Monday, 07 November 2011 12:47

ታይታኒክ - የኒዮሊበራል መርከብ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

እንደምታስታውሱት፤ ሾፐን አወር፤ “ካትን አንብቦ ያልተረዳ ሰው ነፍስ አወቀ ማለት አይቻልም” ብሎ ነበር፡ እኔም የእርሱን ቃል ተውሼ፤ “ገና ከዘገባ ያለፈ የትረካ ቅርፅ ያላገኘውን ይህን ዘመናችንን ያልተረዳ ሰው፤ ነፍስ አወቀ ማለት አይቻልም” እያልኩ ነው፡፡ ደግሞም ታስታውሳላችሁ፤ ስፔንሰር የሚሉት ሊቅ “ካንትን አንብቤ መረዳት አቃተኝ” ስላለ፤ ይህን የሰሙ ሰዎች፤ “ስፔንሰር ፈላስፋ ለመባል ትንሽ ይቀረዋል” አሉ፡፡ “እኔም ይህን ዘመን አንብቤ መረዳት አቃተኝ” እያልኩ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የሰማችሁ ሰዎች፤ “አይ አንተ ፀሀፊ ለመባል ትንሽ ይቀርሃል” ብትሉኝ ቅር አይለኝም፡፡ ግን እዚሁ በእናንተ ፊት፤ የህፃን ልጅ ስዕል የመሰለች አንዲት ገራገር ሙከራ እንዳደርግ ፍቀዱልኝ፡፡

የዚህን ዘመን እውነተኛ መልክ በገራገሩ የሚገልጠው «Yin and Yang´ ነው፡፡ «Yin and Yang´ ወደ ቻይና ይወስደናል፡፡ እናም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ6-5 ዓመተ ዓለም ወደ ነበረችው ቻይና እንሂድ፡፡ በዚያ ዘመን ላኦትዙ (Lao Tzu) የሚሉትን የኮንፊሸስ ዘመነኛ የሆነ አንድ ሊቅ እናገኛለን፡፡ እርሱም «Tao Te Ching´ የሚል መፅሃፍ አለው፡፡ 
ምዕራባውያን ፀሐፍት፤ “ላኦትዙ የሚባል ሰው በአፈ ታሪክ እንጂ በታሪክ አይታወቅም” ይላሉ፡፡ ሆኖም በእርሱ ሥም የሚጠቀስ «Tao Te Ching´ የሚባል መጽሀፍ መኖሩን ያምናሉ፡፡
በሆነ ጊዜ፤ ላኦትዙ ቻይና አስጠላው፡ስለዚህ ዓለምን ለመዞር አስቦ ከሀገር ሊወጣ ተነሳ፡ ሲሄድ የቻይና የድንበር ጠባቂ ወታደሮች አገኙት፡፡ ወታደሮቹ በሬ እየጋለበ ሲመጣ ያዩትን ማንነት አላጡትም፡፡ እናም “አናስወጣም” አሉት፡፡ “መውጣት ከፈለግህ የምታውቀውን ጥበብ በብራና መዝግበህ ሰጥተኸን ነው፡፡ ያኔ ትወጣለህ” አሉት፡ላኦትዙ ከበሬው ወረደ፡፡ ብራና ስጡኝ አለ፡፡ ከዚያም በጥቂት ሣምንታት ውስጥ በ5ሺህ የቻይና ሆሄያት የተጠናቀረ የጥበብ መዝገብ አስረከባቸው፡፡
የ«Tao Te Ching´ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንዲህ ሲል ይጀምራል፤
በሰማይ እና በምድር ፊት አንድ ለመረዳት የሚቸግር እና ድንቅ የሆነ ነገር አለ፡፡
ብቸኛ ነው፡፡ ማህለቅት የለሽ ነው፡፡ በብቸኝነት የቆመ እና የማይለወጥ ነው፡፡ ካሻው ይደርሳል፡፡ የሚገዳደረው የለ
