Thursday, 19 December 2024 21:32

እናት ባንክ፤ ሁለት እናት ተኮር ውድድሮችን ዛሬ በይፋ አስጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
• አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ይበረከትላቸዋል
እናት ባንክ፤ “የዓመቱ ድንቅ እናት” (mother of the year) የተሰኘ ውድድርን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም “ለእናቴ” የተሰኘ አገር አቀፍ የፅሁፍ ውድድርን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ማካሄድ ጀመረ፡፡
እናት ባንክ፤ ሁለት አገር አቀፍ የውድድር መርሐ ግብሮችን በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ አድርጓል፡፡ አንደኛው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው “የዓመቱ የእናት ባንክ ድንቅ እናት” የተሰኘ ውድድር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረገው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር ነው፡፡
ባንኩ፤ ለዘመናት ለሀገርም ሆነ ለቤተሰብ ምሰሶ ለሆኑት የኢትዮጵያ እናቶች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ለአንድ ወር የሚቆዩና ሽልማት የሚያስገኙ፣ ሁለት እናት ተኮር ውድድሮችን በይፋ ማስጀመሩን አብስሯል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው “የዓመቱ የእናት ባንክ ድንቅ እናት” የተሰኘው ውድድር፣ ተወዳዳሪዎች በአካባቢያቸው የሚያውቋቸውን ወይም የራሳቸውን እናቶች፣ በድምፅና በምስል ቀርጸው በቀጥታ በመጠቆም የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረገው “ለእናቴ” የተሰኘ የጽሁፍ ውድድር ደግሞ፣ በዋናነት ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ አክብሮት፣ ውለታና ምስጋና በዝርው ጽሁፍ (ግጥም ያልሆነ፣ በወግ መልክ፣ በደብዳቤ ቅርጽ ወዘተ) የሚገልፅበትና “ለእናቴ” የሚልበት መልካም አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
የዓመቱ የእናት ባንክ ድንቅ እናት ውድድርን አስመልክቶ ተወዳዳሪዎች፣ በፅሁፍ ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው በቃላቸው፣ በድምጽና በምስል ቀርጸው የሚወዳደሩበትን የዓመቱ ድንቅ እናት (mother of the year) የሚያስመርጡበት ሂደት ነው፡፡ “ለእናቴ” በተሰኘው የፅሁፍ ውድድር ላይም፣ ስለ እናታቸው የሚያጋሩትን ፍቅርና ስሜት ዳኞች አወዳድረው የሚያበላልጡበት ሳይሆን ይልቁንም ተወዳዳሪዎች ለእናታቸው ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዴት እንደገለፁ፣ ስሜታቸውን ወደ ሌሎች ለማጋባት እንዴት እንደጣሩ የሚዳኙበት ዐውድ ነው ተብሏል፡፡
የማወዳደሪያ መስፈርቶች በተመሳሳይ መልኩ የተቃኙ መሆናቸውን የጠቆመው የባንኩ መግለጫ፤ የቅርፅ ጉዳዮች 50 ከመቶ፣ የይዘት ጉዳዮች 50 ከመቶ፣ በድምሩ 100 ነጥብ እንዲይዙ ተደርገው መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሃጎስ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ የውድድሩ አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማትና የምስክር ወረቀት የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ የገንዘቡን መጠን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
