Print this page
Saturday, 14 January 2012 10:59

በስለት ወጥቼ በስለት ተመለስኩ

Written by  - ዶሰኛው -
Rate this item
(0 votes)

“እንደ አሜሪካ የማይተኛበት ሀገር ያለ አይመስለኝም”  የሀገሬ ሰው ሲተርት የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም ይላል፡፡ ኢትዮጵያውያኖችና  በሌላ ታዳጊ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ግን አሜሪካን በስም ብቻ ይናፍቋታል፡፡ መቼም ድህነት እንኳን አሜሪካን ሱዳንን እንድናፍቅ አድርጐን የለ!ንይደረግ? በ2010 የዲቪ ፕሮግራም ዲቪ ደርሶኝ አሜሪካ የመሄድ ዕድሉን ሳገኝ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛና ቤተሰብ በጣም ተደስተው እንኳን ደስ ያለህ ብለውኝ ነበር፡፡ ለነገሩ እኔ በተለያየ  ጊዜ ለስራ ወደ ደቡብ አፍሪካና እንግሊዝ ሄጄ ለትንሽ ጊዜ ቆይታ አድርጌ ስለነበር  ብዙም አልሞቀኝም፡፡ በሃገሬ በምህንድስና ሞያ እተዳደር የነበረ ሲሆን አስተማማኝ ገቢና ጥሩ ህይወት ከቤተሰቦቼ ጋር እንኖር ነበር፡፡ ወደ አሜሪካ ስሄድ የነበረው ሽኝት የሠርግ  ያህል ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ያሳፍረኛል፡፡ እንደውም “አትርሳን አደራህን” ያሉኝን ሰዎች  ሳስባቸው አዝናለሁ፤ ምንም ማድረግ ባለመቻሌና ነገሩ የተገላቢጦሽ በመሆኑ፡፡

አሜሪካ እንደሄድኩኝ እህቴ ጋ ሜሪላንድ ነበር ያረፍኩት፡፡ እርግጥ ወንድሜም ቨርጂኒያ ይኖር ነበር፡፡ መቼም ሁለት ወሩን የአሜሪካን ትልቅነት፤ የመንገዱን ስፋት፣ የህንፃውን ጥራት፤ የመኪናውን አይነት፤ የቴክኖሎጂውን እድገት በመመልከት ተደነቅሁ፡፡ ያው የሚያውቁህ ወዳጅ ዘመዶች አሜሪካ እንደሄድክ ለአንድ ለሁለት ወር ያዝናኑሃል፡፡ ከዛ  በኋላ ግን ዞር ብሎ የሚያይህ የለም፡፡ ራስህን ቻል ነው ጨዋታው፡፡ በትርፍ ጊዜዬ መጽሐፍ በማንበብና የፈረደበት Cable ላይ በመጣድ አሳልፋለሁ፡፡ አሜሪካ ውስጥ  አንድ ያልተመቸኝ ነገር ማህበራዊ መስተጋብሩ ነው፡፡ ከጐረቤት ጋር መጫወት ወይም  ሻይ ቡና መጠጣት የማይታሰብ ነው፡፡ ያው ያረፍኩበት የእህቴ ቤት  አካባቢ ነጮች እና ጥቁሮች ያሉበት ነበር፡፡ ብዙ ሃበሻ የለም፡፡ ጓደኛህን አታገኘውም፤ ወይ ስራ ላይ ነው   ወይ ተኝቷል፤ እንኳን እንደዚህ አገር በየቀኑ መገናኘት ቀርቶ በወርም ማግኘት ብርቅ ነው፡፡

