Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:01

“መዝናናት መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!” (ጓድ ሌኒን) የተከበራችሁ አንባብያን፡-

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከሁሉ የስነ-ጥበብ ዘርፎች አዲሱ ወይም ወጣቱ Advertising (ማስታወቂያ) ነው፡፡ ከሱ በፊት እቃህን ይዘህ ገበያ ትወጣለህ፣ ለውጠህ ወይ ሸጠህ ትመለሳለህ፡፡ Advertising ከመጣ ወዲህ ግን አብዛኛውን ልብሳችንን ሳይቀር በማስታወቂያ ተመርተን ነው ምንገዛው (የተመራነው ደግሞ ሳይታወቀን ሊሆን ይችላል!) Shaping Public Opinion (የህዝብን አስተሳሰብ መቅረፅ) የሚባል፣ የሳይኮሎጂና የአትንሮፖሎጂ ውህደት የሆነ የሙያ ዘርፍ አለ፡፡ የማስታወቂያ ስራ ተራውን የዚህ የሙያ ዘርፍ መሆኑ ነው፡፡

ማስታወቂያ art (ጥበብ) ነው፣ የማይቀርለት ምቀኛ እድል ተጠናውቶታል እንጂ፡፡ ይሄ ከይሲ እድል ምንድነው? እስኪሰለቸን፣ እጅ እጅ እስኪለን መደጋገም መደጋገም፣ አሁንም መደጋገም አለበት (ውሸት ከድግግሞሽ ብዛት እውነት ይሆናል፣የሚባለውንም እናስታውሳለን) 
አንድ
ከዛሬ ሀምሳ አመት በፊት መፅሄት ውስጥ ያየኋት ማስታወቂያ እስከ አሁን ድረስ ሳስታውሳት እንደ አዲስ ትሆንብኛለች፡፡ Full page ፎቶግራፍ ነው፣ የ Rolls Royce መኪና ውስጥዋን በነጂው አይን እናየዋለን፣ ከነ ሰአቱ
ከፎቶው ግርጌ ጥቁር መደብ ላይ በነጭ ፊደላት መልእክቱ ተፅፏል፡-
At sixty miles per hour
The only sound you hear is the ticking
of the clock.
መረጃ፡- ያን ጊዜ Rolls Royce ለመግዛት ሁለት አመት አስቀድመህ መመዝገብ ይኖርብሀል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌሎች መኪናዎች በፋብሪካ አይደለም የሚገጣጠሙት፡፡ እያንዳንዷ “ብልት” (ቡሎን እንኳ ሳይቀር) በእጅ ትታነፃለች እንደ ሀውልት፡፡
እያንዳንዱ ሰራተኛ የተመሰከረለት ባለሙያ ነው፡፡
ያዘዝከውን መኪና እቤትህ ድረስ ሲያመጡልህ ከነሾፌሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሮልስ ሮይስ ለመንዳት ልዩ ስልጠና ይጠይቃል፡፡ ሮልስ ሮይስህን ወደ ጋራዥ አትወስዳትም፡፡ ሾፌሩ ራሱ ነው የሚጠግናት (ለዚያውም ምናልባት ጥገና ቢያስፈልግስ? በማለት ነው እንጂ፣ መኪናህ ሶስት ትውልድ እንደሚያገለግል ዋስትና አለው (guaranty)
ሾፌርህ ስልጠና ሲወስድ፣ ወንድ ልጁ ስራውን እንዲወርስ (እንዲረከበው) አባት ያገኘውን ስልጠና ለልጁ ሲሰጠው እንዲችል ጭምር ነው . . .
