Print this page
Monday, 07 November 2011 12:54

አብዮት እያሳደዳቸው “መዝናናት መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!” - ጓድ ሌኒን

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(1 Vote)

በጃንሆይ ሀይለ ስላሴ ዘመን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በምንማርበት ጊዜ የታሪክ አስተማሪያችን Mr Soloduhin የሚባል ሩስኪ ነበር፡፡ ረዥም ዘንካታ ነው፡፡ መነፅር ያደርጋል፣ አይኑ ሰማያዊ፡፡ ከሌሎቹ ፕሮፌሰሮች ለየት ያለ ሰው፡፡
Test ወይም ፈተና ሲኖር፣ ሌሎቹ A, B+, C የሚል ማርክ ይሰጡናል፣ በቃ፡፡ ሚስተር ሶሎዱሂን ግን ውጤታችንን የሚነግረን ዘናጭ በሆነ style ነበር፡፡ ክፍል ከኛ ቀድሞ ገብቶ ውጤታችንን ጥቁር ሰሌዳው ላይ እንዲህ ያሳውቀናል፡፡
History test results
Super geniuses – 5 students
Geniuses – 13 students
Pass – The rest of the students
Failed የሚባል ተማሪ ሚስተር ሶሎዱሂን ክፍል ውስጥ ተመዝግቦ አያውቅም፡፡

የመጀመርያው አመት የመጨረሻው ፈተና ሰባት ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ የምችላቸውን ሁለት ጥያቄዎች ብቻ መለስኩ፡፡ አምስቱ አቃተኝ፡፡ ወረቀቴን አስረከብኩ፡፡ ውጤቱ ሲሰጠን ፈተና ወረቀቴ ላይ በቀይ Genius ተፅፏል፡፡ ሰውየው ተሳስስቷል ብዬ ቢሮው ሄድኩ፡፡ በfounten-pen (እንደ ሀኪም መርፌ ቀለም የሚመጥጥ) ሲፅፍ ነበር፣ አቋርጦ ቁጭ በል አለኝ፡፡
እና ፋውንተን-ፔኑን ሊከድን ሲል - ሳተው! ሰአሊ ለነ ቅድስት! ለካ ድንቅዬው የታሪክ መምህራችን አንድ አይና ኖሯል! በኋላ ደጋግሜ ሳስብበት፣ በጉርምስና አመታት በፍቅር ምክንያት በጩቤ ሲፋለም አይኑ ፈስሶ ይሆን? ወይስ በአጉል ሰአት ተራ accident (ያልታሰበ አደጋ) ደረሰበት?
ለማንኛውም “ውጤቴ Failed ሊሆን ሲገባው “ጂንየስ” ብለኸኛል” አልኩት
“አንዱን ብቻ መልሰህ ቢሆንም ኖሮ ምድብህ እዚያ “ጂኒየስ” ውስጥ ነበር”
ምንም እንዳልገባኝ ፊቴ ላይ አይቶ አስረዳኝ “የአንዱን ጥያቄ መልስ አንብቤ ታሪክ የሚባለው የእውቀት ዘርፍ ምን እንደሆነ በሚገባ የጨበጥከው መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ አራት ጥያቄ መልሰህ ቢሆን ኖሮ Super Genius ነበርክ፡፡…
