Saturday, 31 December 2011 09:30

“የሁለት ምርጫዎች ወግ”

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

መነሻ

“የሁለት ምርጫዎች ወግ “ የደራሲው የበኩር ሥራ ነው፡፡ መጽሐፉን ማንበብ የጀመርኩት አስተያየት ለመፃፍ እያሰብኩ ነበር፡፡ እናም በሂሳዊ ዓይን እያየሁ በንባቡ ገፋሁ፡፡ አሁን ንባቤን ጨረስኩ፡፡ በዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ አንቱታን ትቼ  “በአንተ “ ሄጃለሁ፡፡ አንድም፤ ደራሲን አንቱ ማለት ወግ አይደለም ብዬ፤ አንድም፤ ለለዛው ብዬ፡፡ እንግዲህ ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የፖለቲካ ታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሁለት አገራዊ ምርጫዎች - በሦስተኛው እና በአራተኛው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ታዲያ በረከት የሁለቱ ምርጫዎች ሂደት እና ውጤት ፍፁም የተለያየ መሆኑን ይገልፅና ኢህአዴግ እና ተቃዋሚዎች የተለያየ ምላሽ እንደሚሰጡ ጠቅሶ፤ “የትኛው ምላሽ ትክክል ነው?” የሚለው፤ ጥያቄ ከስሜት ነፃ በሆነ ምርመራ መመለስ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ የእርሱም ጥረት እንዲህ ያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ርዕስ፤ የሁለት ምርጫዎች ወግ - ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ
ደራሲ፤ በረከት ስምኦን
አታሚ፤ አልተገለፀም
ዘመን፤ 2003
ዋጋ፤ 90 ብር
(በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚሸጥ )
መነሻ
“የሁለት ምርጫዎች ወግ “ የደራሲው የበኩር ሥራ ነው፡፡ መጽሐፉን ማንበብ የጀመርኩት አስተያየት ለመፃፍ እያሰብኩ ነበር፡፡ እናም በሂሳዊ ዓይን እያየሁ በንባቡ ገፋሁ፡፡ አሁን ንባቤን ጨረስኩ፡፡ በዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ አንቱታን ትቼ  “በአንተ “ ሄጃለሁ፡፡ አንድም፤ ደራሲን አንቱ ማለት ወግ አይደለም ብዬ፤ አንድም፤ ለለዛው ብዬ፡፡ እንግዲህ ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡
“የሁለት ምርጫዎች ወግ” የፖለቲካ ታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሁለት አገራዊ ምርጫዎች - በሦስተኛው እና በአራተኛው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ታዲያ በረከት የሁለቱ ምርጫዎች ሂደት እና ውጤት ፍፁም የተለያየ መሆኑን ይገልፅና ኢህአዴግ እና ተቃዋሚዎች የተለያየ ምላሽ እንደሚሰጡ ጠቅሶ፤ “የትኛው ምላሽ ትክክል ነው?” የሚለው፤ ጥያቄ ከስሜት ነፃ በሆነ ምርመራ መመለስ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ የእርሱም ጥረት እንዲህ ያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡
እናም የበረከት ጥረት የእውነት ፍለጋ ጥረት ነው፡፡ እውነትን የመፈለግ ሥራ ደግሞ ከባድ እና ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ሊቃውንት፤ “እውነትን ለመፈለግ የተነሳ ሰው፤ እውነትን ባያገኝ እንኳን ራሱን ያገኛል” ይላሉ፡፡ በእኔ አስተያየት በረከት ራሱን ያገኘ ይመስለኛል፡፡ ራሱን ብቻ አይደለም፡፡ ድርጅቱን ኢህአዴግንም አግኝቷል፡፡ ይህን ለማሳካትም የሚደነቅ ጥረት አድርጓል፡፡
“በረከት በሁለት ምርጫዎች ወግ፤ ራሱን አግኝቷል” ስል፤ የድርሰት ክህሎቱን አረጋግጧል ማለቴ ነው፡፡ ኢህአዴግን አግኝቷል ስል፤ በፓርቲው ህይወት ወሳኝ የሆነን የታሪክ ክስተት በመተንተን ለግንዛቤ የተመቸ ስዕል አውጥቷል ለማለት ነው፡፡ በ “ሁለት ምርጫዎች ወግ” ኢህአዴግ በበረከት ዓይን ራሱን ለማየት የቻለበትን ዕድል አግኝቷል፡፡
