Saturday, 16 May 2026 17:32

የሻንግሀይ ዳይመንድ ሊግ፡ አትሌት ብርቄ ሓየሎም የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር ስታሸንፍ፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደማቅ ድል አስመዝግበዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሻንግሀይ፣ ቻይና — ዛሬ በቻይና ሻንግሀይ ጅማሬውን ባደረገው የ2026 የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ የተካፈሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች አዳዲስ ክብረወሰኖችንና የግል ምርጥ ሰዓቶችን በማስመዝገብ ደማቅ ድል መቀናጀታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በዕለቱ በጉጉት በተጠበቀው የሴቶች 1500 ሜትር ውድድር አትሌት ብርቄ ሓየሎም ርቀቱን በ3:55.56 በሆነ አስደናቂ ፍጥነት በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች። አትሌት ብርቄ ያስመዘገበችው ይህ ሰዓት የውድድሩን አዲስ ክብረወሰን ያሻሻለ ከመሆኑም በላይ የወቅቱ የዓለም ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ርቀት ላይ የተካፈለችውና የፓሪስ ኦሎምፒክ የ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት ፅጌ በበኩሏ በ3:55.71 ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ የግሏን ምርጥ ሰዓት ማሻሻል ችላለች። በዚሁ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ መሰለ 3:57.56 በሆነ ሰዓት 4ኛ ደረጃን በመያዝ የዓመቱን ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በሌላ በኩል፣ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የሴቶች 5000 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ2ኛ እስከ 8ኛ ያለውን ደረጃ በበላይነት በመቆጣጠር አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። ውድድሩን ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ እስከመጨረሻው ሰዓት ብርቱ ትንቅንቅ ያደረገችው አትሌት ልቅና አምባው በ14:24.21 የግል ምርጥ ሰዓቷን በማሻሻል 2ኛ ወጥታለች። ሌላኛዋ አትሌት ሰናይት ጌታቸውም በተመሳሳይ 14:24.71 በሆነ የግል ምርጥ ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች።

በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ኡጋንዳዊቷ ፔሩዝ አሸናፊ በሆነችበት በዚህ መርሃ-ግብር፣ አትሌት ኬና ቱፋ በ8:59.66 የግል ምርጥ ሰዓቷን በማስመዝገብ 4ኛ ደረጃን ስትይዝ፣ አትሌት አለምናት ዋለ በ9:10.05 5ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

በመጨረሻም በወንዶች 3000 ሜትር ቀጥታ ውድድር ጀርመናዊው አትሌት መሀመድ አብዱላሂ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ በውድድሩ የተሳተፉት አትሌት ኩማ ግርማ በ7:29.20 (9ኛ) እና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ7:36.73 (19ኛ) በመግባት የግል ምርጥ ሰዓታቸውን አሻሽለዋል። በዚሁ ርቀት አትሌት ጌትነት ዋለ በ7:29.98 14ኛ፣ እንዲሁም ንብረት ክንዴ በ7:34.61 18ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ማጠናቀቃቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Read 835 times