…ከተማሪዎቹ አንድ ሀያ የምንሆን ከክፍል ውጪ ስናገኘው እየከበብነው ቆመን ከታሪክ ጋር የተያያዘ ወይም ጭራሹኑ የማይገናኝ ጥያቄ እየጠየቅነው፣ ስለ ህይወት፣ ስለ ስነ-ፅሁፍ (Literature) በተለይም ስለ ራሽያ ስነ-ፅሁፍ፣ እጅግ በጣም በተለይም ስለ ባለቅኔው Alexander Pushkin ሲያወራልን አፋችንን ከፍተን እናዳምጠው ነበር፡፡ ቲፎዞዎቹ ነበርን ለማለት ይቻላል፡፡
እጅጉን ሀገር ወዳድ ነው፡፡ ራሽያን የሚያክል አገርና ህዝብ የለም፡፡
“Gentlemen” ይለናል Compared to Pushkin, Shakespeare is a babbling baby (ከፑሽኪን ጋር ሲነፃፀር ሼክስፒር የሚንተባተብ ህፃን ነው ለማለት) በብዛት የሚጠቅሰው ግን ሼክስፒርን ነው፡፡
ሀገር ወዳድ ብቻም አይደለም፡፡ ሚስተር ሶሎዱሂን የድሮ ሰው ነው፡፡ በሱ እይታ የሆነ እንደሆነ፣ ሴቶች የአእምሮ ስራ ችሎታቸው ከኛ ከወንዶች በጣም ያነሰ ነው፡፡ አንድ ቀን ከበነው ስናወጋ አንድ መቶ ሜትር በሚሆን ርቀት የክፍላችንን ልጅ ፍኖትን ስታልፍ አየናት፡፡ እና ሚስተር ሶሎዱሂን “I am sorry, gentlemen” አለን “ሴት ብትሆንም ያቺ ፍኖት Super genius መሆንዋን እንድናውቅላት ሀቁ ያስገድደናል” አለን፡፡
ከፕሮፌሰሩ ወደ ግለ-ሰቡ ሶሎዱሂን ስንመጣ፣ ስለ አብዮት መናገር ይኖርብኛል፡፡ የእነ ጓድ ሌኒን አብዮት ፈነዳ፡፡ ሚስተር ሶሎዱሂን ባለ ፀጋ ስለሆነ፣ ማለትም እንደ አድሀሪ ፀረ አብዮተኛ ስለሚቆጠር፣ ሳልታሰር ወይም ሳልገደል መሸሽ ይሻለኛል ብሎ፣ ዘመድ ወዳጆቹን ተሰናብቶ፣ የራሽያ ጐረቤት ወደሆነችው ወደ ቡልጋርያ ገሰገሰ፡፡ ህዝቡ በዘርና በሀይማኖት፤ በባህል ከሩስኪዎቹ ጋር አንድ ሆኖ፣ በቋንቋ ይለያል (የጉርብትናቸውን ያህል ራሽያንኛ እና ቡልጋርያንኛ እህትማማች ቋንቋዎች ናቸው)
አብዮቱ ያባረረውን ያህል የቡልጋርያ አድባር ተቀበለችው፡፡ ባጋጣሚ ከአንዲት ቡልጋርያዊት ጋር ተዋወቀ፡፡ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተግባቡ፡፡
አንድ ቀን “እዚሁ መኖሬ ስለሆነ ቋንቋችሁን የሚያስተምረኝ ሰው አፋልጊኝ” አላት
“ጊዜህን አታጥፋ፡፡ ቡልጋርያንኛ’ኮ ከዚህ አገር ውጪ አይነገርም፡፡ አንተ ደሞ እዚህ እምትኖረው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው”
“ምክንያቱስ?”