ግን  “እውትን አገኘ” ብል ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እችላለሁ፡፡ በረከት በመፅሐፉ ያነሳቸው ነገሮች፤ በጠራራ ፀሐይ የተከናወኑ እና በብዙዎቻችን ምስክርነት የሚደገፉ ነገሮች ናቸው፡፡ እኛ ምስክር ልንሆን በማንችልባቸውና በረከት በድርጅት ሥራ፣ በግል ገጠመኝ እና በድርድር ወይም በውይይት መድረኮች ያገኛቸው መረጃዎች ትክክለኛነትም አያሰጋንም፡፡ ምክንያቱም መረጃዎቹ በህይወት ባሉ ተዋናዮች መኖር ዋስትና ያገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ደራሲው  “የጠላት ወሬ ነው” የሚያሰኝ ሁኔታ ይፈጥራል ብሎ በሚያስብበት አጋጣሚ ሁሉ፤ ገለፃውን በሰነዶች ወይም በሦስተኛ ወገን ቃል የማስኬድ ስልትን በቋሚነት ይከተላል፡፡ ይህም ተዓማኒነቱን ያጠናክራል፡፡
ይህም ሆኖ  “እውነቱን ፈልጎ አግኝቷል” ማለት፤ ለአንዳንዶቻችን ፀሐይን ትክ ብሎ እንደ ማየት ያስቸግር ይሆናል፡፡ ማስቸገር ብቻ አይደለም፤ አስተያየቱ ለሚመለከታቸው የተወሰኑ ሰዎች ህመም ይፈጥር ይሆናል፡፡
ብዙ ጊዜ እንደሚገጥመን፤ ጎራ የለየ ሰልፍ ውስጥ ስንገባ በአመክንዮ ፈለግ የመጓዝ አቅም ይከዳናል፡፡ እንዲህ ሲሆን እውነቱን ከማየት ዓይንን መጨፈን የሚያስመርጥ የስሜት ግፊት ይኖራል፡፡ ይኸ እንዳለ ሆኖ፤ መጽሐፉ ለእንዲህ ያሉ ሰዎችም ይጠቅማል፡፡ ግንዛቤን የሚያዳብር እና የዕይታ ማዕቀፍን የሚያሰፋ ነገር እንደሚያገኙበት አልጠራጠርም፡፡
በዚህ መጽሐፍ፤ ሁሉም የምርጫ ሂደት ዋና ተዋናይ የሆኑ ተቋማት፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች ተካተዋል፡፡ ይሁንና፤ በረከት ስለ ሚያዝያው የድጋፍ ሰልፍ ሲናገር፤ “አንድም ሰው የቀረ ከማይመስልበት ሰልፍ አንድ ሰው አልተገኘም” (ገፅ፣ 89) እንዳለው፤ እንደ አርሶ አደሩ፣ የከተማ ነዋሪው፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ መንግስት፣ የምርጫ ታዛቢ፣ ነጋዴ፣ የምርጫ ቦርድ ወዘተ፤ የምርጫው ሂደት ዋና ተዋናይ ሆኖ ሳለ፤ እንዲያውም  “የምርጫውን ይዘት በእጅጉ ወስኗል” የሚባል ሆኖ ሳለ፤ አንድ ተቋም ብቻ በመፅሐፉ ውስጥ ጥቂት ሥፍራም አልተሰጠውም፡፡ ይህም  የግሉ ፕሬስ ነው፡፡
በጥቅሉ፤ “ታሪክ ለመስራት እንጂ ታሪክ ለመንገር ጊዜ የለውም” የተባለው ድርጅት ግንባር ቀደም መሪ የሆነው በረከት፤ ጊዜ አግኝቶ፤  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የሚል ርዕስ በሰጠው የመጀመሪያ መጽሐፉ፤ የተዋጣለት ታሪክ ነጋሪ ሆኖ ታይቶኛል፡፡
ታዲያ ከዚህ ጋር በተያያዘ የማነሳው አንድ አስተያየት አለኝ፡፡ መቅድሙን ያነበበ ሰው እንደሚያየው፤ “በረከት ታሪክ ነጋሪነትን አኮስሶ ያያል” የሚያሰኝ ገለፃ አለ፡፡  “እንደ ተረት አባት” የሚለው አገላለፁ ይህን ስሜት ይፈጥራል፡፡ ይሁንና ታሪክ ሰሪነት - ታሪክ ነጋሪነትን መጎተቱ አይቀርም፡፡ የታሪክ ነጋሪነት ሥራ፤ ታሪክን የመረዳት ሥራ ነው፡፡ እናም በረከት  “የተረት አባት” ሆኖ  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ሲያወጋን፤ የሰራውን ታሪክ ለእኛ እየነገረን የመሆኑን ያህል፤ እርሱም ያለፈበትን ሂደት በወጉ ለመረዳት እየሞከረ ይመስለኛል፡፡
ታሪክን ስንሰራ - ታሪክ ይተርከናል፡፡ ታሪክን ስንተርክ - ታሪክን እንሰራለን፡፡ የኢራናዊው ራፖር ፃፊ ታሪክ እዚህ ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡ ተበድያለሁ ያለ አንድ ሰው፤ ራፖር ፃፊው ዘንድ ይሄድና  “እባክህ በደሌን ሰምተህ ማመልከቻ ፃፍልኝ” አለው፡፡ ራፖር ፃፊው የሰውየውን በደል በፀጥታ አደመጠ፡፡ ከዚያም መፃፍ ጀመረ፡፡ ጨረሰ፡፡ ጨረሰና፤  “እንግዲህ ስማኝ” አለው፡፡ ግን ባለ ጉዳዩ፤ ንባቡን እንኳን ሳያስጨርሰው እዬዬ ብሎ ማልቀስ ያዘ፡፡ ራፖር ፃፊው በሁኔታው ተደናግጦ፤  “እንዴ፤ ሰውዬው ምን ሆነሃል?” ቢለው፤ ባለጉዳዩ ፈርጠም ብሎ  “ለካ ይህን ያህል ተበድያለሁ” ብሎ መለሰለት፡፡ ትረካ እንዲህ የመረዳት ጎዳና ነው፡፡ ትረካ ልዩ የመረዳት ዕድል ይሰጣል፡፡ እንግሊዝኛው የተመቸ አገላለፅ አለው፡፡  “experiencing experience” ነው፡፡
