ልክ ስራ እንደጀመርኩ ቅዳሜ ከቤቴ ወደ ሜክሲኮ በታክሲ እሄዳለሁ፤ 1.50 ብቻ ከፍዬ። ሜክሲኮ እንደደረስኩ የተቀጣጠርኩት ሰው ካለ ከሰው ጋር፣ ከሌለም ብቻዬን የምወደውን እንቁላል ፍርፍር አዛለሁ፤ በላዩ ላይ ቆንጆ ቡና እጠጣለሁ። የእለቱን ጋዜጦችና መፅሔቶች በስሙኒ ኪራይ አነባለሁ፤ የወደድኩትን ጋዜጣ ወይም መፅሔት እገዛለሁ። ጠቀም ያለ ቲፕ ለአስተናጋጆች እተዋለሁ፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
በታክሲ ወደ ፒያሳ አቀናለሁ። አራዳ ህንፃ ላይ አረፍ ብዬ ውሃ አዛለሁ፤ ለስራ የማገኛቸው ወዳጆቼ ጋር እናወራለን። «ቁርስ ካልበላችሁ ብሉ፣ ጠጡ» እላለሁ። እናም ለመክፈል ግብግብ እንገጥማለን፤ «እኔ ነኝ የምከፍለው... ስርዓት ያዝ!» እየተባባልን፤ ምክንያቱም ...ስራ አለን!
ከዳላስ ሙዚቃ ቤት አለፍ ብሎ የሚገኝ ካፌና ሬስቶራንት ነበር፤ እዛ እንሄዳለን። ማኪያቶ ቡና እንጠጣለን፣ እናወራለን፤ ፒዛቸውም አሪፍ ነበር፣ ፒያሳ በወርቅ ቤቶቹ መደዳ አልፎ ያሉት ካፌወች ውስጥ .... እንዝናናለን፤ ምክንያቱም... ስራ አለን!
ምሳ ሰዓት ይደርሳል፤ ብዙ ምርጫ ነው ያለው። ወደ አራት ኪሎ አመራለሁ፤ ሮሚና ቋንጣ ፍርፍር ወይም እዛው ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል። (ምሳ ሰዓት ፒያኖ የምትጫወት ጠይም ሴት ነበረች)፤ አጤ ሚኒሊክ ራሳቸው እዛ ሆቴል እንደ እኛ አልተዝናኑም፤ ምክንያቱም... ስራ አለን! ስራ ለራስ የሚሰጠው ንግስና አለ።
ከሰዓት ሌላ ጀመዓ ይመጣል፤ በልቶ ጠጥቶ የሚያዛጋ። «እናንተ ልጆች ይሄን ጫት ተው ብል በቃ አልሰማ አላችሁ?» እልና፣ «እግዜር ለጫት አዋጣህ እንዳይለኝ፤ እስቲ አሪፍ ራት ማታ ብሉ» ብዬ የሆነ ብር ሸጎጥ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
ስንለያይ ወደ አሮጌ ተራ ወይም ኤልያስ ጨበሬው ጋር ጎራ እልና ወይም እግር ከጣለው አዟሪ አዲስ የታተመ መፅሐፍ ካለ መፅሐፎች እሸምታለሁ። አለፍ ስል አንዱ ሱቅ ቆንጆ ቲሸርት ወይም ጫማ ካየሁ እሸምታለሁ፤ምክንያቱም.. ስራ አለኝ።
ማሳረጊያዬ ቲያትር ነው፤... ቲያትር አያለሁ። ወደ ቤት ስመለስ «ሺህ ዓመት አይኖር!» እልና 40 ወይም 50 ብር ሆጭ አድርጌ በኮንትራት ላዳ ታክሲ ነው። መግቢያዬ ላይ ካለች ፍራፍሬ መሸጫ የተወሰነ ማንሳቴም አይቀርም፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
ሩቅ አይመስልም? ከአስር ዓመት ብዙ አይርቅም! እኔ የምለው... ስራ አላችሁ? እስቲ «ስራ አለኝ» ብላችሁ ጀምሩና ስራችሁ እንዴት እንደሚያኖራችሁ አካፍሉን...
(አሌክስ አብርሃም)