የምድረ ዓለም እናት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ስሙን አላውቀውም፡፡ ስለዚህ “ታኦ” ብዬ ሰየምኩት፡፡
ስሙን መጥቀስ ከፈለጋችሁ “ታላቁ” ብላችሁ ጥሩት፡፡
ላኦትዙ እንዲህ ብሎ የጀመረውን መጽሃፍ ጨረሰ፡፡ ለጠረፍ ጠባቂዎቹም አስረከበና በሬውን ጋልቦ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ነጎደ፡፡ ዛሬ ቻይና ብትሄዱ በሬ ጋልቦ የሚነጉደውን ላኦትዙ የሚያሳይ ስዕል በየቦታው ታገኛላችሁ፡፡ ቻይናውያን ይህን ሰው እንደ ታላቅ ፀሐፊ እና ነቢይ ብቻ ሳይሆን ሞት የማይነካው ዘላለማዊ ፍጡር አድርገው ያዩታል፡፡
ታዲያ ላኦትዙን በ”ፍፁም ባለመኖር” እና “በዘላለማዊነት” መካከል ባለ ሥፍራ የሚያስቀምጡት ሰዎች፤ በ6ኛው ዓመተ ዓለም ቹ በተባለ ግዛት ጁረን በተባለች ሀገር ተወለደ ይሏችኋል፡፡
Tao Te Ching ወይም “ምርጡ ጎዳና እና ኃይሉ” ወይም Classic of the way and its power በሚባለው በዚህ መጽሀፍ ከተገለፁት ሀሳቦች አንዱ «Yin and Yang´ ነው፡፡ ሁሉም ምድራዊ ነገሮች ሁለት ገጽታዎች አሏቸው፡፡ «Yin´ በአንስታይ ይወከላል፡፡ ጥቁር፣ ለስላሳ እና ገራም ነው፡፡ «Yin and Yang´ ተባዕታይ ነው፡፡ ብሩህ፣ ጠንካራ እና ግርር - ድርቅ ያለ ነው፡፡ ምድራዊ ነገሮች ሁሉ አንስታይ እና ተባዕታይ ገጽታ አላቸው፡ሁሌም በለውጥ ሂደት ውስጥ ናቸው፡፡ አንዴ «Yin ´ ይነግሳል፡፡ ሌላ ጊዜ «Yang´ ይገንናል፡፡ ላአትዙ ሲቀጥል፡-
የሰው ልጆች ለስላሳ እና ገራም ሆነው ይወለዳሉ፡ ግና ሲሞቱ ድርቅ - ግርር - ግትር ይላሉ”.
ዕፅዋት ሲበቅሉ ለስላሳ እና ለጋ ናቸው፡፡ ሲሞቱ ይጠወልጉና ይደርቃሉ”.
ስለዚህ ግትር እና ደረቅ የሞት ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ለስላሳ እና ገራም የህይወት ሐዋርያ ነው፡፡
ስለዚህ፤ ለስላሳ እና ተጣጣፊ ያልሆነ ሠራዊት ድልን አያገኝም፡፡ የማይታጠፍም ዛፍ ተሰባሪ ነው፡ ደረቅ እና ግትሩ እያነሰ፤ ለስላሳ እና ገራሙ እየጨመረ ሊሄድ ግድ ነው፡፡
ታዲያ ላኦትዙ፤ “ሁሉም ነገር አንድ ፈለግ ወይም ጎዳና አለው” ይላል፡፡ “እናም ሰዎች “ጎዳናውን መከተል፤ ለጊዜ እና ለተፅዕኖዎች መገዛት አለባቸው፡፡ ሰዎች ገራምና ለስላሳ መሆን ያለባቸው በደጉ ዘመን ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ የክፉው ዘመን መሸጋገሪያ ብልሃቶችም ናቸው” ይላል፡፡