ትረካ፤ በአድራጊው እና በድርጊቱ መካከል ያለን የባዕድ ግንኙነት ያስወግዳል፡፡ እንደምናየው፤ ክስተቶች ተነጣጥለው ሲሄዱ ዝምድናቸውን ይደብቁብናል፡፡ ያሳስቱናል ወይም ያታልሉናል፡፡ የምንረዳቸው፤ በአንድ ዓይነት መዋቅር ተደራጅተው፣ የሆነ ቅርፅ ይዘው፣ በሆነ የንድፈ ሃሳብ ዓውድ ገብተው  “ሲፈከሩ” (interpret) ወይም ሲተረጎሙ ነው፡፡ እናም በምርጫ ዘጠና ሰባት ሂደት ተሳታፊ ወይም ተመልካች ሆኖ ያለፈ አንድ ሰው፤ በህይወቱ የሚያውቃቸው ክስተቶች እንዲህ ተደራጅተው ሲተረኩ መልካቸው ይቀየርበታል፡፡ እሴታቸውና ጥልቀታቸው ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የታሪክ ድርጊቶች፤ በማለፊያ ተራኪ ተተርከው ወደ ህሊና ሲመጡ፤  “እሴት” ጨምረው በመምጣት፤ ዕውቀት እና ልምድ በመሆን መልሰው ድርጊትን ያበለፅጋሉ፡፡  «An un-narrated life is not worth living´ የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ይህን የምለው፤ የስህተት ትርጉምን ለመዝጋት እንጂ፤ በረከት  “ለመፃፍም ጊዜ አለው” ከማለት ተሻግሮ  “ታሪክ ነጋሪነት ከንቱ ሥራ ነው” የሚል ሀሳብ እንደ ሌለው በድርጊት ተናግሯል - ታሪክ ጽፎ በማሳተም፡፡ ወደፊትም መፃፉን እንደሚቀጥል ገልፅዋል፡፡
ታሪክ የመፃፍ ሥራ፤ ተግባርን ዘወር ብሎ ከማየት፣ ከመገምገም እና በዚያ ላይ ተመስርቶ ልምድ ከመቀመር ሥራ ይለያል፡፡ ደራሲው እንደ  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ባሉ ሥራዎች የሚያደርገው ደረቅ ክስተትን ቅደም ተከተል አስይዞ መተረክ አይደለም፡፡ ይልቅስ፤ ክስተቶቹን ለመረዳት የሚያስችል የንደፈ ሃሳብ ማዕቀፍ በመፍጠር፤ የነገሮች የምክንያት እና ውጤት ትስስር አጉልቶ እንዲታይ በማድረግ፤ ሌላው ቀርቶ የድርጊቱ ዋና ተዋናይ እንኳን  አውቀዋለሁ የሚለው ነገር አዲስ ሆኖ እንዲታየው በሚያደርግ አኳኋን ይተርካል፡፡ በዚህም ጥልቅ ግንዛቤን ያጠራል፡፡ የበረከት ሥራ እንዲህ ያለ ፋይዳ ያለው ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማየት የመፅሐፉን ቅርፅ እና ይዘት መቃኘት ነው፡፡ ሆኖም ይህን ቅኝት “ደራሲው ማነው?” በሚለው ጥያቄ መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ከዚያም የመፅሐፉን አደረጃጀት (Organization) አየት አድርጌ ወደ መዋቅር አልፋለሁ፡፡
ደራሲው
አቶ በረከት የአደባባይ ሰው (Public figuer) ነው፡፡ መነሻውን ከኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ በሚስብ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ፤ በትጥቅ ትግል ውስጥ አልፎ፤ በ1983 ዓ.ም የደርግ ስርዓት ሲወድቅ የመንግስት ስልጣንን የጨበጠው፤ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓትን የዘረጋውና ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ የዚህችን አገር ዕጣ- ፈንታ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እያሳለፈ የመጣው ኢህአዴግ የተባለ የፖለቲካ ድርጅት አባል ነው፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከሚባሉት ሰዎች በግንባር ቀደም የሚጠቀስ ነው፡፡ እናም በፓርቲውም ሆነ በመንግስት መዋቅር ከፍተኛ ሥልጣን ይዞ ሲሰራ የቆየና እየሰራ ያለ ነው፡፡
አቶ በረከት ለፅሁፍ እና ለሥነ-ፅሁፍ ሥራዎች ቅርብ እንደሆነ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ የተወሰኑ ግጥሞቹንም አንብቤአለሁ፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራም ይታወቃል፡፡ ጥሩ አርታዒ መሆኑንም እሰማለሁ፡፡ ከዚህ በመነሳት  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የመጀመሪያ ሥራው ቢሆንም ከፅሁፍ ሥራ ጋር ለረጅም ጊዜ የኖረ ሰው ነው፡፡ ደራሲው ማነው የሚለውን እንዲህ በአጭሩ ካሳየሁ ወደ መጽሀፉ አደረጃጀትና መዋቅር አልፋለሁ፡፡
መዋቅር እና አደረጃጀት