አሜሪካ ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ ስራ ለማግኘት ደፋ ቀና ማለቴ አልቀረም፡፡ Online በሙያዬ አመለክት ነበር ግን መልስ አላገኘሁም፡፡ በዚህም ላይ የሄድኩበት ጊዜ አሜሪካ ኢኮኖሚዋ ደክሞ የስራ አጡ ቁጥር ወደ 10% የደረሰበት ወቅት ስለነበር ስራ ያውም በሞያህ ማግኘት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ አሜሪካ ውስጥ በሞያህ ለመስራት መጀመሪያ ዲግሪህን በነሱ ደረጃ ማሳደግ ከዛም በተለይ በምትፈልገው የሥራ መስክ ፈቃድ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ መሀንዲስ ከሆንክ ሁሉንም የመሀንዲስ ስራ መስራት አትችልም፡፡ ወይ Supervion, ወይ Cost estimation ወይ design ወዘተ ወዘተ መምረጥ አለብህ እና ይህንንም ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ምን አይነት ስራ የሚለው አነጋጋሪ ነው፡፡ ወደ Online application (በኢንተርኔት የሥራ ማመልከቻ መላክ) ልመልሳችሁና አሜሪካ ውስጥ ዘረኝነት የለም ይባላል ግን እኔ መኖሩን አይቻለሁ፡፡ በ Online application from ላይ እንዳየሁት የአመልካችን ዘር የሚጠይቅበት ክፍል አለ፡፡ White ነህ፤ Indian ነህ፤ African - American ነህ፤ Hispanic ነህ፣ African ነህ ወይም ሌላ፡፡ ይህ በኔ አመለካከት ለብልሹ የዘረኝነት አሰራር ይዳርጋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ዘሩን ስለሚቀጥርና ስለሚመርጥ፡፡ እናም አልተመቸኝም፡፡ በተጨማሪም ከሴፕቴምበር 9/11  ጥቃት በኋላ አሜሪካኖች ለስደተኞች የምትመች ሀገር አልሆነችም፤ ምክንያቱም በጐሪጥ ትታያለህ፡፡ በዛም ላይ ስራ ላይ በቂ እድገት ያለማግኘት እና ጭራሹኑም የስራ ዕድሉን ያለማግኘት ነገር አለ፡፡ ዕድገት ቢኖር እንኳ ውስን ነው፡፡ ጣሪያውን አታልፍም፡፡

አሜሪካ ውስጥ የተሳካላቸው ሀበሾች ቢኖሩም በጥሩ ጊዜ ተምረው ጥሩ ስራ የሚሰሩና በጥሩ ጊዜ ሰርተው ንግድ የጀመሩት ናቸው፡፡ ብዙ ሀበሻ እንደታዘብኩት የሚሰራው ዝቅተኛ ስራ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎችም ፓርኪንግ፣ ሱፐርማርኬት፣ የህንፃዎች ጥበቃ ስራ፤ ኤርፖርት የሻንጣ ጫኝነትና በሞል ውስጥ የዕቃ አሻሻጭነት እንዲሁም በትናንሽ ካፌዎች ውስጥ በአስተናጋጅነት መስራት ነው፡፡ ለአንድ ተማርኩ ለሚል ሀበሻ ደሞ ይሄ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ከራስ ጋር መሟገትን፤ መጋጨትን ያስከትላል፡፡

እኔ በሙያዬ ስራ ስላላገኘሁ 7/11 የሚባል ስቶር ውስጥ Wheaton, Maryland ውስጥ ተቀጠርኩ፡፡ መጀመሪያ ኮርስ ሰጥተውን sales associates (የሽያጭ ተባባሪዎች እንደማለት) ናችሁ ነበር የተባልነው፡፡ የገባው ዕለት የጠበቀኝ ግን መወልወያ ነበር፡፡ አዳራሽ የሚያህል ቤት እጠብ ተባልኩ፤ የሚገርመው ደግሞ አለቃ የተባለው ፓኪስታናዊ መወልወያ አያያዝህ ትክክል አይደለም፤ እንደዚህ አድርገው ማለቱ ነው፡፡ አሜሪካ ሀገር ያሉ ሱፐር ማርኬቶች እንደኛ አገር አይደሉም፡፡ ቡናና ሻይ ይቸበችባሉ፤ ፋስት ፉድ እዛው እያበሰሉ ይሸጣሉ፡፡ ሌሎችንም ቁሳቁሶች እንዲሁ፡፡ እናም የሽያጭ ተባባሪ ተብለህ ቡና ማፍላት፣ ፋስት ፉድ ማብሰል ግዴታህ ነው፡፡ ሶስት ሆነህ ስለምትመደብ ተከፋፍለህ ትሰራለህ፡፡ ከሁሉም የሚከብደው cooler room (ማቀዝቀዣ ክፍል) ውስጥ የተለያዩ ጁሶችን፤ የወተት ተዋጽኦዎችን፤ ለስላሳዎችን ማስገባት ማስወጣትና መሸከም ማውረድ እንዲሁም መረከብ መደርደሩ ነው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም ቤቱን፤ ሽንት ቤቱን፤ ማሽኖችን ማጽዳት የዕለት ተዕለት ስራ ነው፡፡ የስራው ትልቁ አስቸጋሪነት ለ8 ሰዓት ያህል መቆሙ ነው፡፡ ደከመኝ ብሎ ቁጢጥ እንኳ የለም፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ልለምደው አልቻልኩም ነበር፤ በኋላ ግን ሳልወድ በግዴ ለመድኩት፡፡  ያው ለትንሽ ግዜ ማለቴ ነው፡፡ ትንሽ እንኳን ቁጭ ብትል ካሜራ ስላለ በነጋታው እገሌ በዚህ ሰዓት ለምንድን ነው ቁጭ ያልከው ተብለህ ማስጠንቀቂያ ይደርስሀል፡፡ ያባቴ አምላክ ድረስ ነው የምትለው፡፡

