Saturday, 12 November 2011 07:31

ከማህበራዊ ድረ - ገጾች በስተጀርባ

Written by  ከበፍቃዱ አባይ
Rate this item
(0 votes)

ዘመን በዘመን ላይ በተሻገረ ቁጥር ቴክኖሎጂው እልፍ እየሆነ መጓዝን ልማድ አድርጐታል፡ የኢንዱስትሪ አብዮት (Industrial revolution) መከሰትን ተከትሎ በሒደት እየዘመነ ያለው ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ ትንሽ መንደርነት ለመለወጥ አብቅቶታል፡ከዘመን ወደ ዘመን የሰው ልጅ በሚኖረው ሰንሰለታዊ ቅብብሎሽ ውስጥ ጥቂቶች በሚኖራቸው ሚና 7 ቢሊዮንን ያስከነዳው የአለም ህዝብ ሕይወቱን ቀላልና ብሩህ ለማድረግ ችሏል፡፡ ጥቂቶች ተደስተው ብዙሐን በሚሳቀቁባት ዓለም፣ የዚያኑ ያህል ጥቂቶች ለብዙዎቻችን ብርሃንና ተስፋ መሆናቸውም የሕይወታችንን ጉራማይሌነት ያመለክታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎችም (Social medias) የሰው ልጆችን ህይወት ቀላልና ሳቢነትን የተላበሰ በማድረግ በኩል የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአራቱም ማዕዘናት የሚፈሱ መረጃዎችን በእኩልነት መቃመስ እንችል ዘንድ በረከታቸውን አቋድሰውናል፡፡ ከቀደምቱ የጋዜጣ ህትመት እስከ ዘመነኛው ማህበራዊ ሚዲያዎች ድረስ በዘለቀው የመረጃ ቴክኖሎጂ ርቀትም የየዘመናት ጥዕምናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበልፀጋቸውን ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ከዘመን አመጣሽ ትሩፋቶች መሐከልም ማህበራዊ ድህረ - ገጾች አስደናቂ ማሳያ ናቸው፡፡ 
ቴክኖሎጂው ከባለገመድ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መዝለቁን ተከትሎ ይበልጥ እየተስፋፋና ተወዳጅ ለመሆን የቻለው የኢንተርኔት አብዮት ነው፡፡ የዚህን አብዮት መፈንዳት ተከትሎ ቀስ በቀስ እየተፈለገ የመጣው የማህበራዊ ድህረ - ገጾች ጥቅምና ድርሻ አሌ ልንለው የማንችለው አስተዋጽኦ እያበረከተልን ስለመምጣቱ ብዙ ተብሏል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያው (የማህበራዊ ድረ - ገጽ) ለአጠቃቀም ምቹ፤ ቀላል ወጪን የሚጠይቅ መሆኑ፤ ፈጣንና በአንድ ጊዜ ብዙ ምርጫዎችን የሚሰጠን በመሆኑ ተመራጭ የእለት ተዕለት የእንቅስቃሴያችን መሰረት ለመሆን ችሏል፡ ታድያ የማህበራዊ ድህረ- ገጾች መስፋፋታቸው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች በሻገር እየታዩ ያሉ ጣጣዎችንም መመተሩ ፋይዳ ሳይኖረው አይቀርም፡በተለይም የማህበራዊ ድረ - ገጾች በሀገራችን ካለው አነስተኛ ተደራሽነት አንጻር ብቻም ሳይሆን ባለን መጠን ያህል ያስተዋልናቸውን የጀርባ ገጾች መጥቀሱና የጐንዮሽ ጉዳቶቻቸው (side effects) ላይ ሀሳብ ማዋጣቱ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጥቅሙ ዓለም ዓቀፋዊ (Universal) እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ የጋራ እውነቶቻችንንም ከገጾቹ ጀርባ አሰምርባቸዋለሁ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት የሚሆኑ ማጣቀሻዎችን ሳፈላልግ ያገኘሁት መረጃ በመላው ዓለም እንደ ትዊተር (twitter) እና ፌስ ቡክ (face book) ያሉ ማህበራዊ ድረ ገጾችን የሚጠቀሙ ከ1.1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች መኖራቸውን ያትታል፡፡ ይህ የቁጥር ዕድገት አሁን ካለበት ደረጃ በፍጥነት የማደግና የመሻሻሉ ሁኔታም ይበልጥ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ አዲሱ የኢትዮ - ቴሌኮም ባወጣው መረጃ፣ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን 500.000 የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይጠቅሳል፡፡ በእርግጥ ሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ ላላት ሀገር ከላይ ተጠቀሰው ቁጥር ፌዝ ቢመስልም አንድ ቀን ተስፋችን እውን እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ከማህበራዊ ድህረ - ገጾች ጀርባችንን የምናነበውም በእነዚህ ጥቂት ጅማሮዎቻችን ታጅበን ነው፡፡
