• የቀላቲ ሂውማን ሄር ብራንድ አምባሳደር ሆናለች
• ለቀላቲ ሂውማን ሄር ቆንጆ ዘፈን ሰርቻለሁ
ታዋቂዋ ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ፣ የቀላቲ ሂውማን ሄር አምባሳደር ተደርጋ የተመረጠች ሲሆን፤ ለሁለት ዓመታት የቀላቲ ቢውቲን ምርቶች ታስተዋውቃለች ተብሏል፡፡
በትላንትናው ዕለት ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በቤስት ዌስተርን ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው ሥነስርዓት ላይ የቀላቲ ቢውቲ መሥራችና ባለቤት አቶ ሮቤል ቀላቲ፣ ከድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ ጋር የሥራ ውል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የቀላቲ ቢውቲ የኦንላይን ሽያጭ መጀመርም በዚሁ ሥነስርዓት ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡ ለኦንላይን ግብይቱ በአማርኛና እንግሊዝኛ የተዘጋጀ ዌብሳይትም ተዋውቋል፡፡
ከተመሰረተ 9 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተነገረለት ቀላቲ ቢውቲ፤ የሰው ጸጉር (ሂውማን ሄር)፣ የፊትና የቆዳ ውበት መጠበቂያዎች እንዲሁም የወንድና የሴት ሽቱዎችን ለደንበኞቹ በማቅረብ ይታወቃል፡፡
በአዲስ አበባና በዱባይ መደብሮች ያሉት ቀላቲ ቢውቲ፤ በቅርቡ ሦስተኛ መደብሩን በሰሜን አሜሪካ እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡
”ቀላቲ” በትግርኛ ስጦታ ማለት እንደሆነ ያስረዳው የድርጅቱ መሥራች፤ “አባቴን በጣም ስለምወደው ነው ድርጅቱን በእሱ ስም የሰየምኩት” ብሏል፡፡
ትኩረታችን ውበት ላይ ነው የሚለው አቶ ሮቤል ቀላቲ፤ ለደንበኞቻችን ጥራት ያለው ምርት ስለምናቀርብ አሁን ላይ ድርጅታችን መቶ ፐርሰንት ትርፋማ ነው ብሏል፡፡
የወደፊት ራዕዩንም ሲገልጽ፤ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ እስከ 300 የሚደርሱ የውበት መጠበቂያ መደብር ቅርንጫፎች የመክፈት ዓላማ እንዳለው ይናገራል፡፡ “በአገራችን የመጀመሪያው የውበት ፍራንቻይዝ ለመሆን እንፈልጋለን” ብሏል፤የቀላቲ ቢውቲ መሥራች፡፡
ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለመንግሥት ተገቢውን ግብር በመክፈል ለአገር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚሻም አቶ ሮቤል ተናግሯል፡፡
ተወዳጇ ድምጻዊ ቬሮኒካ አዳነ በበኩሏ፣ የቀላቲ ሂውማን ሄር ብራንድ አምባሳደር ሆና መመረጧን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት፤ “ዛሬ በጣም ደስ የሚል ቀን ነው፤ በብራንድ አምባሳደርነት ስፈራረም ይሄ የመጀመሪያዬ ነው፤ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡” ብላለች፡፡
ድምጻዊቷ አክላም፣ ከቀላቲ ሂውማን ሄር ጋር ግንኙነት የፈጠረችበትን አጋጣሚ አውስታለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ገና ጀማሪ ድምጻዊት ነበረች፤ የታዋቂዎቹን አርቲስቶች ሥራዎች በምሽት ክለቦች የምታቀነቅን፡፡ ቬሮኒካ እንደምትለው፤ የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራዋን ስትሰራ ሂዩማን ሄር ያስፈልጋት ነበር፤ ነገር ግን የመግዛት አቅም አልነበራትም፡፡ በነጻ የሚሰጣት ወይም ስፖንሰር የሚያደርግ መፈለግ ነበረባት፡፡ የመጀመሪያ ሙከራዋ አልተሳካም፡፡ ሁለተኛው ሙከራዋ ያገናኛት ከቀላቲ ሂውማን ሄር ጋር እንደነበር ድምጻዊቷ ታወሳለች፡፡
የቀላቲ ቢውቲ መሥራች አቶ ሮቤል ቀላቲ ባለቤት ጋር ተገናኝታ ችግሯን እንደነገረቻት ትገልጻለች፡፡ “ሳያውቁኝ አምነውኝ ሂውማን ሄር ስፖንሰር አደረጉኝ፤ በነጻ ሰጡኝ፡፡ የመጀመሪያ ሥራዬ ላይ እንደዚያ ፏ ፍንትው ብዬ የምታዩኝ በቀላቲ ሂውማን ሄር ስፖንሰር ተደርጌ ነው፡፡” ስትል ከቀላቲ ሂውማን ሄር ጋር ግንኙነታቸው የተጀመረበትን አጋጣሚ አስረድታለች፡፡
አሁን በብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠችው፣ ያኔ ሂውማን ሄር ስፖንሰር ላደረጋት ድርጅት ነው - ለቀላቲ ቢውቲ፡፡
“ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ ለብዙ ሴቶች አርአያ ትሆናለሽ ተብዬ የፊት ገጽ በመሆኔ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ያለችው ድምጻዊቷ፤ “በብራንድ አምባሳደርነት ስፈራረም ይሄ የመጀመሪያዬ ነው” ብላለች፡፡
በብራንድ አምባሳደርነት ያላት ሃላፊነት ምን እንደሆነ ከጋዜጠኞች የተጠየቀችው ድምጻዊቷ፤ የፊት ገጽ በመሆን ሂውማን ሄርን ጨምሮ የቀላቲ መዋቢያዎችን ማስተዋወቅ ዋና ሃላፊነቷ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ከቀላቲ ቢውቲ ጋር ያላት ግንኙነት እንደ ቤተሰብ ቢሆንም ቅሉ፣ በብራንድ አምባሳደርነት ለመሥራት የተስማማችው ለሁለት ዓመት መሆኑን ገልጻለች፤ቬሮኒካ፡፡
ለብራንድ አምባሳደርነቱ ምን ያህል ተከፈለሽ በሚል ለቀረበላት ጥያቄ፤ ባለፈው የተከፈለኝን ተናግሬ ከደረሰብኝ አንጻር ስለ ክፍያው ባልናገር እመርጣለሁ ያለችው ድምጻዊቷ፤ ነገር ግን የሚመጥነኝን ጥሩ ክፍያ አግኝቻለሁ፤ ስትል መልሳለች፡፡
የቀላቲ ሂውማን ሄርም ሆነ ሌሎች መዋቢያዎች እጅጉን ጥራት ያላቸው መሆናቸውን የመሰከረችው ብራንድ አምባሳደሯ፤ “እኔ ሂውማን ሄርም ሆነ ምንም ዓይነት መዋቢያ ከቀላቲ ነው የምጠቀመው” ስትል ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡
ድምጻዊቷ፤ ለቀላቲ ሂውማን ሄር “ቆንጆ ዘፈን” መሥራቷንም ገልጻለች፡፡

