Thursday, 14 May 2026 14:31

ኢትዮጵያ አንጸባራቂ ኮከቧን አጣች፤ ጀግናዋ አትሌት በክብር ተሸኘች

Written by 
Rate this item
(0 votes)
በዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ስሟ በደመቀ ሁኔታ የሚነሳውና የበርካታ ድሎች ባለቤት የሆነችው አትሌት የብሩጓል መለሰ፣ በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። አትሌቷ ለታማራክ ሆምስ ኦታዋ ዓለም አቀፍ ማራቶን ዝግጅቷን በአዲስ አበባ በማድረግ ላይ ሳለች፣ በድንገት ባጋጠማት የጤና እክል ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም ህይወቷ ሊተርፍ አልቻለም።
የብሩጓል መለሰ ላለፉት 15 ዓመታት በሩጫው ዓለም ስሟ በከፍተኛ ደረጃ ሲጠቀስ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም እ.ኤ.አ በ2018 እና 2019 የሻንጋይ ማራቶንን በበላይነት በማጠናቀቅ ታሪክ ሰርታለች። በተጨማሪም በ2015 የፕራግ እና የሂውስተን ማራቶን አሸናፊ የነበረች ሲሆን፣ በቺካጎ ማራቶንም ሁለተኛ በመውጣት ድንቅ ብቃቷን አሳይታለች። የግል ምርጥ ሰዓቷን (2:19:36) በዱባይ ማራቶን ያስመዘገበችው የብሩጓል፣ በሩጫው ዓለም እጅግ ፈታኝ የሚባለውን የ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች ማጠናቀቅ የቻለች ድንቅ አትሌት ነበረች። በመጨረሻው የውድድር ዘመኗም በባርሴሎና ማራቶን ሁለተኛ በመውጣት አሁንም ድረስ በብቃት ላይ መሆኗን አስመስክራ ነበር።
አትሌት የብሩጓል መለሰ በውድድር መድረኮች ላይ ባላት ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ በመጨረሻዎቹ 10 ኪሎ ሜትሮች ላይ በምታሳየው አስደናቂ ፍጥነትና ብርታት ትታወቃለች። ይህቺ ጀግና በሞት ብትለየንም በስፖርቱ ዓለም ያስመዘገበቻቸው ድሎች ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ። የብሩጓል መለሰ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፣ ህልፈቷ ለቤተሰቦቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሀገራችን ስፖርት ትልቅ ኪሳራ ነው። ለአትሌቷ ቤተሰቦች፣ ለጓደኞቿና ለደጋፊዎቿ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን። ነፍስሽ በሰላም ትረፍ ጀግናዋ!
Read 531 times