ሱሰኝነት (substance less Addiction)
“የ12 ዓመቷ ታዳጊ በትምህርት ቤት መምህሯ አማካይነት የተሰጣት የቤት ስራ ከብዷታል፡፡ በእርሷ አቅም እንደማትወጣው የተረዳቸውን የቤት ስራ ወላጅ እናቷ ኒውተን (Newton) ትረዳት ዘንድ አስባ ከመኝታ ክፍሏ እናቷ ወዳለችበት ክፍል አመራች፡፡ እናቷ ግን በማህበራዊ ድረ - ገጾች ምልልስ ተመስጣ ስለነበር ልታስተውላትና ልትረዳት አልቻለችም፡፡ በሁኔታው የተበሳጨው ታዳጊ መኝታ ክፍሏ ገብቷ ለእናቷ የቤት ስራዋን ትረዳት ዘንድ መልዕክት (e-mail) ላከችላት፡፡ እናት አሁንም መልዕክቷን አንብባ እናታዊ ግዴታዋን ልትወጣ አልቻለችም፡፡ ምክንያቱም በቀን ለበርካታ ሰዓታት የምትጠቀመው የማህበራዊ ድረ ገጽ ሱሰኝነት የልጇን ጥያቄ ትመልስ ዘንድ እድል አልሰጣትም፡፡ ይላል ሲ.ኤን.ኤን በአፕሪል 23/2009 የማህበራዊ ድረ - ገጾችን ሱሰኝነት አመስልክቶ ባተተው ዘገባው፡፡
ቀደም ባሉት አመታት የሰው ልጅ እርስ በእርስ ግንኙነቱን (social interaction) ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደነበር የጋራ ግንዛቤ አለ፡፡ ይህ የማህበራዊ ግንኙነት ቀስ በቀስ እየሸረሸረና ሰዎች ወደ ግለኝነት (individualism) እየተሳቡ ስለመምጣታቸውም ይነገራል፡፡ በስልጣኔ ከፍ ወዳለው ማማ በዘለቁት ሀገራት እንደ ትልቅ ችግር እየታየ ያለው የግለኝነት መስፋፋትም መንግስታትን ጭምር ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ በዚህ መሰሉ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጐቻቸውም የብቸኝነቱ መንገድ አልገፋ ሲላቸው ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርሱ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጭምር እያስገደዳቸው ስለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ መሰሉ የብቸኝነት ችግር እንደ መንስኤ ከሚታዩት ጠንቆች መሀከልም በማህበራዊ ገጾች ሱስ መጠመድ (Internet Addiction) ተጠቃሽ ነው፡፡ ሰዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች አማካይነት በሚኖራቸው ግንኙነት ማህበራዊ ትስስራቸውን ያቀናጁና ያጠበቁ ቢመስላቸውም የሰው ልጅ በአካል ተገናኝቶ እንደሚኖረው ማህበራዊ ትስስሮች አይነት እውነተኛ ባለመሆኑ እውነተኛ ያልሆነ (artificial) ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ይህ ስሜት አልባ ግንኙነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ ሲመጣ ትርፍና ጉዳቱን ለማመጣጠንም ያስቸግራል፡፡ በማህበራዊ ግንኙነቱ ውስጥ ማህበራዊ ድህረ ገጾችን ብቻ መምረጡም ራስን ከእውነተኛው ዓለም መለየትን ወይም መገንጠል (social alienation) ጭምር ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች በየዕለቱ በዚህ መሰሉ የግንኙነት ሱስ ሲጠመዱ ለስራ፤ ለትምህርት፤ ለማህበራዊ ግንኙነትና ለሌሎች አስፈላጊ ሰውኛ ግብአቶች ተገቢውን ጊዜ መስጠት ያቅታቸዋል፡በጀርመን በ700 ጀርመናውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ እያንዳንዱ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በየሳምንቱ ለ35 ሰዓት ጊዜውን ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደሚያጠፋ ተረጋግጧል፡፡
