Saturday, 22 October 2011 11:20

ሰውን በቧልታይ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

“ሰው ተረፈ?”
… መድፍ ሲተኮስ፣ እሳት ሲለኮስ፣ መኪና ሲጥስ… ሀበሻ ምድር ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መጠይቅ፡፡
“ሰው ከተረፈስ ሌላው ይተካል”
ሌላ ምን አለን? የተረፈን ሰው፣ የተትረፈረፈን ሰው… የዛኑ ያህል የማንጠግበው ሰው፡፡ ደረታችንን የምንደቃው፣ ፊታችንን የምንነጨው፣ ከል የምንለብሰው፣ አመድ የምንነሰንሰው… ለሰው፡፡ ደግሞ - ደግሞ…

“የሰው ደህናው፣ መቃብር የተኛው” እንላለን ሲመጣብን፡፡ ለሰው አንተኛም፣ ጠርጣሮች ነን፡፡ የኑሯችን ብሒሉ ይሄ ነው፡፡ “የሰጋ ቤቱን ዘጋ፣ የዘነጋ ተወጋ” (መቼም አውሬ ጦር ወርውሮ አይወጋን፣ ያው ሰው ነው) ቤታችንን ዘግተንም ነፍሳችን አተርፍ፡፡ ሰው ይሉት መንፈስ ጥሎብን፡፡ “የሰው መዋደዱ - መዋለዱ” እንላለን እንጂ ሐሰት! ምክንያቱስ? “የሰው ጠላቱ፣ ይወጣል ከቤቱ” ነውና… 
ሰ-ዎ-ች በዚህ ከቀጠልን ነገር አበላሸን፣ እንዳማረብን፣ (ውርደት ሳይከተለን) ወደ ውጭ!
ለመሆኑ ሰው ምንድነው?
ለዚህ ጥያቄ እንደ ከተፎ ተማሪ ምላሹን በፍጥነት ያደረሰን የጥንታዊቷ ግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ ነው፡፡ “Man is biped without feathers” (የሰው ልጅ ላባ ያልለበሰ የሁለት እግር ተራማጅ እንስሳ ነው) እንዴት ነው ነገሩ? የሰው ልጅ በሁለት እግሩ በመጓዙ ብቻ ከዶሮ ሊቆጠር? ክብሩሳ? ማዕረጉሳ?... ያልን መትከንከን መብታችን ነው፡፡
ፈረንሳዊው የሒሳብ ሊቅና ፈላስፋ ብሌዝ ፓስካል (1623-1662) በሁለት ሺህ ዓመታት የዘገየ ምላሹን ለፕሌቶ ሰጥቷል፡፡ “እንዴት የሰው ልጅ በሁለት እግሮቹ ስለሄደ ብቻ ላባ ያልለበሰ ዶሮ ተደርጐ ይታያል? የሰው ልጅ’ኮ እግሩ ቢቆረጥም ያው ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ዶሮ ላባውን (እንደጢም) ሙልጭ አድርጐ ቢላጭም ሰው መሆን አይቻለውም” (A man without legs is still a man, but rooster can never become a man even if he loses all his feathers.)
በፓስካል ንግግር አንጀታቸው ቅቤ የጠጣ የጥበብ ቂም በቀለኞች በፕሌቶ ላይ ላንቃቸው እስኪታይ አውካኩ፡፡ (በሰፈሩት ቁና… አለ አሉ ፕሌቶ) ቅድሚያ ጥንታዊውን ሰው አይተን ወደ ፕሌቶ ንትክክ ብንመለስስ?
