Print this page
Saturday, 22 October 2011 11:22

“ዓላማዬ የተቸገሩ ት/ቤቶችን መርዳት ነው” አቶ ፈቃደ ወ/ማርያም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ፈቃደ ወልደማርያም ተወልዶ ያደገው ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከልጅነቱ አንስቶ በትምህርቱ ጐበዝ የነበረ ቢሆንም ትምህርቱን በአግባቡ ለመከታተል የማያስችሉ በርካታ እንቅፋቶች እንደገጠሙት ይናገራል፡፡ የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈልና የመማሪያ ደብተርና መጽሐፍትን ማሟላት ታላቅ ፈተናዎቹ ነበሩ፡፡ እነዚህን የት/ቤት ወጪዎች ለመሸፈን ዶሮ አርብቶ እስከመሸጥ የሚደርሱ ልዩ ልዩ ሥራዎች መስራቱንም ያስታውሳል፡፡ ከኑሮ ችግሮች ጋር እየታገለ ትምህርቱን እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለመዝለቅ ህልም የነበረው ፈቃደ፤ ይሄንን ህልሙን የሚያደናቅፍ ትልቅ ችግር እንደገጠመው ይናገራል፡ በወቅቱ የደርግ መንግስት ወጣቶችን ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ይመለምል ስለነበር ከዚያ ለማምለጥ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት ሁሉን ትቶ ስደትን መረጠ፡፡

ከአገር የመውጫ ብቸኛው አማራጭ በህገወጥ መንገድ መሰደድ ነበርና በ1981 ዓ.ም ከሰባት ጓደኞቹ ጋር በሞያሌ በኩል ኬኒያ ገቡ ቲካ በተባለ የኬኒያ የስደተኞች ካምፕ ከቆየ በኋላም ወደ አሜሪካ የመግባት ዕድል አገኘ፡፡ ያኔ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል አመቺ ዕድል ስላገኘ በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ትምህርቱን ተከታትሎ የመጀመሪያ ድግሪውን አገኘ፡፡  
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ አገሩ ሲመጣ የመንግስት ለውጥን ጨምሮ በርካታ ነገሮች ተቀይረው ነበር፡፡ የቤተሰብ፣ የአገርና የወገን ናፍቆት ወደቀዬው የመለሰው ወጣት ፈቃደ፤ ተወልዶ ያደገባትን ወልቂጤንና አዲስ አበባን ተዘዋውሮ ተመለከተ፡፡ በልጅነቱ ከድህነት ጋር እየታገለ የተማረባት ትምህርት ቤት ከድሮው የበለጠ መጐሳቀሏን አስተዋለ፡፡ የበለጠ ትኩረቱን የሳቡት ግን ተማሪዎቹ ነበሩ፡፡ በፊታቸው ላይ ተስፋና ለውጥ ቢነበብም እሱ ያሳለፈው አይነት የችግር ህይወትን እየተጋፈጡ እንደሚማሩ ለመገንዘብ አላቃተውም፡፡
በወልቂጤም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው ት/ቤቶች አብዛኛዎቹ የተጋፈጡት ችግሮች በእሱ አቅም ብቻ ሊፈቱ የማይችሉ እንደሆኑም ተገንዝ|ቧል፡፡ የሚበሉት ምግብ ሳይኖራቸው ወደ ት/ቤት የሚመጡ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ የሌላቸው፣ የተቀዳደዱ ልብሶች የለበሱ፣ መጫሚያ የሌላቸው ወዘተ ሁሉንም አየ፡፡ በሁኔታው ልቡ ተነካ፡፡ ይሄኔ ነው አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ በችግሮች የታጠሩ ት/ቤቶችን ለማገዝ የወሰነው (ለሁሉም ግን መጀመሪያ ወደ መኖሪያ ሥፍራው ካሊፎርኒያ መመለስ ነበረበት፡፡
እዚያም ስለ ት/ቤቶቹና ተማሪዎቹ ካጫወታቸው ጥቂት ጓደኞቹና ሌሎች ሰዎች የተለያዩ የት/ቤት ቁሳቁሶች አሰባሰበና ወደ አገሩ በመመለስ ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ለሚገኘው ራስታስላሴ የተባለ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ለገሰ፡፡ እስካሁን ለዚህ ትምህርት ቤት ከ20ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችንና የስፖርት ቁሳቁሶችን በእርዳታ እንዳበረከተ ፈቃደ ይናገራል፡፡
እርዳታውን በተናጠል ብቻ ማድረግ ፋይዳ ያለው ለውጥ እንደማያመጣ የተረዳው ፈቃደ፤ እዛው አሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር የአገሩ ት/ቤቶች ያለባቸውን ችግሮች በዘላቂነት የሚያቃልሉበትን መንገድ በጋራ መምከር እንደጀመረ ይናገራል፡፡ ከዚያም የት/ቤቶቹን ችግሮች ለማወቅና ለመለየት ወደ አገሩ ተመልሶ በመምጣት ጥናት ማካሄዱን ገልጿል፡፡
ፈቃደ ጥናት አድርጌባቸዋለሁ ባላቸው የአዲስ አበባና የክልል ት/ቤቶች ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባው የቀድሞ በየነመርዕድ የአሁኑ፣ እድገት በህብረት ት/ቤት ውስጥ ያያቸው ህፃናት ልቡን ነክተውታል አብዛኛዎቹ ወላጆቻቸውን በኤች አይ ቪ ኤድስ ያጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ፍቅር ማጣት በተጨማሪ የሚበሉትና የሚጠጡት በማጣት ይቸገራሉ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ላሉ ህፃናትም አቅሜ የፈቀደውን እርዳታ አድርጌአለሁ ይላል - ፈቃደ፡፡ በቅርቡም ሰፋ ባለ መንገድ እርዳታ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ይናገራል፡፡ እስከአሁን ድረስ በዚህ ወጣት ለትምህርት ቤቶች ከተሰጡ እርዳታዎች መካከል ኮምፒዩተሮች፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ የስፖርት መስሪያ ቁሳቁሶች፣ የመፀዳጃ ቤት ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ ይህን እርዳታ የሚደግፍና የሚያስተባብር Ethiopian Educational fund የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተቋቁሞ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡም እዛው አሜሪካ ታላቅ ኮንሰርት በማዘጋጀት እርዳታውን በተጠናከረና በተሻለ መልኩ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልጿል፡፡ ከጊዜያዊ እርዳታ በዘለለ መልኩ ተማሪዎች የአርት ጥበብ ስሜታቸውንና ፍላጐታቸውን የሚያዳብሩበት ሁኔታ ከማመቻቸት አንስቶ ለየትምህርት ቤቶቹ ክሊኒክ ማቋቋምም በዕቅድ ከተያዙ ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ ፈቃደ ተናግሯል፡፡

 

Read 1317 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:24