“የሁለት ምርጫዎች ወግ” በሁለት ክፍሎች እና በአስር ምዕራፎች የተደራጀ  “የፖለቲካ - ታሪክ” መፅሐፍ ነው፡፡ ክፍል አንድ፤ አራት ምዕራፎችን ይዟል፡፡ በ191 ገጾች የተካተተ ትረካ ያስነብበናል፡፡ ክፍል አንድ፤ የመመልከቻ አንፃር የሚያስይዙ ነገሮችን ከሰጠን በኋላ፤ የምርጫ ዘጠና ሰባትን ሂደት፤ ከቅስቀሳ ዘመቻው ተነስቶ፣ የድምጽ መስጠት፣ የድምጽ ቆጠራ እና የድህረ ምርጫ ክስተቶችን ይተርክልናል፡፡
በሌላ በኩል፤ ክፍል ሁለት ስድስት ምዕራፎችን ይዟል፡፡  ከገጽ 195 እስከ 314 ያሉትን ገጾች ይሸፍናል፡፡
የትረካ ጉዞው  “ዜና መዋዕላዊ” (Chronicle) ዘይቤ አለው፡፡ ድርጊቱ፤ የድርጊት ዋና ተሳታፊ ወይም ውስጥ አዋቂ ከሆነ ሰው አንጻር (Emic perspective) የሚተረክ ነው፡፡ ትረካው በ “እኔ ባይ” ተራኪ የሚሄድ መሆኑን ብናውቅም፤ ይህ ድምፅ ብዙ አይሰማም፡፡ አንዳንዴ “እከሌን አገኘሁት፣ ደወለልኝ፣ እንዲህ አለኝ” ወዘተ ሲል እንጂ በአብዛኛው ጎልቶ የሚሰማው  “እኛ” የሚል ድምፅ ነው፡፡
የትረካው ድምፀት (tone) በሁለቱ ክፍሎች ይለያያል፡፡ በክፍል አንድ ጎልቶ የሚሰማው የውጥረት፣ የቁጭት፣ የድንጋጤ እና የፀፀት ድምፀት ነው፡፡ በክፍል ሁለት ጎላ ብሎ የሚሰማው ድምፀት ደግሞ የእርጋታ እና የ “አይደገምም” ዓይነት ድምፅ መሰለኝ፡፡
የቃላት ምርጫው ግርታን የማይፈጥሩ እና ቀላል ናቸው፡፡ ዓረፍተ ነገሮቹ ቀላል እና ግልፅ ናቸው፡፡ ረጅም ወይም አጭር ዓረፍተ ነገሮችን እያፈራረቀ ይጠቀማል፡፡ አቶ በረከት ውስብስብ ሀሳቦችን በቀላል መንገድ የመግለፅ ልዩ ችሎታ ያለው ደራሲ ነው፡፡ ምፀት፣ አሽሙር፣ ሂዩመር፣ ስላቅ፣ አኔክዶት፤ በመፅሐፉ በተደጋጋሚ የሚታዩ የመልዕክት ማጎላመሻ ቴክኒኮች ናቸው፡፡ በረከት፤ የትረካውን ትኩረት ሳያዛንፍ በእነዚህ ቴክኒኮች የመጠቀም ብቃት አለው፡፡
ደራሲው በተቻለው መጠን  “በገለልተኛ” ስሜት ለመተረክ ይሞክራል፡፡ ሆኖም አሽሙር እና ስላቅን ሲጠቀም፤ ተቆጣጥሮ የያዘው የወገንተኝነት ስሜት ያመልጠውና በቶሎ ይመለሳል፡፡ እናም በበረከት መጠን ወገን ይዞ ግብግብ የገጠመ ሰው፤ አሁን በታየው ደረጃ ስሜቱን ገዝቶ መሄዱ ትልቅ ስኬት መስሎ ይታየናል፡፡
መዋቅር
ማንኛውም የድርሰት ሥራ ሁለት ጥቅል ጓዞች አሉት፡፡ እነሱም ይዘት እና ቅርፅ ናቸው፡፡ ይዘት እና ቅርፅ፤ በትንታኔ እንጂ በኑባሬ አይነጣጠሉም፡፡ ይዘት እና ቅርፅ እንደ ሥጋ እና አጥንት በተዋህዶ የሚገኙ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን ጓዞች ለመመርመር ምቹ የሚሆነው ጎዳና መዋቅር መመርመር ነው፡፡
እናም  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ምን ዓይነት መዋቅር እንዳለው ማወቅ የሚፈልግ ሰው ሊያደርግ የሚገባው አንድ ጥያቄ መጠየቅ ነው፡፡  “በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ሊገባ ሲችል የወጣው ወይም ሊወጣ ሲችል የገባው ምንድን ነው?” ብለን ጠይቀን፤ የምናገኘው ምላሽ መዋቅሩን ያመለክተናል፡፡ በዚህም፤ ደራሲው መጽሐፉን ለምን እንደ ፃፈው፣ ጭብጡ እና ይዘቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት እንችላለን፡፡
መጽሀፍ የሚፃፈው ሀሳብ እና ድርጊትን ለመግለፅ ነው፡፡ የሚገለፁት ሀሳብና ድርጊቶች ቅደም ተከተል ይዘው፤ በጭብጥ ዝምድና ፈጥረው፤ተፈላጊውን መልዕክት ማስተላለፍ በሚያስችል መልክ ተሰድረው ይቀርባሉ፡፡ በዚህ ሂደት ደራሲው በመጽሐፉ የሚካተቱ ጉዳዮችን ይመርጣል፡፡ ምርጫ ካለ፤  “ሊገባ ሲችል የወጣ ወይም ሊወጣ ሲችል የገባ ነገር አለ” ማለት ነው፡፡ አቶ በረከት፤ “የታሪክ መፅሀፍ የሚያዘጋጅ ሰው የመጀመሪያው ችግር ከየት መጀመር እንዳለበት በትክክል መወሰን ላይ ነው” (ገፅ 10) ይላል፡፡ ደግሞም  “የቱን ትቼ የቱን ላንሳ የሚለውም ጉዳይ ማቸገሩ አይቀርም” (ዝ.ከ) ይላል፡፡ ከየት ልጀምር? የቱን ትቼ- የቱን ላንሳ፤ የርዕስ ጉዳይ ምርጫ ውሳኔ ነው፡፡