. . . እንግሊዝ መሳፍንትና መኳንንት ቤት ብቻ እንጂ ሌላው ፈረንጅ አለም ውስጥ የሌለ butler የሚባል የወንድ ልጅ ሙያ አለ፡፡ በትለር የአሳዳሪው Lord ታማኝ ተላላኪ፣ ሚስጥር ጠባቂ እና ሁነኛ ቀኝ እጅ ነው፡፡ በትለር እና ሚስቱና ልጆቹ ግቢው ውስጥ ለብቻው የተሰራ መኖሪያ ቤት አለው፡፡
የሎርድ ቤት ባለ ሁለት ፎቅ ሆኖ አርባ ያህል የተለያየ ክፍል ቢኖረው፣ የዚህ ሁሉ በር ቁልፍ በበትለር እጅ ነው (ገንዘብ የሚቀመጥበት ካዝና፣ እነሱ Safe የሚሉት፣ ብቻ ነው በትለር ሊከፍተው የማይችለው)
የዚህ የበትለር ልጅ ሲያድግ ለአሳዳሪው ሎርድ ለበኸር ልጁ በትለር ሆኖ ያገለግለዋል፣ በሶስተኛው ትውልድ ዘመንም ለሎርዱ የልጅ ልጅ የበትለሩ የልጅ ልጅ አገልጋይ ይሆነዋል፡፡
እንደሚባለው ከሆነ፣ አንድ ሎርድ እንደ ዊንስተን ቸርቺል ወይም እንደ ሎርድ ባይረን አይነት ስለሆነ ፖለቲካ ውስጥ ካልገባ በስተቀር፣ ምንም ስራ አይሰራም፡፡ እንድያውም “An aristocrat does not even have to think. His butler does it for him” ይሉ ነበር አሪስቶክራት ያልሆኑ ሰዎች፡፡
ሁለት
በ1960ዎቹ (በነሱ አቆጣጠር) ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በብዛት ከሚሸጡት ሶስቱ ዋና ቢራዎች አንዱ Schlitz ይባላል፡፡ ሁለት አይነት ቢራዎች በእኩል ብዛት ይጠመቃሉ - Schlitz እና Schlitz Light.
ሽያጩ ሲታይ ታድያ፣ ላለፉት ዘጠኘ ወራት ያህል Schlitz Light አከታትሎ 20% ያነሰ ሆነ፡፡ የማስታወቂያ ባለ ሙያዎች ሳይካሎጂስት ስለሆኑ የሰፊውን ህዝብ አስተያየት መቅረፁን ተክነውበታል፡፡ Market research (የገበያ ጥናት?) በሚያካሂዱበት ወቅት አብረው በስነ-ልቦና ሲፈትሹት፣ Light የተባለው ቅፅል የአልኮልነት ጉልበቱ ቀላል ነው የሚል አስመስሎታል፡፡ ማለትም Lights የሚጠጣ ወንድ ሴታ ሴት ነው በውስጠ ታዋቂነት፡፡
ይህን የሽያጭ መዛባት ለማስተካከል አንድ genius የፈጠራት ማስታወቅያ ብቃት አሳየች፡፡ ዝርዝሩ እንደሚከተለው ተካሄደ፡-
በዚያን ወራት The magnificent Seven የሚል Western (ማለት ሁለት ተፋላሚዎች ፊት ለፊት ይቆሙና፣ ቀድሞ ሽጉጡን ከአፎቱ አውጥቶ የተኮሰ የሚገድልበት ፊልም) አገሩን ቀውጦት ነበር፡፡
The magnificent Seven, the magnificent Seven! They were seven, yet they were fought like seven hundred! ይላል አጃቢያቸው ሙዚቃ ከሰባቱ አንደኛው የደስ ደስ ያለው ቀጭን ረዥም ፉንጋ ሰውዬ ነው፡፡ ሊፋለመው የደፈረውን ፈጣን ባለ ሽጉጥ “በሴንጢ ልግደልህ ወይስ በሽጉጥ? ምረጥ!” ይለዋል፡፡ ሰውየው ሴንጢ ይመርጣል፡፡
የመሽቀዳደም ደቂቃይቱ ስትደርስ፣ ሰውየው ሽጉጡን ከአፎቱ ገና እየመዘዘው እያለ፣ ሴንጢዋ ጉሮሮው ላይ ተሰክታለች!