አሁን የጀመርነው ፍልስፍና ነው፡፡ ዘመንን ለማወቅ ፍልስፍና የግድ ነው፡፡ ፍልስፍናችንም ታሪካዊ ፍልስፍና ሊባል ይችላል፡፡ እንደምታውቁት የሂሳብ ሰዎች “በሁለት ነጥቦች መካከል ያለው አጭሩ ርቀት ቀጥተኛ ጉዞ ነው” ይላሉ፡፡ ይኸ በፍልስፍና አይሰራም፡፡ በፍልስፍና፤ “ረጅም ርቀት በሁለት ነጥቦች መካከል ቀጥተኛ ጉዞ ነው፡፡” ስለዚህ ዘመኑን ለማወቅ የሚፈልግ ሰው ዙሪያ ዙሪያውን መሄድ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ቻይና ጎራ ብለናል፡፡ እንግዲህ ዞረን የአሁኑ ዘመን ቅርፅ ወደያዘበት ወደ ምድረ - አውሮፓ እናቅና፡፡
የዘመን ጉዞ
የአሁኑ ዘመን በዳርዊን መርከብ ተሳፍሮ ጉዞ ጀመረ፡፡ መርከቧ ጉዞ የጀመረችበት ዘመን ሁኔታ መለስ ብለን እንየው፡፡ የዓለምን ህዝብ ህይወት በመርከብ መስለነዋል፡፡ ይህች መርከብ በየጊዜው የተነሱ፤ እንደ ሱናሚ ያሉ የሃሳብ ማዕበሎች እየመቱ አንገላተዋታል፡፡ በድንጋጤ እና በፍርሃት እየራደች ብዙ ጊዜ “የነፍስ-የነፍስ” እያለች ጮኻለች፡
መቼም የሰውን ልጅ የታሪክ ወይም የሥልጣኔ ጉዞ ስናወራ፤ ሳንወድ በግድ፤ ግብፅን ይዞ ከሜዲትራኒያን ባህር ባሻገር ያለውን የአውሮፓ ምድር ታሪክ ማውራታችን ነው፡፡ የ «Yin and Yang´ ታሪክን ማውራታችን ነው፡፡
አራት መቶ አመታት ወደ ኋላ እንሂድ፡፡ በዚያ ጊዜ የአውሮፓን ምድር ያየ ሰው፤ የሚመለከተው የክርስትና እምነትን አጥብቀው የያዙ ምዕመናንን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የግሪክ - የሮማ ሥልጣኔ ከተረሣ ቆይቷል፡፡ ስመ ገናናው የቄሳር መንግሥት ወድቆ አፈር ትቢያ ሆኗል፡፡
አሁን ጆሮ የሚሰማውም የቄሳርን ነጋሪት አይደለም፡፡ ተሰልፎ የሚሄድ የቄሳር ሰራዊት ትጥቅ ቅጭልጭልታንም አይደለም፡፡ ጥሩር፣ የራስ ቁር፣ ጎራዴና ጀበርና የታጠቁ ወታደሮች አፈፍ - አፈፍ በሚል እርምጃ የሚፈጥሩት ድምፅ አይደለም፡፡
የሚያየው፤ በግሪክ - ሮማ የስልጣኔ ዘመን የነበሩ ውብ ህንፃዎችን እና በጎዳና የሚያስተምሩ ፈላስፎችን አይደለም፡፡ የሚሰማው፤ የቤተክርስቲያን ደወል እና ቅዳሴን፤ የባህታውያንን ስብከት ነው፡፡ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ” የሚሉ ካህናትን ድምፅ ነው፡፡ የሚያየው፤ ነጠላውን አጣፍቶ ወደ ቤተክርስቲያን የሚተም ህልቁ መሣፍርት የሌለው ምዕመንን ነው፡፡ የሚያየው፤ በአሣማ ኩስ የተበከሉ እና የቆሸሹ መንደሮችን ነው፡
ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው ስልጣኔ ቅርስ የሆኑ ህንፃዎች አልፎ-አልፎ ቢታዩም ዙሪያው ጠፍ አገር ነው፡፡ የዚያ ዘመን ሰው፤ ከመፅሐፍ ቅዱስ እና ከአሪስጣጣሊስ ኢንሳይክሎፒዲያ በቀር ሌላ የሚገልጠው መፅሐፍ አያውቅም፡፡ የዚህ ዘመን ሰው፤ ምድራዊውን ዓለም ለመመልከት የሚያስችል ስሜት እና ሃሳብም አልነበረውም፡፡ የዘመኑ ህይወት፤ በክርስትና መርከብ መሰስ እያለች ፀጥ - ደብ ባለ ውቂያኖስ ትቀዝፋለች፡፡ የመርከቧ ሸራ የተሰቀለበት ተራዳ ክርስትና ነው፡፡ የአውሮፓ ህዝብ፤ በፍካሬ-ኢየሱስ የተገለፀው “ፍፀሜተ - ዓለም መጣ” እያለ ከአንዴም ሁለቴ አቅሉን ስቶ ወደ ቤተክርስቲያን ሸሽቷል፡፡ ግን መርከቢቱን የሚያናውፅ ማዕበል ሳይፈጠር ብዙ ዘመናት አለፉ፡፡ ግና የኋላ ኋላ ማዕበል ተነሳ፡፡ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ይህ ማዕበል የመጣበትን ዘመን “ዘመነ - ኢንላይትመንት” ወይም የ”ዳግማዊ ልደት” ዘመን ይሉታል፡፡ “የጥንቱ የግሪክ - ሮማ ሥልጣኔ ዳግም ተወለደ” ሲሉ ነው፡፡ ይህን አዲሱን ዘመን “ዳግማዊ ልደት” የሚሉት እነ ቮልቴር፤ ያለፈውን ዘመን “የጨለማ ዘመን” አሉት፡ ብሩህ ዘመን መጣ ብለው ተደሰቱ፡፡
የእምነት መርከብን ያፈራረሰው ማዕበል መጀመሪያ መገላበጥ የጀመረው፤ በቀሳውስቱ በእነ አባ በርክሌይ (George Berkley) መንደር ነበር፡፡ እነ አባ ከጉያቸው የተነሳውን ማዕበል እንደ ጋኔን ጎትተው ካመጡት በኋላ ሊገስፁት አልቻሉም፡ ቄሱ እንግሊዛዊ /የኢቮሉሽን ቲዮሪ ፈጣሪ/ አባ ዳርዊን ናቸው፡፡ እርሳቸው ሲፈሩ ሲቸሩ ቆይተው “ማዕበል” ሃሳባቸውን ይፋ አደረጉት፡፡ ከዚያ ወዲህ መርከቢቱን ነክቷት የማያውቅ ወጀብ እና ዝናብ የቀላቀለ ውሽንፍር መጣ፡፡
አንድ ሰው፤ ጥሮ - ግሮ ያፈራው ሃብቱ፤ የሞቀ ትዳሩ ወይም ልጆቹ የሚቦርቁበት ለምለም መስክ ዓይኑ እያየ በድንገት ቀውጢ ሲሆን፤ መሬት እንደ ቁና ስታነፍሰው የሚፈጠርበት ዓይነት ድንጋጤ በዘመኑ ላይ ወደቀ፡፡
ገበሬው ጉብታ ላይ ሆኖ የሚጠብቃት ማሣው በተምች እና በዝንጀሮ ስትመደመድ ሲያይ የሚደርስበት ሃዘን ገጠመው፡፡ ከግራ ከቀኝ እየጎተቱ፤ የዘመናት እምነቱን ሊነጥቁት የሚታገሉ ብርቱ “ተኩላዎች” ወረሩት፡፡ የዘመኑ ህዝበ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ነገር ገጠመው፡፡