ሌላው የጥቁር አሜሪካዊያን ሌብነት በጣም ያማርርሃል፡፡ ተው ብትለው ቤቱ ሄዶ መሳሪያውን ይዞ መጥቶ በግንባርህ ይለቅብሃል፡፡ ለአንዲት እሽግ ቺፕስ ብለህ ውዱን ህይወትህን ማጣት ይመጣል፡፡ ዝም ብለህ ሳትቆጣጠር ብትቀር ደሞ ስራህን የማጣት አደጋ ይጋረጥብሃል፡፡ ስለዚህ ሰውረኝ ማለት ብቻ ነው የሚያዋጣህ፡፡ በአንድ ወቅት ጓደኛዬ DC ውስጥ ባለ አንድ የ7/11 መደብር ውስጥ ሲሰራ ተዘርፎ ነበር፡፡ ሌቦች የሒሳብ ማሽኑ ውስጥ የነበረውን 40 ዶላር እና በብዙ ሺህ ዶላር የሚቆጠር የታሸገ ሲጋራ ዘርፈው ሲሄዱ እንደ እድል ሆኖ ሳይገድሉት አልፈዋል፡፡ በቀን ከ50 ዶላር፣ በማታ ከ30 ዶላር በላይ በሂሳብ ማሽንህ (Register) መያዝ አይጠበቅብህም፡፡ ያው ድርጅቱ ብዙ እንዳይዘረፍ በሚል ነው፡፡ ያንተስ ህይወት?  የሚዳቋ ይሆን? ብዙዎቹ ሱቆች ጥበቃ የላቸውም፤ ስለዚህ አንተው ጥበቃ እንደሆንክ ማስመሰል አለብህ፡፡ ችግሩ ኩንግፉ ደሞ አላስተማሩንም፡፡

ሌላ የስራው አስቸጋሪነት በሽፍት መሆኑ ነው፤ ሶስት ሽፍት ሲኖር አንዱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 8 ሰዓት፤ ሁለተኛው ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ከሆንክ ነገ ከሰዓት ነህ፤ ከነገወዲያ የሌሊት ትሆናለህ፡፡ ይህም እራስህን አስተምረህ ለማደግ ያለህን ተስፋ ያቀጭጭብሃል፡፡ ስለዚህ አንድ አመት መስራት አንድ አመት መማር ሊኖርብህ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ እርግጥ በህጋዊ መንገድ አሜሪካ ከገባህ በብድር የመማር እድል ሊኖርህ ይችላል፡፡ እሱም የራሱ ችግር አለው፤ ህይወትህን ሙሉ ዕዳህን ስትከፍል ትኖራለህ፡፡ ምክንያቱም የትምህርት ክፍያ ውድ ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪ ለምግብህና ለቤት ኪራይህ ሰርተህ መከፈል ይኖርብሃል ወይም ትምህርትህን እስክትጨርስ ድረስ የሚያስጠጋህ ዘመድ ያስፈልግሃል፤ ግን በአሜሪካ ይሄ ህልም ነው፡፡ ሌላው የብዙ ነጮች እንዲሁም ጥቁሮች አስቸጋሪ ፀባይ በስራ ላይ ይፈታተንሃል፡፡ የማንም ነጫጭባ መጥቶ ሲጨማለቅብህ ስሜትህ ይጐዳል፡፡ ሀገሩ ተከብሮ በሃላፊነት ቦታ ላይ ሲሰራ ለነበረና በቆዳ የተለበጠ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሲያዝ ለነበረ ሀበሻ  ሁኔታውን አምኖ መቀበል ይቸግረዋል፡፡ ዘራፍ የመይሳው ካሳ ልጅ ያስብላል፡፡