አሁን ወደ ማስታወቂያችን መጣን፡፡ እላይ ያስተዋወቅኩአችሁ ቀጫጫ ሴንጢ ወርዋሪ ፉንጋ ለዋናው Show down (ፊት ለፊት ቆመው ሲፋጠጡ፣ በመጨረሻ የሚለይላቸው ጥይት ሲተኰስ) ለብሷል፣ ሁለት ሽጉጡን ታጥቋል (ባርኔጣውም ይታያችሁ)
ከውጪ ወደ Saloon ሲገባ ሁለቱን ዥዋዥዌ ተጫዋች የበር ግማሾች በእግሩ ገፍትሮዋቸው ገብቶ ወደ መጠጥ ባንኮኒው ሲራመድ፣ ፈረስ መኰርኰርያዋ ክብ ብረት እግሩ ወለሉን ሲረግጥ ቅጭል! ትላለች፡፡
በየጠረጴዛው ዙሪያ ተቀምጠው የነበሩት ጠጪዎች ካርታ ጨዋታቸውን አቋርጠው ግማሾቹ ቶሎ በጓሮ በር ውልቅ ይላሉ፣ ግማሾቹ ፈርተውም፣ ፍልምያውን ለማየት ቸኩለውም ቆመው ይመለከታሉ፡፡
ጀግናው የእርምጃዎቹ ቅጭል - ቅጭል ቤቱን በፍርሀት እየሞላው ባንኮኒው ጋ ሲደርስ፣ በቀኝ እጁ ባንኮኒውን ጧ አድርጎ ይፀፋዋል፡፡ ልትፈነዳ የደረሰች አንዲት ቅፅበት ካለፈች በኋላ፣ በጣም በሚያስፈራ አዛዥ ድምፅ፡-
“Schlitz Light!” ይላል
ይህ ድራማ በተሰራጨ በሁለም ሳምንቱ ሁለቱም Schlitz ቢራዎች ሽያጫቸው እኩል በእኩል ሆነ፡፡
ሶስት
Indirect advertising አለ፡፡ shaping public opinion እንዳልነው አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ Gone with the Wind የሚባል በጊዜው Box office hit የነበረ ፊልም አለ፡፡ ዋናውን ገፀባህሪ የሚተውነው መልከ መልካሙ ዘንካታው Clark Gable ነው፡፡ ፊልሙ ተሰርቶ ሲያልቅ ለማየት የሚወስደው ጊዜ ዘጠና አራት ደቂቃ ሆነ፡፡ Edit ተደርጎ (ማለት ቆርጠውት ቆራርጠውት፣ ቆርጠው ቀጥለውት) አራት ሰአት የሚወስድ ፊልም ሆነ፡፡
ክላርክ ጊብል ሌሎች ፊልሞች ውስጥ እየተወነ አመታት አለፉ፡፡ አንድ ፊልም ውስጥ ሸሚዝና ሱሪ እንጂ ካናቴራ (Under-Shirt) ሳይለብስ ይታያል፡፡ ይህ ፊልም ከተሰራጨ ከጥቂት ሳምንት በኋላ፣ ትልልቆቹ ከተማዎች ውስጥ የካናቴራ ሽያጭ 20% ቀነሰ፡፡
የነጋዴዎች ማህበር Holly wood ውስጥ ለሚመለከታቸው የሲኒማ ሙያተኞች ችግሩን አመለከተ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተወነበት ፊልም ሲታይ ሸሚዝ እና ካናቴራ (እደግመዋለሁ “እና ካናቴራ”)፡፡ ይህ ፊልም ከተሰራጨ ከጥቂት ሳምንት በኋላ የካናቴራ ሽያጭ ወደ ቀድሞው ብዛት ተመለሰ፡፡
አራት
Johnny Walker Whiskey በአይን የሚታወቀው፣ ሚስተር ዎከር ዘንጠው፣ ባታቸው ድረስ የሚሸፍን ጠባብ boot ጫማ አድርገው፣ እንደ በትረ መኰንን አጭር የሆነ ዱላ ከብብታቸው ወሽቀው፣ አንድ ረዥም እርምጃ ሲወስዱ እየታዩ ነው፡፡
ጆኒ ዎከር ኩባንያ ከአንድ ዊስኪ ወዳድ gentleman ጋር ኮንትራት ተፈራረመ፡፡ ኩባንያው ጧት ጧት አንድ ጠርሙስ ዊስኪ ሊያቀርብለት፣ እሱ ደግሞ አንድ በሚልዮን ኮፒ የሚታተም ጋዜጣ ውስጥ ማስታወቂያ ላይ እንዲታይ ልክ ጠርሙሱ ላይ ያለውን ጆኒ ዎከር መስሎ!