ለምሣሌ፤ በ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተካተቱትን ሀሳብ እና ድርጊቶች ዘና አድርገን በዘመን ድካቸውን እንወስናቸው ብለን ብንነሳ፤ የተተረኩት ድርጊቶች ከ1990 እስከ 2002 ዓ.ም ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ እነዚህም አስራ ሁለት ዓመታት፤ እጅግ በርካታ ፖለቲካዊ ወይም ድርጅታዊ፣ መንግስታዊ ወይም አገራዊ ድርጊቶች የታጨቁባቸው ዓመታት ናቸው፡፡ ዘመኑን ጠበብ አድርገን፤ የመፅሀፉ ዋና ትኩረት በሆኑት ጉዳዮች ከተመራን ደግሞ ከ1997 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ያሉት ስድስት ዓመታት ተለይተው ይወጣሉ፡፡ ታዲያ ደራሲው በስድስቱ ዓመታት የተከናወኑትን ሁሉንም ተግባራት አይጠቅስም፡፡ ይልቅስ፤ ለርዕሰ ጉዳዩ ተገቢ የሆኑትን ጉዳዮች ብቻ ወስዷል፡፡
ለምሳሌ፤ ደራሲው “አቶ መለስ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት” በሚል የጠቀሰውና በመጽሀፉ የጀርባ ሽፋን ገፅ ጭምር የሚነበበው ሀሳብ በደራሲው ምርጫ እንዲገባ የተደረገ ነው፡፡ በምርጫ የገባ ከሆነ፤ በምርጫ የመቅረት ዕድልም ነበረው፡፡ ነገር ግን ገብቷል፡፡ እንዲሁም፤ የመጽሀፉ ርዕስ መነሻ ከሆነው የቻርልስ ዲከንስ  “የሁለት ከተሞች ወግ” ልብ ወለድ ተወስዶ የተጠቀሰ ቃል አለ፡፡ እነዚህ ሀሳቦች ደራሲው መዝኖ አጢኖ እንዲገቡ ያደረጋቸው ሀሳቦች ናቸው፡፡ እንዲያውም የትረካው ኃይለ - ቃላት አድርጌ ከማየቸው ሦስት ጉዳዮች ሁለቱ እነዚህ ናቸው፡፡ ከቻልኩ ወደ ኋላ አብራራአዋለሁ፡፡
“የሁለት ምርጫዎች ወግ” በሦስተኛው የ1997 ዓ.ም፤ በአራተኛው የ2002 ዓ.ም አገራዊ ምርጫዎች ላይ የሚያተኩር መፅሐፍ ነው፡፡ ደራሲው የመጽሐፉን መዋቅር ሲያበጅ  “ይህ መጽሐፍ በሁለት ምርጫዎች ላይ የሚያጠነጥን ቢሆንም” ለእነዚህ መነሻ ሆኖ ያገለገለው የተሃድሶ ንቅናቄው ነበር” ይልና በዘመን ወደ ኋላ ይሄዳል፡፡ ደግሞ ለጥቆ  “ተሃድሶው ደግሞ የኢትዮ- ኤርትራ ግጭትን ተከትሎ የመጣ ነበር” ይልና እንደገና ወደ ኋላ በመሄድ ትረካውን ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት መጀመርን መርጧል፡፡ እናም በመጽሐፉ የምናነበው ታሪክ መዋቅር በዚህ ተደንግጓል፡፡ በዚህም የመጽሐፉን መዋቅር ሲያዋቅር የሚያካትታቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ወስኗል፡፡ መዋቅሩም ቅርፅ እና ይዘቱን ያውጃል፡፡ እነዚህ ሁለቱ፤ የመጽሐፉን ጭብጥ እና መልዕክትን ያበጃሉ፡፡ ይህን ካየን በኋላ፤ በመጽሐፉ መርጦ ያስገባው ወይም ያስቀረው፤ በጀው- ከፋበት ማለት እንችላለን፡፡ ከዚያም ደራሲው እየመረጠ ያስገባቸውን ሀሳብና ድርጊቶች በክፍል እና በምዕራፍ ያደራጃል፡፡ እንዲህ አድርጎ፤ ትረካውን በርዕስ እና በንዑስ ርዕስ እየሸነሸነ እስከ ፍፃሜው ይዘልቃል፡፡  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” በአስር ምዕራፎች ተደራጅቶ፤ ምዕራፍ እየከፈተ እና እየዘጋ ሲሄድ የመጽሀፉን መዋቅር ይናገራል፡፡
እናም  “ምን መርጦ አስወጣ - ምን መርጦ አስገባ?” የመዋቅር ጥያቄ ሆኖ፤ “እዛው ሳለ” የይዘት ጥያቄ ይሆናል፡፡ “እዛው ሳለ” የጭብጥ ጥያቄ ይሆናል፤  “እዛው ሳለ” የደራሲው መልዕክት ይሆናል፡፡ በዚህ አኳኋን  “የሁለት ምርጫዎች ወግ”ን መቃኘት እንችላለን፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘን፤ መሠረታዊ የድርሰት አላባውያን እመረምራለን፡፡ ለምሣሌ፤ የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ የሀሳብ ፍሰቱ፣ ግጥምጥምነቱ (coherence) የመልዕክት ማጉያ እና ማጎላመሻ ቴክኒኮቹ፣ የትረካ አንፃሩ እና ሌሎች የድርሰት አለባውያን ሁሉ ይፈተሻሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ የድርሰት ጓዞች እዚህ ማየት አይቻልም፡፡ እናም እንደ ደራሲው ለመምረጥ እገደዳለሁ፡፡
ታዲያ  “ሁሉ አማረሽ” ዓይነት ስሜቴን ሊያረካ የሚችለው  “መዋቅር” የሚባለው ጓዘ ብዙ ርዕስ ነው፡፡ መዋቅር፤ ሁሉንም ነገር ነካ- ነካ የማድረግ ዕድል ስለሚሰጠኝ እርሱን መርጫለሁ፡፡ ደግሞ ጓዘ ብዙ ርዕስ በመሆኑ ብቻ አይደለም የመረጥኩት፡፡ አንድም፤ ምላተ - መጽሐፉ የተደራጀበትን ልዩ ስልት ለማሳየት ስለሚያስችለኝ ነው፡፡ አንድም፤ የደራሲውን ልዩ ብቃትና ጥበብ ለመመልከት ስለሚረዳኝ ነው፡፡ አንድም፤ የትንታኔውን ኃይለ - ቃላት ለማውጣት እና ለመተንተን በር ስለሚከፍትልኝ ነው፡፡ አንድም፤ ወዘተ
