ማዶና እና ቢቲኤስ ያሉ የዓለም የምንጊዜም ተወዳጅ ኮከቦች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
ይህ በ2014 የተመሰረተውና በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቃቸው የዳንስ ቪዲዮዎች የዓለምን ትኩረት የሳበው የኡጋንዳው ጌቶ ኪድስ ቡድን አሁን ላይ ወደ ላቀ ታሪክ እየተሻገረ ይገኛል። ሻኪራ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ እነዚህን የኡጋንዳ ታዳጊዎች ማካተትዋ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ሌሎች ድንቅ የዳንስ ችሎታ ያላቸውን ሰዎችም ለማካተት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፤ «በዚህ ትልቅ ሾው ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ሰዎች እንዲቀርቡ እና ልዩ ልዩ ባህሎች እንዲንጸባረቁ እፈልጋለሁ» ስትልም አክላለች።
Read 6711 times