Monday, 18 May 2026 17:23

የቢሊዮን ዶላሩን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያስደነገጡት እናት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)
በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት የሚኖር አንድ የገበሬ ቤተሰብ ለእርሻ መሬታቸው የ26 ሚሊዮን ዶላር ግዙፍ የገንዘብ ጥያቄ ቀረበላቸው። አብዛኛው ሰው ይህንን እድል ሳያቅማማ እንደሚቀበለው ግልጽ ቢሆንም፣ የ82 ዓመቷ አሮጊት ገበሬ አይዳ ሀድልስቶን ግን የቀረበላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በአጭሩ «አይሆንም!» በማለት ውድቅ አድርገውታል። ይህ የገንዘብ አቅርቦት የመጣው ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዳታ ሴንተር መገንቢያ የሚሆን 600 ኤከር የእርሻ መሬት ለመግዛት ከፈለገ አንድ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነበር።
ይህ መሬት የቤተሰቡ አጠቃላይ ንብረት ግማሽ ያህሉ ቢሆንም፣ ለአይዳና ለልጃቸው ዴልሲያ ቤር ግን መሬቱ ተራ ንብረት አልነበረም። ለእነሱ መሬቱ ምግብ ነው፣ ታሪክ ነው፣ የህልውናቸው መሠረትና መኖሪያ ቤታቸው ነው። ልጃቸው ዴልሲያ ነገሩን ባጭሩ ስታስረዳ፦ “እኔን ከጠየቁኝ እዚሁ እቆያለሁ፤ መሬቴን ይዤም ህዝብን እመግባለሁ። 26 ሚሊዮን ዶላር ለእኔ ምንም ትርጉም የለውም” ስትል የመሬቱን ክብር ከገንዘብ በላይ መሆኑን ገልጻለች።
ኩባንያው የእነሱን መሬት ማግኘት ባለመቻሉ በአቅራቢያው ያሉ ሌሎች መሬቶችን ገዝቶ ወደ ሥራው ቢቀጥልም፣ ይህ ቤተሰብ ግን ንብረቱን አሳልፎ ለመስጠት ፍጹም ፈቃደኛ አልሆነም። ለጋ እርሻ መሬቶች በግዙፍ መጋዘኖች፣ በቴክኖሎጂ ካምፓሶች እና በዳታ ሴንተሮች በከፍተኛ ፍጥነት እየተዋጡ ባሉበት በዚህ ዘመን፣ ይህ ቤተሰብ ከቴክኖሎጂው ዓለም ይልቅ ለምለሙን አፈር መርጧል። በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን የናቁት፣ በእነሱ እምነት ሰዎችን የሚመግብ መሬት ማሽኖችን ከሚመግብ መሬት በላይ እጅግ የላቀ ዋጋ ስላለው ነው።
Read 3115 times