ፈረንጆቹ «Seeing is seeing connection´ ይላሉ፤ ማየት ግንኙነትን ማየት ነው፡፡  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ደራሲው የሚገልጻቸውን ድርጊቶች ምን ያህል እንደሚያውቃቸው በማየት የምንደነቅበት መጽሐፍ አይደለም፡፡ ለዚህ እንደ አቶ በረከት ዕድል ያለው ሰው ጥቂት ነው፡፡ የደራሲው ችሎታ የነገሮችን ግንኙነት ማየት መቻሉ ነው፡፡ ይህ ጥንካሬው፤ ቀዳሚው ምዕራፍ ወይም አንቀጽ ከተከታዩ ጋር የጉዲፈቻ ሳይሆን የደም ዝምድና እንዲኖረው አድርጎለታል፡፡አዎ፤ በአንድ ርዕስ ላይ በማትኮር ብቻ የሀሳብ አንድነት ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግንኙነትን በማየት ነው፡፡ ደራሲው ግንኙነትን ማየት መቻሉ፤ የሚጠቅሳቸው ድርጊቶች መለያየት ዜማ ሳይሰብርበት፣ ትንታኔውን እና ትረካውን ሳያንቦጫርቅበት፣ ምዕራፍ በዘፈቀደ ከፍቶ ሳይዘጋ ተጠየቃዊ ትልምን ተከትሎ እስከ መጨረሻው ለመዝለቅ አግዞታል፡፡ እንዴት? ካላችሁኝ?
የመዋቅር ፍተሻችን ለዚህ መልስ ይሰጠናል፡፡ ግን ፍተሻችንን፤  “አቶ በረከት፤ ይህን መፅሐፍ ለምን ጻፈው?” በሚል ጥያቄ እንጀምር፡፡ “በሦስተኛው እና በአራተኛው አገራዊ ምርጫዎች ላይ የሚያጠነጥነውን ይህን መጽሐፍ ከማዘጋጀቴ በፊት በነበረኝ ሀሳብ፤ በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ብቻ የሚያተኩር መፅሐፍ ማዘጋጀት ነበር” ይላል፤ (ገፅ፤7)
ለምን በሦስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ማትኮር ፈለገ? በኋላስ ለምን ሀሳቡን ቀይሮ አራተኛውን መጨመር መረጠ? ደራሲው እንዲህ ይላል፤ “ነገር ግን በሁለቱ ምርጫዎች መካከል ባለው ጊዜ በከባድ ሥራዎች ተጠምደን ጊዜው በመግፋቱ አራተኛ አገራዊ ምርጫ ተካሄደና ሁለቱን ምርጫዎች በማነፃፀር ለመፃፍ የተመቸ አጋጣሚ ተፈጠረ” (ገጽ፤ 9)
የዘጠና ሰባቱ ምርጫ የየትኛውንም ፀሐፊ ቀልብ የሚጎትት አጀንዳ ነው፡፡ “ኢህአዴግ በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ወይም በዘጠና ሰባቱ ምርጫ በአያሌው ተንገዳግዶ” (ገጽ፤ 7) ስለ ነበር፤ የ97 ምርጫ እንደ ርዕስ የአቶ በረከትን ቀልብ መሳቡ አይደንቅም፡፡ እናም ስለዚሁ ለመፃፍ ዛሬ ነገ ሲል አራተኛው አገራዊ ምርጫ መጣ፡፡ በሁለቱ ምርጫዎች መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ድንቅ ነው፡፡ “መሬት አንቀጥቅጥ ተቃውሞ” በታየበት የመስቀል አደባባይ  “መሬት አርገድግድ የድጋፍ ትዕይንት” ተስተናገደ፡፡ ይህን ማየት ልዩ የንፅፅር ሀሳብን ያመጣል፡፡ እናም የቀደመ ሀሳቡን ቀይሮ ሁለቱን ምርጫዎች በማነፃፀር ለመፃፍ ወሰነ፡፡ ምናልባት፤ ስለ ዘጠና ሰባቱ ምርጫ ብቻ ቢፅፍ  “እሪ በይ አገሬ” ዓይነት ርዕስ ሊይዝ ይችል የነበረው መጽሐፍ፤ አሁን  “የሁለት ምርጫዎች ወግ” በሚል ቀርቧል፡፡ አራተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ያካተተ መጽሐፍም ለመፃፍ ወሰነ፡፡
“ሁለቱም ምርጫዎች በመሠረታዊ ባህሪያቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም በብዙ ጉዳዮች ደግሞ በጣም የተለየ ተነፃፃሪነት ይታይባቸው ነበር” የሚለው ደራሲው፤ ተነፃፃሪነታቸውን ሲገልፅ፤  “አንደኛው በሰላም ተጀምሮ በብጥብጥ የተቋጨ ሲሆን፤ የኋለኛው በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተቋጨ ነበር” ይላል፡፡ ንፅፅሩንም ይቀጥላል፡፡ “በቀዳሚው ምርጫ 12 የነበረው የተቃዋሚዎች ወንበር ወደ 170 ሲያድግ፤ በኋለኛው ከ170 ወደ አንድ ወንበር አሽቆለቆለ፡፡ በተቃራኒው፤ በዘጠና ሰባቱ ምርጫ በአያሌው ተንገዳግዶ የነበረው ኢህአዴግ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ሁሉንም ወንበር ያዘ፡፡”