ኮንትራቱ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ሀያ አመት! ሁለቱም ተኰናታሪዎች ቃላቸውን ጠብቀዋል፡፡ ይሄ advertizing coup (ኩ) ይባላል እንበል፡፡
The Pied Piper of Hamlin Town
by Robert Browning
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
ብራውኒንግ እቺን ተረት ከጀርመን ወስዶ፣ እንደ አይጠሞገጥ በሚሯሯጡ ማራኪ ስንኞች ፅፎአታል፡፡ እንዲህ ትላለች፡- ሀምሊን ከተማ ውስጥ ምን ሀጢአት እንደተሰራ እንጃ፣ ተቆጥሮ የማያልቅ መንገዶቹን ሁሉ አይጠ - ሞገጥ ይንጋጋባቸዋል፡፡
አይ ብዛታቸው ማስፈራታቸው መቅፈፋቸው ማበሳጨታቸው ማሳበዳቸው!! ሰው ሁሉ በዱላ ደበደባቸው ጨፈጨፋቸው ፈጃቸው፣ ክንዱ ዝሎ ደንዝዞ ተስፋ ቆርጦ ተዋቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በብስጭት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡
የሀምሊን ኗሪዎች እንዲህ በከንቱ ታታሪነት ሲወራጩ እየዋሉ እያደሩ፣ እንቅልፉ ሲፈነግላቸው አይጠ-ሞገጦቹ የህፃናቱን ጆሮ፣ አፍንጫ፣ ጣት እየበሉ ሲያሰቃዩዋቸው፣ ሁሉም ደነዘዙ፣ አንዳንዶቹ አበዱ፡፡ አይጠ-ሞገጦቹ እርስ በርስም ይናከሳሉ ይባላሉ ከይሲ ናቸው፡፡ . . . በሰባተኛው ቀን ብቅ አለ Pied Piper - ዋሽንቱን (flute) እየተጫወተ፡፡ አይጠ-ሞገጦቹ ወድያው አወቁት፣ በስነ ስርአት እየተሰለፉ ተከተሉት፤ እስከ ማዘጋጃ ቤቱ ድረስ አለባበሱ እንዲታየን፣ ጣቃ ሙሉ ጨርቅ በመጫወቻ ዳማ ነጭና ጥቁር አራት ማእዘኖች (Squares) የተሰባጠሩበት፡፡ ከዚህ ጣቃ ጨርቅ ተቀዶ የተሰፋ ይመስላል፡፡ እና ላዩ ላይ እንደ ድርብ ቆዳ ልክክ ብሎ ተጣብቋል፡፡ የሰውነቱ ቅርፅ ራቁቱን ያለ ያህል ወለል ብሎ ይታያል፡፡
“ምን እንርዳህ?” አሉት ባለስልጣናቱ
“እኔ እንጂ ልርዳችሁ” አላቸው “አይጠ-ሞገጦቹን ከከተማችሁ ባጠፋቸው አንድ መቶ የወርቅ እንክብል ትከፍሉኛላችሁን?”