“ምክንያቱም ቡልጋርያ በቂ አቅም ስለሌላት ራሽያ በምትሄድበት መንገድ መሄድ ይኖርባታል፡፡ እና የሌኒን አብዮት ከአንድ ወይ ከሁለት አመት በኋላ በግል የሚያሳድድህ እስኪመስልህ ወደዚህ ተጋብቶ ይፈነዳል፡፡”
ሴት ብትሆንም እንደ ክፍላችን ልጀ እንደ ፍኖት Super Genius የሆነች ባለ ዲግሪ ሊቅ ኖራለች ሴትዮዋ፡፡ ምክንያቱም የቀጠረችው ይመስል ከራሽያ ተሻገረና ፈነዳ፡፡
እስዋም እሱም እኩል ፀረ አብዮተኛ አድሀሪዎች ስለሆኑ፣ እጣ ፈንታቸው ከመግባባታቸው ጋር ተቀናጅቶ እስከ ዘለቄታው አቆራኛቸው፡፡
ሚስተር እና ሚስዝ ሶሎዱሂን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዱ፡፡ እንግዳ ተቀባይዋ ቅድስታገር መልካም ፈቃድዋ ሆኖ ሚስተር ሶሎዱሂን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የታሪክ መምህርነት ስራ ያዘ…
…ለኛ ለቲፎዞዎቹ ሚስተር ሶሎዱሂን ከሌሎቹ መምህራን የሚልቅበት ምክንያት ሰአሊ መሆኑ ነበር፡፡ በቃላት የሚነግረንን በስእል ይገልፅልናል (“አንድ ሺ ቃላት ከመናገር አንድ ማሳየት ይበልጣል ይላሉ የጥንት ቻይናዎች” ብሎኝ ያውቃል) ለምሳሌ “ፊደልን ምን አይነት ሰው የፈጠረው ይመስላችኋል?” ጠየቀን
“የጥንት ዘመን ደብተራ ሳይሆን አይቀርም” አልነው
አይደለም (አለን መምህራችን) አንዱ Super genius ነጋዴ ነው፡፡ ለምሳሌ የአምስት ቀን ጉዞ ርቆ የሚሰራ ሸሪክ አለው፡፡ እሱ እሚነግድበት ገበያ ግመል በጣም ተወደደ እንበል፡፡ ወደ ሸሪኩ መልእክት በጠፍጣፋ ድንጋይ ወይም በከብት የትከሻ አጥንት ላይ ይፅፋል፡፡ በምን መፃፍያ? ሲነድ ቆይቶ በጠፋ እንጨት ጥቁር ጫፍ የግመል ስእል እንደዚህ ይስላል (ሶሎዱሂን ሰሌዳው ላይ ምን የመሰለ ግመል ፈጥሮ ያሳየናል) ቁጥራቸው ሰባት ስለሆነ፣ አራት መስመር ከላይ ወደታች፣ አንድ መስመር አራቱን ከጐን ወደ ጐን ይሰርዛቸዋል፡፡ አምስት አልሆነም? ከጐኑ ሁለት መስመር ከላይ ወደታች፡፡ ሰባት ግመል ይላክለታል፡፡
በርካታ ትውልዶች ካለፉ በኋላ፣ አንድ ሌላ super genius ነጋዴ ይከሰታል፡፡ ግመልን ለመግለፅ ሻኛው በቂ ስለሆነ፣ እግር የሌለው ግመል በመላክ ስእሉን አቃለለው
ሌሎች ብዙ ትውልዶች አለፉ፡፡ ተረኛው super genius ነጋዴ ግመሉን ካንገት በላይ ብቻ እየሳሉ መላክን አመጣ፡፡
ተረኞች ብዙ ትውልዶች በተራቸው አለፉ፡፡ አንድ super genius of the highest order [የሱፐር ጂንየሶች ቁንጮ] ተከሰተ፡፡ እና ከነጭራሹ የግመል ስእልን እርግፍ አርጐ ጥሎ፣ በምትኩ የድምፅ ስእልን ፈጠረ፣ ይኸውና ገ(ገመል በአረብኛ)…
…ሶሎዱሂን ራሱ እንደ መምህር super genius ነበር፡፡ ለምሳሌ Ancient History (የጥንት ዘመናት ታሪክ) ሲያስተምረን “Gentlemen” ይለናል (ወይዘሪት ፍኖትና ሌሎች ሴቶች አብረውን እየተማሩ ነው፡፡ እሱ ግን በስነ-አእምሮ የጥንት ወንድ ስለሆነ፣ Ladies ለማለት ክብሩና ህሊናው አይፈቅድም) ከስልጣኔዎች መጀመርያው የፈርኦናዊት ግብፅ ነው ይባላል፡፡ እኔ ግን የቻይና ስልጣኔ ይቀድማል ባይ ነኝ፡፡ The Great Wall of China አስደናቂነቱ ከፒራሚዶቹ ይበልጣል ወይስ ያንሳል ብላችሁ ብትጠይቁኝ መልስ አይኖረኝም፡፡