እኔ እንደነገርኩአችሁ እህቴ ጋር ነው ያረፍኩት፡፡ እህቴ ከባሏ ጋር ለ14 አመታት አሜሪካ ቢቆዩም ከትምህርቱ ስለሌሉበት ብዙ መረጃ የላቸውም፤ እኔ እንደውም መረጃዎችን ፈላልጌ ስነግራቸው ይገርማቸዋል፡፡ መስሪያ ቤትም ያወቅኩዋት ሴት 15 ዓመት ይህንኑ የ7/11 Store ስራ ነው የሰራሁት ብላኝ ገርሞኛል፡፡ እንዴት ሰው ተምሮ እንኳን አይለወጥም፡፡ 15 ዓመት ብዙ ነው፡፡ የልጅቷ ችግር ወይስ የሀገሩ … እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እህቴ ስራዋን ትታ ልጇን ስትጠብቅ ባሏ ታክሲ ይሾፍራል፡፡ ቀን ስምንት ሰዓት ወጥቶ ከለሊቱ አስር ሰዓት ቤቱ ይገባል፡፡ መቼም እንደ አሜሪካ የማይተኛበት ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ህይወት ከባድ ነች፤ ሌሊት ከስራ መጥተህ ያበሰልከውን ምግብ ሳትበላ እዛው ሶፋ ላይ እንቅልፍ ይወስድሀል፡፡ ቀንና ሌሊቱ እንደተምታታብህ ትኖራለህ፡፡ እኔ ዕድለኛ ስለነበርኩ 8 ሰዓት በመስራት በወር 1000 ዶላር አካባቢ ሳገኝ እህቴ ጋር ስለነበርኩ ከቤት ኪራይ ጣጣ ተገላግዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ቤት ተከራይቶ፣ ምግቡን በልቶ ትራንስፖርት ከፍሎ፣ የጤና እና የመኪና ዋስትና ላለበት … ይህንንም ከፍሎ የስልክ እና የመብራት እንዲሁም የኬብል ቴሌቪዥን ወዘተ ወዘተ ተከፍሎ እንዴት ይቻላል? ለቤት ኪራይ ብቻ በአማካይ እስከ 500 ዶላር  ይከፈላል - ለአንድ ክፍል ቤት ከነመታጠቢያው፡፡ የመንግስት ቤት ለማግኘት ደግም ዝቅትኛ ገቢ እንደምታገኝ ማረጋገጫ ማቅረብ እንዲሁም ለብዙ ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አይ አሜሪካ! የማትበላ ወፍ ሆናለች፡፡ አሁን ይባስ ብሎ ዝቅተኛ ስራ እንኳን ለማግኘትም በመከራ ሆኖአል፡፡ ሁለት ስራ ብታገኝ እንኳን 16 ሰዓት ቆሞ የመስራት የብቃት ማረጋገጫ ከአዕምሮ ክፍልህ ማግኘት መቻል አለብህ፡፡ (ራስህን ማሳመን ማለት ነው)

በአሜሪካ ሀበሻ ሲያይህ ባታውቀውም እንኳ ጠላት እንደመጣበት ሰው መደናበሩና ፊቱን ማጨፍገጉ አስገርሞኛል፡፡ የምታውቀው “እንኳን መጣህ” ብሎ ሻይ ቡና ማለትና አቀፍ ደገፍ ማድረግ ሲገባው ጠላት እንደመጣበት ሰው ለምን እንደሚደናበር አላውቅም፡፡ የአሜሪካን የኑሮ ውድነት ይሆን? የሚያሳዝነው ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች አብሮ የመስራትና የመኖር ባህላቸው እዚያም አሜሪካም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰመ መምጣቱ ነው፡፡ በአሜሪካ ከሀበሻ መረጃ (Information) ከማግኘት ከዘንዶ አፍ አሳ ማውጣት ይቀላል፡፡ የቅርብ ዘመድ እምትለው እንኳን የሚያውቀውን Information አይሰጥህም፡፡ አንተም እንደሱ እንድትዳክርና በጊዜ ሂደት እንድታውቅ ነው የሚፈልገው፡፡ ምናለ  Information ነግሮህ፣ ተሳክቶልህ ሀገርህንም ወገኖችህንም ብትረዳ? ነውር አለው?  ቅንነት ከኢትዮጵያ ደጅ መጥፋቱ ያሳዝናል፡፡