“ደስ እያለን እንከፍልሀለን” አሉት ከንቲባው
“እና አንዲት አይጠ-ሞገጥ እንዳታስቀር” አሉት ምክትል ከንቲባው (አንዱ እንክብል መጠኑ ከኛ ሀምሳ ሳንቲም ተለቅ ይላል)
“እንካ አስር እንክብል ቀብድ” አሉት የሂሳብ ሹሙ “እዚህ ላይ ፈርም”
አቶ Pied Piper ሆዬ ዋሽንቱ እየጫወተ ሲራመድ፣ አይጠ ሞገጦቹ የሂትለርን ወታደራዊ ሰልፍ በሚያስንቅ ስነ ስርአት በስምንት ረድፍ እየተሰለፉ ተከተሉት፡፡ ከከተማው በስተምእራብ እተጐለተው ተራራ ጋ ሲደርሱ አፉን ከፍቶ ተቀበላቸው፣ ሁሉም ገቡ ጠፉ፣ የገቡበት ጉድጓድም ጠፋ፣ እዚህ ጋ ነበር፣ የለም እዚህ ጋ ነው የነበረው እየተባባሉ እስከ መወራረድ ደረሱ፡፡
በሶስተኛው ቀን Pied Piper እየጫወተ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ ተመለሰ - ገንዘቡን ለመቀበል፡፡ “አስር የወርቅ እንክብል ተከፍሎሀል፣ ይበቃሀል፡፡ እንድያውም ሲበዛብህ ነው፡፡ ዋሽንትህን መንፋት ትልቅ ስራ ሆኖ ነው” አሉት
“ተው ይቆጫችኋል” ብሎ ቢዝት
ከንቲባው አፍ አውጥተው
“Do your Worst!
Blow your pipe till you burst!” ብለው አስወጡት
Pied Piper ዋሽንቱን እየነፋ፣ ልክ ከትላንት ወድያ በሄደበት መንገድ ተራመደ፡፡ ልክ አይጠ-ሞገጦቹ እንደተከተሉት ከሰባት አመት እድሜ በታች ያሉ ልጆች ሁሉ በሰልፍ ተከተሉት፡፡ ተራራው አሁንም አፉን ከፍቶ ተቀበላቸው፡፡ ሁሉም ገቡ፣ ጠፉ . . .
. . . አንድ የአምስት አመት ልጅ ብቻ ሳይሄድ ቀረ፣ ሽባ በመሆኑ፡፡ የሚያውቋት ሴቶች “እንኳ ደስ አለሽ፣ ልጅስ ተረፈልሽ” ሊሉዋት መጡ “ታድለሽ!” አለቻት አንዷ “ምነው እኔ እውር ወልጄ በሆንኩ ኖሮ! ይህን ጊዜ ልጄን አቅፌ ተኝቼ ነበረ . . .”
አህያና አያ ጅቦ
መሽቶ ሰውም ከብቱም ተኝቷል፡፡ አህያ ግን በጣም ስለጠገበ የደስ ደስ ማናፋት አሰኘው፡፡
“እኔ ልጮህ ነው” አለ
“ተው አያ ጅቦ ይሰማሀል”
“ቢሰማ ባይሰማ የራሱ ጉዳይ!”
“ኋላ እኔ የለሁበትም”
“አትኑርበት” አለና ጮኸ “ሀ! ሀ! ሀ! ነፋኝ ቀበተተኝ ሀ! ሀ! ሀ!”
ደጋግሞ ደጋግሞ ጮኸና “እሰይ” ብሎ ገና ከመጋደሙ
“ቤቶች አላችሁ?” አለች ቀበሮ “አያ ጅቦ እንዳለ፣ ርቦኝ የምበላው ጨንቆኝ እያለ፣ ያንተ ማናፋት ረሀቤን አባብሶብኛል፡፡ አሁኑኑ ፈጥነህ የደረስክ እንደሆነ፣ ባንዳፍታ ቦጫጭቄ እበላህና ትገላገላለህ፡፡ የዘገየህብኝ እንደሆነ ግን ቀስ ብዬ ተንቀባርሬ፣ ዋይታህን እየሰማሁ መጀመሪያ አንድ እጅህን አጣጥመዋለሁ፡፡ ቀጥሎ ቀኝ እጅህን ብበላ ይሻልሀል ወይስ …. ”
አህያ አቋረጠውና፣ ከብቶቹን ደህና ሁኑ እንኳ ሳይል እየጋለበ አያ ጅቦ ቤት ከተፍ አለ
“እንኳን ደህና መጣህ!” አለ አያ ጅቦ በጓዳዊ ፈገግታ
“እንኳን ደህና ቆየኸኝ! እንዳልዘገየሁ ተስፋ አደርጋለሁ”
ጥቅስ “የጠገቡ እለት ሞት ይገኛል”
[ደራሲ “እመው”]
እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን!!

 

Read 2088 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:05