ለማንኛውም ወደ ቻይና እንሂድና፣ ዘመናት ነግተው ገና በሺዎች መቆጠር ከመጀመራቸው በፊት The Son of Heaven (የሰማያት ልጅ) የነገስታቱ መጠርያ ማእረግ በነበረበት ጊዜ ንጉሱ super genius plus የሆነ አርክቴክት ቤተ መንግስት ገነባለት፡፡ ባለፉት ዘመናት ታይቶ የማይታወቅ፣ በሚመጡት ዘመናትም ይታያል ተብሎ የማይታሰብ ነው ተባለ፡፡
አንዱ super genius plus ሰአሊ ደግሞ ይህ እንቁ ስራ ስላስደነቀውና ስለመሰጠው ቀለሞቹን ቀመመ፡፡ ስእሉ ተመልካቹን ሁሉ አስደመመ፡፡ ከቤተ መንግስቱ እና ከስእሉ የቱ የየትኛው ግልባጭ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡
የሰማያት ልጅ እንደ እሳተ ገሞራ ተቆጣ፡፡ “ቤተ መንግስቴን እነዚህ ምስክሮች እያዩ ሰርቀኸኛል፡፡ ሞት ይገባሀል” አለና በገዛ እጁ የሰአሊውን አንገት በሰይፍ ቀላው! Super genius መሆን አንዳንድ ጊዜ አደገኛ ነው ይኸውላችሁ፡፡
ንጉሱ ይህም አልበቃውም፡፡ አርኪቴክቱን “አንተ ደ’ሞ ሌላ ይህን ያህል የሚያስደምም ህንፃ እንዳትገነባ ተፈርዶብሀል” ብሎ አይኑን አስፈሰሰው፡፡
ብዙ ብዙ ምእታት አመታት አለፉ (ይቀጥላል ሶሎዱሂን) በሰሜን ህንድ አግራ በሚባል ከተማ ንጉሰ ነገስት Shah Jahan ከሚስቶቹም ከእቁባቶቹም አብልጦ የሚያፈቅራት Mumtaz አስራ አራተኛ ልጅ ስትወልድለት ሞተች፡፡ የሱን ሀዘንና የሷን ውበት የሚገልፅ መስጊድ አሳነፀ፡፡ እዚያ ተቀበረች፡፡ ምናልባት ያንን ያህል የሚያምር ህንፃ ተሰርቶ አያውቅም ይባላል፡፡ ጥንታዊው አለም ከተስማማባቸው Seven Wonders of the World አንዱ ታጅ ማሀል ይባላል (Athens ውስጥ የሚገኘው Acropolis ቤተ መቅደስ ውበቱ ከታጅ ማሀል ሳይበልጥ አይቀርም የሚሉም አሉ)
ታጅ ማሀል በፈረንጅ በ1632 ተጀምሮ በ1653 ተጠናቀቀ (The Great Pyramid of Giza የሚባለውን ለመገንባት አራት አመት ብቻ የበለጠ ጊዜ ወሰደ ማለት ነው)
ታጅ ማሀልን ለመገንባት በሺዎች የሚቆጠሩ ጠበብትና የእጅ ስራ ባለሙያዎች ተሰማርተው ነበር፡፡ ነጩን እብነ በረድና ሌላ ሌላውን አስፈላጊ ቁሳቁስ ለማመላለስ አንድ ሺ ዝሆን ተመድቦ ነበር፡፡
ታጅ ማሀል “የቤተ መንግስታት ቁንጮ” ማለት ነው፡፡
Gentlemen (ይለናል ሶሎዱሂን) ከዚህ ቀጥዬ የምነግራችሁ እውነት ይሁን ወይስ ፈጠራ በእርግጥ ለማወቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ታጅ ማሀልን የፈጠረው አርቲስት የጥንታዊት ቻይና super genius አርኪቴክት የደረሰበት የአይን መፍሰስ በሱ እንዳይደገም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ወሰደ፡፡
ብዙ ይቅርታ ከለመነ በኋላ “የምናዘዘው ሀጢአት አለ፡፡ ህንፃው አልቆ ከተመረቀ በኋላ ነው ስህተቴ የታየኝ፡፡ ዝናብ ሲወርድ ወደ ህንፃው ውስጥ ውሀ ቀስ ብሎ ይወርድና ነጩ እብነ በረድ ላይ ቆሻሻ አይኑን ስለምትቆረቁረው የህንፃው ውበት አይታየውም፡፡ ሰውነታችን ላይ ትንሽ ቁስል ካለ ትኩረታችንን ሳንወድ እንደሚስበው አይነት፡፡”
“እና ምን ይሻላል?”
