Monday, 18 May 2026 17:36

ከንፍሮ እደላ እስከ ጥፍር መቁረጥ ሥርዓት፦ አስደናቂው የራያ ባህላዊ ሰርግ ሚስጥር!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
በራያ ምድር ሰርግ ማለት የሁለት ወጣቶች ጥምረት ብቻ ሳይሆን የይሉኝታ፣ የክብር፣ የደስታ እና የማህበረሰቡ አንድነት የሚገለጽበት ትልቅ አደባባይ ነው። ይህ እጅግ ደማቅ ባህላዊ ሥርዓት ከእጮኝነት ጀምሮ እስከ ሰርጉ ማግስት ድረስ በደራ ጨዋታ፣ በዜማ፣ በእንጉርጉሮ እና በፈጣን የዳንኪራ ምት የታጀበ የራያን ማህበረሰብ ሥነ-ልቦና በግልጽ የሚያሳይ ውብ እሴት ነው።
የሰርጉ ዝግጅት የሚጀምረው ሴት ሙሽራ እንደታጨች ለዘመድና ለጎረቤት ንፍሮ ተቀቅሎ በማደል ነው። ይህ ንፍሮ የመቅቀል ባህል ሙሽሪትን ሌላ የተመኛት ወንድ ካለ እንዳያጫት በይፋ ማሳወቂያ ዘዴ ነው። ማጫው ከተጠናቀቀ በኋላ የሴቷ ቤተሰቦች ለወንዱ ሙሽራ "ታጋ" (እንደ አልባሳት፣ ገንዘብ፣ መሬትና ከብት ያሉ የቀጣይ የጋራ መተዳደሪያ ሽልማት) ከአቅማቸው ጋር አገናዝበው ይሰጣሉ። ወንዱም በተራው ለሙሽሪት የተለያዩ ስጦታዎችን ያበረክታል።
ሌላው አስገራሚ ሥርዓት ደግሞ ከሰርጉ ከሁለት ወይም ከሦስት ቀን በፊት ሙሽሪት እየተጨፈረላትና እየተመረቀች በቤተሰቦቿ ጥፍሯ መቆረጡ ነው። ይህ የሚደረገው ክፉ መንፈስ እንዳይለክፋት ለመከላከል ነው። በተጨማሪም ሙሽሪት ገና ከወንድ ጋር ትውውቅ እንደሌላት ለማሳየት እስከ ሰርጉ ቀን ድረስ አትዋብም፤ ሙሽራው ወንድ ግን በሰርጉ ቀን ቅቤ ተቀብቶ፣ አይኑን ስር ኩል ተኩሎ (የሰውን ክፉ አይን ትኩረት ለማስቀየር) እና ባህላዊ ልብሱን ለብሶ ይሄዳል።
ሙሽሪት በበቅሎ ተጭና ወደ ወንዱ ቤት ከሄደች በኋላ ባህላዊ ቀሚሷን ለብሳ በወተት ትታጠባለች፤ ጋሜ እና ቁንጮዋንም ትላጫለች። ምንም እንኳን ይህ ውብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበረዘ የመጣበት ሁኔታ ቢኖርም፣ አሁን ላይ ወደ ነበረበት እሴት እየተመለሰ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የሰሜን ወሎ ዞን ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ይህንን ነባር ሥርዓት ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ጥናቶችንና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
AMECO-
Read 5582 times