ወርኃ ጥቅምት 2017 ዓ.ም መንግሥት አድርጌዋለሁ ያለው 300% የደሞዝ ማሻሻያ ተግባራዊ ሊደረግ ነው የሚል ዜና በሰማንበት ማግስት፣ ደጉ አከራያችን ሆስፒታል አድሬ ስመለስ ጠብቀው ያዙኝና “ቁርስ በልተህ ቡና ጠጥተህ ተመለስና የማናግርህ ነገር አለኝ” አሉኝ። የታዘዝኩትን ፈፅሜ ተመለስኩና ለምን እንደፈለጉኝ ስጠይቃቸው፣ ወቅቱን ያማከልና ከጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የቤት ኪራይ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰናቸውንና ልጅ አሳዳጊ መሆናቸውን፣ የኑሮ ውድነቱም እየናረ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ በወር 700 ብር ብቻ እንደጨመሩብኝ አረዱኝ።
በተመሳሳይ ቀን እኔና ዝናዬ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ከተወያየን በኋላ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ደረስን። አንበላም አንጠጣም ብለን የገዛናትን ቤት አዘገጃጅተን ለመግባትና ዶሮ እርባታ ለመጀመር ተስማማን። ውሳኔው ቀላል የሚባል አልነበረም ፤ ጭካኔ ይፈልጋልና ጨክነናል። ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሯን አስገጥመን፣ ውስጧን አስለስነን፣አጥሯንም በቆርቆሮ አሳጥረን በእለተ ሐሙስ ህዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም (የህዳር ሚካኤል እለት) እቃችንን ጠቅለለን ወደ ቤታችን ገባን። የቤት መግዣውን ሳይጨምር ውስጧን ለማስለሰን 16ሺ ብር፣በርና መስኮት በላሜራ ለማሰራት 17ሺ ብር፣ አጥሯን በቆርቆሮ ለማሳጠር 24ሺ ብር በድምሩ 57ሺ ብር ጨርሶብናል።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ወደፊት የግል ክሊኒክ ለመክፈት የገዛሁትን centrifuge(15ሺ ብር )፣ autoclave(15ሺ ብር )፣ examination bed(6500 ብር)፣ ፍሪጅ (25ሺ ብር ተገዝቶ 18ሺ ብር የተሸጠ)፣ እንዲሁም ለማንበቢያ የገዛኋትና እንደ ዓይኔ ብሌን የምወዳትን Tablet(9ሺ ብር) መሸጥ ነበረብኝና ሽጥኩ። መጨከን ነበረብኛ!
ዶሮ እርባታውን ለመጀመር ግን ጨክኖ መነሻ በጀቱን የሚሸፍንልን sponsor እንፈልጋለን።
አስቻይ ሁኔታዎች
1ኛ. የተመቻቸና በቂ ቦታ ያለን መሆኑ
2ኛ. ቀዳማዊት እመቤቷ (ወ/ሮ ዝናሽ መኬ)የተመሰከረላቸው የዶሮ እርባታ expert መሆናቸው
3ኛ. የጠቅላዩ ዶሮ እርባታን የሚያበረታታ አቋም
በጀት
የቄብ ዶሮ መግዣ: 100*300=30,000
የዶሮ ቤት መስሪያ: 10,000-15,000
የቄብ መኖ 5 ኩንታል*5000ብር =25000
መመገቢያ 4*300= 1200
መጠጫ :2700
የእንቁላል መጣያ ሳጥን: 1500
የእንቁላል መሰብሰቢያ: 270
አካፋና መዶሻ :2*500=1000
ሳፋ :2*400=800
ፕላስቲክ ባሊ:2*200=400
ለውኃ ማስገቢያ :10,000-15,000
ሮቶ :2000
ለክትባትና መድኃኒቶች(H2O2ና ሳሙናን ጨምሮ) :5000-7000
ሌሎች ወጪዎች 15000-20000
ጠቅላላ ድምር 80000-120000
እኔና ዝናዬ ጨክነናል!
ዝናሽ የዶሮ እርባታ ማእከል እውን ይሆናል።
19 ዓመት ተምሮ ለምድር ለሰማይ የሚከብድ ማእረግ እንደተጫነበት አንድ ኢትዮጵያዊ ሀኪም፤ ይህን ጦማር ይዞ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መውጣት በራሱ ሌላ ከፍ ያለ ጭካኔ ይጠይቃል።
ገረማችሁ አይደል?! አትገረሙ ደግሞም አትሰስቱ። ይልቁንም የአቅማችሁን ጠጠር ወርውሩ ፤ share በማድረግም ለሚመለከታቸው አጋር አካላት አድርሱልን።
Saturday, 21 December 2024 20:09
እኔና ዝናዬ ጨክነናል!!
Written by ዶ/ር ጌታነህ ካሴ
Published in
ንግድና ኢኮኖሚ