ከቀጥታውና ሰውኛው የማህበራዊ መስተጋብሮች አንጻር ሰዎች ለኢንተርኔት ግንኙነቶች (Online socialization) ቅድሚያ መስጠታቸው በጤናቸው፤ በምርታማነታቸውና ሌሎች መደበኛ ጠባዮቻቸው ላይ ጭምር ችግሮችን አስከትሏል፡፡ ይህን ዓለማቀፋዊ ችግር ወደ ሀገርኛው አውድ (context) ስንሰበውም የሚሰጠን ተጨባጭ ስዕል አለ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በእነዚህ ድረ - ገጾች ለመጠቀም ዕድልን ባገኙቱ ዘመነኞች ዘንድም የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በተለይም እነዚህ አይነት ግንኙነቶች ካላቸው ሱስ የማስያዝ ባህሪ አንጻር ብዙዎቻችን ሥራችንን መከወን ሲያቅተን ይስተዋላል፡፡ የስራ ጊዜያችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም እክሎችን በራሳችን ላይ በመጋበዛችንም ስንቶቻችን በአለቆቻችን ወቀሳ ደርሶብናል፡፡ አንድ የቅርብ ወዳጄ በዚህ ዙሪያ በነበረን ወዳጃዊ ጨዋታ አንዳንድ ቀን እስከ ግማሽ ቀን ለሚሆን ጊዜ በፌስ ቡክ ላይ ብቻ ሊያሳልፍ እንደሚችል አጫውቶኛል፡፡ በአንዳንድ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ይህ መሰሉ የማህበራዊ ድረ - ገጾች ሱሰኝነት በመጠንከሩና ስራ በመስተጓጐሉ ምክንያት የጊዜ ገደብ ለማውጣት የተገደዱ አለፍ ሲልም እነዚህን መሰል አገልግሎቶች ሰራተኞቻቸው እንዳያገኙ እስከማገድ ድረስ የዘለቁ ተቋማት እንዳሉም ይነገራል፡፡ ሱስን የመጠጥና የሲጋራ ብቻ ያደረገው ማን ነው፡፡
በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ ግንኙነት መጠንከር
ይህ መሰሉ የሰዎች የዕለት ተዕለት ግንኙነት ሌላው ጐጂ ጐን ዕውቀት አልባ መስተጋብርን (interaction) ማዳበሩ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ በእርግጥ ቴክኖሎጂው ንባብን ለማበረታት ቀላል የማይባል ሚና እንዳለው እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በርካታ ታላላቅ አብያተ - መጻሕፍት የመጻሕፍት ክምችቶቻቸውን ወደ ዲጂታል (digital) መጽሐፍት እየለወጡ ይገኛሉ፡፡ ድረ - ገጾቹ ውይይትን ቢያበረታቱም ውይይቶቹ ግን በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡ሰዎች በተለዋወጡአቸው ቁም ነገሮች ዙሪያ በቂ ንባብን እንዲያደርጉ ከማገዝ ይልቅ በግምትና በልምድ የተገኙ ተመክሮዎችን ብቻ ያዘወትሩ ዘንድ ያስገድዳሉ የሚሉ አልጠፉም፡፡ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በድረ - ገጾቹ ላይ ለማጥፋት ስለሚገደዱ ለንባብ የሚሆን በቂ ጊዜ አይኖራቸውም፡ በእኛ ሀገር በኤፍ ኤም ሬድዮኖቻችን ላይ በሚነሱ ውይይቶች ዙሪያ በሁሉም ርዕሶች ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡቱ ደፋሮች እንደማለት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ አጋጣሚ የተዋወቅኋቸው የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ በመስሪያ ቤታቸው በሚገኝ ቤተ-መጻሕፍት ሊነበቡ የሚገባቸው መጻሕፍት ቢኖሩም በማህበራዊ ድረ - ገጾች ምክንያት ሰራተኞቻቸው አንብበዋቸው እንደማያውቁና በዚህም ብዙውን ጊዜ ከሰራተኞቻቸው ጋር እንደሚጋጩ አጫውተውኛል፡፡
እነዚህና ሌሎች ተጠቃሽ የማህበራዊ ድረ - ገጾችን የሚመለከቱ ትዝብቶቻችንን ዛሬ ላይ ሆነን ለማረም ደፈር ማለት ያስፈልገናል፡፡ እንደ ቀልድ አሁን የምንተዋቸው ህፀጾች ምነው በእንቁላሉ ጊዜ…እንዳለው ታዳጊ ከመሆን ያድነናል፡፡ ሌሎቻችሁም ሐሳብ አዋጡና በአዲስ አድማስ ላይ እንወያይ፡፡

 

Read 2016 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:37