አንድ ጓደኛዬን በመከራ ስልኩን አግኝቼ ደውዬለት አውርተን ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ለምን እንደሆነ እንጃ ድራሹ ጠፋ፡፡ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይር ዘንድ ይቻለዋልን” ተብሎአል - በቅዱስ መፅሐፍ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ባስ ስቴሽን ላይ ቆሞ ሲለምን አይቼ ነበር፡፡ ያው የአሜሪካን ህይወት ውጥረት የበዛበት ስለሆነ እብድ ማየት አያስገርምም፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ (Drug) ሱስ  ውስጥ የገባ  ሰው ሲዘላብድ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ ልጁ ጎረቤቴ ሲሆን ባይኔ ብቻ ነው የማውቀው፡፡ ምናልባት ቤተሰቦቹ “ልጄ አሜሪካ ነው ያለው፤ ይረዳኛል” ይሉ ይሆናል፡፡  ግን እንዴት እንደሚረዳቸው እሱና ፈጣሪ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡  በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዘር ክፍፍል አሜሪካም በምሰራበት ቦታ አጋጥሞኝ ነበር፡፡  እናም ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ አማራ ተብሎ ተቦዳድኖ መስራት አልተቻለም፡፡ መናናቅ ተጀመረ፡፡ ስራዉ እንዴት ይሰራ? ከምንሰራው ወደ 15 ሰራተኞች ውስጥ ከአንድ የሀይቲና የቻይና ዜጋ በስተቀር ሌላው ሀበሻ ነበር፡፡ የመጀመሪያ አለቃችን ጥቁር አሜሪካዊት ስትሆን ገራገር ስለነበረች እርምጃ ባለመውሰዷ ከሃላፊነቷ ተነሳች፡፡

በምትኩ የመጣችው ቻይናዊት ግን እርምጃ በመውሰድ ነገሮች መስመር እንዲይዙ አድርጋለች፡፡ የእርስ በርስ መቦጫጨቁ እዛ ምን ያህል እንደከረረ ታዝቤአለሁ፡፡ የምታገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የፖለቲካ ምሁር ሲሆንብህ ድንቅ ይልሀል፡፡ በሬ ወለደም አለ፡፡ አንዱ ሀበሻ 1 ዶላር 20 ብር ገቦ እኮ አለኝ፡፡ እኔ መስከረም 17 ቀን 2003 ወደሀገሬ ስመለስ 16.70 ብር አካባቢ ነበር፡፡ (ከእውነታው ውጭ የሚወሩ ወሬዎች አይመቹኝም)

ብዙ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸው መመለስ ቢፈልጉም ምን ይዤ ልግባ የሚለው ነገር ያስጨንቃቸዋል፡፡ በተለይ ያልተማሩ ከሆነ፡፡ አሜሪካ 5 ወይም 10 አስጨናቂና አስቸጋሪ አመታት ካሳለፈ በኋላ ጥቂት ሺ ዶላሮች ይዞ መጥቶ፣ ጨፍሮ ብሩን ነዝቶ ተበድሮ ሲሄድ ያየ ሰው እኔስ መቼ ሄጄ እንደሱ ባደረግሁ ማለቱ አይቀርም፤ ግን ውስጡን ለቄስ ነው፡፡ ገንዘቡ እንዴት ይመጣል ነው ጥያቄው፡፡  በአሜሪካ የሚኖር አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ስርዓት እንደዚህ አገር አይደለም፡፡ የአሜሪካ ህግ ሴቶችንና ህፃናትን ይደግፋል፡፡