ይህን አይቶ፤ “ኤሎሄ ኤሎሄ” ማለት በያዘው የዘመኑ ምእመን ዙሪያ፤ አዲሶቹ “የኢንላይትመንት ሐዋርያት” እንደ አንበሳ አገሱበት፡፡ የ”ዘመነ አመክንዮ” (The age of reason) አጋፋሪዎች እነ ቮልቴር ተነሱ፡፡ ያ የዘመኑ ቀሳውስት በጥርጣሬ የጎሪጥ ሲያዩት የነበረው እንግሊዛዊው ሊቅ ፍራንሲስ ቤከን እሣት ለኮሰ፡፡ እርሱ የለኮሳት እሣት ድፍን አውሮፓን ታግለበልበው ገባ፡፡ እኒያ ካህናት የፈሩት እና የጠረጠሩት ነገር አልቀረም፡፡ ቢገስፁትም - ቢገዝቱትም በጓዳ ሊያስቀሩት ያልቻሉት የፍራንሲስ ቤከን ሃሳብ ብዙ ተቀባይ አገኘ፡፡ “የሰው ልጅ የሚገጥመውን ችግር ሁሉ በሳይንስና በሎጂክ ሊፈታቸው ይችላል” የሚለው የቤከን ሃሳብ በአጭር ጊዜ ሥር ሰደደ፡፡ “ሳይንስ እና ሎጂክ የሰውን ልጅ ከማያቋርጥ ፍፅምና ያደርሱታል” የሚለው ሀሳብ እና እምነት እግር ተክሎ ቆመ፡፡ ከፈረንሳዊው ሩሶ በቀር ይህን ማዕበላዊ ሃሳብ ሊጋፈጥ የሞከረ አንድ ሰው አልተገኘም፡፡
18ተኛው ክፍለ ዘመን በዕውቀት እና በአመክንዮ ላይ በእጅጉ ታመነ፡፡ ይህን እምነት የሚያጠናክሩ በርካታ ስራዎች መጡ፡፡ ኮንደርሰት (Condorcet) የተባለ ሰው በእስር ቤት ሆኖ “የሰው ልጅ የመንፈስ ዕድገት ታሪካዊ ትዕይንት” (Historical tableau of the progress of human spirit) በሚል ርዕስ የፃፈው መፅሐፍ ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ ነበር፡፡ “ዓለም ውብ የምድር ገነት ትሆናለች፡፡ የገነት መግቢያ ቁልፍ ትምህርት ነው” ተባለ፡፡ ትምህርትን ለሁሉም የማዳረስ አስፈላጊነት በየቦታው ተሰበከ፡፡ እኒያ የያዙትን ነገር በቶሎ የማይለቁት ጀርመኖች እንኳን በማዕበሉ ተወሰዱ፡፡ ትንሽ ነገር “የሚያሰክራቸው” ፈረንሳዊያንም “አበዱ፡፡” የፓሪስ አብዮተኞች፤ በጎዳና ላይ ሳብ - ረገብ በምትል ቆንጆ ሴት ለመሰሏት “የአመክንዮ አማልዕክት” ሰገዱ፡፡
ይህ በአመክንዮ አጥብቆ የመታመን ነገር፤ ስፒኖዛ በሚሉት ፈላስፋ ውስጥ ድንቅ የተባለ የጂኦሜትሪና የሎጂክ ጥበብ አፈለቀ፡፡ እናም፤ “ሙለኩሌው” (Universe) የረቂቅ ሂሳብ ስርዓት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ሙለኩሌውን፤ ከአንድ ተቀባይነት ካለው አጠቃላይ እውነታ ተነስተን “በተዋረድ” ትንታኔ (Deduction) ልንገልጸው እንችላለን አለ - ስፒኖዛ፡፡ እንግሊዛዊው ቶማስ ሆብስም፤ ሳይፈራ-ሳይቸር “እግዜር የለም” አለ፡፡ ያፈጠጠ አካላዊነት ወይም ማቴሪያሊዚም ሀሳብ አራማጅ ሆኖ ቆመ፡፡ በመጀመሪያ፤ “አቶምና ጥልቁ (Void) ብቻ ነበሩ” ብሎ አለ፡፡