እናም “በሁለቱ ምርጫዎች እንዲህ የተለያየ ውጤት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው?” ሲል የጠየቀው አቶ በረከት፤ ለዚህ ጥያቄ ተቃዋሚዎች እና ኢህአዴግ የሚሰጡት ምላሽ የተለያየ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ከሁለቱ ምላሾች “የትኛው ትክክል ነው?” የሚለውም ከስሜት ነፃ በሆነና በሰከነ አኳኋን ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ እንደሆነ ጠቁሞ፤ እኔ “በሁለት ምርጫዎች ወግ ለማድረግ የሞከርኩትም ይህንኑ ነው” ይላል፡፡
ደራሲው፤ በአንድ በኩል እርሱ ራሱ ሂደቱን ከስሜት ባሻገር በሰከነ አኳኋን ለመመርመር መሞከሩን ይናገራል፡፡ ይኸ አልዋጥ ለሚላቸው ሰዎች እንዲመቻቸው ደግሞ  “ሂደቱን ከስሜት ባሻገር ለመመዘን ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቃሚ” የመሰሉትን መረጃዎች ሁሉ ለማቅረብ መጣጣሩን ገልጧል፡፡
አክሎም፤ ተጨባጭ ሃቆችን ሳያዛቡ የማቅረብ ግዴታን ለመወጣት መጣጣሩንና በግል አተያዩ ላይ ተመስርቶ ትንታኔ መስጠቱን ይገልፅና  “እውነታውን ሳያዛባ የማስቀመጥ ግዴታውን እና የግል ትንታኔውን በነፃነት የማቅረብ ኃላፊነቱን ላለመደባለቅ ያደረገው ጥረት መሳካት - አለመሳካቱን ለአንባቢ ሚዛን መተው መርጧል፡፡ እናም “ለዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ በትክክል በመፃፍ የበኩሌን አስተዋፅዖ” ማድረግ እችል እንደሁ በሚል ስሜት “መጽሐፉን እንደፃፈ አመልክቷል፡፡
በረከት መጽሐፍ የመጻፍ ሀሳብ ማውጠንጠን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ሆኖም “ኢህአዴግ በዛሬውና በነገው እንጂ በትናንቱ የሚኖር ድርጅት ባለመሆኑ፤ ዛሬና ነገን ለማቃናት ስንረባረብ ባለን ሰፊ የመረጃ ሀብት ልክ መጻህፍት የማዘጋጀቱን ጉዳይ ወደ ጎን ካልነው ቆየን” ይላል፤ (ገጽ፤ 9)
ታዲያ በረከት “የትግል ጉዞውን ታሪክ ለመፃፍ ሲችል፤ የቅርብ ክስተት በሆኑ ሁለት ምርጫዎች ላይ አትኩሮ መጻፍ የመረጠው ለምን ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ በምላሹም፤ የምርጫዎቹ ጉዳይ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ያልጠፉ የቅርብ ትውስታዎች ያሉበትና በርዕሰ ጉዳዩ ለመጻፍ ቀለል ያለ መሆኑ አንድ ምክንያት ሣይሆን አይቀርም” (ገፅ 10) ይላል፡፡
እናም በሁለቱ ምርጫዎች ላይ ያተኮረ ትረካው ከኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ይነሳና የተሃድሶ ንቅናቄውን ይይዛል፤ ከዚያም ምርጫዎቹን ይጨብጣል፡፡ እዚህ ላይ የፈጠረው ትልም ትረካውን ጠንካራ ተጠየቂያዊ ሀረግ ሰጥቶታል፡፡ በዚህ ውስጥ የሚያደርገውን ትንታኔ ደግሞ በሦስት ኃይለ-ቃላት አስሮ ይጓዛል፡፡ እነሱም በአቶ መለስ ሪፖርት የተጠቀሰው ከናዳ የማምለጥ ወይም ከአርማጌዶን የመሸሽ ጉዳይ፤ በቻርልስ ዲከንስ የተገለፀው የብርሃን እና የጨለማ ውህድ የሆነ ዘመን ትዕይንት እና የሽግግር ዘመን የህብረተሰብ ባህርያት ናቸው፡፡ ይህን ካልኩ ይዘቱን ለማሳየት እሞክራሁ፡፡
የመፅሐፉ፤ የመክፈቻ ምዕራፍ  “የብራ መብረቅ” የሚል ርዕስ የያዘ ነው፡፡ “ሲፈርድብን የምንኖረው በተተራመሰው የአፍሪካ ቀንድ ነው” በሚል የሚነሳው የምዕራፍ አንድ ትረካ፤ ኢህአዴግ የመንግስት ሥልጣን እንደ ያዘ፤ ከቀንዱ ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትናን የማጠናከር ፍላጎት ቢኖረውም፤ ዲሞክራሲን የማስፈን እና ልማትን ለመፍጠር ቢንቀሳቀስም፤  “ብዙም ሳንራመድ ከሌሎች ጎረቤቶቹ ጋር ሲጋጭ የከረመው የኢሳያስ መንግስት ባድሜ የእኔ ነች በሚል ሽፋን በድንገት ኢትዮጵያን በመውረሩ ተገኝቶ የነበረው አንፃራዊ ሰላም ደፍርሶ በላያችን ላይ የግጭትና የጦርነት ደመና አንዣበበ” ይላል፤ (ገፅ 16)
ከዚያም ይህን ወረራ ለመከላከል የተወሰደውን እርምጃ እና ችግሩን በሰላም ለመፍታት የተደረገውን ጥረት በመጠኑ ካመለከተ በኋላ፤ ሁሌም ጦርነት ከሰከነ አስተሳሰብ ይልቅ ለእልህ፣ ለጀብደኝነት እንዲሁም ለለየለት ፀረ - ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መነሳት ወይም ማቆጥቆጥ ለም አፈር ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ፤ ጦርነቱ “በኢህአዴግ አመራር መካከል የሀሳብ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት መሆን ጀመረ” (ገፅ 21) ይላል፡፡
