Saturday, 22 March 2025 12:32

የእናት ባንክ “እማዬ” ቅርንጫፍ ሥራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ለእናቴ”  የጽሁፍ ውድድር ለ10 ቀናት ተራዝሟል



          እናት ባንክ፤ የድካማቸውን ያህል ያልተነገረላቸውን ብዙኃን ኢትዮጵያውያን እናቶችን የሚወክል “እማዬ” የተሰኘ ቅርንጫፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በይፋ ከፍቶ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፤ ቅርንጫፉ ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነፃ ማከናወን የሚችሉበት ነው ተብሏል፡፡
“እማዬ” የተሰኘው ቅርንጫፍ የተከፈተው ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ፊት ለፊት በሚገኘው የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት ህንጻ ላይ ሲሆን፤ የእናት ባንክ አመራሮች የቅርንጫፉን መከፈት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሃጎስ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ባንኩ “እማዬ” የሚል ስያሜ የሰጠው ይኸው ቅርንጫፍ፤ በእናትነታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ፣ ነገር ግን የልፋታቸውን ያህል ያልተጻፈላቸውና ያልተነገረላቸው እናቶች ውክልና እንዲኖራቸው ታስቦ የተከፈተ ነው፡፡” ብለዋል፡፡    
 “ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነጻ ማከናወን የሚችሉበት፣ ዲዛይኑም ሆነ በውስጡ ያሉት ግብዓቶች ብዙኃኑን የአገራችንን እናቶች እንዲወክል ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፤ምክትል ፕሬዚዳንቷ፡፡
ማንኛውም ሰው በቅርንጫፉ ተገኝቶ ስለ እናቱ ስሜቱን የሚገልጽበት እንዲሁም በእናቶች ዙሪያ የተጻፉ መጻህፍትን የሚያነብበትና ራሱም የሚጽፍበት ሥፍራ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር መጠናቀቁን የጠቀሰው ባንኩ፤ የ”እማዬ” ቅርንጫፍ መከፈትን ምክንያት በማድረግ ውድድሩን ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ማራዘሙን አስታውቋል፡፡
ለ”እናቴ” የተሰኘው የጽሁፍ ውድድር ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ አክብሮት፣ ውለታና ምስጋና በዝርው ጽሁፍ (ግጥም ያልሆነ፣ በወግ መልክ፣ በደብዳቤ ቅርጽ) የሚያቀርብበት ሲሆን፤ “የዓመቱ ድንቅ እናት” የተሰኘው ውድድር ደግሞ ተወዳዳሪዎች በአካባቢያቸው በሕይወት ያሉና የሚያውቋቸውን ወይም የራሳቸውን እናቶች በጽሁፍ በድምጽና በምስል ቀርጸው በቀጥታ የሚሳተፉበት ነው፡፡
አዲስ አበባ የሚገኙና በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ በአዲሱ “እማዬ” ቅርንጫፍ እንዲሁም በክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራዎቻቸውን ማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የዘንድሮ የጽሑፍ ውድድር የመዝጊያ መርሃ-ግብር፣ የእናቶች ቀን በሆነው የግንቦት ወር መጀመሪያ፣ በደማቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ባንኩ አስታውቋል፡፡    
በመላ ሃገሪቱ “እማዬ” ቅርንጫፍን ሳይጨምር 206 ቅርንጫፎች ያሉት እናት ባንክ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ለሃገርና ለወገን በጎ በዋሉና  ዝናን ባተረፉ እንስቶች ስም ሲሰይም መቆየቱን አስታውሶ፣ ወደፊትም ቅርንጫፎቹን በመሰል እንስቶች ስም መሰየሙን  እንደሚቀጥልበት  ጠቁሟል፡፡

Read 6910 times