በዚህ ሁኔታ ያች የሰውን ልጅ ለአምስት መቶ ዓመታት ይዛው የተጓዘችው የእምነት መርከብ፤ ከነአባ /ፈላስፎች/ ደሴት በተነሳ ማዕበል ወደቀች፡፡ እንደ ታላቋ ታይታኒክ ከ”አመክንዮ አማልዕክት” ፊት ስብርብር አለች፡፡ በፍጥነት እየቀዘፈች በምትሄደው “የአመክንዮ መርከብ” ፊት ጨርሶ ልትሰምጥ ተቃረበች፡፡ ነባሩ ቀኖና አንድ-አንድ እያለ ጠፋ፡፡ ሰማይ የፈጣሪ ዙፋን መሆኑ ቀርቶ ሰማያዊ ገዋ ሆኖ ታየ፡ መካከለኛው ዘመን በሚባለው የሰው ልጅ ታሪክ ዘመን የታነፀው ውብ የእምነት ካቴድራል ፈራረሰ፡ የረቀቀ ጥበብና ሀሴትን የሚያጎናፅፍ ኪነቱን ይዞ ሸሸ፡፡ “ዮዲት ጉዲት”ን የሆኑ የምዕራብ አውሮፓ ፈላስፎች እግዚሃርን ከመንበሩ “አወረዱት፡፡” ገነት እና ሲኦል ለስሜት ጓዝ መግለጫ የሚጠቀሱ ተራ ቃላት ሆኑ፡፡ ኢ--አማኒነት የዘመናይነት ጌጥ እና መገለጫ ሆነ፡፡ በዚህ መልክ ምድረ - አውሮፓ “ሰለጠነ፡፡”
በምድረ አውሮፓ ባሉ እልፍ አእላፋት ደብሮች የሚዜመው፤ ከእምነት እና ተስፋ ማህፀን የሚፈልቀው እና ለምዕተ ዓመታት ይወርድ የነበረው የውዳሴ - ቅዳሴ ዜማ በድንገት ፀጥ አለ፡፡ በብዙ ሚሊዮን ሰዎች ልብ እና አድባራት ያደረው ጥልቅ ክርስቲያናዊ እምነት በአመክንዮ ጨካኝ ፍርድ ተመትቶ ከመንበሩ ለቀቀ፡፡
እንዲያ የተኮነነው እምነት እና ሰማያዊ ተስፋ፤ በዙፋን ችሎት የተቀመጠችውን “አመክንዮ” መልሶ ተጠየቂ ማለቱ፤ ፍትሃ ነገስት ተገልጦ፤ የዳኝነት ችሎት ተሰይሞ “የሃይማኖትም ሆነ የአመክንዮ የእውነት ባለቤትነት ይጣራ” ቢባል የመጣ ለውጥ አልነበረም፡፡ እምነት “ሁከት ይወገድልኝ” ብትልም የሚሰማት አልተገኘም፡፡ በአጭሩ ለመናገር፤ የአመክንዮ፣ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ዘመን ሆነ፡ ሃይማኖታዊ መንግስት ተሻረ፡፡ የዓለም ፖለቲካ - ኢኮኖሚ ተቀየረ፡፡ የካፒታሊስት እና የወዛደራዊ አምባገነን ዲሞክራሲዎች ተፋለሙ፡፡ የምስራቅ እና የምዕራብ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ዓለምን በሁለት ጎራ አሰልፈው ተዋጉ፡፡ በቅርቡ የምሥራቁ ኮሙኒስታዊ ጎራ በምዕራቡ ካፒታሊስታዊ ኃይል ድል ተነሳ፡፡ ሁለት አስርት አለፈ፡፡ ከዛሬው ዘመን ደረስን፡፡
በቻርልስ ዳርዊን መርከብ፤ በቮልቴር ነዳጅ፤ በካፒታሊዝም ተራዳ የምትቀዝፈው የምዕራቡ ጎራ መርከብ ማርክሲዝምን እያወገዘች ግሎባላይዜሽን እየቀዘፈች ተመመች፡፡ ምዕራባዊት ዓለም የክላሲካል ሊበራሊዝምን ባንዲራ እያውለበለበች፤ ኮሚኒስቶችን እና ሶሻል ዲሞክራቶችን እያጥላላች፤ የ”አካባቢስቶችን” ጩኸት እያንቋሸሸች ተጓዘች፡፡