እናም፤ “የችግሮቻችን ሁሉ መነሻ የኢሳያስ መንግስት ስለሆነ “ጦርነቱ የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ፡፡ ኤርትራን ለማንበርከክና ከተቻለም አሰብን ቆርሰን ለማምጣት ልንቆጥበው የሚገባን ህይወትና ሃብት ሊኖር አይገባም” በሚል ጦርነቱን ለማራዘም የሚፈልገው የእነ አቶ ተወልደ ማርያም እና ስዬ አብርሃ ወገን በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል፤ “ጦርነቱን በአጭሩ ቋጭተን ፊታችንን ወደ ልማት እና የኢህአዴግን ውስጣዊ ችግሮች ወደ ማየት ማዞር አለብን” በሚለው የአቶ መለሰ ሀሳብ ደጋፊ ወገን መካከል በለየለት የአቋም ልዩነት ላይ የተተከለ የሃሳብ ትግል እንደተከፈተ ይተርካል (ገፅ 22)
የእነ አቶ መለስ ወገን “ከመከላከል ጦርነቱ ባልተናነሰ ደረጃ የድርጅቱን ውስጣዊ የዲሞክራሲ ባህል ለማጥበብ ጦርነቱን እንደ ሰበብ እየተጠቀመበት ያሉትን ኃይሎች መታገል አስፈላጊ ነው” ይላል፡፡ ቀደም ሲል የኃይል ሚዛኑ ወደ እነ አቶ ተወልደ እና ስዬ ወገን ያደላ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ይህ እየተለወጠ መጣ፡፡ ደራሲው  “ጀብደኝነት የተጠናወተው” ሲል የሚጠቅሰው “ቡድን ቅጥ ያጣ ፖሊሲ እና አቋም ማራመድ ሲጀምር መሠረቱ እየተሸረሸረና በውስጡ መከፋፈል እየተፈጠረ ሲመጣ ለሰላም መፍትሄ እና ለልማት የቆመው ኃይል እየተጠናከረ መጣ ይላል፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅም ከድርጅቱ ውስጣዊ ዲሞክራሲ ችግር አልፎ የስርዓቱን ችግሮች በግላጭ ለመመርመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ይተርካል፡፡ በእነዚህ አጀንዳዎች ዙሪያም ሰፊ የሃሳብ ትግል መካሄዱን ይነግረናል፡፡
ከሰኔ 1992 ዓ.ም ጀምሮ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ሀሳባቸውን ለማሳየት የሚያስችሉ ፅሁፎችን ወደ ማዘጋጀት እና ወደ የሀሳብ ትግሉ በአንድ ልብ ገቡ የሚለው ደራሲው፤  “ውስጣዊ ችግር የለብንም የሚለው ወገንም፤ የድርጅት ውስጣዊ ችግሮችና የስርዓቱን አደጋዎች መተንተንና መከራከር ያዘ” ይላል፡፡
ይህ በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተካሄደ ትግል እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ዘለቀ፡፡ እናም ይህ የሀሳብ ትግል የህዳሴው ስንቅ የተቋጠረበት መሆኑን ደራሲው ይተነትናል፡፡ ትግሉም በህዳሴው ጉዞ አራማጆች አሸናፊነት መደምደሙን ይገልፃል፡፡
ከደራሲው ትንተና የምንረዳው፤ ደስተዮቭስኪ፤ “ሁላችንም የወጣነው ከጎጎል ካፖርቱ ነው” እንዳለ፤ በሁለቱም ምርጫዎች ሲፋለሙ የምናያቸው ወገኖች የወጡት ከሁለት ካፖርቶች ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከዶ/ር ነገደ ጎበዜ “ህገ-መንግስት ምርጫና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” ከሚል ካፖርት፤ ኢህአዴግ ደግሞ ወደ ኋላ ለወጡት የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ሰነዶች መጋቢ ከሆነው  “የህዳሴው ንቅናቄ” ካፖርት የወጣ መሆኑን ይነግረናል፡፡
እንግዲህ ከዚህ በላይ መሄድ አልቻልኩም፡፡ ለጨዋታ የሚሆን ጊዜ አጥቼ ፈገግታን የሚያጭሩ ስላቆችን፣ አሽሙሮችን፣ ምፀቶችን ሳላነሳ፤ አቶ መለስ ለአቶ በረከት ስልክ ደውለው  “ሰውዬው” በማለት ያወጉትን ነገርም ሳላወሳ ፅሁፌን ጨረስኩ፡፡ ኢህአዴግ በ97 ምርጫ ከጊዜ ናዳ ለማምለጥ ያደረገው ሩጫ እንዳልተሳካት፤ እኔም  “ከገፅ” ናዳ ለማምለጥ ያደረግኩት ሩጫ አልተሳካም፡፡ በዚሁ ይብቃኝ፡፡ ግን ምን ያህሉ የኢህአዴግ አባል የምርጫውን ሂደት በዚህ ደረጃ ይረዳው ይሆን?

 

 

 

Read 2177 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 09:53