ጥራታዊው ሰው እራሱን የሚመለከተው ከተፈጥሮ ጋር የሥጋ-ዝምድና ያለው ጥንቅር አድርጐ ነው፡፡ የነፋስ፣ የእሳት፣ የውሃና የመሬት ቅልቅል ነኝ ይላል፡፡ ስለዚህ ከተፈጥሮ ጋር “የቤተዘመድ - ጉባኤ” ይቀመጣል፡፡ የተፈጥሮ ቁጣ በደረሰ ጊዜ ግሳፄዋን በልምምጥና በድለላ ለማስታገስ ይጥራል፡፡ በሠመረለት ጊዜ ደግሞ አስራቱን ያገባል፡፡ “Animism” የሚባለው መሆኑ ነው፡፡ የኃይማኖቶች ሁሉ መሰረት ተደርጐ ይታያል፡፡ እነዚያን ንፋሳት፣ ማዕበላት፣ ሰደዳት፣ ጐርፋት፣ የመሬት መንቀጥቀጣት… እየወከለና እየወካከለ ከተፈጥሮ ጋር የቤተ-ዘመድ ጉባኤውን ገፋበት፡፡
(“እንዲያ-እንዲያ እያለ…” አለ ዘፋኙ፡፡)
ከጥንታዊነት ወዲህ ጥቂት ፈቅ ያለው የሰው ልጅ እምነቱ ብቻ ሳይሆን ስለራሱ ያለውም አመለካከት ተሻሽሎ ተስተውሏል፡፡ እንግዲህ ፈጣሪ ሰማይን ያለማማ ምድርን ያለ ካስማ ሲዘረጋ የሁለንተና (Universe) ማዕከል ያደረገው መሬትን ነው . . . (Geocentric) የሰው ልጅ ይሄን ተገን አድርጐ ለራሱም ቦታ አፈላላጐ አግኝቷል፡፡ ሰው እንደመሬት ሁሉ የሁለንተናው ማዕከል ነኝ አለ፡፡ (Anthropogeocentric) ፀሐይ ነሽ፣ ጨረቃ ነሽ፣ ፕላኔት ነሽ፣ ከዋክብት ነሽ… በመሬት ዙሪያ እንደሚሽከረከሩት ሁሉ ሰውም የነገሮች ማንፀሪያ ማዕከል እኔ ነኝ አለ፡፡ አንዳንዴ ባጠጠ ማለት ይቻላል፡፡ ለራሱ የሰጠውን “ግዛት” እያሰፋ ፈጣሪውንም እስከመጋፋት ደረሰ፡፡ R.G.INGERSOLL የተባለው ሰው “An honest God is the noblest work of man” እንዳለው ነው፡፡ ኧረ ይሄ መባጠጥ በእኛም አለ:-
“ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ” አላልንም እንዴ?
ዘመንና የእኛ ትዝብት እጅ-ለእጅ ተያይዘው ሲቀጥሉ…
…ልክ 1473 ዓ.ም ላይ ኮፐርኒከስ ከወደ ምዕራቡ ዓለም ብቅ አለ፡፡ ብቅ ብሎም አልቀረ በሥነ-ፈለክ ጥናት በኩል ነባሩን ግንዛቤ መታው፡፡ መሬት የሁለንተና ማዕከል ሳትሆን የራሷ ተሽከርካሪ “ባተሌ” መሆኗን አረጋገጠ፡፡ ውሻ የታሰረበትን ምሰሶ እንዲዞር መሬትና የተቀሩት ፕላኔቶች እንዲሁ የፀሐይ ደጅ ጠኝዎች ሆነው ተገኙ፡፡ (Heliscentrism) እናስ?
እናም የመሬት ክብር ተጋሪ የነበረው ሰው “የዱላውም” ቀማሽ ሆነ፡፡ እንደ ጥንቶቹ መኳንንቶች “የሞትንም እኛ፣ ያለንም እኛ” እያለ አዋጅ እንዳላስነገረ ከነበረበት ሁለንተናዊ አመለካከት ውስጥ “በክብር” እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ወደ ፕሌቶ “ንትርክ” መመለስ የሚኖርብን፡፡
ሰው ምንድነው?
“ሰውማ ላባ ያልለበሰ የሁለት እግር ተራማጅ እንስሳ ነው”
“ትክክል!” የሚሉ ፈላስፎች የተፈጠሩት የኮፐርኒክሰን የሥነ-ፈለክ ግኝት ከመረመሩ በኋላ እሱኑ ዋቢ እያደረጉ ሆነ፡፡ ሰው ለእናት ተፈጥሮ ምንድነው? ከዶሮ፣ ከውሻ፣ ከላም… በምን ይለያል? ከንቱ መታበይ ይዞት እንጂ ሰው ከእንስሳቱ እንደ አንዱ አይደለምን? ሐሳቡ እስኪለመድ “እግዚኦ!” አሰኘ፡፡
“የባሰ አለ አገርክን አትልቀቅ” ማለት ደግ ነበር፡፡ የቻርልስ ዳርዊን “የዝግመተ-ለውጥ ንድፈ-ሀሳብ” ደግሞ ሰውን የጊዜ ምጣድ ላይ በእርጋታ የበሰለ ዝንጀሮ አድርጐ አቀረበው፡፡ ከዚህ የባሰ ይኖር ይሆን?