በ1970ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ዜማዋን ከክላሲካል ሊበራሊዝም ወደ ኒዮሊበራሊዝም ቀይራ፤ የሠራተኞችን ድምፅ እያፈነች፤ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን በየጊዜው እያጠበበች፤ መንግስታትም ለታላላቅ ኩባንያዎች ድምፅ እንጂ ለሠራተኛው ድምፅ ጆሮአቸውን እየደፈኑ፤ የግሎባላይዜሽን መዝሙር እየዘመሩ ዓለም ጉዞዋን ቀጠለች፡፡ ሳይንሱም የእነሱን ድምፅ እየተከተለ ዘፈነ፡፡ የኒዮሊበራሊዝም ካፒቴኖች ኃይል እየበረታ ሄደ፡፡ “መሀል ቀኞች” እና (Center Right) “መሀል ግራዎች” (Center left) እየተሰኙ ወደ ኒዮሊበራሊስት ጎራ ገቡ፡፡ ዓለም በኒዮሊበራሊስት የፋይናንስ ተቋማት፣ ኃያላን መንግስታት እና ሚዲያዎች ኒዮሊበራሊስታዊ ተግሳፅ ፀጥ ረጭ አለች፡፡ግን ከሁለት ሦስት ዓመታት ወዲህ፤ የምዕራቡ ዓለም የኒዮሊበራሊዝም መርከብ ችግር እየገጠማት ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን “የኒዮሊበራሊዝም መርከብ ሽንቁር የሚፈጠረው በፋይናንስ ገበያው በኩል ነው” ይሉ ነበር፡፡ የፈሩት አልቀረም፡፡ በዚያው በኩል ተሸነቆረ፡፡ ታይታኒካዊ የኒዮሊበራሊስት መርከብ ተቀደደች፡፡
የሠራተኛ ማህበርን ድምፅ እያፈኑ፤ የብዙሃን ዜጎችን ጩኸት ቸል እያሉ፤ የታላላቅ ኮርፖሬሽኖችን ፊት እያዩ የሚያድሩት የምዕራቡ መንግስታት የሚሰሙት የለመዱትን የባለፀጎቹን ድምፅ ሆነ፡፡ በፈራ - ተባ የሚናገሩ የአንዳንድ ምሁራንን ማሳሰቢያ፤ የብዙሃን ዜጎችን ድምፅ ጆሮ ዳባ ያሉት እነኚህ መንግስታት መርከቧ አደጋ ሲገጥማት የባለፀጋዎችን ነፍስ ለማዳን “ላይፍ ሴቨር” ላኩ፡፡ የብዙሃኑን ጥያቄ ቸል አሉት፡፡ ስለዚህ ከዘጠኝ መቶ በላይ የሚሆኑ የምዕራቡ ዓለም ከተሞች በሰላማዊ ሰልፍ ተናወጡ፡፡ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ከተሞች ፖሊሶች ተራወጡ፡፡ ፖሊሶች ሰላማዊ ሰልፈኞችን እያፈሱ አሰሩ፡፡ ግን የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ነገሩ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እንዳሉት ይሆናል፤ “Those who make peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable.”
ሶሻሊዝም በከሰረበት፤ ኒዮሊበራሊዝም በተሸነቆረበት፤ ለዓለም መድህን የሚሆን አዲስ ፍልስፍና በሌለበት ሁኔታ ክፍተቱን የሚሞላው ሃይማኖት መሆኑ አይቀርም እላለሁ፡፡ «Yin and Yang´ ማለት ይኼ ነው፡፡ ግን የትኛው? ጥያቄዬ ነው፡፡ እናንተስ ምን ይመስላችኋል?

 

Read 2200 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:53