“ውሀው ወደ ውስጥ እንዳይፈስ ወጥቼ ዝናብ እየተደበደብኩ ውሀውን በእጄ ወደ ውጭ እንዲፈስ እመራዋለሁ”
“ብልሀቱን ለአንዱ ረዳትህ አሳየው”
“አይገባውማ”
“አንተ ስትሞትስ?”
“ከዚያ በፊት ራሱን የቻለ ብልሀት ይመጣልኝ ይሆናል”
ንጉሱ ሳይወድ ተስማማ፡፡ ክረምቶቹ እየመጡ ሲሄዱ፣ ከእለታት አንድ ቀን አርኪቴክቱ ሞተ፡፡
ክረምት መጣ፡፡ ንጉሱ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ያ የተፈራው ውሀ አልገባም፡፡ ለከርሞም አልገባም፡፡ ለካ ያ ገብቶ አይን ይስባል የተባለው ውሀ ህይወቱን ለማትረፍ ሲል የፈጠረው ውሸት ኖሯል! [እኛ ስንስቅ ሶሎዱሂን ፈገግ እንኳ አላለም]…
…አብዮቱ ይህችን ቅድስት አገርም ደፍሮ ሊፈነዳ ሲል፣ ውድ መምህራችን የሚያውቃቸው ጥቂት ምልክቶች ገና ብቅ ማለት ሲጀምሩ፣ Mister and Misses Soloduhin ወደ Australia በረሩ፡፡
ሁልጊዜም በባእድ አገር ባይተዋር ሰው ሆኖ የኖረውን ውድ መምህራችንን ለማሰናበት እድል አላጋጠመንም፡፡

የኔታ ገብረ መድህን
መምህር ሶሎዱሂንን የማደንቀውን ያህል፣ የኔታ ገብረ መድህንን እወዳቸዋለሁ፡፡ በአስራ ሶስት አመቴ የግእዝ አስተማሪያችን ነበሩ፡፡ ገና በመተዋወቅያው የትምህርት ሰአት ነበር የዋህና ደግ ሰው መሆናቸውን ያወቅነው፡፡
የኔታ ገብረ መድህን አጭር ቀጭን ናቸው፣ ፂም የላቸውም እንዳንል ግን ፊታቸው ለስሙ ያህል ጥቂት ፀጉር አብቅሏል፡፡ ሲናገሩ እንደ ህንዶቹ ጭንቅላታቸውን ከጐን ወደ ጐን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ሁልጊዜ የሚለብሱት ያንኑ ቡኒ ካኪ ኮትና ሱሬ ነው፣ ግን ሁልጊዜ ንፁህ፡፡
“ትምህርታችንን በግስ እርባታ እንጀምራለን፡፡ ነፍሀ ማለት ነፈሰ ነው፡፡ እንግዲህ በአማርኛ ‘ነፈሰ፣ ይነፍሳል፣ ይነፍስ ዘንድ፣ ይንፈስ’ ብለን እንደምናረባ፣ በግእዝ ‘ነፍሀ፣ ይነፍህ፣ ይንፋህ፣ ይንፋህ እንላለን’”
ሁለት ጊዜ ‘ይንፋህ’ ሲሉ፣ እኛ በአማርኛ ሰማናቸውና በሳቅ ፈነዳን!
እሳቸው ግን ሳቃችንን የሰሙት አይመስሉም፡፡ አልተቆጡንም፣ ፈገግም አላሉም፡፡ ሰሌዳው ላይ እየፃፉ እርባታውን በሌላ ግስ ሲያሳዩን “በርሀ ማለት በራ ነው፡፡ ስናረባው ‘በርሀ፣ ይበርህ፣ ይብራህ ይብራህ ይሆናል፡፡” እያሉ ቀጠሉ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ሊያስተምሩን ሰሌዳው ላይ መፃፍ ገና ከመጀመራቸው፡፡ አንዱ “የኔታ፣ ‘ነፍሀ’ አልገባኝም” አላቸው
አንገታቸውን እያቅለሰለሱ “ቀላል ነው ምን ያቅታል?” አሉት “ነፍሀ፣ ይነፍህ፣ ይንፋህ፣ ይንፋህ” ሲሉ
እኛ በሳቅ ፈነዳን!