አለ እንጂ አንዳንዶቹ “Mechanism” ይሉታል፡፡ የተቀሩት ደግሞ “Mechanistic Materialism” ያም ሆነ ይህ የሰውን ልጅ ከነሁለንተና (univers) ቅንብሩ ረቀቅ አለ እንጂ በማሽን ህግ የሚተዳደር ማሽን ነው ብሎ የሚያስብ ፍልስፍና ነው፡፡ ቃል በቃል “Man himself (in the opinion of these philosophers) was but a very sophisticated – mechanism” ተባለ፡፡ የጋሊሊዮ ጋሊሊ፣ የኒውተንና የተቀሩት ሳይንቲስቶች መነሳትና ማሽን በሰፊው ተግባር ላይ መዋል የፈጠረው አመለካከት እንደነበር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ጁሊየን ኦፍሬይ ዲ ላ ሜትሪ የተባለ ፈረንሳዊ ፈላስፋ “Man – Machin” ብሎ በሰየመው መፅሐፉ ሰውን ከሰብአዊነት ተርታ አውጥቶ ከመኪኖች ጋር ደባለቀው፡፡
በዘመኑ ሰውና ማሽን ከአንድ ወንዝ ተቀዱ፡፡ ፍልስፍናው እንደ ትንቢት ተተገበረ፡፡ በኢንዱስትሪ አብዮቱ ዘመን የሰው ልጅ ሰውነቱ የማያሳስበው፣ ሥነ-ምግባር ግድ የማይለው ለሥራው ብቻ ያደረ ብረት-አከል ሰብእና ተላበሰ፡፡
ይሄንን ሁኔታ በትዝብት ያጤነው ሳይኮአናሊስቱና የማህበረሰብ ጥናት ምሁሩ ኤሪክ ፍሮም “The Sane Society” የተሰኘ መፅሐፉ ላይ እንዲህ አለ፡-
“In the nineteenth century the problem was that GOD IS DEAD; in the twentieth century the problem is that Man is Dead” (አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ላይ ዋነኛ ችግር የነበረው “እግዚአብሔር ሞቷል” ነበር፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ አሳሳቢው ችግር “የሰው ልጅ ሞቷል” የሚለው ሆነ፡፡)
ኤሪክ ፍሮም የጠቀሰው “God is Dead” ቃል በቃል ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬደሪክ ኒች ያለውን ነበር፡፡ ኒች “እግዚአብሔር ሞቷል” ያለው የሰውን ልጅ ማሳበቢያ ልዕለ-ተፈጥሮ ነጥቆ ሐላፊነቱን እራሱ ሰው እንዲወስድ ለማስቻል ነበር፡፡ በህልውናዊነት (Existensialism) ፍልስፍና መሰረት፣ የሰው ልጅ የጥፋቱ ተጠያቂ፣ የልማቱ ተሸላሚ እራሱ ሰው መሆኑን ለማስተማር የተጠቀመበት ብሂሉ ነበር፡፡ ይሁንና ኤሪክ ፍሮም አባባሉን ወደ አንድ ደረጃ አሳድጐ ዘመንና ሰው የደረሱበትን ለማሳያ ተጠቀመበት፡፡
“የሰው ልጅ ሞቷል”
የሰው ልጅ፣ የኢንዱስትሪው አብዮት ባጨቀየው የብረት አረንቋ ተይዞ ማንነቱን መፈለግ ተስኖታል፡፡ ማን ይታደገው? መጀመሪያ እግዚአብሔሩን ገድሏል፣ ከዚያ እራሱን አጥፍቷል፡፡ እናስ? ነብይ ማን ያስነሳለት?