እርግጥ ለሴቶችና ለህፃናት የህግ ከለላ መሠጠቱ ባይከፋም በኢትዮጵያውያኖች ያለ አግባብ ሲተረጎም መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሚስቶች ባሎቻቸውን የሚያስፈራሩበት፣ ህፃናቶች አባቶቻቸውን የሚያሳቅቁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ደበደበኝ፣ ሰደበኝ ብለው 911 ደውለው ባሎቻቸውን፣ አባቶቻቸውን የሚያሳስሩ ሚስቶች እና ህፃናት ትንሽ አይደሉም፡፡ ይህም ቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ጥቁሮች እና ነጮች አሜሪካውያን የሃሺሽ ተጠቃሚ ስለሆኑ የዚህ ዳፋም ለኢትዮጵያዊው ልጅ ይደርሳል፡፡ ከዛስ? የት ይደርሳል የተባለው ልጅ በእብድት ጎራ ይሰለፋል፡፡ ይህም ቤተሰብና ልጅ እንዲለያዩ ያደርጋል፡፡ ያው ልጅ ልዩ የህክምና ተቋም ውስጥ ስለሚገባ ማለት ነው፡፡ እንደ ሀገሬ ልጅን ቀጥቶ ማሳደግ የሚባል ነገር አሜሪካ የለም፡፡ አሜሪካ ስትኖር የሃገርህ ባህል፤ የሃይማኖት እሴት፤ የቤተሰብ ፍቅር፤ የጓደኛና፤ የዘመድ ጨዋታ እጦት ያሳብድሀል፡፡

ለፋሲካ እኔ፣ እህቴና ባሏ ከሚጢጢዬ ልጃቸው ጋር በዓሉን ስናከብር ዕውን ይህ ፋሲካ ነው ወይስ ምንድን ነው ብያለሁ፡፡ ቤቱ ጠላ ጠላ ካልሸተተ፤ ቄጠማ ካልተጎዘጎዘ፤ ዳቦ ካልተቆረሰ ምኑን ዓመት በዓል ነው? ምንም አሜሪካ ሀብታም ሀገር ብትሆንም አይደለም በዶላር በአልማዝ የማትገዛው ባህል፤ ኃይማኖት፤ ወግና ልማድ እንዳለህ መዘንጋት የለብህም፡፡  የአሜሪካ የአየር ፀባይ ሌላ ፈተና ነው፡፡ ከእኛ ሀገር የአየር ፀባይ ጋር አራንባ እና ቆቦ ነው፡፡ ሙቀቱ እስከ 40°ሴ ሲደርስ ብርዱም እንደዛው እስከ -10°ሴ የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንንም መቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ወንጀሉም ደሞ በዛው ልክ ነው፡፡ ጥላህን እየፈራህ ነው የምትንቀሳቀሰው፡፡ ሁሉም ባይባሉም ጥቁር አሜሪካዊያን ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ ዘርፎ መበልፀግን የሚመርጡ ይመስላሉ፡፡ ወጣህ ዘግተህ ነው፤ ገባህ ዘግተህ ነው፡፡

ይሄ ደሞ ሥነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራል፡፡  እኔ እንኳን በ6 ወር የአሜሪካ ኑሮ በዝረራ ተሸንፌ “አቢሲኒያ ትግደለኝ” ብዬ መሪዬን  አዙሬ ሀገሬ ተከብሬ ለመስራት ተመለስኩ፡፡

እርግጥ አማራጭ የሌለው 12ኛ ክፍል ጨርሶ የተቀመጠ ሰው የተገኘውን ስራ ሰርቶ ለመኖር፣ ከዛም ቀስ በቀስ ተምሮ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ይችል ይሆናል ግን መንገዱ አባጣና ጎርባጣ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥሩ ኑሮና ጥሩ ሥራ ያለው ሰው የፈለገ ዲቪ ቢደርሰው እግሩን ባያነሳ መልካም ነው እላለሁ - ስቃይ ካላሰኘው በቀር፡፡ በእርግጥ ተምሮ ለመመለስ ከሆነ ችግር የለውም፡፡  በእኔ በኩል ግን ከአገሬ ተስዬ እንዳልወጣሁ ተስዬ ተመለስኩ እላችኋለሁ፡፡ ቢከፋም ቢደላም ሀገር ይሻላል፡፡

 

 

Read 2844 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 11:01