“አሀ! ይንፋህን ነው የፈለግከው? በል ይንፋህ!” አሉትና፣ እኛ የባሰውን ጮኸን ስንስቅ፣ አልተቆጡንምም፣ ፈገግም አላሉም፡፡
እሳቸው ትምህርታቸውን ማናችንም ብንከተል፣ ማናችንም ችላ ብንለው የሚያስተውሉ አይመስሉም፡አንዳንድ ቀን እርስ በርሳችን እንኳ ለመደማመጥ እስከያቅተን ድረስ ሁካታውን ስናበዛው፣ የኔታ ገብረ መድህን ወደኛ ዞረው፣ አንገታቸውን እያቅለሰለሱ፣ በዚያው ረጋ ባለ ሰላማዊ ድምፃቸው፣
“ኢትዮጵያ እናንተን አፈራች?! ዝንጀሮዎች!” ብለውን ወደ ሰሌዳቸው ይመለሳሉ፡፡
ጩኸት ጫጫታው ከዚያም ከባሰ ግን፣ ጠመኔውን ያስቀምጣሉ፡፡ ወደኛ ሳያዩ “በዚህ ጩኸት ማስተማር አልችልም” ብለውን ይወጣሉ፡፡
ሁለት ሶስቱ ተማሪዎች ተከትለዋቸው ወጥተው “በጣም ይቅርታ፣ የኔታ! ሁለተኛ አንንጫጫም፡፡ ይኸው ክፍሉ ፀጥ ብሏል” ሲሉዋቸው ወይም አምነውን ወይም ይቅር ብለውን ተመልሰው ይገባሉ፡፡
እኛን ግን ተቆጥተውን አያውቁም፡፡ ኧረ ማናችንንም ገላምጠው አያውቁ! ፈተና መጣ፡፡ የኔታ ገብረመድህን የጥያቄ ወረቀቶቹን አደሉና፣ እንዳንኮራረጅ በዝግታ እየተዘዋወሩ ይጠብቃሉ (ደምብ ስለሆነ)፡፡ የፈተና ውጤት አማርኛ፣ እንግሊዝኛ 200 ማርክ አለው፡፡ ሂሳብ፣ ሳይንስ፣ ታሪክ 150 አለው፡፡ ሌሎቹ የትምህርት አይነቶች 150፡፡ ግእዝ ግን 25 ማርክ ብቻ ያለው ስለሆነ፣ ባጠቃላዩ የክፍል ማለፍ ጉዳይ ያን ያህልም አያሳስበንም፡፡
ለማንኛውም አንዱ የሚያውቀውን መልስ ሁሉ ከፃፈ በኋላ፣ እጁን አውጥቶ የኔታን ጠራቸው፡፡ የአንዱን ጥያቄ መልስ በጣቱ እያሳያቸው፣ በሹክሹክታ… “ይሄ ልክ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
እሳቸውም “እዚህ ጋ አንድ ቃል ዘልለሀል” አሉት፡፡
የኔታ ገብረመድህን ይህን ያህል የዋህ ነበሩ፡፡ በእድሜ ከበሰልኩ በኋላ አንድ የአረብኛ አባባል ሰማሁ “ለንፁህ ልብ ሰው ሁሉ ንፁህ ነው” ስለ የኔታ ገብረመድህን የነገረኝ መሰለኝ፡፡
ቴዎድሮስ ፅጌ የሚባል የክፍላችን ልጅ “አታምነኝም” አለኝ “የኔታ ገብረመድህን በዮሀንስ ቤተክርስትያን ቁልቁለቱን ሲሄዱ አየኋቸው፡፡ violin ይዘዋል!”