ካርል ማርክስ…
…Christopher Dawso የተሰኘ ፀሐፊ ማርክስን የኢንዱስትሪው አብዮት ነብይ ነው ይለዋል፡፡ “What is more likely is that the undying hopes of Jewry in the advent of a messiah and the kingdom of Israel influenced consciously or unconsciously his mind.” (ማርክስ አውቆም ይሁን ሳያውቅ አእምሮው በአይሁዶቹ መሲሐዊ የተስፋይቱ ቀንና መንግሥት ተፅእኖ ሥር የወደቀ ይመስላል እንደማለት ነው፡፡)
እናስ?
እናማ ማርክስ “በቁስአካላዊነት” (materialism) እስራኤል የተገባላትን መንፈሳዊ ቃልኪዳን ለመፈፀም ተነሳ፡፡ (by materialism creat the kingdom of the spirit which Israel had been promised) መንፈሳዊ ድህነትን በኢኮኖሚያዊ ድህነት ተካ፤ ምድረ-ግብፅን በኢንዱስትሪው አብዮት ተካ፣ የግብፅ ፈርኦኖች ደግሞ ጨቋኞቹና በዝባዦቹ ናቸው አለ፡፡ በባርነት ሥር የነበሩትን እስራኤላውያንን በሠራተኛው መደብ ተካ፣ እራሱን በሙሴ ተካ፣ የተስፋይቱን ምድር በኮሙኒዝም ተካ… ይሄንን የሚለን Martin c.D’arcy “Communism and Christianity” በተሰኘ መፅሐፉ ነው፡፡ የ”Christian Socialism”ን አንደምታ ትተን ወደተነሳንበት “ሰው ምንድነው?” እንመለስ፡፡
/ማርክስ/ ሠራተኛው ሰው የመሆንን ማዕረግ ተነፍጓል፡፡ እራሱም ሰውነት አይሰማውም”” ብሏል፡፡ “Karl Marx, Economic and Philosophic Manuscripts of 1844” የተሰኘ መፅሐፍ ላይ ማርክስ እንዲህ እንዳለ ተፅፏል፡- “What is animal becomes human and what is human becomes animal” ዘመኑን ነው “እንስሳ ሰው፣ ሰው እንስሳ የሆነበት” የሚለው፡፡
የማርክስ ፍልስፍና ማዕከሉ ሰው ነው፡፡ ከሰውም ደግሞ እራሱን በራሱ ድር ተብትቦ እጅ እግሩን ያሰረው ሰው፡፡ እንዲህ ብሏል:-
“Man’s most pnecious treasure, his greatest wealth is man himself” (የሰው ልጅ ብርቁ ሐብት እና ታላቁ ፀጋ እራሱ ሰው ነው)
አ-ይ ሰው! ደግሞ ወደ ክብር ስፍራው መጣ፡፡
የሰው ልጅ ስለ ብረት ፍቅር ብረት እስከመሆን ክብሩን አዋረደ፣ ጠባዩን መረዘ፣ ህይወቱን አጐመዘዘ፡፡ ማርክስ ሰውን ከዚህ የብረት አረንቋ መዝዞ ባያወጣውም በቀረርቶው ዓለምን ከሁለት የሚሰነጥቅ ኃይል እንዳለው እንዲያሳይ ረድቶታል፡፡
“ዞረን-ዞረን ከቤት…” ልንል ነው፡፡
አኗኗራችን፣ እምነታችን፣ ጥበባችን፣ ማህበራዊ ተራክቧችን፣ ፍልስፍናችን፣ ሀሜታችን፣ መወድሳችን፣ ታሪካችን… ሁሉ ሰውን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ገና ሥም ያልወጣለት የሰው ማዕከላዊነታችንን ስትፈልጉ Anthropogeocentric በሉት፡፡ ግድ የለንም - ብቻ አታዛንፉብን፡፡ የኛ ኮፐርኒከስ መጥቶ ኢትዮጵያዊውን ከማዕከላዊነቱ እስኪያነሳው በዚያው መቀጠል ነው፡፡ ለዚህ አኗኗራችን ፍልስፍናዊ ዋቢ ለሚሹ የጂጂን (እጅጋየሁ ሽባባው) “አድዋ” ጋብዘን እንለያለን፡፡ “ሰው ሊኖር ሰው እንዴት እንደሞተ” እሷ ታስረዳልናለች፡፡
በደግነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር - ሰው ሞቶ፤
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፤

 

Read 3094 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:24