Monday, 18 May 2026 17:39

"ህዶቴ" የተሰኘው አዲስ ፊልም በአድዋ ሙዚየም ሊመረቅ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)
በሀገራችን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ጥቃትና የሴት ልጅ ግርዛትን በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚያሳየው “ህዶቴ” የተሰኘው አዲስ ፊልም ሊመረቅ መሆኑ በዛሬው ዕለት በተሰጠ መግለጫ ተረጋግጧል። “ህዶቴ” የወላይትኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “ተስፋነሽ" ማለት ነው። ይህ ፊልም ማህበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን አጥብቆ እንዲቃወም ለማድረግ እንደ አንድ ትልቅ የማንቂያ ደወል ሆኖ የተዘጋጀ ሲኒማዊ ስራ ነው።
ለመሥራት አንድ ዓመት የፈጀውና ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ፊልም፤ 75% ቀረጻው በወላይታ ዞን እንዲሁም 25% በሀዋሳ ከተማ የተከናወነ ነው። ፊልሙ ለዓለም አቀፍ ዕይታ እንዲበቃ በእንግሊዘኛና በጀርመንኛ ቋንቋዎች የፅሁፍ ትርጉም የተደረገለት ሲሆን፤ እነ ጽናት ተረፈ፣ ሄኖክ አለማየሁ፣ አማኑኤል የሺወንድ እና ናርዶስ አንትዋን ጨምሮ ከ215 በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል። ፊልሙን ከዚህ ቀደም “ጀቢና” እና “ጋዜጠኛዋ” የተሰኙ ፊልሞችን ያዘጋጀው ሳሙኤል ተሻገር (የእማዬ ልጅ) የደረሰውና የመራው ሲሆን፤ ታምራት በርሄ በኤግዚኪዩቲቭ ፕሮዲውሰርነት ሰርቶበታል።
የቀለም ፊልም ፕሮዳክሽን ስራ የሆነው "ህዶቴ" በአውሮፓ እንዲሰራጭ ከጀርመኑ “ግሩምበርግ ፊልም” ኩባንያ ጋር የ3 ዓመት ስምምነት ተፈጽሟል። ፊልሙ በመጪው ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም (ፓን አፍሪካ አዳራሽ) እና በጀርመን ፍራይቡርግ ከተማ በተመሳሳይ ቀን በድምቀት ይመረቃል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 4359 times