ቫየሊን መጫወቱ እና እንደዚያ ሰላማዊ ሰው መሆናቸው ፈጣሪ ፀጋውን አብዝቶ የለገሳቸው ቢሆኑ ነው እላለሁ፡፡ ግን ትሁት ሰው ስለሆኑ፣ በሆነ አጋጣሚ ለባለ ቫዮሊን ሰው ተልከው ቢሆንስ?
ከሰው ጋር ኑር ቢሉኝና ምርጫዬ በተአምር ሊሳካልኝ ቢችል፣ ከየኔታ ገብረመድህን ጋር እኖራለሁ፡፡ እና ቫዮሊናቸው እንደ ጠባያቸው ሰላም ይሰጠኛል፡፡
ምርቃት
አንድ አምስት አዛውንት ዘና ብለው ይጫወታሉ፡፡
አንዳቸው “እሳቸውማ እንደ ተራ ሰው አይደሉም” ሲሉ ነበር ጆሮዬን ጣል አድርጌ በፀጥታ ማዳመጥ የጀመርኩት “በግብረ ስጋ አይደለም’ኮ የተወለዱት”
“አንተ ደሞ! ታድያ በምን ሊወለዱ ኖሯል?”
“እሱ ነው’ሚገርማችሁ፡፡ የፀሎት ቅዳሴ ስነስርአት እየተካሄደ ነው፡፡ አንድ ሰው ባልታወቀ ምክንያት የግብረ-ስጋ ምኞት እንደ እሳት ስላቃጠለው ቀስ ብሎ በስውር ከኪሱ መሀረቡን አውጥቶ ዘሩን ረጨበት፡፡ ማእበሉ እንዳለፈለት ቀስ ብሎ መሀረቡን ወለሉ ላይ ጣለው፡፡”
“ከዚያስ?” አሉ እንደኔ የተመሰጡ ሰውዬ እየተቻኮሉ
“በዚያችው ደቂቃ አንዲትዋ ኰረዳ የወር አበበዋ ድንገት ሲወርድና መሀረቡ ሲወድቅ ስታየው እኩል! እፍረትዋን ለመደበቅ መሀረቡን አንስታ ብልትዋን ደፈነችው፡፡ መሀረቡ ላይ የፈሰሰው አባለ ዘር ግብረ ስጋ ሳትፈፅም፣ ባለመሀረቡ ማን እንደሆነም ሳትለይ አረገዘች”
“እውነት’ኮ ነው ጃል! ያለ ግብረ ስጋ ወለደችው”
“እሱም ሀጢአት የሌለበት ህይወት ኖረ”
ጨዋታው በዚህ አዝማምያ ሲቀጥል፣ እኔ ለራሴ “ስለ የኔታ ገብረ መድህን የሚያወሩ አይመስልም?” ብዬ እያሰብኩ፣ ጆሮዬን ወደ ሌላ ጭውውት አነጣጠርኩ፡ሌላ ስራ ያዝኩ እና ነው እንጂ ምናልባት ስኬታማ ጆሮ ጠቢ ሊወጣኝ ይችል ነበር እላለሁ፡፡

ሌላ ምርቃት
ለለውጥ ያህል ከዚህ ወግ ወጣ ያለ ሁለት ነገር ላጫውታችሁ፡፡
. Murphy’s Law Number One: You do not understand the situation. [ሁኔታው ወይም ጉዳዩ አልገባህም]
Murphy’s Law Number Two: If anything can go wrong, it will. [ሊበላሽ የሚችል ነገር ካለ መበላሸቱ አይቀርም]
Murphy’s Law Number Three: There is no such thing as Murphy’s Law. [የመርፊ ህግ የሚባል ነገር የለም]
. The Johari Window የሁላችንን የተፈጥሮ ማንነት የሚገልፅ ሲሆን፣ መስኮቱ እንደሚከተለው ስእል በአራት ይከፈላል፡፡
የተከበራችሁ አንባብያን፣ ያነበብነውን በልባችን ያሳድርልን አሜን፡፡
እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን!!

 

Read 2251 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:58