የዓመቱ ድንቅ እናት ውድድር ከታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ “ለእናቴ” የጽሁፍ ውድድር ደግሞ ከነገ ታህሳስ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 11 ቀን 2047 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር እንደሚቆይ የእናት ባንክ መረጃ ይጠቁማል፡፡
“ተወዳዳሪዎች፣ ስለ እናታቸው ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በፈለጉት መንገድ የሚገልፁባቸው ሁሉም የ“ለእናቴ” ጽሁፎች ሆኑ የዓመቱ ድንቅ እናትን የማወዳደሪያ ጥቆማዎች የህብረተሰቡን ስነ ምግባር፣ ሀገራዊ መልክና የሃይማኖት ልዩነት ወዘተ ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡” ብሏል፤ መግለጫው፡፡
“ለእናት የጽሁፍ ውድድር” በአዕምሮአዊ ንብረት ተመዝግቦ፣ የእናት ባንክ ንብረት መሆኑን የባንኩ አመራሮች በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል፡፡
የዓመቱን ድንቅ እናት ውድድር
ይሄ ውድድር በህይወት ያሉ እናቶች የሚመሰገኑበት የውድድር አይነት ሲሆን ከ “ለእናቴ የፅሁፍ ውድድር” የሚለይባቸው የራሱ መመዘኛዎች አሉት፣ መወዳደሪያ መስፈርቶቹም፡-
* ለውድድር የሚቀርቡት ባታሪኮች በህይወት ያሉ እናቶች መሆን አለባቸው፤
* ታሪካቸው የሚነገርላቸው እናቶች ግዴታ ወላጅ እናተ (የስጋ እናት) መሆን አይጠበቅባቸውም፤
ለምሳሌ አሳዳጊ ወይም ደግሞ በሰፈር አሊያም በጎረቤት ያ እናቶችን ታሪክ ማቅረብ ይቻላል፡፡
* በዚህ ውድድር ላይ ስለ ሚያቀርቡት ታሪክ ከፈለጉ በፅኁፍ አሊያም በድምፅ ወይንም ደግሞ በቪዲዮ ስዎቻቸውን ቀርፀው ማቅረብ ይችላሉ፡፡
* ውድድሩ የሚቆይበት ጊዜ ከታህሳስ 14/2017 ዓ.ም እስከ ጥር 14/2017 ዓ.ም ይሆናል፡፡
* መወዳደሪያ ስራዎቻችሁን አቅራቢያችሁ በሚገኙ የእናት ባንክ ቅርንጫፎች ማስረከብ የሚል ሲሆን በቪዲዮና በድምፅ ቅጂ ለምታስገቡ እና ውጭ ሀገር ለምትኖሩ ደግሞ በኢሜል፣ አሊያም በእናት ባንክ ኦፊሻል የፌስቡክ ገፃችን ላይ መልዕክት ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡
“ለእናቴ” የጽሁፍ ውድድር
የውድድሩ ጽሁፎ መወዳደሪያ መስፈርቶች፡-
* በሌሎች የህትመት እና የኤሌክቶኒክስ የመገናኛ ብዙሀን ላይ ያልቀረበ ወጥ ፣ አዲስና የተለየ መሆን ይኖርበታል፤
* ጽሁፉ ግልጽ እና ተነባቢ እንዲሆን በኮምፒውተር ተጽፎ፣ በ12 ፎንት የፊደላት መጠን እና በ1.5 የኅዳግ መስመር መቅረብ አለበት፤
* በኤ ፎር ( A4 ) የወረቀት ምጣኔ፣ ከሦስት /3/ ገጽ ያልበለጠ መሆን ይኖርበታል፤
* ለተመረጡ አሸናፊ ጽሁፎች የገንዘብ ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ይበረከትላቸዋል፤
* ተወዳዳሪዎች፣ ስማቸውን እና አድራሻቸውን የፅሁፍ ስራቸውን ባቀረቡበት ወረቀት ላይ መፃፍ የለባቸውም፣ ይልቁንም ስራቸውን በሚገያሸ፴ጉት ፖስታ ላይ ብቻ መፃፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
* እናት ባንክ አሸናፊ ጽሁፎን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡
* የማስረከቢያ ጊዜ ከዛሬ ከታህሳስ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 11 ቀን 2047 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር የሚቆይ ይሆናል፡፡
* ተወዳዳሪዎች ጽሁፋቸውን በአቅራቢያቸው በሚገኙ የእናት ባንክ ቅርንጫፎች በአካል በመገኘት ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የውድድሩ መዝጊያ በተመለከተ የተወሰኑ የውድድሩ ተሳታፊዎች፣ የውድድሩ አሸናፊዎች፣ ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች ባሉበት በታላቅ ድምቀት የሚደረግ ሲሆን በእለቱም ለአሸናፊዎች ተወዳዳሪዎች የተዘጋጁላቸው ሽልማቶች ይበረከቱላቸዋል፡፡
የኢሜል አድራሻ፤ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Read 5022 times